Print this page
Saturday, 13 June 2020 11:21

“እኔ እምመክረው ለልጄ፣ የሚያዳምጠኝ ጐረቤቴ”

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ታዋቂና ጉረኛ አዳኝ በአንድ መንደር ይኖር ነበር፡፡ ጉረኛነቱን የሚያውቁ የመንደሩ ሰዎችም፤ ቡና ሲጠጣም፤ ድግስ ላይም፣ ሐዘን ቤትም ጨዋታ ገና ሲጀምሩ፤
“ዛሬ ምን አጋጠመኝ መሰላችሁ?”
አንደኛው፤
“ምን አገኘህ?” ይለዋል ጨዋታውን እንዲቀጥል
አዳኙም፤
“ጐሽ ነው! ጐሽን አግኝቼ ደፋሁት!”
ሁለተኛው፤
“ብራቮ! ድንቅ አዳኝ’ኮ ነህ አንተ!
ሌላስ?”
አዳኙ፤
“ሌላማ ትላንትና ነው!”
ሁለተኛው፤
“ትላንት ምን አጋጠመህ ወዳጄ?”
አዳኙ፤
“ትላንትናማ አጋዘን አገኘሁ”
ሁለተኛው፤
“ከዛስ?”
“ከዛስ፣ ትለኛለህ እንዴ? ሌባ ተይዞ ዱላ ይጠየቃል እንዴ? ደፋሁታ!”
ከዚያ አንዲት የባለቤቱ ጓደኛ ጣልቃ ገባች ድንገት፡፡ በጣም ደፋር፣ ግልጽና የማይጥማትን ነገር ዝም ብላ መቀበል አይሆንላትም፡፡
“ዛሬስ? ምን ልታድን ነው ዝግጅትህ?”
“ኦ! ዛሬማ አደኔ ከሁሉም ቀን የተለየ ነው፤ ነብር ነው ማደን አለብኝ ብዬ የተነሳሁት!”
“እንዴ! ነብር’ኮ አደገኛ ነው” ትለዋለች ሴቲቱ፤ በጥያቄ መልክና በድንጋጤ
“አውቃለሁ፡፡ ለአደን ስወጣ አስቀድሜ ስለማድነው አውሬ ጠባይ፣ በደንብ አድርጌ ጥናት አካሂዳለሁ!”
በዚህ ማህል አንድ የጥንት አዳኝ የነበረ ሰው ይመጣል፡፡
“ምን እያወጋችሁ ነው?” አለና ጠየቀ፡፡
“አዳኙ ዛሬ ስለሚያድነው አውሬ እየነገረን ነው”
የጥንቱ አዳኝም፤
“እሺ፤ እኔም ልስማ?”
ሴቲቱም፤ “አንተማ ሙያህም ነው፣ ይመለከትሃል”
የጥንቱ አዳኝ፤
“እሺ ምን ልታድን አሰብክ? ወዳጄ?”
አዳኙም፤ “ነብር” አለው፡፡
የጥንቱ አዳኝም፤ እራሱን በመዳፉ መሀል ይዞ፤
“ኧረ! ነብር አደገኛ እኮ ነው!”
የአሁኑ አዳኝም፤
“ነው! ግን እስከዚህም አያሰጋኝም፡፡ ጥሩ አነጣጣሪ ነኝ!”
“ከሳትከው ግን ወየውልህ፡፡ በጣም አልሞ መቺ ጐበዝ፤ መሆን አለብህ!”
“ጐበዝ ነኝ!”
“እሺ፤ በመጀመሪያ ስትተኩስ ብትስተውስ?”
አዳኙም፤ “ልምድ ያለኝ ሰውኮ ነኝ፡፡ ቶሎ ብዬ አቀባብልና ሁለተኛውን እለቅበታለሁ!”
“በሁለተኛው ብትስተውስ?”
“ወዲያው ፈጥኜ ሦስተኛውን እተኩስበታለሁ!”
“በሦስተኛውስ ብትስተው?”
“እንዴ! ሰውዬ! አንተ ከኔ ጋር ነህ ከነብሩ ጋር?!” አለው፡፡
*   *   *
በሀገራችን ጉራ አሉታዊ ቃል ነው፡፡ ጉራ የተነዛበት ጉዳይ አብዛኛውን ጊዜ በሥራ ላይ አይውልም፡፡ በአበሽኛ ሲታሰብ አንድ ብዙ የተወራበት ነገር ለፍሬ ሳይበቃ ከቀረ - “ማን ጉራህን ንዛ አለው? ማን ሆዱን ረገጠው? ምነው አርፎ ቤቱ ቢቀመጥ? ምነው አፉን ቢዘጋ? “እዩኝ እዩኝ ያለች ኋላ ደብቁኝ ደብቁኝ ትላለች!” ወዘተ ይባልበታል፡፡ “ዝም ባለ አፍ ዝምብ አይገባበትም!” “ዝም አይነቅዝም”፤ “ሥራ በልብ ነው!” “አላርፍ ያለች ጣት…” “ፊት የተናገረን ሰው ይጠላዋል፡፡ ፊት የበቀለን ወፍ ይበላዋል!” አያሌ ተረቶች፣ አያሌ አባባሎች፣ አያሌ ምሳሌያዋ አነጋገሮች አሉን:: ከሁኔታዎች ጋር፣ ከባህላዊ ትውፊቶቻችን ጋር ተዋህደው ለወቅታዊ ጉዳዮች መገለጫ ሆነው በህያውነት በማገልገል ላይ ያሉ ናቸው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ የብዙ ዘመን ታሪክ ያላት አገር፣ የልሣናዊ አገር ብትሆንና ከጽሑፋዊነት ተራኪነት ቢገዝፍባት አይገርምም፡፡ Story – teller Society (ተራኪ - ህብረተሰብ) ቢሉንም ዕውነት አላቸው፤ አንደበተ - ርቱዕነት፣ ደስኳሪነት መልካም ነገር ነው፡፡ ክህሎትም ነው! ይህን የምንለው ግን “ነገር ቢያበዙት በአህያ አይጫንም”ን ሳንዘነጋ ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ ኢትዮጵያ “የበላ ልበልሃ” “የተጠየቅ ልጠየቅ” አገር መሆኑዋ ገሃድ ዕውነታ ነው! ስለዚህም ነገር በምሳሌ፤ ጠጅ በብርሌ ማድረጋችን፣ የሥር- የመሠረታችን ደርዝ ነው! ከአኗኗራችን፣ ከአስተማመራችን፣ ከፈጠራ - ክህሎታችን ጋር በጥኑ የተሳሰረ ነውና የአስኳላ ትምህርት ዘለቅን ብለን አንተወውም፡፡ ይልቁንም በተገኘው አጋጣሚ አንቱ እንለዋለን፡፡
እንደ ዛሬ ነገሩ ሁሉ ግልጽነት (Transparency) ወደሚለው ዲሞክራሲያዊ ገጽታና ዕሳቤ ሳናድግ፤ መላችን ሁሉ በድብቅነት፣ በሃሳዊ ግንዛቤ ላይ የተመሰረተ ይሆንብናል፡፡ ይህንን መግታት ይገባል፡፡ ወጣቶቻችን በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ግልጽነትን ባህል ያደርጉ ዘንድ የውይይት ባህልን፣ የትምህርት ባህልን፣ የመተጋገዝ ባህልን በቅጡ እንዲጨብጡ፣ ይሁነኝ ብሎ መኮትኮት፣ ማጠንከርና ዳር ድረስ ማጐልበት ያስፈልጋል፡፡ በዙሪያቸው ያለውን ክልልና ከባቢ ብቻ ሳይሆን በሀገራቸው ዙሪያ ያሉትን ሀገሮች አውቀው፣ ተረድተውና አመለካከታቸውን አስተውለው፣ አህጉራዊ ማንነታቸውን፣ ህልውናቸውንና ትግላቸውን በማጤን፤ የተሳሰረ ትግልንና ብልጽግናን በንቃት - ህሊናዊ ምጥቀት በማገዝ፣ የአህጉራዊነትን መንፈስ ማለምለም ያስፈልጋቸዋል፡፡ ፓን-አፍሪካኒዝም ቢውጠነጠንና ቢዳብር፤ አስተሳሰብ ሀገራዊም አህጉራዊም እንዲሆን መጣር ጤናማ መንገድ ነው፡፡ አበው ልጆቻቸው ምክራቸውን አልሰማ ሲሉና ጐረቤት አገሮች ሲያድጉ፤ የነሱ ህይወት ግን አልሰማ ሲልና ረብ - የለሽ ሲሆን፤ ቁጭታቸውንና እልሃቸውን ለመግለጽ “እኔ እምመክረው ለልጄ፣ የሚያዳምጠኝ ጐረቤቴ” ይላሉ፡፡ የሚነገረውን የሚሰማ፣ የሚመከረውን ልብ- የሚል ወጣት እንዲኖረን፣ ከቤት እስከ ህብረተሰብ ጥረት እናድርግ፡፡ ስለ ጤና በሚነገረን ነገር ላይ በተለይ ልብ እንግዛ!

Read 13422 times
Administrator

Latest from Administrator