Sunday, 07 June 2020 00:00

በሃሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(0 votes)

     “እውነትህን ከመጠበቅ በላይ ጽድቅ ምን አለ?…”
                          
              ጨዋታችንን በድሮ ቀልድ እንጀምር፡-
አንድ ሰውዬ፤ ወደ አንድ መድሃኒት አዋቂ ዘንድ በመሄድ፤ “ጤና ይስጥልኝ አባት” ሲል ሰላምታ አቀረበ፤ ከዛፍ ስር ቁጭ ብለው ስራስር ሲጨምቁ ወደነበሩት ሰው ቀርቦ፡፡
“አብሮ ይስጥልን ልጄ” አሉ፤ የመንደሩ ቅጠል በጣሽ፡፡
ሰውዬአችንም ቁጭ ብሎ ህመሙን አወሳቸውና መድሃኒት እንዲፈልጉለት ጠየቃቸው፡፡ እሳቸውም ፈዋሽ ቅጠል መኖሩንና ምን ዓይነት እንደሆነም አስረድተው ስለ ዝግጅቱ መንገር ሲጀምሩ ድንገት ብድግ ብሎ፡-
“የት አገኘዋለሁ?” በማለት አቋረጣቸው::
ሊያስረዱት ቢሞክሩም ሰውየው፡-
“ንገሩኝ” ብሎ ተጣደፈ፡፡
ትንሽ አሰብ አድርገው፡-
“በማስተዋል ከፈለግኸው አታጣውም” አሉት፡፡
አጅሬውም በቅጡ እንኳ ሳይሰናበታቸው የተባለውን ዛፍ ፍለጋ ሮጠ፡፡ ከቦታ ቦታ፣ ከአገር አገር እየዞረ ሲፈልገው ዘመናት አለፉ፡፡ ግን አልቀናውም፡፡ ተስፋ ቆርጦ ወደ መኖሪያው ተመለሰ፡፡ መንደሩ አካባቢ ሲደርስ አዋቂውን አስታውሶ መድሃኒቱን እንዳላገኘ ሊነግራቸው ወደ ስፍራቸው አቀና:: መኖር አለመኖራቸውን እየተጠራጠረ አሻግሮ ሲመለከት፣ ቀድሞ ካገኛቸው ቦታ ተቀምጠዋል፡፡ አጠገባቸው ሲደርስ ግን መራመድ ተሳነው፡፡ ምን ሆኖ ይሆን?
*   *   *
ወዳጄ፡- በልጅነቴ ያየሁት ሲኒማ ነበር - “The Fish Called Wanda” የሚል፡፡ ባለ ታሪካችን የሚንከባከባቸው የጌጥ ዓሳዎች አሉት፡፡ “ዋንዳ” እያለ የሚጠራውን ዓሳ ግን ከሁሉም በላይ ይወደዋል፡፡ ሰውየው ስራው ከወንጀለኞች ጋር በመሆኑ ዓቅም አልባ የሆነን ንፁህ ሰው ሲገድል እንኳ “ለምን?” ብሎ የማያመነታ ጨካኝ ነው:: ወንጀሉ ተነቅቶበት ሲያዝ ግን ሽምጥጥ አድርጐ ይክዳል፡፡ አንድ ቀን ለዓሶች ያለውን ፍቅር የተረዳው መርማሪው፤ ትንንሾቹን ዓሶች ከሳጥናቸው እያወጣ መብላት ጀመረ:: የዋንዳ ተራ ላይ ሲደርስ ግን ባለ ዓሳው  ዘገነነው፡፡ ለራሱና ለሌላው ህይወት ያልተጨነቀው ይኼ ሰው፤ “ዋንዳ ከሚሞት እኔ ልሙት” ብሎ ጥፋቱን አመነ፡፡
“አለማሰብ ከሀጢዓት ይከፋል” ይል ነበር፤ ዶስቶይቭስኪ፡፡ ኤዲት ሴትዌል ደግሞ፡-
“I am patient with stupidity but not with those who are proud of it” በማለት ትሳለቃለች፡፡ ወዳጄ፤ ማስተዋል አይሳንህ!
ብረት አቅልጦ ወርቅ እንዳነጠረው አልኬሚ፤ ውሸት አፍልቶ እውነት ማንጠር ቢቻል ታላቅ ብቃት ነበር፤ አይቻልም እንጂ:: ምክንያቱም እውነት በራሱ የነጠረ ስለሆነ ዝቃጭ የለውም፡፡ እንደ ንፁህ ውሃ በሙቀት ቢተንም፣ ወቅት ደርሶ ወደ ታች እስኪወርድ ድረስ አየሩ ውስጥ ይኖራል:: ውሸት ግን አጥፍቶ ይጠፋል፡፡ ህይወት የለውም፡፡
ወዳጄ፡- እያሰለሰች “ጠብ” የምትል ውሃ በጊዜ ብዛት ኮንክሪት ታፈርሳለች፡፡ ትንንሽ ውሸቶችም በጊዜ ካልታረሙ፣ ስር ይሰዱና አገር ይነቀንቃሉ፡፡ ከመፍረስ ባልተናነሰ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ አገሮች ሲጠኑ የችግራቸው ስረ ምክንያቱ ውሸት ነው፡፡ “ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው” እንዲሉ፡፡
ወዳጄ፡- ሃሳብን እየለዋወጡ እውነትን መፈለግ ችግር የለውም፡፡ የሌሎችን መብት እስካልተገፋ ድረስ የስልጣኔ መገለጫ ሆኖ ቢቆጠርም ተገቢ ነው፡፡ ‹ካፈርኩ አይመልሰኝ› ብሎ “ልክ” ባልሆነ አስተሳሰብ ላይ መቸከል ግን ጉዳት አለው፡፡
“Even if you are on the right track, you will get run over if you just sit there” የሚለን ዊል ሮጀርስ ነው፡፡ (መንገድህ ላይ ብትሆን እንኳ ቆመህ ከቀረህ ትገጫለህ፤ እንደ ማለት ነው)፡፡ ወዳጄ፡- ማስተዋል ይስጥህ!
*   *   *
የጥንት ሰዎች “እውነት” የሚሉት ውስጣዊ መንፈስ በሚተኙበትና በሚሞቱበት ጊዜ እንኳን እንዳይለያቸው ለአማልክቶቻቸው “አደራ” እንደሚሰጡ ተጽፏል፡፡ በሃይል በሚያስነጥሱበት ጊዜም እንዳያፈተልክ ጥንቃቄ ያደርጉ ነበር:: ምናልባት ‹ወጥቶ ከሆነ› በማለትም እንዲመለስላቸው አማልክቱን ይለማመጡ ነበር፡፡ እስከ ዛሬም ድረስ “እግዜር ይማርህ፣ እግዜር ይባርክህ” የሚባለው ከዛ ጋር ተያያዥነት ባለው ምክንያት እንደሆነ ኸርበርት ስፔንሰር ‹The study of Sociology› በሚል ጽሑፉ ላይ አስፍሮታል፡፡ ስፔንሰር በዚሁ መጣጥፍ ውስጥ ‹god› የሚለው ቃል ቀጥተኛ (literary) ትርጉሙ ‹የሞተ ሰው›፣ Jehovah (ይሆዋ) ደግሞ ጀግናና ጦረኛ ማለት መሆኑንም እንደፃፈ ታላቁ የታሪክ ተመራማሪ ዊል ዱራንት ‹የፍልስፍና ታሪክ› በሚለው መጽሐፉ ይገልጻል፡፡ ወዳጄ፡- እውነትህን ከመጠበቅ በላይ ጽድቅ ምን አለ?… መልሱን እያሰብክ ‹ቃሉ›ን ተጋበዝልን፡፡
ቃሉ
ያ… ካይኔ ሚቀርበኝ
እንዳገሬ ጩኸት ያራራኝ
ተጓድኜው የነበር ቃል
እንዳምና ክረምት ብረሳው
ከርሞ እንደ ንጋት ጮራ
በተኛሁበት እየጠራ
‹የታለ ያ ቃል?› ይለኛል፡፡
*   *  *
ኃጢዓት ላይፀዳ ከቶ
ባጥንትና ደም ተቦክቶ
ተዋህዶ ስጋ ደሙ
ሰርፀ መንፈስ ለስሙ
‹ሰው› የሚለው ቃል ማህተሙ
በቀና ልቡ ታትሞ
ሳይታመም ለሰው ታሞ
ወደ መሬት ተሰደደ
*   *  *
ቃልም ጎኑን ተወግቶ
አብሮት ጉድጓድ ወረደ፡፡
*   *  *
ትንቢትም ይሞላ ዘንድ
ስጋ እንደገና ተነሳ
ቃል ግን እዛው ተረሳ፡፡
*  *  *
እናም ገጣሚው አለ፡-
   ያንን ቃል ለማግኘት
   ያን መንፈስ ፍለጋ
   ደግሞ ይሞታል ወይ?
ሰው - ባተሌ ስጋ!
*  *  *
ወደ ተረታችን ስንመለስ፡- ሰውዬአችን የመድሃኒቱን ዛፍ ፍለጋ አገር ላገር ሲንከራተት ቆይቶ መመለሱን፣ እንዳልቀናውም ለመንገር ወደ ሽማግሌው ቀዬ ማቅናቱን፣ ዐዋቂው ወደ ተቀመጡበት ስፍራም እየቀረበ ሳለ ተደናግጦ እንደ ቆመ ተጨዋውተናል:: ሰውዬአችንን በድንገት የገተረው፡- ያ … ዘመኑን በፍለጋ የፈጀበት የመድሃኒት ዛፍ ሽማግሌው ከስሩ የተቀመጡበት መሆኑን በማወቁ ነበር፡፡ ወዳጄ፡- ማስተዋል አይንሳህ!
ሠላም!!  


Read 1538 times