Saturday, 13 June 2020 11:13

በሱማሌ ክልል የኮረና ቫይረስ ስርጭት መባባስ ስጋት ፈጥሯል

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(1 Vote)

  የክልሉ ሃላፊዎችም ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል ተብሏል
              
               በሱማሌ ክልል የኮረና ቫይረስ ስርጭት መባባስ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ የተገለፀ ሲሆን ክልሉ ከአዲስ አበባ በመቀጠል በርካታ የቫይረሱ ተጠቂዎች የሚገኙበት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
እስከ ትላንት ድረስ በክልሉ 215 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን በትናንትናው ዕለት የአንድ ሰው ህይወትም  በቫይረሱ በሽታ ሳቢያ አልፏል፡፡
የሱማሌ ክልል ከ2ሺ ኪሎ ሜትር በላይ ከተለያዩ ጐረቤት አገራት ጋር የሚያዋስነው የድንበር አካባቢ ያሉት በመሆኑ በክልሉ የሚታየው የኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭት እጅግ ከፍተኛ መሆኑንና ይህም በአሁኑ ወቅት ከክልሉ አቅም በላይ እየሆነ መምጣቱን የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር የሱፍ መሐመድ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
ኮረናን የመከላከሉ ስራ ከክልላችን አቅም በላይ ሆኗል ያሉት የጤና ቢሮ ኃላፊው፤ የፌደራል መንግስቱ እያደረገልን ያለው ድጋፍ በቂ አይደለም፤ ትኩረት ሊሰጠን ይገባል ብለዋል:: ከ2 ቀናት በፊት በክልሉ 57 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መገኘታቸውን ያመለከቱት ኃላፊው፤ ይህ ሁኔታም ችግሩ ያለበትን አሳሳቢ ደረጃ አመላካች ነው ብለዋል፡፡
ክልሉ ከሱማሌያና ከጅቡቲ የሚመጡ ኢትዮጵያውያንን የሚቀበል ሲሆን፤ እነዚህን ኢትዮጵያውያን በለይቶ ማቆያዎች ውስጥ በማስገባትና ምርመራ በማካሄድ ከህብረተሰቡ ጋር እንዲቀላቀሉ የማድረጉ ሥራ ከአቅሙ በላይ ሆኖበታል ብለዋል፡፡
በደዋሌ አካባቢ ያሉ ት/ቤቶች፣ ባቡር ጣቢያዎች፣ የመንገድ ሥራ ካምፖች፣ የቻይናዎች መኖሪያ ካምፖች ሁሉ ለለይቶ ማቆያነት ተዘጋጅተው እንደነበር የጠቆሙት ኃላፊው እነዚህ 500 ያህል የሚሆኑ ሰዎችን ለመቀበል የተዘጋጁት ቤቶች ከ1ሺ 115 በላይ ሰዎችን ለመቀበል ተገደዋል ብለዋል፡፡
በድሬደዋ ዩኒቨርስቲ ለሁለት ጊዜያት ያህል ሰዎችን የተቀበለን ቢሆንም፤ ከዚያ በኋላ ግን “የራሳችንን ሰዎች ማስተናገድ የምንችልበት ስፍራ ስለሌለን እናንተ ራሳችሁን ቻሉ ስለአሉን፤ አሁን ትልቅ ችግር ላይ ወድቀናል” ይላሉ ኋላፊነት፡፡
በአሁኑ ወቅት ወቅቱ የሙቀት ጊዜ በመሆኑ በርካታ ሰዎች ከጅቡቲ ወደ ክልሉ እየገቡ እንደሆነ የተናገሩት ኃላፊው እነዚህን ሰዎች ተቀብሎ ለማቆየት የሚያስችል ስፍራ የሌለን በመሆኑ ድንኳኖችን በማዘጋጀት ለመቀበል ዝግጅት እያደረግን እንገኛለን ብለዋል፡፡
በክልሉ ከሚገኙ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች መካከል በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መገኘታቸውን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ ከሥራ ኃላፊዎቹ ጋር ንኪኪ አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ ሰዎችም በለይቶ ማቆያ ውስጥ መግባታቸውንም እነዚሁ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

Read 11153 times