Print this page
Saturday, 06 June 2020 14:38

የመሳሳም ጥበብ

Written by  ደራሲ - ጌ ደ ሞፓሳ ትርጉም - አንተነህ ይግዛው
Rate this item
(3 votes)

      የኔ ውድ…
ባልሽ ጥሎሽ ስለሄደ አለም ጨለመብሽ አይደል?... የምታደርጊው ግራ ቢገባሽ፣ ነጋ ጠባ ተንሰቅስቀሽ ታለቅሻለሽ አይደል?... የኔ ምስኪን… አልቅሰሽ አልወጣልሽ ቢል፣ ዙሪያው ገደል ቢሆንብሽ፣ መላ ቅጡ ቢጠፋሽ… እኔን አሮጊቷን አክስትሽን “ምን ይሻለኛል ይሆን?” ብለሽ፣ ምክር እንድለግስሽ ጠየቅሽኝ፡፡ አይ አንቺ!... ‘አክስቴ በፍቅር ጉዳይ ላይ ጥልቅ እውቀት አላት’ ብለሽ በማሰብ ነው አይደል፣ ምክሬን ፍለጋ ወደ እኔ የላክሽብኝ?... እውነቴን ልንገርሽ… የምታስቢውን ያህል ሁነኛ መፍትሄ ልሰጥሽ እችል እንደሆን አላውቅም፡፡ እርግጥ ሌሎችን የማፍቀርን ወይም ራስን ተፈቃሪ የማድረግን ጥበብ ጭራሽ የማላውቅ ፍጹም መሃይም ሰው አይደለሁም፡፡ አየሽ የኔ ውድ… አንቺ በተወሰነ ደረጃ ይጎድልሻል ብዪ የማስበው፣ ራስን ተፈቃሪ የማድረግ ጥበብ ነው፡፡ ልክድሽ አልፈልግም፣ እኔም በአንቺ እድሜ እንዲህ ነበርኩ፡፡ በአጠቃላይ አንቺ ማለት ለባለቤትሽ ትኩረት፣ ፍቅር፣ መሳሳምና መደባበስ እንደሆንሽ ነግረሽኛል፡፡ የችግሩ ዋነኛው ምንጭ ይህ ሊሆን ይችላል፡፡ እንደሚመስለኝ ባልሽን በወጣ በገባ ቁጥር ትስሚዋለሽ፡፡ የኔ ውድ፣ እኛ እኮ… በአለም ላይ አቻ የሌለውን ታላቅ ሃይል ነው በእጆቻችን የያዝነው፡፡ ይህ ሃይል ፍቅር ይባላል፡፡ ወንድ በአካላዊ ጥንካሬ የታደለ በመሆኑ፣ ሃይል መጠቀምንም ያዘወትራል። ሴት ደግሞ በተራዋ ውበትን ታድላለች፡፡ አቅፋ እየደባበሰች ነው የምታሸንፈው፡፡
ለእኛ ለሴቶች፣ ውበታችን በዋዛ የማይረታና የማይበገር መሳሪያችን ነው፡፡ ታዲያ ግን አጠቃቀሙን ካላወቅንበት ዋጋ የለውም፡፡ እኛ የአለሙ ሁሉ እመቤቶች መሆናችንን በሚገባ መረዳት አለብሽ!!... ከዘፍጥረት አንስቶ ያለውን የፍቅርን ታሪክ መናገር፣ የራሱን የሰው ልጅን ታሪክ መተረክ ማለት ነው፡፡ ሁሉም ነገር የሚመነጨው ከፍቅር ነው፡፡ ጥበባትም ሆኑ ታላላቅ ሁነቶች፣ ጦርነቶችም ሆኑ የነገስታት ውድቀቶች ሁሉም ፍቅር ነው መነሻቸው፡፡ የመጽሃፍ ቅዱስ ታሪኮችን ፈትሺ፣ ደሊላንና ዮዲትን ታገኛቸዋለሽ፡፡ በተረቶች ውስጥ እነ ሄለንን፣ በታሪክ ድርሳናት ደግሞ እነ ክሊዮፓትራን፣ ኸረ ስንቶችን!… ብዙ ብዙ ተጠቃሽ ሴቶችን እናገኛለን። እኛ ሴቶች ታላላቆችን አስገብረናል፣ በሃያላን ላይም ነግሰናል፡፡ ይሄም ሆኖ ግን፣ እንደ ንጉሳውያን ሁሉ፣ ተለሳልሶ የማስገበርን ጥበብ መጠቀም ግድ ይለናል። የኔ ውድ… ፍቅር የሚገነባው፣ ጎልተው ከማይታዩ ጥቃቅን ስሜቶች ነው፡፡ ፍቅር የሞትን ያህል ብርታት እንዳለው እናውቃለን፡፡
ያም ሆኖ ግን፣ እንደ ሸክላ በቀላሉ ተሰባሪ ነው፡፡ ተሰብሮ ለመድቀቅ ትንሽ ነገር ነው የሚበቃው፡፡ ፍቅር በትንሽ ነገር ሲሰበር፣ አይሆኑ ሆነን ልንነካክት እንገደዳለን፡፡ የታጠቅነው ሃይል ተሟጦ ያልቃል፡፡ ዳግም ነፍስ በማንዘራበት፣ አገግመን በማንነሳበት በአጉል ቀውስ ውስጥ እንወድቃለን፡፡ እኛ ሴቶች ራሳችንን በሌሎች ዘንድ ተፈቃሪ የማድረግ ታላቅ ሃይል ቢኖረንም፣ አንዲት ትንሽዪ ነገር ትጎድለናለች፡፡ ይህም ሌሎችን መንከባከብ የምንችልባቸውን የተለያዩ መንገዶች በተመለከተ ግንዛቤ አለመያዛችን ነው፡፡ ወንዶችን አጥብቀን ስንናፍቅና እኛነታችንን ሙሉ ለሙሉ ለእነሱ ስንሰጥ፣ ተሰባሪ መሆናችንን እንዘነጋለን፡፡ ይሄኔ ልቡን ገዝተነዋል ብለን የምናስበው ወንድ፣ የራሱ አለቃ ሆኖ ይቀራል፡፡ ለአድናቆት ብለን የምንሰነዝራቸውን ቃላት ከሞኝነት መቁጠር ይጀምራል፡፡ አደራሽን የኔ ውድ… ራሳችንን ከጥቃት የምንከላከልበት ጥሩር በወጉ ያልተሰራ መሆኑን ልብ በይ! እውነተኛው ሃይላችን የሚገለጠው መቼ እንደሆነ ታውቂያለሽ?... ስንስማቸውና ስንስማቸው ብቻ!... መሳማችንን እንዴት መጀመርና መጨረስ እንዳለብን በተረዳን ጊዜ፣ ያኔ የንግስትነትን ክብር እንቀዳጃለን፡፡ መሳሳምን እንደ መቅድም ውሰጂው፡፡ ግን እንደሚያስደስት ማራኪ መቅድም፡፡
ከዋናው ነገር የበለጠ ማራኪ የሆነ መቅድም፡፡ አለ አይደል… ሁሌም ደጋግመሽ ደጋግመሽ ብታነቢው እንደማትሰለችው መቅድም አስቢው፡፡ አንድ ሰው ምንም ያህል ቢጥመው፣ አንድን ሙሉ መጽሃፍ ሁሌም ደጋግሞ ሊያነበው አይችልም:: የከናፍርት ግንኙነት ፍጹም ደስታንና ሰማያዊ ስሜትን ይጎናጸፉበት ዘንድ ለሰው ልጆች የተሰጠ ጸጋ ነው፡፡ የደስታ የላይኛው ጣራ ያለው እዚያ ላይ ነው፡፡ አንድ ሰው በመሳሳም ብቻ፣ ከሚወደው ሰው ጋር የነፍስ ጥምረት የፈጠረ ያህል ጥልቅ ስሜት ሊሰማው የሚችልበት ጊዜ ያጋጥመዋል። ይህ ደግሞ ሁላችንም የምናልመው ነገር ነው - የልቦች ውህደት መፍጠር! “አስፈሪ ደስታ ነው መሳም፣ የሚወዱትን ማሻሸት ፍቅር ነፍሶችን ለማዋሃድ፣ የሚፈጽመው ከንቱ ኩሸት…” የሚሉት የፈረንሳዊው ባለቅኔ የሱሊ ፕሩዶም ስንኞች ትዝ ይሉሻል?... ለአፍታ ተቃቅፎ መተሻሸትና መሳሳም ብቻ፣ ጥንዶችን በአንድ የተዋሃዱ ያህል ጥልቅ ስሜት እንዲሰማቸው ያደርጋቸዋል:: አለሙን ሁሉ ቢገዙ፣ ሃብትን ሁሉ ቢይዙ የሚወዱትን ሰው ለመጀመሪያ ጊዜ ለመሳም ሲጠጉ እንደሚፈጠረው የከንፈር መንቀጥቀጥ፣ ትንፋሽ ለትንፋሽ እንደመግጠም፣ ከንፈር ለከንፈር ተጎራርሶ በጸጥታ ተቃቅፎ እንደመቆየት ልብን የሚያጠፋና በደስታ የሚያጠምቅ ስሜት የሚያጎናጽፍ ነገር የለም፡፡
ስለዚህ የኔ ውድ… መሳም ወንዶችን የምናሸንፍበት ጠንካራው መሳሪያችን እንደሆነ ልብ በይ!... አሳሳምሽ አሰልቺ እንዳይሆን ግን መጠንቀቅ አለብሽ፡፡ የመሳሳም ዋጋና የሚፈጥረው የእርካታ ስሜት አንጻራዊ እንደሆነ አትዘንጊ፡፡ በመሳሳም ውስጥ የሚፈጠረው ስሜት እንደ ሁኔታዎች፣ እንደነበረን የቀድሞ ግምት ወይም እንደምንጠብቀው ነገርና እንደ ውስጣችን ፍንጠዛ በየጊዜው የሚቀያየር ነው፡፡ እዚህ ላይ አንድ ምሳሌ ላንሳልሽ… ሌላኛው ገጣሚ ፍራንኮይስ ኮፔ የጻፋት አንዲት ስኝን አለች… የሁላችንን ልብ በስሜት የምታሞቅ ስንኝ… ገጣሚው በአንድ የክረምት ምሽት ቤቱ ውስጥ ቁጭ ብሎ ፍቅረኛውን በጉጉት ስለሚጠብቅ አንድ የናፈቀ አፍቃሪ ይነግረናል፡፡ በውስጡ ስለተፈጠረው ጭንቀት፣ ትዕግስት አጥቶ ስለመቅበጥበጡ፣ ‘ሳላያት ላድር ነው’ ብሎ በፍርሃት ስለመራዱ ይተርክልናል። በስተመጨረሻም ያቺ በጉጉት ስትጠበቅ የነበረች ተፈቃሪ ድንገት ከተፍ ማለቷን ይገልጽልናል፡፡ የሚወዳት ልጅ ትንፋሷ እየተቆራረጠ፣ በክረምቱ ምሽት የንፋስ ሽውታ ውስጥ በጥድፊያ ስትመጣ የተመለከተውና አቅፎ መሳም የጀመረው አፍቃሪ፣ ድንገት እንዲህ ብሎ በማጋነን ተናገረ ይለናል ገጣሚው ኮፔ… “ኤጭ!... የከናፍርቷ ጣዕም፣ በአይነ እርግቧ ውስጥ ጠፋ!...” እጅግ ድንቅ ስሜት፣ ውብ እይታ፣ ፍጹም የሆነ እውነታ የያዘ… ደስ የሚል ገለጻ ነው አይደል?... የሚወዱትን ሰው በድብቅ ለማግኘት የተጣደፉ፣ በፍቅር አቅላቸውን ስተው በወንዶች ክንድ ላይ የወደቁ ሴቶች ሁሉ፣ በአይነ እርግብ ውስጥ ተከልለው ያደረጓቸውን ጣፋጭ መሳሳሞች ጠንቅቀው አይረሷቸውም፡፡
ከዘመናት በኋላ ተመልሰው ባስታወሷቸው ቁጥርም በስሜት ይቃትታሉ፡፡ የሚስሟቸው ወንዶችስ?... እስኪ የዚህን ገጣሚ አፍቃሪ ገጸባህሪ ታሪክ ልብ ብለሽ አስቢው የኔ ውድ… ወጣቷ በሚያንቀጠቅጥ ውርጭ ውስጥ በፍጥነት እየተራመደች ወደ አፍቃሪዋ ትመጣለች… በቀዝቃዛ ትንፋሿ እንፋሎት የረጠበ፣ ጤዛ የቋጠረ አይነ እርግብ ተከናንባለች… መጣች ቀረች እያለ በር በሩን እያየ በጭንቀት ሲባዝን ያመሸው አፍቃሪ፣ ዱካዋን ሲሰማ በደስታ ይፈነጥዛል፡፡ ጨለማውን ሰንጥቃ የመጣችለትን ፍቅሩን ደጃፍ ድረስ ወጥቶ እየተፍለቀለቀ ይቀበላታል:: በጥድፊያ በእቅፉ ውስጥ አስገብቶ በክንዶቹ ይጨምቃታል፡፡ እቅፍ አድርጎ እንደያዛት ጎምጅቶ ወደ ከናፍሯ ይሄዳል፡፡ ቀዝቃዛ ትንፋሿን በትኩስ ከናፍሩ ለብ ያደርገዋል። በዚህ መሃል… የአይነ እርግቧ ጤዛ ጺሞቹን ሲያረጥባቸው፣ አፍንጫ ቆርጦ የሚጥል ጠረን ከእሷ ገላ ላይ ተንኖ ድንገት ሲተነፍገው… ይሄ ሰው ምን ይሰማዋል?... ጓጉቶ የጠበቃትን የሚወዳትን ሴት ከናፍርት በወጉ ማጣጣም ይችላል?... በፍጹም!... የከናፍርቷን ጣዕም አይነ እርግቧ ይነጥቀዋል፡፡ ከቀዝቃዛ ትንፋሿ ይልቅ፣ አይነ እርግቧ የታጠበበት ኬሚካል መጥፎ ጠረን ጎልቶ ይሰማዋል፡፡ ይሄኔ ነው … “ኤጭ!... የከናፍርቷ ጣዕም፣ በአይነ እርግቧ ውስጥ ጠፋ!...” ያለው:: ምን ማለቴ መሰለሽ… እንዲህ ያለው ፍቅር አሰጣጥ የሚኖረው ዋጋ በሁለቱ ተፋቃሪዎች ስምምነትና በውስጣቸው በሚፈጥረው ስሜት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ፣ ነገሩን እንዳናበላሸው መጠንቀቅ አለብን፡፡ የኔ ውድ… ቅልጥፍና የጎደለሽ ገልጃጃ ቢጤ መሆንሽን በተደጋጋሚ ለማስተዋል ችያለሁ፡፡ እርግጥ ይህ የአንቺ ብቻ ችግር አይደለም፡፡ አብዛኞቹ ሴቶች መሳሳም የሚባለውን ትልቅ ነገር፣ አግባብ ባልሆነ ሁኔታ ያለወቅቱ ይከውኑታል፡፡ ይህን በማድረጋቸውም በሚወዷቸው ወንዶች ላይ ያላቸውን የበላይነትና ስልጣን ያጣሉ፡፡
የትዳር አጋራቸው ወይም ፍቅረኛቸው ድካም ቢጤ እንደተሰማውና መንፈሱም አካሉም እረፍት እንደሚሻ እያወቁ፣ በውስጡ ያለውን ስሜት ከማጤን ይልቅ በጉትጎታ ለመደባበስና ፍቅር ለመስጠት ይሞክራሉ፡፡ እንዲስማቸው በመገፋፋትና በመለመን እንዲሁም ያለ ምክንያት በመደባበስ የበለጠ ያደክሙታል:: ከልምዴ በመነሳት የምሰጥሽን ምክር በጥርጣሬ አትመልከቺው፡፡ የመጀመሪያው ነገር ፍቅረኛሽን ሰው በተሰበሰበበት በአደባባይ አትሳሚው፡፡ እንዲህ ያለው መሳሳም ጣዕም የለውም፡፡ ለራስሽ ስሜት ብቻ ተገዝተሽ በአደባባይ ብትስሚው፣ ሀፍረት ሊሰማውና ይቅር የማይሉት ቅያሜ ሊይዝብሽ ይችላል፡፡ ጥቅም የሌላቸው መሰል መሳሳሞች በመካከላችሁ ክፍተት ይፈጥራሉ፡፡ እርግጠኛ ነኝ አንቺም እንዲህ ስታደርጊ ነበር፡፡ ለምሳሌ አንድ የሆነ ቀን አስደንጋጭ ነገር እንዳደረግሽ አስታውሳለሁ፡፡ ምናልባት አንቺ ትዝ ላይልሽ ይችላል፡፡ እኔ፣ አንቺና ባለቤትሽ አንድ ክፍል ውስጥ ነበርን፡፡ ከባለቤትሽ ጭኖች ላይ ቁጭ ብለሽ አሻግረሽ በሩቁ ከኔ ጋር ስታወሪ፣ እሱ እንደምንም እየተንጠራራ ከንፈርሽንና አንገት ስርሽን ይስም ነበር፡፡ በወሬያችን ተጠምደሽ ስለነበር፣ ሲስምሽ ከጉዳይ አልጣፍሽውም፡፡ ችላ ብለሽው ከኔ ጋር ስታወሪ ቆይተሽ፣ በመካከል ጥግ ላይ ወደነበረው ምድጃ ታያለሽ፡፡ አጥፍቼዋለሁ ያልሽው እሳት እንደገና ተያይዞ እየተንቀለቀለ ነበር፡፡ ትዝ ይለኛል... “እሳቱ!... እሳቱ!” እያልሽ መጮህ ጀመርሽ፡፡ ባልሽ ጩኸትሽን ሲሰማ በድንጋጤ ክው አለ፡፡
በፍጥነት አፈፍ ብሎ በመነሳትም በሩጫ ወደ ምድጃው ሄዶ እሳቱን ለማጥፋት መጣደፍ ያዘ፡፡ እንደምንም ከወላፈኑ ጋር እየታገለ የፍም ጉማጆችን እየመዘዘ ማውጣት ጀመረ፡፡ አንቺ ታዲያ፣ በዚህ ጊዜ ባልሽን ተከትለሽው ወደ ምድጃው ሄደሽ ከንፈርሽን አሞጥሙጠሽ፣ “ሳመኝ!...” ስትይ እየተሞላቀቅሽ ጠየቅሽው፡፡ ባልሽ ከምድጃው በመዘዘው የፍም ጉማጅ እጆቹ እየተቃጠሉ እንደምንም ዘወር ብሎ አየሽ፡፡ አንቺ መች በዚህ በቃሽ!... በእሳት የሚለበለበውን ያንን ምስኪን ባልሽን፣ ጠምዝዘሽ ይዘሽ ልቡ እስኪጠፋ ሳምሽው:: ይሄኔ በእጁ ይዞት የነበረውን ጉማጅ ጣለና በንዴትና በተስፋ መቁረጥ ተነፈሰ:: በቁጣ ገንፍለሽ መሳምሽን አቋረጥሽና ባልሽን ገፋ አደረግሽው፡፡ ከዚያም… “አሳሳምህ እንዴት ነው የሚያስጠላው ባክህ!?” አልሽው በመጸየፍ እያየሽው፡፡ የኔ ውድ… እውነቴን ነው የምልሽ… በእንደዚህ አይነት ነገሮች ላይ ጥንቃቄ ማድረግ አለብሽ!... ልብ ባንለው እንጂ፣ አብዛኛዎቹ ሴቶች ምቹ ያልሆኑ ሁኔታዎችን ለፍቅር ልፊያና ኩሸት የመምረጥ እንዲህ ያለ የቂል አመል አለብን። ፍቅረኛችን ወይም የትዳር አጋራችን በጥም ተቃጥሎ አንድ ብርጭቆ ውሃ በሚፈልግበት፣ ጫማውን ለማጥለቅ ባጎነበሰበት፣ ከረባቱን ለማሰር በሚጣደፍበት… በአጠቃላይ ምቹ ባልሆነበት አጣዳፊ ሁኔታ ውስጥ ሲሆን ነው፣ ለመሳምና ለመተሻሸት የምንፈልገው:: ይህ ደግሞ የጀመረውን ነገር አቋርጦ ከእኛ ጋር እንዲላፋ ማስገደድ ነው፡፡ እንዲህ ስናደርግ ፊቱ ላይ የመሰላቸትና ምነው በተገላገልኳት የሚል ምሬት የወለደው ስሜት ሲፈጠር እናነባለን፡፡ የምልሽን ነገር ከከንቱ ትችት አትቁጠሪብኝ። የኔ ውድ… ፍቅር ስሱ ነው፡፡ ተራ የሚባል ነገር ፍቅርን ሊረብሸው፣ ተፈቃሪንም ሊያስቀይመው አቅም አለው፡፡
ሁሉም ነገር የሚመሰረተው በፍቅር አሰጣጣችን ላይ እንደሆነ እወቂ። ቦታውን ያልጠበቀ መሳሳም ፍቅርን ክፉኛ ሊጎዳው ይችላል፡፡ “ባሌ በማላውቀው ነገር ነው የራቀኝ፣ ለምን ትቶኝ እንደሄደ ምክንያቱን አላውቀውም!... ምን አስቀይሜው ይሆን ብዪ ባስብ ባስብ መልስ ላገኝ አልቻልኩም” ብለሽኛል፡፡ ምናልባትም ያን ቀን፣ “አሳሳምህ እንዴት ነው የሚያስጠላው ባክህ!?” ብለሽ በተናገርሽው ነገር ተቀይሞ ሊሆን ይችላል። በይ አንግዲህ የኔ ውድ… ምናልባት ባልሽ ተመልሶ የሚመጣ ከሆነ፣ የሰጠሁሽን ምክር ተቀብለሽ ተግባራዊ ለማድረግ ሞክሪ፡፡ አሮጊቷ አክስትሽ - ኮሌቴ፡፡
(ከአዲስ አድማስ ዌብሳይት የተወሰደ፤ 11ጃንዋሪ 2014)

Read 2845 times