Saturday, 13 June 2020 11:14

ተፎካካሪ ፓርቲዎች የፌዴሬሽን ም/ቤት ውሳኔን ተቃውመውታል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

  ትግራይ ክልል ምርጫ ለማካሄድ ወስኗል

             በ6ኛው አገራዊ ምርጫ እጣ ፈንታ ላይ የተላለፈውን የፌዴሬሽን ም/ቤት ውሳኔ ኦፌኮ፣ ኦነግ፣ ኦብነግና አብሮነት የተቃወሙ ሲሆን ከመስከረም 2013 በኋላ አገሪቱ ወደ ፖለቲካ ቀውስ እንዳታመራ ስጋት አለን ብለዋል።
ተፎካካሪ ፓርቲዎቹ ለአዲስ አድማስ በላኩት መግለጫቸው፤ የፌዴሬሽን ም/ቤት ቀጣዩ ምርጫ የኮሮና ወረርሽኝ ስጋት አለመሆኑ ከታወጀበት ጊዜ ጀምሮ ባለው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ይካሄዳል የሚለው ውሳኔ ሕገ መንግሥቱን የሚጥስና ለሕገ መንግሥታዊ ቀውስ ሁነኛ መፍትሄ እንደማይሆን ጠቁመዋል።
ምርጫው ሕገ መንግሥቱ በሚያስቀምጠው መሰረት የ5 አመት የጊዜ ገደብን መሰረት አድርጎ ዘንድሮ መካሄድ ነበረበት ያሉት ፓርቲዎቹ፤ ምርጫውን ማካሄድ የማይቻልበት ሁኔታ መፈጠሩን ተከትሎ መንግሥት ሕገ መንግሥታዊ ትርጉም አሰጥቶ ስልጣኑን ለማራዘም የሄደበት አቅጣጫ ግልጽ የሕግና የፖለቲካ ስህተት ነው ሲሉ ተችተዋል። መንግስት ማድረግ የነበረበት የፖለቲካ ድርጅቶች በጉዳዩ ላይ እንዲወያዩና እንዲደራደሩ ሁኔታዎችን ማመቻቸት እንደነበረበት የሚገልፁት ፓርቲዎቹ፤ መንግሥት ከዚህ አግባብ ውጪ በሕገ ወጥ ውሳኔ የጊዜ ገደቡ ለማይታወቅ ጊዜ ስልጣኑ መራዘሙ ተቀባይነት የለውም ሲሉ ተቃውመዋል፡፡
አገሪቱ ወደ ሰላምና መረጋጋት ለመጓዝ የጀመረችውን መንገድ የሚያደናቅፍ ውሳኔ መተላለፉን ያወሱት ኦፌኮ እና ኦነግ፤ በሕገ መንግስታዊ ትርጉም አቀራረብ ወቅትም የተለየ ሀሳብ ያላቸው ምሁራን እንዳይሳተፉ መደረጉንና የገዥው ፓርቲ ሀሳብና ተፅዕኖ የጎላበት ውሳኔ መተላለፉንም ጠቁመዋል - በመግለጫቸው።
የፌዴሬሽን ም/ቤትን ውሳኔ ፈጽሞ እንደማይቀበሉት ያመለከቱት የፖለቲካ ድርጅቶቹ፤ ውሳኔው ተስፋ የተጣለበትን የአገሪቱን የዴሞክራሲ ጅማሮ የሚያኮላሽ ነው ይላሉ።
የፌዴሬሽን ም/ቤት ባለፈው ረቡዕ ሰኔ 3 ቀን 2012 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባ፤ ቀጣዩ ምርጫ የኮሮና ወረርሽኝ ከእንግዲህ ስጋት አይሆንም ተብሎ ከሚታወጅበት ጊዜ ጀምሮ ከ9 ወር እስከ 12 ወር ባለው ጊዜ ውስጥ ምርጫ እንዲካሄድ መወሰኑ አይዘነጋም።
እስከዚያው ድረስም የፌደራልና የሁሉም ክልልና ከተማ አስተዳደር ም/ቤቶች በመደበኛ ተግባራቸው እንዲቀጥሉ ም/ቤቱ ውሳኔ አሳልፏል።  የሕዝብና ቤቶች ቆጠራም በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ውሳኔ መሰረት ለ3ኛ ጊዜ የተራዘመ መሆኑም ታውቋል።
ኢዜማና ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ እንዲሁም ቀደም ብለው ባቀረቡት ሀሳብ ምርጫው ኮሮና ስጋት መሆኑ ባለቀ ባለው 1 ዓመት ጊዜ ውስጥ እንዲካሄድ ሀሳብ ማቅረባቸው አይዘነጋም።
አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንድነት (አብሮነት) በበኩሉ፤ የፌደሬሽን ም/ቤት ውሣኔ ህገመንግስታዊ ያልሆነ፣ ሀገሪቱንም ለፖለቲካ ትርምስ የሚዳርግ መሆኑን በማሳሰብ፣ አሁን ያለው መንግስትም ያልተገደበ ስልጣን እንዲኖረው የሚያደርግ ውሳኔ ነው ሲሉ ተቃውመውታል፡፡
በዚህ የፌዴሬሽን ም/ቤት ውሣኔ በሀገሪቱ ለሚፈጠረው ፖለቲካዊ ቀውስ የለውጡ አመራር፣ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት እና የፌደሬሽን ም/ቤት በታሪክ ተጠያቂ እንደሚሆኑም አብሮነት አስገንዝቧል፡፡
ከመጀመሪያውም የምርጫውን መራዘም በጽኑ ሲቃወም የቆየው የትግራይ ክልል ገዥ ፓርቲ ህወኃት በበኩሉ የፌዴሬሽን ም/ቤት ውሣኔ ተቀባይነት እንደሌለው ገልጿል፡፡
የትግራይ ክልል የህዝብ ተወካዮች ም/ቤትም ይህ አመት ከመጠናቀቁ በፊት ምርጫ እንዲካሄድ በሙሉ ድምጽ ትናንት መወሰኑ ታውቋል፡፡  



Read 11767 times