Monday, 08 June 2020 00:00

ኮቪድ-19፤ ማኅበራዊ ፈቀቅታና አዲስ አበባ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

   ”የኮቪድ-19 ክትባት እስኪገኝ ድረስ ማኅበራዊ ፈቀቅታን በአግባቡ መተግበር ወሳኝ የቫይረሱ መከላከያ ሆኖ ይቆያል። በህዳር በሽታ ወቅት ተተግብሮ የነበረው አገር በቀል የማኅበራዊ ፈቀቅታ በርካታ ኢትዮጵያውያንን አትርፏል። ይህ ትውልድ ደግሞ የራሱ መፍትሄ ያሻዋል።--” (በዳንኤል ካሣሁን)

                   እንደ መግቢያ
ድንገቴው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መላው ዓለማችንን ተቆጣጥሯል። ሚሊዮኖች በበሽታው ተጠቅተው፣ መቶ ሺዎች ውድ ሕይወታቸውን ተነጥቀው፣ በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ቫይረሱ በኢኮኖሚው ላይ ባደረሰው ቀውስ ሳቢያ ለወራት በመኖሪያ ቤታቸው ተወሽበው አሉ። ወደፊት የሚሆነውን በርግጠኝነት ለመናገር ይቅርና አሁን ያለውን የቫይረሱን ጠባይ ገና በቅጡ መች ተረድተነው? ዛሬ ስለ ቫይረሱ የሚገኘው አዲስ መረጃ፣ የትላንቱን መረጃ እየተቃረነ፤ ለጥንቃቄ የሚሰጠን ምክርም እንደ አየሩ ጸባይ እየተቀያየረ ነው። ዶናልድ ራምዝፊልድ “ያወቅነው እውቀት አለ፤ አለመታወቁን የምናውቀው እውቀት አለ፤ ፈታኙ ግን አለመታወቁን የማናውቀው እውቀት ነው” ያለው አባባል የዘመነ ኮሮና እንቆቅልሽን በመጠኑ ሊገልፀው ይችላል።
ኮቪድ-19 እያገረሸ አብሮን ሊቆይ በመሆኑ የችግሩ ውስብስብነት አይቀሬ ነው። ክትባቱ ቢገኝ እንኳ ከሕዝብ ዘንድ ሊደርስ የሚችለው እጅግ ዘግይቶ ነው። ካለን የሆስፒታል፣ የህክምና ባለሙያ፣ የህክምና ቁሳቁስና መድሃኒት አቅርቦት አንጻር እንኳንስ ኢትዮጵያ በርካታ ያደጉ ሃገራትም ተፈትነው የወደቁበት ጉዳይ ነው። ዛሬ መንግሥት፣ የሃገር ውስጥ በጎ አድራጊዎችና ሕዝቡ እጅና ጓንት ሆነው እየተረባረቡ መሆናቸው ተስፋ ቢያጭርም፣ የኮሮናን ዘርፈ-ብዙ ችግር ከህክምና አንፃር ብቻ መፍትሄ ልናበጅለት አንችልም። ለምሳሌ ከሃገር ውስጥና ከሌሎች ያደጉ ሃገራት ከሚገኝ እርዳታ ጋር ተደማምሮ የሚገኘውን ውስን ሃብት በየቱ ሥፍራ ቀድመን ትኩረት ብናደርግ ከፍተኛ ውጤት (multiplier effect) እናመጣለን? አንደ ወሳኝ መፍትሄ የቀረበውን የማኅበራዊ ፈቀቅታን አንዴትስ ውጤታማ አናደርገዋለን? መልስ የሚያሻቸው ጥያቄዎች!
ትንቢተ ኮሮና?
በኢትዮጵያ ለኮሮና ወረርሺኝ የቀረቡ ትንበያዎችን በሁለት ልንከፍላቸው እንችላለን። አንደኛው ፍጹም የተጋነነ (ሟርት የመሰለ) “የራስጌ ግምት” ሲሆን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በየዕለቱ እንደሚረግፉ የሚተነብይ ነው። የዚህ ምድብ አስቀድሞ በቻይና፣ በጣሊያንና በደቡብ ኮሪያ የተከሰተውን የኮሮና ሥርጭት ሥሌት ኮርጆ፣ እንደወረደ ለኢትዮጵያ በመሸለም “አስቀድሜ ተናግሬ ነበረ” ብሎ ይጠባበቅ የነበረ ይመስላል። የሁለተኛው ምድብ (አዘናጊ የመሰለ) ለኮሮና ወረርሺኝ የተቃለለ “የግርጌ ግምት” የሰጠ ነበር። ማስረጃውም ኢትዮጵያ የራሷ ባሕላዊ መድሃኒቶች ስላሏት፤ ፈጣሪ ሀገራችንን ከሌላው በበለጠ ስለሚጠብቃት፤ የዘመናችን ‘ነቢያት’ ኮሮና ኢትዮጵያን እንደማይደፍራትና ቢመጣም ድራሹ እንደሚጠፋ ስለተገለጸላቸው፤ ወዘተ--። ሃገርኛው ኮሮና ያለው ግን በሁለቱ የተለጠጡ ግምቶች መሃል ነው።
ከሥፍራም ሥፍራ አለ?
ኮቪድ-19 ከሰው ወደ ሰው በትንፋሽ የሚተላለፍ እንደመሆኑ የእርስ በርስ ቅርርብ ባህላችንና ትግበራችን የበሽታውን ሥርጭትና ቆይታ ይወስነዋል። በሰዎች መሃል ያለ የርቀት ዝንባሌን በተመለከተ ጥናቶች ሁለት ባህሎችን ይቆጥራሉ። የቀረቤታ (ይጠጌ) እና የፈቀቅታ (አይጠጌ) ባሕሎች። ይጠጌ ባህል በተንሰራፋባቸው አካባቢዎች የኮሮና ሥርጭትን ለመዋጋት አዳጋች ሲሆን በአይጠጌው ባህል ግን የቀለለ ይሆናል። የደቡብ አውሮፓ፣ የደቡብ አሜሪካ፣ የአረቢያ ሕዝቦች ከይጠጌ ባህል ሲመደቡ፣ በአመዛኙ በሞቃታማ የአየር ንብረት ክልል ይገኛሉ። ለምሳሌ ከአውሮፓ- ጣልያንና ስፔይን ሲገኙበት፣ እኛ ደግሞ የድሬዳዋ፣ ናዝሬት፣ ሞጆ፣ ወዘተ ከተሞችን ማከል እንችላለን። እንዳለመታደል ሆኖ፣ የይጠጌ ባህል አገራት ባመዛኙ የደኸዩ ናቸው። በሌላ በኩል፤ በሰሜን አውሮፓ ያሉ ሃገራት ከአይጠጌ ባህል ሲመደቡ አየር ንብረታችው በጣም ቀዝቃዛ፣ በኢኮኖሚያቸው ደግሞ ሃብታም የሚባሉ ናቸው።
እንደ ኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሪፖርቶች ከሆነ፤ የአዲሳባ ከተማ በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 እንቅጥቅጣፍ (epicenter) ናት። ምንም አንኳ በኢትዮጵያ የከተሜው መቶኛ ድርሻ ጥቂት ቢሆንም የወረርሽኙ መናኽሪያ በመሆኑ የከተሞችን የሥፍራ ባህሪ መመርመር ግድ ይላል። ወረርሺኙ በሁሉም ሥፍራ እኩል አይገኝምና የሚብስባቸውም ሆነ የሚቀንስባቸው ቦታዎች ይኖራሉ። የቫይረሱ ፍጥነትም ሆነ ሥርጭት የሚወሰነው አንደ ቦታው (site) ጠባይ (ለምሳሌ የአየር ሙቀት፤ ርጥበት፣ ዝናብ፣ ንፋስ፣ ወዘተ) ብቻ ሳይሆን ቦታው ከአካባቢው ጋር ባለው ትስስር (situation) ጠባይ (መንገድ፣ የገበያ ቁርኝት የህክምና ጣቢያ አቅርቦት፣ ወዘተ) ላይ ተመርኩዞ ነው።
ሥፍራ ከሰው ልጅ መሰረታዊ ህይወት ጋር የተሳሰረ ነው፤ በተለይም ደግሞ ከጤና ጋር ያለው ጉድኝት ሲበዛ ቀጥተኛ ነው። በዘመናዊ መልኩ የማኅበረሰብ ጤናንና የሥፍራ ቁርኝትን ያስረዳው እንግሊዛዊው ዶ/ር ጆን ስኖው ነበር። በ1854 (እኤአ) የለንደን ከተማ በኮሌራ ወረርሺኝ ሕዝቡ እንደ ቅጠል እየረገፈ በነበረበት ወቅት በሽታው ከምድር ወደ አየር በተንነት መልክ ይሰራጫል ተብሎ በስህተት ይታመን ነበር። ዶ/ር ስኖው ግን የተለየ መላምት ይዞ በኮሌራ ሳቢያ የሞቱትን ሰዎች መኖሪያ አድራሻና የውሃ ፓምፖች የሚገኙበትን መረጃ አሰባሰበ፤ በከተማው ካርታ ላይ አድራሻዎቻቸውን አነጠበ (plot)፤ የሟቾቹንና የውሃ ፓምፖችን ሥርጭቶች ልክ አንደ አነባበሮ ላይና ታች አድርጎ ካዛመደ (multi layering system) በኋላ የኮሌራ ወረርሽኝን መነሻና የሥርጭቱን ዘይቤ ለመተንበይ የሚያስችል ዘዴ ፈለሰመ። በተለይም አንዱ የውሃ ፓምፕ የሚገኝበት ሥፍራ ከበርካታ ሟቾች አድራሻ ጋር በእጅጉ በመቀራረቡ የተለየ ፍተሻ አደርጎ ከመኖሪያ ቤቶች የሚወጣው የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦ ያፈስ እንደነበርና የጉድጓድ ውሃውም በፍሳሹ በመበከሉ ለኮሌራ በሽታ መንስዔ እንደነበር አረጋገጠ፤ የታመሙት ሰዎች ደግሞ የፓምፑን እጀታዎች ስለሚበክሏቸው ኮሌራው ወደ ሌሎች ተጠቃሚዎች እንደሚተላለፍ አበሰረ። ስለዚህ መላው የለንደን ከተማ እኩል የኮሌራ መነሻና መስፋፊያ ሥፍራ አልነበረም። ይህ ውጤት ዶ/ር ስኖውን ኤፒዲሚዮሎጂ (Epideomology) ለሚባለው የጤና ዘርፍ “አባትነት” ያበቃው ብቻ ሳይሆን ጂ.አይ.ኤስ (GIS: Geographic Information System) ለሚባል የትምህርት ዘርፍ የማዕዘን ድንጋይ ሆኗል። በጣም ተበክሎ የነበረው የውሃ ፓምፕ ሥፍራም፣ ለመታሰቢያ በብሮድዊክ ጎዳና ላይ ሃውልት ተሰርቶለት በአላፊ አግዳሚው እየተጎበኘ ይገኛል።
ፈቀቅታ ዋጋው ስንት ነው?
ማኅበራዊ ፈቀቅታ የሚጠይቀው የሥፍራ መጠን በቀላሉ የሚመተር ቁንጽል ነገር አይደለም። ይልቁንም በሰዎች የዕለት ተዕለት ሕይወት ጋር የተገመደ ነው። የአንድ ግለሰብ የሀብትና የሥልጣን ደረጃ እያደገ ሲመጣ ከሌላው ግለሰብ ጋ ሊኖረው የሚገባው አካላዊ ርቀት እየሰፋ ይመጣል። ለምሳሌ ተራ ባለጉዳይ ሆነን ቀርበናል አሉ። ከቀበሌ ሊቀ መንበሩ ይልቅ ሚንስትሩን ስናነጋግር ሊፈቀድልን የሚችለው አካላዊ ርቀት የትየለሌ ነው። ገንዘብና ሥልጣን ካለ መጠነ ሰፊ አካላዊ ርቀት አለ። ለምሳሌ አውሮፕላን ገንዘብ ላለው ተጓዥ ሁሉ የተፈቀደ ቢሆንም፣ ሁሉም ባለገንዘብ ግን እኩል አይገለገልበትም። የጆርጅ ኦርዌልን ድንቅ አባባል ለዚህ ጽሁፍ ስንል ብናሻሽለው “ሁሉም ተጓዦች እኩል ናቸው፣ ነገር ግን ጥቂት ተጓዦች ከሌሎች ይበልጥ እኩል ናቸው” እንዲል … የቢዝነስ ክላስ ተጓዥ እግሩን አንሰራፍቶ ሲንደላቀቅ፣ የኢኮኖሚ ክላስ ተጓዥ ግን የሚመተርለት የሥፍራ መጠን ብዙ የሚያፈናፍን አይደለም። ስለሆነም የሁለት ሜትር የእርስ በርስ መራራቅ ትግበራ ጥሩ ገቢ ላላቸው ግለሰቦች የምርጫ ጉዳይ ሲሆን ለደሃ (በደሳሳ ቤት ጠላ/ሻይ ለምትሸጠው፣ ጉልት ሽንኩርት ለምትቸረችረው፣ የከተማ አውቶቡስ ለሚጠቀመው፣ ወዘተ) ግን ቅንጦት ነው። ልክ ቻርለስ ዲክንስ “space is a luxury”  እንደሚለው።
ደሃ ሞት አይፈራም?
በበርካታ የመድረክ ስዎች “ኮሮና ደሃና ሃብታምን እኩል አደረገ” ተብሎ ሲወደስ ይደመጣል። በጥልቀት ቢታይ ግን የኮቪድ-19 ጥቃት ከሃብታሙ ይልቅ በድሃው ላይ በእጅጉ የሚያይል መሆኑን ነው። ለድሃ “መቀመጥ” ማለት “መቆመጥ” ነው እንዲሉ፤ ለክፉ ጊዜ ተብሎ የሚቀመጥ እርሾ ስለማይኖር፤ እንቅስቃሴ ሲቆም ህይወትም ትጨልማለች። የኒውዮርክ ታይምስ መጽሄት አንደዘገበው፤ በኒውዮርክ ከተማ ከበርቴዎች ከሚኖሩባቸው ሰፈሮች የኮሮና ወረርሺኝ በከተማቸው እንደተከሰተ ወደ 40% የሚሆኑት ኗሪዎች በሽታው ወዳልተንሰራፋባቸው አካባቢዎች መሸሽ ችለዋል። መሸሽ ያላስፈለጋቸው ሀብታሞች ደግሞ ከቤታቸው ሳይወጡ የሚፈልጉትን በቀላሉ እያገኙ ሰንብተዋል። በተቃራኒው በኩል ደግሞ በኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅተኛ የሆኑት ጥቁሮችና እስፓኞች መኖሪያቸውን ሳይለቁ ወላፈኑን እየተጋፈጡት ይገኛሉ። ለምሳሌ በአሜሪካ የሚዘወተር አባባል አለ፡- “አሜሪካ ስታስነጥስ ጥቁር ድሆቿ በኒሞኒያ ይያዛሉ”። በቅርቡ ይፋ የተደረገ ሪፖርት የሚያሳየው፤ ከሌላው ማህበረሰብ ይልቅ ጥቁሮች በኮቪድ-19 የበለጠ ተጠቅተዋል። አመዛኙ የሥራ ዘርፋቸው ጽዳት፣ ጤና፣ ጥበቃ፣ ሾፌር፣ እቃ አቅራቢ፣ ታክሲ አገልግሎት ወዘተ-- በመሆኑ ደግሞ ከኮሮና ጋር በሚደረገው ትግል፣ የግንባር መስመር ተሰላፊና ተጋላጭ አድርጓቸዋል።
እንደ ሪቻርድ ፓንክረስት፤ በ1918 (እ.ኤ.አ.) አዲስ አበባ በወቅቱ ከነበራት 50,000 ኗሪ ወደ 10,000 የሚሆኑት (20%) በተለይም ወጣቱ፣ ባለሥልጣናቱና በጣት ከሚቆጠሩት ዶክተሮችም ጭምር በህዳር በሽታ ህይወታቸው ተቀጥፏል። የሃያ ስድስት ዓመቱ ራስ ተፈሪ መኮንን በመጀመሪያው ዙር ወረርሺኝ ተጠቅተው በህይወትና ሞት መሃል የነበሩ ሲሆን “በለጋ እድሜያቸው ሊሞቱ ነው” ተብሎ በዲፕሎማቶች መሃል የመረጃ ልውውጥ እየተካሄደ ነበር። ራሳቸው ወደ አዲስ አበባ እንደተመለሱ በወረርሺኙ ሳቢያ ክፉኛ ታመሙ እንጂ ፊታውራሪ ሃብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ ለስራ ተልከው ከነበሩበት የወላይታ አውራጃ ባስቸኳይ ተመልሰው በተፈሪ መኮንን ሞት ሊፈጠር የሚችልን አለመረጋጋት እንዲያመክኑ ታቅዶ ነበር፡፡ በወቅቱ ወረርሺኙን ለመሸሽ አቅሙ የነበራቸውና ወደ ከተማው ዳርቻ በመሄድ ተወሽበው (ቀሣ ገብተው) ህይወታቸውን ያዳኑት ለምሳሌ ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ማቴዎስ (አድዋ ድረስ ሄደው ግንባራቸውን ለጥይት ለመስጠት ያላመነቱት)፣ ከንቲባ ነሲቡ ዘአማኑኤል (ወዲያውኑ ወደ ከተማይቱ ተገደው ተመለሱ’ንጂ)፣ የበታች ሹማምንቶች፣ ወዘተ ነበሩ። ንግስት ዘውዲቱ ራሳቸው ወደ አንኮበር ለመሸሽ ተነስተው ነበር ተብሎ በወቅቱ ታምቷል፡፡ በዘመኑ ወደ አዲስ አበባ ከተማ ዳርቻ ባይሄዱም፣ በርካቶች በሚኖሩበቸው ግቢዎች ውስጥ ተራርቆ ለመቆየት የሚያስችል መተናፈሻ ነበራቸው። ለሥልታዊ ማፈግፈግም’ኮ ቦታና ፍራንክ ሊኖር ግድ ይላል።
ረሃብ ቀጠሮ ይሰጣል?
በኢትዮጵያ ሚዲያ የሚተላለፉትን መረጃዎችን ስንቃኝ፣ የማኅበራዊ ፈቀቅታን ጣጣ በቅጡ ያለመረዳት ጉዳይ ይስተዋላል። የኮሮናና የማኅበራዊ ፈቀቅታ ግንዛቤ ሃዋርያ ሆነው የቀረቡት ከሃኪሞቹ ይልቅ አርቲስቶቻችን ናቸው። ጥረታቸው ይደነቃል። ሆኖም ግን ሁሉም ናቸው ባይባልም አንዳንዶቹ ገና ራሳቸው በውል የተረዱት አይመስልም። ከዚህ ቀደም ገበሬው ዛፍ ቆርጦ ለተለያየ ግልጋሎት ሲጠቀም “ለምን” ብሎ የችግሩን ምንጭ ከመመርመር ይልቅ በየመድረኩና በየሚዲያው ልክ ገበሬው የዛፍን ጥቅም እንደማያውቅና አሉታዊ ውጤቱንም እንደማያስተውል፤ ወይንም አማራጭ ኖሮት ሳለ በግዴለሽነት እንደሚከውነው በመተርጎም- ልክ የወተትን ጥቅም ለድመት ማስተማር በመሰለ ምክር- በእርዳታ ሰጪዎች በጀት እየተደጎመ፣ በራዲዮና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ይሰራጭ ነበር። ሌላም አለ። “ከወንዶች ይልቅ ሴቶች ለኤች-አይ-ቪ ኤድስ ተጋላጭ ናቸው” ሲባል ልክ ወንዶቹ የኤድስን አስከፊነት የተገነዘቡና ሴቶቹ ደግሞ ለሕይወት ዋጋ የማይሰጡ ይመስል፣ “የግንዛቤ ማስጨበጫ ዲስኩሮች” እየተንቆለጳጰሱ ለህዝብ ይቀርቡ ነበረ። አሁን ደግሞ ስለ ኮቪድ-19 አስከፊነት ተነግሮ ሳለ ህዝቡ በከተማው ሲንቅሳቅስ ታየ ተብሎ አንዳንድ አርቲስቶቻችን “ዳቦ በነጻ ይታደላል የተባለ ይመስል ህዝቡ በከተማው ተተራመሰ” በማለት ሲናገሩ በድራማዎቻቸው እየታዘብን ነው። ህዝብን በደፈናው መኮነን አግባብ አይደለም። ጥቂቶች ለቅንጦት ሲሉ ያጠፋሉ። ለምሳሌ በሺሻና ጫት ቤቶች ታጉሮ በመገኘት ሊሆን ይችላል። አብዛኛው የሚንቀሳቀሰው ግን የሞት ሽረት ጉዳይ ሆኖበት ነው። ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድኅን፣ የረሃብን አስከፊነት እንዴት ነበር በግጥም የገለፀው?
ጠቅጥቅ ዝም ብለህ?
ከመሃል አዲሳባ ተነስተን በሁሉም አቅጣጫ ወደ ከተማዋ ዳርቻ ብንጓዝ፣ የሰዎች ቁጥር እየቀነሰ፣ በቤቶች መሃል ያለው ርቀት እየሰፋና የግቢዎች ስፋት እያደገ መሄዱን እንታዘባለን። እንዳሁኑ ከመጠን በላይ ከመተፋፈጉ በፊት በአዲሳባ በርካታ ባዶ ሥፍራዎች የነበሩ ቢሆንም ከጊዜ ወደ ጊዜ ተመናምነዋል። በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በሰባዎቹና በሰማንያዎቹ የተቀረፁ የሙዚቃ ክሊፖች የሚያስገነዝቡን ነገር ቢኖር፣ መሃል አዲሳባ በሰውም ሆነ በተሽከርካሪ ብዛት እንዳሁኑ መተናፈሻ አላጣም ነበር። አሁን አሁን የሙዚቃ ክሊፖች እየተቀረጹ ያሉት በከተማዋ ዳርቻ ከሚገኙ ተራርቀው የተገነቡ ቅንጡ መንደሮች ላይ መሆኑ የግጥምጥሞሽ ጉዳይ ብቻ ይሆን? በተለይም መሃል አዲሳባ አካባቢ የነበሩ ማናቸውም ቤት ያላረፈባቸው ሥፍራዎች (በዛፍና በጓሮ እርሻ ተሽፍነው የነበረ ቢሆንም እንኳ) ለግንባታ ማስፋፊያ ውለዋል። ቀድሞ በየመንደሩ የነበሩ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ደብዛቸው ጠፍቷል። ተጨማሪ የመኖሪያ ክፍሎችን ሰርቶ በማከራየት ኑሮን መደጎም ስለሚቻል በርካቶች በመኖሪያ ግቢያቸው የነበሯቸውን ባዶ ሥፍራዎች ገንብተውበታል። ባንዳንድ ሰፈሮች በከተማው ፕላን መሰረት፣ ቀድሞ በቂ ሥፋት የተመደበላቸው መንገዶች ከአዋሳኝ ጊቢዎች በሚደረግ ህገወጥ ማስፋፊያ እየተሸራረፉ በእጅጉ ጠበዋል። ችግሩ በበረታባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ጠባብ የመተላለፊያ መንገዶች ለልብስና ጌሾ ማስጫ፣ ለድንኳን መትከያ፣ ወዘተ-- ጭምር ስለሚያገለግሉ የእድር መኪና እንኳ የማይገባባቸው በርካታ መንደሮች አሉ። አያርገውን’ጂ እንዲህ አይነት መንደር ኮቪድ-19 አንዴ ከገባ በቀላሉ አጅ ይሰጣል?
እል፟ፍ ሲሉ እልፍ ይገኛል?
አንድ የከተማ ኗሪ የኢኮኖሚ አቅሙ ሲጎለብት ፍላጎቱም ሆነ ስጋቱ ስለሚንር ወደ ከተማ ዳርቻ ሄዶ (suburbanization በሚባለው) አመቺ የመኖሪያ ቤት ይገዛል/ይከራያል። ባብዛኛው ይህ ሥፍራ ወንጀል የማይበዛበት፤ የትምህርት ቤት ክፍሎች የማይጣበቡበትና የመኪና ማቆሚያ እጥረት የማይኖርበት ነው። የሞላለት ኗሪ ወደ ዳርቻው በተዘዋወረ ማግስት በምትኩ ወደ ከተማው የሚመጣው አዲስ ኗሪ ይተካበታል። ከተማ ሲሰፋ በዙርያው ያሉ የእርሻ መሬቶችን ይበላል፤ በፍትሃዊነትም ይሆን በኢ-ፍትሃዊነት አርሶ አደሮችን ያፈናቅላል። ለአብነት ሕዝቡን አስተባብሮ በቀድሞው የኢሕአዴግ መንግሥት ላይ ከፍተኛ ጫና ካደረጉ አጀንዳዎች አንዱ የአዲሳባ ከተማ ቅጥ አልባ መስፋፋትና ማስተር ፕላኑ ያስከተለው ጣጣ ነበር።
ለአዲሳባ የህዝብ እድገት አንዱ መንስዔ፣ ከሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ወደ ከተማው የሚፈልሰው ቁጥር መበራከቱ ነው። ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ከተሞች ላይ የተደረገ ጥናት አንደሚያሳየው፤ ከከተሞች ርቀው በሚኖሩ ህዝቦች የሚዘወተር የጎሳዎች መሃል ጥርጣሬና ግጭት አለ። ይህ የደህንነት ሥጋት በርካቶቹን ወደ ከተሞች እንዲጎርፉ ያነሳሳቸዋል (push factor የሚባለው)። በበርካታ ክልሎች የሚገኙ ባለሃብቶች ካፒታል ሲያፈሩ፣ በቀጣይ የሚያልሙት በአካባቢያቸው የሚገኝ ንግዳቸውን ወደላቀ ደረጃ ማሳደግ ሳይሆን ወደ አዲሳባ በመምጣት ቤት መግዛትና ኑሮን መመስረት ነው። ወደ አዲሳባ ከተማ የሚደረገው ፍልሰት እንዲጨምር ያስቻለው ከተማው በአማላይ የኢኮኖሚ አማራጮች (pull factors የሚባሉት) ተንበሽብሾ ሳይሆን በከፊልም ቢሆን አንጻራዊ የኑሮ ዋስትና ስለተጎናጸፈ ጭምር ነው።
ችግሩ ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአዲሳባ ዳርቻ ያሉ መንደሮች በፖለቲካው ትኩሳት ሳቢያ የሰላምና የመኖር ዋስትናቸው ከጥያቄ ውስጥ መውደቁ ነው። ባንድ በኩል ወደ አዲሳባ በተናጠልም ሆነ በቡድን የሚተመው ሕዝብ እንደቀጠለ ነው፡፡ ለምሳሌ አማራው ከጉራ ፈርዳ፣ ኦሮሞው ከሶማሌ ክልል ሲፈናቀሉ መዳረሻቸው አዲሳባ እንደነበር ተመልክተናል፡፡
በሌላ በኩል፤ አዲሳባ እንደ ቀድሞው ወደ ጎንዮሽ የመስፋት እድሏ ተመናምኗል። ይባስ ብሎ ቀድሞ በከተማው ዳርቻ መንደሮች የነበሩ አንዳንድ ኗሪዎች ወደ መሃል አዲሳባ የሚደረግ የምልሰት አዝማሚያ (reverse suburbanization) እያሳዩ ነው።
እንደ  መውጫ
የከተማ ኗሪ ለኮቪድ-19 አጅግ ተጋላጭ ቢሆንም በደንብ ከተያዘ ስርጭቱን መቆጣጠር ይቻላል። ታይዋን፤ ደቡብ ኮርያና ሲንጋፖር ከተሞች ችምችም ያለ የሕዝብ ሥርጭት ኖሯቸው ሳለ አስቀድመው እርምጃ በመውሰዳቸው ነው አስከፊውን የኮሮና እልቂት ያስቀሩት።  የኮቪድ-19 ክትባት እስኪገኝ ድረስ ማኅበራዊ ፈቀቅታን በአግባቡ መተግበር ወሳኝ የቫይረሱ መከላከያ ሆኖ ይቆያል። በህዳር በሽታ ወቅት ተተግብሮ የነበረው አገር በቀል የማኅበራዊ ፈቀቅታ በርካታ ኢትዮጵያውያንን አትርፏል። ይህ ትውልድ ደግሞ የራሱ መፍትሄ ያሻዋል። ከሌሎች ሃገራት መኮረጅ ካለበትም ከአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር እየተገናዘበ መሆን ይኖርበታል። የችግሮች መጠንና ውስብስብነት ከሥፍራ ሥፍራ እንደ መለያየቱ ሁሉ መፍትሄውም ያልተማከለ መሆን ይኖርበታል። ለዚህ ስኬት እንዲረዳ ደግሞ በሃገሪቱ ያሉ የፕሮፌሽናል አሶሴሽኖች የዘንድሮውን አመታዊ ኮንፈረንሶቻቸውን (ቨርቹዋሊም ቢሆን) በኮቪድ-19 ላይ አትኩረው አባላቶቻቸው የመፍትሄው አካል እንዲሆኑ ይተጉ ይሆን?
በሌሎች ሃገራት የኮሮና ቫይረስ ቅድሚያ ሰለባዎች በበሽተኛ መንከባከቢያ ጣቢያዎች (Nursing Homes) የሚገኙ ታካሚና ነርሶች ነበሩ።  ይህ እንዳይደገም በአዲስ አበባ ከተማ ያሉ በርካታ የአረጋውያን ማዕከላት መላ እየዘየዱ ይሆን? በተለይም የምስራቁን ድንበራችን በባህሪው ወንፊታማ በመሆኑ በድንበር ተሻጋሪ የሰዎች ዝውውር ላይ የቁጥጥር ሥርዓት ተዘርግቶ ይሆን?
የቅርብ ጊዜ የኢትዮጵያ ታሪክ የሚያሳየን ታላላቅ አደጋዎች፣ የቀድሞ መንግስታት መሰረትን ሲያናጉና በቀጣይ አመታትም መንግሥታቱ እንደሚወድቁ ነው። በንጉሡ ጊዜ የወሎ ረሃብን፣ በደርግ ጊዜ የሰባ ሰባቱ ረሃብን መጥቀስ ይቻላል። አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት፤ ይህን ወረርሽኝ ቀዳሚ አጀንዳው አድርጎ፤ ዜጎችን አስተባብሮ፤ እውቀት-መር በሆነ መንገድ ሕዝቡን ይታደጋል? ወይንስ ችግሩን በማለባበስ ለውድቀቱ ጉድጓድ ይምሳል? የተቃዋሚ ፓርቲዎችስ? አጀንዳቸውን ፈታኝ በሆነው የኮቪድ-19 ወረርሺኝ ላይ አተኩረው ከሕዝቡ ጋር ይረባረባሉ? ወይንስ እንደ ወትሮው ስቱዲዮና መድረክ ላይ ከትመው በታዛቢ ማሊያ ይጫወታሉ?
በመጨረሻም፤ ፈተናው ይከብድ ይሆናል እንጂ ሁሉም ያልፋል፤ ኮሮና ቢሆንም’ኳ፡፡


Read 1398 times