Saturday, 13 June 2020 11:19

ኦፌኮ፤ በኦሮሚያ የሰብአዊ መብት ጥሰት ተፈጽሞባቸዋል ያላቸውን የ198 ሰዎች ዝርዝር ይፋ አደረገ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

   ኢሠመኮ በጉዳዩ ላይ ጥልቅ ምርመራ እንዲያደርግ ጠይቋል

               በኦሮሚያና በአማራ ክልል (ኦሮሞ ብሔረሰብ) አስተዳደር ዞን ውስጥ በዚህ አመት ተፈጽመዋል ያላቸውን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በዝርዝር የገለፀው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)፤ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በጉዳዩ ላይ ጥልቅ ምርመራ እንዲያደርግ ጠይቋል፡፡
ኦፌኮ ትናንት ከሰዓት በኋላ ባወጣው መግለጫና ዝርዝር ሪፖርት፤ በዚህ አመት (2012) በኦሮሚያ በምዕራብ ወለጋ፣ ምስራቅ ወለጋ፣ ምዕራብ ሀረርጌ፣ ቡኖ በደሌ፣ ምዕራብ ጐጂ፣ ጅማ፣ ምዕራብ ሸዋ፣ ቦረና፣ ቄለም ወለጋና አማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ ዞኖች ተፈጽመዋል ያላቸውን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ይፋ አድርጓል፡፡
በምዕራብ ወለጋ ዞን አሰቃቂ ግድያና እንግልት የተፈፀመባቸው ያላቸውን የዘጠና አንድ ሰዎችን ስም ዝርዝርና የሚገኙበትን አድራሻ በሪፖርቱ አካትቷል - ኦፌኮ፡፡
በምስራቅ ወለጋ ደግሞ 13 የኦፌኮ አባላትና አመራሮች እንዲሁም ደጋፊዎች ለእስር መዳረጋቸውን ጠቁሞ፤ በእስር ወቅትም አካላዊ ድብደባን ጨምሮ የተለያዩ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች ተፈጽሞባቸዋል - ብሏል በመግለጫው፡፡
በቡኖ በደሌ ዞን እንዲሁ 14 የኦነግ ደጋፊዎች መገደላቸውን፣ ከ10 በላይ የሚሆኑ ግለሰቦች መታሠራቸውን በመግለጫው አመልክቷል፡፡
በአጠቃላይ በኦፌኮ መግለጫ እንደተመለከተው፤ ከላይ በተጠቀሱት ዞኖች ውስጥ አንድ መቶ ዘጠና ስምንት (198) ሰዎች ግድያን ጨምሮ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት እንደተፈፀመባቸው በዝርዝር አቅርቧል፡፡
ይህን የቀረበለትን ጥቆማ መነሻ በማድረግም፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በገለልተኝነት ጥልቅ ምርመራ አድርጐ እውነቱን እንዲያሳውቅ፣ እንዲሁም ዜጐችን ያለ አግባብ ያስገደሉ፣ ያሰቃዩ፣ ያሳሠሩ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት የፈፀሙና ያስፈፀሙ በሙሉ ለህግ እንዲቀርቡ፤ ተጐጂዎችም እንዲካሱ ጠይቋል - ኦፌኮ በመግለጫው፡፡  

Read 11373 times