Tuesday, 09 June 2020 00:00

ፈተና የፀናባት አገር፤ በፖለቲካ ብሽሽቅ ትጠመድ?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)


             ችግር፣ “በራሱ ጊዜ” መፍትሄን እንደማይወልድ፣ የአገራችን ታሪክ ምስክር ነው፡፡ አልያማ፤ በችግር መዓት ብቻ ሳይሆን፤ በመፍትሄ ብዛትም፤ ኢትዮጵያ፣ በጣም ዝነኛ አገር በሆነች ነበር፡፡ ነገር ግን፤ ችግር፣ መፍትሄን አያመጣልንም፡፡
አንዱ ፖለቲከኛ ውሸት ሲነዛብን፤ ሌላ ተቀናቃኝ ፖለቲከኛ እንዲፈጠርና ተጨማሪ ውሸት እንዲግተን በመጋበዝ ነው፤ “እውነት” የሚወለደው? ሁለት ተቀናቃኝ ውሸቶች፤ እርስ በርስ ሲበሻሸቁ ውለው፤ ሲጨቃጨቁ ቢያድሩ ቢከርሙ፤ አንዳች እውነት አይወለድም፡፡
አንድ “ዘረኛ አክቲቪስት” ያቧደናቸው አጥፊዎች ዛሬ ወንጀል ሲፈጽሙብን፤ ነገ ሌላ ተቀናቃኝ “ዘረኛ አክቲቪስት” እንዲፈጠርና አጥፊዎችን እንዲያዘምትብን ብንመቻች፤ ነፃነትን እናገኛለን? ወንጀል ሲበዛ ነፃነትን ይወልዳል? አይወልድም፡፡
አንድ “የብሽሽቅና የዘረኝነት አውራ”፤ ክፋትንና ጥፋትን ሲዘራ፣ አደገኛነቱን የሚገነዘቡ ሰዎች ይኖራሉ፡፡ ነገር ግን፤ ሌላ ተቀናቃኝ “የብሽሽቅና የዘረኝነት አለቃ” እንዲመጣ በር ይከፍታሉ፡፡ በአንድ አደገኛ ችግር ላይ፤ ሌላ አደገኛ ችግር ሲከመርበት፤ አንዳች መፍትሔ የሚወለድ ይመስላቸዋል፡፡
በተቃራኒው፤ የሕይወት ፈተና እየበዛ፤ ትርምስ ይበረክታል፡፡ ያኔ ድንጋጤ ይበረታል:: የዘረኝነት ቅስቀሳ እየተራገበ፣ አገር በጥላቻና በጥቃት ዘመቻ ስትታመስ፣ ሚሊዮኖች ከኑሮ ሲነቀሉ፤ ዝርፊያና ግድያ እንደ ዘበት ሲዛመት… ብዙ ሰው ይደነግጣል፡፡ እናም፣ የዘረኞችን ቅስቀሳ እየተቀበለ ከማጨብጨብና ከማራገብ ይቆጠባል - ለትንሽ ጊዜ፡፡ በጭፍን ስሜት ከመንገብገብና በጅምላ ከመንጋጋት ይታቀባል - ለጥቂት ቀናት፡፡
የዘረኝነትና የክፋት ፊታውራሪዎች፤ አራጋቢ ሲያጡ፣ አጃቢ ሲርቃቸው፣ ጩኸታቸው ይሳሳል፡፡ ብሽሽቃቸው ይመክናል፡፡ ይሄኔ፤ ከመጥፎ አመል ያገገሙ፣ አገራችንም ፍፁም የተለወጠች ይመስለናል፡፡ የዘረኝነትን መዘዝ በግላጭ ተመልክተው፣ “የብሽሽቅ መጨረሻ እጅግ ክፉ እንደሆነ” በገሃድ አይተው፣ “ትምህርት ይወስዳሉ” ብለን እናስባለን፡፡
አብዛኞቻችንም፤ “መከራ መክሮናል:: ከደረሰብን ችግር፣ ሁነኛ የመፍትሄ ችግኝ ይፈጠራል” የሚል እምነት ያድርብናል፡፡ ለጊዜው ይመስላል፡፡ እሳቱ ለአፍታ ይዳናል:: ከስንት ጥፋትና ስቃይ በኋላ፣ ከብዙ ክፋት በስንት መከራ፣ አገሪቱ፣ ለትንሽ ተርፋ፣ ቀስ በቀስ የመረጋጋት ምልክት ብቅ ይላል፡፡ የእፎይታ ስሜት ይፈጠራል፡፡ ግን ለትንሽ ጊዜ ነው፡፡
ብዙም ሳይቆይ፤ ነባሩ ጭፍን ስሜትና የዘረኝነት ቅስቀሳ፤ እንደ ቀድሞው መቀጣጠል ይጀምራል፡፡ የአገራችን ቅኝት፤ እንደተለመደው፤ ወደ “default setting”   ይመለሳል፡፡ ምንም ያልተፈጠረ፤ መዘዙንና ዘግናኝነቱን ጨርሶ ያላየን እናስመስላለን፡፡ ነባሩ ጭፍንነትና ብሽሽቅ፣ አስቀያሚው የዘረኝነት በሽታና ቅስቀሳ፣ እንደገና ተመልሶ ለመግለብለብ ጊዜ አይፈጅበትም፡፡
በአዲስ የጥፋት ዙር፣ ነባሩ ክፉ አዙሪት ይቀጥላል፡፡
“ኧረ ይሄ የብሽሽቅ በሽታ፣ ይቅርብን! ኧረ ይሄ የዘረኝነት አዙሪት፤ ሕይወትን ያረግፋል፤ የሚሊዮኖችን ኑሮ ያፈርሳል፤ እልፍ ወጣቶችን ለስደትና ለሞት ይዳርጋል” የሚል ሀሳብና ንግግር ይደበዝዛል፡፡ መስሚያ ጆሮ ይደነድናል፡፡
ከጥቂት ወራት በፊት፤ ብዙ ዘግናኝ ጥፋት እንደተፈፀመ፣ …. ብዙ ሰዎች፤ ሕይወትና ኑሯቸውን እንዳጡ ከምኔው ተረሳ? ከመቼው ወደ ብሽሽቅና ወደ ዘረኝነት ቅስቀሳ ዞረን ተመለስን? መዘዙንም ማሰብ አቃተን፡፡ የሚነግረንንም ጠላን፡፡
ብሽሽቅ ሲሟሟቅ፤ ዘረኝነት ሲራገብና ሲዛመትኮ፤ ከአምናው ካቻምናው የተለየ ትርጉም፤ አዲስ ውጤት የለውም፡፡ አስቀያሚ በሽታና ዘግናኝ እልቂት እንጂ፤ አንዳች የተለየ አዲስ ነገር አይመጣም፡፡ አይናችንን ካልጨፈንን በስተቀር፣ መዘዙ ግልፅ ነው፡፡
“Winter in Coming”
ብሽሽቅን ካልናቅን፤ ዘረኝነትን ካልተፀየፍንና ካልተከላከልን በስተቀር፤ ለእልቂት በራችንን እንደከፈትን ይቆጠራል፡፡ አራጋቢና አጨብጫቢ ከሆንንማ፤ ለጥፋት ቸኩለን እልቂትን እየጋበዝን ነው ማለት ይቻላል፡፡
ቃል በቃል፤ በእውን፤ “ሞትን እየጠራችሁ ነው፣ ሞት እየመጣ ነው” ብሎ እውነታውን እንድናይ፤ አይናችንን እንድንገልጥ የሚማፀን አንዳች መለኮታዊ ሀይል ካላገኘን አንታረምም? ካሁን በፊት ብዙ ጥፋቶችን ከነመንስኤያቸው አይተናል፡፡ ግን አልታረምንም፡፡
የሞት መዓት እንደ ጎርፍ ሲጋልብ፣ ፊት ለፊት ብንመለከት እንኳ፤ ለትንሽ ጊዜ መደንገጣችን ባይቀርም፤ ከስህተት ሳንታረም፤ ከክፋት መንገድ ሳንላቀቅ፣ ጭዳና ማገዶ እንሆናለን:: የሞት ማዕበልን አይተን እንዳላየን፤ ምንም ያልተፈጠረ ያህል፤ ሳምንትና ወር ሳንቆይ ነባሩን ጭፍንነት እናስተናግዳለን፡፡ “Game of the thrones” ይሉሃል እንዲህ ነው፡፡
“የሞት ሠራዊት እየመጣባችሁ ነው” ቢባል፣ ወይም በአይኑ በውን አይቶ ቢያረጋግጥም እንኳ፤ ሁሉም ሰው ከዚህ ጥፋት ለመዳን፣ “በአውቶማቲክ”፣ መላ ይፈጥራል ማለት አይደለም፡፡ ወይም ደግሞ፣ ችግር ሲመጣ፣ “በራሱ ጊዜ” መፍትሄ ይወለዳል ማለት አይደለም፡፡ አንዳንድ ብልሆች፤ “winter is coming”፤ “the army of the dead is marching…” እያሉ ተናገሩ፣ አስጠነቀቁ፡፡ የአቅማቸው ያህልም፤መፍትሄ ለማበጀት፣ መላ ለመፍጠር ሞክረዋል፡፡ ሌሎችስ?
“ለማገዶነት የተመቻቹ” እና “ሊማግዱ ያሰፈሰፉ” ቅኝቶች፡፡
የብዙ ሰዎች የዘወትር ቅኝት (default setting) ከችግር የማምለጥ ምኞት ይኖረዋል፡፡ ነገር ግን፤ ችግርን ለመፍታት፣ ፈተናን ለማሸነፍ ያነጣጠረ የአላማ ጥረትን የሚያጎላ አይደለም - ነባሩ ቅኝት፡፡ የአብዛኛው ሰው ቅኝት፣ ለቅንነት ቦታ የሚሰጥ መሆኑ አይካሄድም፡፡ ወደ ክፋት ያነጣጠረ ባይሆንም ግን፤ ክፋትን ተከላክሎ የሚገታ ቅኝት አይደለም፡፡
ለክፋት የተጋለጠ፣ ለማገዶነት የተመቻቸ ቅኝት ነው - የአብዛኛው ሰው ነባር ቅኝት:: ለክፉ ሰዎች ይመቻል፡፡ ቁጥራቸው ጥቂት ቢሆንም፤ ብርቱ ተቃውሞ አይገጥማቸውም:: የሚገታ ሳይሆን የሚንጋጋ ይበረክትላቸዋል፡፡ ችግር ሲፈጠር፣ መፍትሄ ለማበጀት ሳይሆን፣ ተጨማሪ ችግር ለማራባት ይዋከባሉ፡፡ ችግር በራሱ ጊዜ፣ መፍትሄን አይወልድም፡፡
የዘረኝነት ፊታውራሪዎች፤ የዘወትር ጥድፊያ፣ ችግሮችን ማባባስና መፈልፈል፤ በመንጋ እያቧደኑ፣ በሰበብ አስባብ መናቆርና መበሻሸቅ፤ አገሬውን ማቃጠልና  ሰዎችን መማገድ ነው፡፡
በተለይ የአገራችን ነገር፤ ያን ሁሉ ዘግናኝና አሳዛኝ ጥፋት አይተን፤ የችግር መአት ተቆልሎብን እያየን፤ ይሄ ሳያንስ፣ ከባድ ወረርሽኝ አፍጥጦብንም እንኳ፤ ከጥፋት ቅኝት አልተላቀቀም፡፡
እውነትም፤… የችግር ብዛት በላይ በላዩ ቢከመር፤ በራሱ ጊዜ ቅንጣት መፍትሄን አይወልድም፡፡ እርግጥ፤ የወረርሽኝን አደጋ እየመጣ እንደሆነ ያወቅን ጊዜ፤ ለጥቂት ጊዜ፣ ብዙዎች ወደ ህሊና ተመልሰው ነበር፡፡ የፖለቲካ ብሽሽቅና የዘረኝነት ቅስቀሳ አጋፋሪዎችም፤ ትንሽ አጨብጫቢ ርቋቸው፣ ጩኸት ረግቦባቸው፤ ለተወሰነ ጊዜ “ቤት መዋል” ጀምረው ነበር፡፡ ግን ለጊዜው ብቻ ነው፡፡
ብዙም ሳይቆይ እንዴት እንዳገረሸባቸውና፤ በምን ያህል ፍጥነት ወደ default setting  እንደተመለሱ አይተናል፡፡
አሁን፤ ከሦስት ሳምንት ወዲህ፣ የወረርሽኝ አደጋው እየገዘፈ ስለመጣ፤ የፖለቲካ ብሽሽቅና የዘረኝነት ቅስቀሳው እንደገና ቢረግብ አይግረማችሁ፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ፤ ወደ ዘወትር አስቀያሚ የዘረኝነት ቅኝት ወደ (default setting) መመለሱ አይቀርም፡፡
ያልተስተካከለ ችግር፤ ሌሎች ችግሮችን ይጠራል፡፡
በአስቀያሚና በዘግናኝ የዘረኝነት ጥፋት ላይ፤ የኢኮኖሚ ችግርና የስራ አጥነት ቀውስ ሲታከልበት፤ ይሄም በተራው ጭፍን ስሜትንና ግርግርን ይጋብዛል፡፡ “ማህበራዊ ፍትህ” ወይም “ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል” በሚሉ የስካር እና የምቀኝነት ፈሊጦች አማካኝነት፤ የፍትህ ትርጉም እየተናደ፤ ሰርቶ ንብረት ማፍራት እንደ ወንጀል እየተቆጠረ፤ ማህበራዊነት ወደ አውሬነት ይወርዳል፡፡ በዚህም ዝርፊያንና ውድመትን እያራባ፤ ድህነትንና የኑሮ ቅሬታን ያባብሳል፡፡ በሌላ ጎንም፤ የኢኮኖሚ ቀውስ፤ በጥሬው፤ እንደ ሙስናና እንደ ሌብነት ብቻ እየተቆጠረ፤ በዘረኝነት ስሜት እየተተረጎመና እየተመነዘረ፤ የዘረኝነትን አዙሪት ያጦዘዋል፡፡
ይህም ብቻ አይደለም፡፡ የባሰም አለ፡፡ በጣም ካልተጠነቀቅን በቀር፤ ሀይማኖትና ፖለቲካ፤ ሃይማኖትና መንግሥት፣ በየፊናቸው ሊኖራቸው ከሚገባ ትክክለኛ ገደብና ቀይ መስመር እንዳያልፉ ካልተገቱ በቀር፤ ከዘረኝነትም የባሰ አደጋ ያመጡብናል፡፡
በአንድ በኩል፤ እንደ አብዛኛው የሰው ሀሳብና የሰው ኑሮ፤ ሀይማኖትም የግል ነው፡፡ በሀይልና በግዴታ “እንዲህ እመን፤ ያንን ትዕዛዝ ተከተል” ብሎ የሚመጣብህ፣ ብለህ የምትሄድበት ሰው ሊኖር አይገባም፡፡ በሰው የግል ሃሳብና የግል ሃይማኖት ውስጥ፤ መንግስት ቦታ ሊኖረው አይገባም፡፡
በሌላ በኩል፤ የሃይማኖት ተቋማትና ትዕዛዛት፤ በመንግሥትና በሕጎች ውስጥ ድርሻ ሊኖራቸው አይገባም፡፡ በሌላ አነጋገር፤ የሃይማኖት ተቋማት በተዘዋዋሪ ጉልበተኛ እንዲሆኑ፤ የሃይማኖት ትዕዛዛት በተዘዋዋሪ አስገዳጅ ሕግ እንዲሆኑ መፍቀድ፤ ለማንም ቅን ሰው አይጠቅምም፡፡  


Read 4310 times