Print this page
Saturday, 06 June 2020 14:39

የፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

      “ኮሮና” እና የሽግግር መንግስት!
በምርጫ 97 ወቅት ሰኔ 1 እንዲሁም ጥቅምት 23 እና 24 በዋናነት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በተካሄደው ጭፍጨፋ ማን ምን ሚና ነበረው? የግንቦት 30ው ወረቀትስ እንዴት ተቀነባበረ? በማንስ ተበተነ? ወዘተ የሚለው የማይታለፍ እንደሆነ ቢታወቅም፣ ይህ ግን ለኔ ለጊዜው ወቅታዊ አይደለም። በተመሳሳይ ከ2010 ለውጥ ወዲህ ከተካሄዱ ፍጀቶች በስተጀርባ የማን ሚና ምን ነበር? የሚለውን ጨምሮ የቅርቡ የ86ቱ ሟቾችም ጉዳይ በተመሳሳይ የማይታለፍ ቢሆንም፣ አሁን ላይ ሰዎቹን ከሚጠረጠሩበት ጉዳይ ጋር አያይዞ ማንሳቱ ፋይዳ የለውም።
ፋይዳ የማይኖረው የጥፋተኛነትም ሆነ የጸጸት ስሜት የሌለባቸውን ሰዎች በማያፍሩበት ምናልባትም በሚኮሩበት ጉዳይ ለመግጠም መሞከር የሚለውጠው ነገር ስለማይኖር ነው። አንዳንዶች የሚገርማቸው ከዚያ ሁሉ ወንጀልና ነውር በኋላ ግለሰቦች አደባባይ ሲወጡ በአደባባይ የሚደግፏቸውና ፌስቡክ ላይ የሚያጨበጭቡላቸው ሰዎች መገኘታቸው ነው። መታወቅ ያለበት ለነዚህ ወገኖች ድጋፍ የሚሰጠው ጽንፈኛው ብሄርተኛ ሃይል መሆኑ ግልጽ ነው።ይህ ሃይል ደግሞ በጭፍን ብሄርተኝነት ድንዛዜ ውስጥ ያለ በመሆኑ መቃወሙን እንጂ ውጤቱ ምን እንደሚሆን አይረዳውም። የሚገባው ወይንም የሚባንነው አዲስ አበባ አሌፖ፣ ኢትዮጵያም ሶርያ ሲሆኑ ነው። ይህ ሃይል በማናቸውም ሁኔታ ሥርዓት እንዲፈርስ የሚቋምጥ፤ በጥላቻም ሆነ በሌላ ተቃውሞ ለተባለ ነገር ሁሉ ድጋፍ የሚሰጥ በመሆኑ ይህን በድንዛዜ ውስጥ ያለ ሃይል በአምክንዮ ማንቃት አይቻልም።
በዚህ ወይንም በዚያ ብሄር ሥር የተኮለኮለው ድንዛዜ ውስጥ ያለው ሃይል የጥላቻ፣ የዘረፋና የሰቆቃ ፊታውራሪዎች የሆኑት ስብሃት ነጋ፣ የአማራ ነጻ አውጪ ነኝ ብለው ቢመጡ የሚያጨበጭብ፤ አባይ ጸሃዬ ኦሮሞ ን ነጻ ላወጣ ነው ቢሉ የሚከተል፤ ጌታቸው አሰፋ የደቡብ ብሄሮችን ልታደግ ነው ቢሉ ቀይ ምንጣፍ የሚዘረጋ ወዘተ መሆኑን የሚጠራጠር የድንዛዜያቸውን መጠን ያልተረዳ ብቻ ነው።
በመሆኑም ለማይሰሙት የሥልጣን ረሃብተኞች፣ ሃጢያታቸውን ከማስታወስ እንዲሁም በድንዛዜ ውስጥ ያሉ ተከታዮቻቸውን ለማንቃት ከመጨነቅ፣ ግለሰቦቹ የትናንት ወንጀላቸውን እንዳይደግሙት መንግስት የሕዝቡን ሰላምና ደህንነት የመጠበቅ ሕጋዊ ሃላፊነቱን እንዲወጣ ማሳሰቡ አስፈላጊ ይሆናል። እንደ ፓርቲ ለመመዝገብ አራት ሺህ ፊርማ ማሰባሰብ ያልቻሉ የት ይደርሳሉ፣ የሚለው ንቀትም ተገቢ አይመስለኝም።
ግለሰቦቹ የራሳቸው ችግር ቢኖርባቸውም፣ መንግስት በሕገ ወጥ መንገድ ሥልጣኑን የሚያራዝምበት ሁኔታ ውስጥ ከገባም በጉዳዩ ላይ መወያየቱ ክፋት የለውም።ለዚህ ምላሽ ለማግኘት ግን ሥልጣን ያለው መንግስት ምርጫውን ለማካሄድ ፍላጎት ነበረው ወይንስ አልነበረውም ? የሚለውን መጠየቅ ግድ ይላል። ቀን ተቆርጦ ዝርዝር መርሃ ግብር ወጥቶ ሂደቱ በቀጠለበት የኮሮና ቫይረስ መከሰቱ በፈጠረው ስጋት ምርጫው መስተጓጎሉ ግልጽ ሆኗል። በዚህ ሂደት ውስጥ መንግስት ምርጫው እንዲራዘም መፈለጉን የሚያሳይ ሁኔታ በግሌ አልታየኝም። ይህ የመቶ ሺህዎችን ሕይወት የቀጠፈውና ሚሊዮኖችን የለከፈው ኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) እንኳን ምርጫ አድርጋ የማታውቀውን ኢትዮጵያን በምርጫ ውስጥ ክፍለ ዘመናት ያስቆጠሩትን አጣብቂኝ ውስጥ አስገብቷል። እንኳንስ ግለሰቦችና ቡድኖች ሕግ ሆነው በኖሩባት ኢትዮጵያ ይቅርና ሕግና ሥርዓት ለዘመናት በገነባችው አሜሪካ ሕገ መንግስት ላይ ኮሮና ቫይረስ እያንዣበበ ይገኛል።
International Institute for Democracy and Electoral Assistance (IDEA) የተባለ ተቋም ይፋ እንዳደረገው፤ እ.ኤ.አ ከየካቲት 21 እስከ ሚያዚያ 29 ቀን 2020 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ 52 ሃገራት የምርጫ ጊዜያቸውን አሸጋሽገዋል። ከእነዚህ ውስጥ 17ቱ ያሸጋገሩት ዋና ምርጫና ሪፈረንደም ሲሆን፣አሜሪካውያንም ከ175 ዓመታት በኋላ የምርጫ ቀን ልንቀይር ይሆን ወይ ? የሚል ጥያቄ ማንሳታቸው ይፋ ሆኗል። የአሜሪካው ዕጩ ፕሬዚዳንት ዴሞክራቱ ጆ ባይደን በመጪው ህዳር 3 ቀን 2020 የሚካሄደውን ፕሬዚዳንታዊ ውድድር፣ ትራምፕ በኮሮና አሳብበው ሊያሻግሩት ይሞክራሉ ሲሉ ከሰዋል። ይህንን ተከትሎም፣ በአሜሪካውያኑ ዘንድ የህግ ክርክር ተነስቷል። በርግጥ የምርጫ ቀኑን የመለወጥ ስልጣን የፕሬዚዳንቱ ሳይሆን የኮንግረሱ መሆኑን ዋሺንግተን ፖስት የህግ ባለሙያዎችን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል። ኮንግረሱም ቢሆን በየአራት ዓመቱ በህዳር ወር የመጀመሪያው ማክሰኞ ምርጫ ይካሄዳል የሚለውን ከ1845 ጀምሮ የተተከለውን የምርጫ ቀን ማሻሻል ቢችልም፣ የምርጫ ቀኑን በሳምንታት መግፋት እንጂ ፥ፕሬዚዳንት ትራምፕ እ.ኤአ ከጥር 20 ቀን 2021 እኩለ ቀን በኋላ በኋይት ዋይስ  ቤተ መንግስት ውስጥ እንዲቆዩ የማድረግ ስልጣን የለውም። ሁኔታው ወደዚያ ካመራ ሕገ መንግስታዊ ማሻሻያ የግድ የሚል መሆኑን አሜሪካውያኑ የህግ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
ምርጫቸውን በፖስታ ቤት ጭምር መላክ በሚችሉት አሜሪካውያን ላይ የኮሮና ቫይረስ ተጽዕኖ የጎላ እንደማይሆን ቢታመንም 2/3 ኛ የሚሆኑት አሜሪካውያን ኮሮና ቫይረስ የአሜሪካንን ፕሬዚዳንታዊ ምርጭ ሊያስተጓጉል እንደሚችል ስጋታቸውን መግለጻቸውን የአሜሪካውያኑ የጥናት ተቋም ፒው ሪሰርች ከ10 ቀናት በፊት ይፋ አድርጓል። ኮሮና ቫይረስ ለዓለም ሕዝብ ምን ያህል ፈተና እንደሆነ በዝርዝር ማየቱ ያስፈለገው የኢትዮጵያን ሁኔታ ከዚያ አንጻር ለመመዘንም ጭምር ነው።
ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ሕገ መንግስት የፓርላማውም ሆነ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የስልጣን ዘመን የሚያበቃው መስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም ነው። (እነ ጃዋር መስከረም 30ን ከየት እንዳመጡት አይገባኝም። ምክንያቱም ፓርላማው ስልጣኑ የሚያበቃው በ2013 ዓ.ም የመጨረሻው ሰኞ፣ መስከረም 25 ነውና) ፓርላማው የስልጣን ዘመኑ ከማብቃቱ በፊት ባለው አስገዳጅ ሁኔታ ስልጣኑን ለማራዘም ያለውን አማራጭ በተመለከተ መንግስት በባለሙያ ማስጠናቱን ይፋ አድርጓል። ጥናቱን ያካሄዱት ባለሙያዎች መሆናቸው ከመነገሩ ባሻገር ያቀረቧቸው አማራጮች ሕገ መንግስታዊ መሆናቸውን ሌሎች ገለልተኛ ባለሙያዎችም እየመሰከሩ ነው። የሽግግር መንግስት ብሎም ከዚያ አለፍ ያለ ጥሪ ለማድረግ በአንድ መድረክ በተገኙት አቶ ልደቱና አቶ ጃዋር መካከል እንኳን በዚህ ዙሪያ አንድነት የለም። ልደቱ ሕገ መንግስቱን በማሻሻል ማራዘም ሕጋዊ መሆኑን ተቀብሎ ግን በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ያስገምታል ሲል ጃዋር ደግሞ ምንም ሕጋዊ ምክንያት የለም ሲል ተደምጧል። አወያዩ ግርማ ጉተማም ጉዳዩን ለማጥራት ያልፈለገው፣ ለማስተላለፍ በወሰኑት የጋራ መልዕክት ላይ ውዥንብር እንዳይፈጠር ይመስለኛል።
ህገ መንግስቱን ለማራዘም ህጋዊ መንገድ ካለና ይህም በአስገዳጅ ሁኔታ የተገባበት ከሆነ የሽግግር መንግስት ለምን ያስፈልጋል? ከሽግግር መንግስት የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያተርፈው ምንድን ነው? እነማን ይሳተፋሉ? መመዘኛው ምንድን ነው? የሕወሃት አጫዋች የነበሩና ለውጥ እንዳይመጣ ከሕወሃት ጎን ሆነው የታገሉትስ ይሳተፋሉን? ሕወሓትስ እንደ ደርግ/ኢሰፓ ይገለላል? ወይንስ ይሳተፋል? ከ10 የማያንሱ የኦሮሞ ድርጅቶች እንዳሉ ይታወቃል። ለነዚህ የሚሰጠው ወንበር ከሕዝብ ቁጥር ፕሮፖርሽን አንጻር ይሆናል ወይንስ እንዴት ይደለደላል? ማን ምን ያህል ወንበር እንደሚያገኝ መመዘኛው ምንድን ነው? የካቢኔ ቦታ የሚሰጣቸው ድርጅቶች እነማን ይሆናሉ? በምንስ መመዘኛ?
አንዳንዶቹ ተጽዕኖ ፈጣሪ ድርጅቶችና ግለሰቦች መለያቸው ይበልጥ ረብሻና በግርግር ከመሆኑ አንጻር የሽግግር መንግስቱ እነሱን ቀና በማድረግ ሁከት ማንገስ እንጂ መረጋጋት እንዲመጣ ያደርጋልን? ሃገራዊ ራዕይና ኢትዮጵያዊነት እየለመለመ፣ አክራሪነት እየከሰመ ባለበት ሁኔታ ውስጥ አክራሪዎች የበዙበት የሽግግር መንግስት፣ የትናንት ጭለማን ከመጥራት ውጭ ምን መፍትሄ ያመጣል?
ለኢትዮጵያ መድህን የሚሆናት ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ነው። ለዲሞክራሲያው ምርጫ ደግሞ መረጋጋት ያስፈልጋል። ለመረጋጋት ደግሞ የተረጋጋ መንግስት ግድ ይላል። የተረጋጋ መንግስት እንዲቀጥል ደግሞ ሁላችንም ከሕግ በታች መሆናችንን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። በለውጡ ማግስት የተፈጠሩ ግርግሮች እንዳያገረሹ የሚያሳስበን ዜጎች ትግል እየሸጡ የከበሩና በብሔረሰብ ተሟጋችነት ሞት የሚነግዱትን የህወሓት ጉዳይ ፈጻሚዎችን እረፉ ልንላቸው ይገባል፡፡
(ከሲሳይ አገና ፌስቡክ)
***

Read 1246 times
Administrator

Latest from Administrator