Print this page
Tuesday, 09 June 2020 00:00

ኮሮና አሁንም መስፋፋቱን ቀጥሏል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  ለ5 ተከታታይ ቀናት በየዕለቱ 100 ሺህ አዳዲስ የኮሮና ተጠቂዎች ተገኝተዋል

           “ቫይረሱ መስፋፋቱን ቀጥሏል… ላለፉት ተከታታይ አምስት ቀናት በመላው አለም በየዕለቱ 100 ሺህ አዳዲስ ሰዎች በቫይረሱ እንደተያዙ ሪፖርት እየተደረገልን ነው ሳምንቱን የገፋነው” ነበር ያሉት የአለም የጤና ድርጅት ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ባለፈው ሐሙስ በወረርሽኙ ዙሪያ የሰጡትን መግለጫ ሲከፍቱ፡፡
እሳቸው እንደሚሉት፤ በተለይ በሰሜንና ደቡብ አሜሪካ አገራት፣ በየዕለቱ በኮሮና ቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከተቀረው አለም ድምር የተጠቂዎች ቁጥር ከበለጠ ሳምንታት ተቆጥረዋል፡፡ በምስራቃዊ ሜዲትራኒያን፣ በደቡብ ምስራቅ እስያና በአፍሪካም በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን ቀጥሏል:: የወርልዶ ሜትር መረጃ እንደሚያሳየው፤ እስካለፈው ሐሙስ አመሻሽ ድረስ ኮሮና ቫይረስ በመላው አለም ከ6.7 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ያጠቃ ሲሆን በቫይረሱ ሳቢያ ለሞት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥርም ወደ 400 ሺህ ተጠግቷል፡፡
እስከተጠቀሰው ጊዜ ድረስ ከ1.9 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የተጠቁባት አሜሪካ፤ በቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ከአለማችን አገራት በአንደኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች ሲሆን፣ ብራዚል በ587,017፣ ሩስያ በ441,108፣ ስፔን በ287,406 እና እንግሊዝ በ279,856 ተጠቂዎች እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡ በኮሮና ሳቢያ 110 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች የሞቱባት አሜሪካ፤ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በቫይረሱ የሞቱባት ቀዳሚዋ የአለማችን አገር ስትሆን፣ እንግሊዝ በ40 ሺህ፣ ጣሊያን በ34 ሺህ፣ ብራዚል በ33 ሺህ፣ ፈረንሳይ በ29 ሺህ ያህል ሞት ይከተላሉ:: ቫይረሱ በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋና ጥፋት እያደረሰባት ያለችዋ ሌላዋ የአለማችን አገር ሜክሲኮ ባለፈው ረቡዕ 1 ሺህ 92 የኮሮና ሞት የተመዘገበባት ሲሆን፣ ይህም በአንድ ቀን ብዛት ያላቸው ሰዎች በቫይረሱ የሞቱባት ቀዳሚዋ የአለማችን አገር አድርጓታል ተብሏል፡፡

 ድርብርብ የኮሮና ተጽዕኖ በአፍሪካ
*በናይጄሪያ ከ812 በላይ የጤና ባለሙያዎች በኮሮና ቫይረስ ተይዘዋል
ኮሮና እስካለፈው ሃሙስ አመሻሽ ድረስ ከ165 ሺህ በላይ ሰዎችን ባጠቃባትና ከ4 ሺህ 700 በላይ ሰዎችን በገደለባት አፍሪካ ላይ እያሳደረ ያለውና በቀጣይም የሚያሳድረው ተጽዕኖ ድርብ ድርብርብ እንደሆነ ነው በተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን በሳምንቱ መጀመሪያ ያስታወቀው፡፡ ወረርሽኙ መስፋፋቱን ተከትሎ 42 የአፍሪካ አገራት የእንቅስቃሴና ሌሎች ገደቦችን በመጣላቸው ብቻ አህጉሪቱ በድምሩ 69 ቢሊዮን ዶላር ያህል እንደምታጣ ኮሚሽኑ ማስታወቁን አናዶሉ ኤጀንሲ ዘግቧል፡፡
የአህጉሪቱ የኢኮኖሚ እድገት በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቆመው ዘገባው፤ የአፍሪካ ቱሪዝም ክፉኛ መጎዳቱንና የአቪዬሽ ዘርፉም ከአየር መንገደኞች ሊያገኝ ይችል የነበረውን የ6 ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚያጣ ይጠበቃል ብሏል፡፡ ቪኦኤ በበኩሉ፤ በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ የአለም የጤና ድርጅት በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሁለተኛ ዙር የኢቦላ ወረርሽኝ መከሰቱን አረጋገጠ ሲል በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍን የሚያስተርት ሌላ ክፉ ዜና አስነብቧል፡፡
በናይጄሪያ ለጤና ባለሙያዎች በቂ የመከላከያ ግብዓቶች ባለመኖራቸው ሳቢያ ከ812 በላይ የጤና ባለሙያዎች በኮሮና ቫይረስ መጠቃታቸውን የአገሪቱ የበሽታ መከላከያና መቆጣጠሪያ ማዕከል ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ ማስታወቁን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ ካሜሩን በኮሮና ወረርሽኝ ስጋት ተዘግተው የቆዩ ትምህርት ቤቶችን ባለፈው ሰኞ መክፈቷን ተከትሎ በቫይረሱ የተያዙ አዳዲስ ሰዎች መጨመራቸውንና በዕለቱ 254 ሰዎች መያዛቸው መረጋገጡንም የቢቢሲ ዘገባ አመልክቷል፡፡
በደቡብ አፍሪካ፣ የደቡብ አፍሪካ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመከላከል የወጡ አንዳንድ እገዳዎችና መመሪያዎች ከአገሪቱ ህገ መንግስት ጋር የሚጋጩና የቫይረሱን ስርጭት በማስቆም ወይም በመቀነስ ረገድ ይህ ነው የሚባል ፋይዳ የሌላቸው እንደሆኑ የገለጸው የአገሪቱ ፍርድ ቤት፤ መንግስት መሰል መመሪያዎችን እንዲያሻሽል ጥሪ ማቅረቡን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

በኮሮና የሞቱ ነርሶች ቁጥር በ1 ወር በእጥፍ ጨምሯል
በመላው አለም በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ለሞት የተዳረጉ ነርሶች ቁጥር በግንቦት ወር በእጥፍ በማደግ ከ600 በላይ መድረሱንና 450 ሺህ ያህል የጤና ባለሙያዎች በቫይረሱ መጠቃታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ አለማቀፉ የነርሶች ምክር ቤት ባለፈው ረቡዕ ይፋ ያደረገውን መረጃ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ በግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ 260 ብቻ የነበረው የኮሮና ቫይረስ ሟቾች ቁጥር ከእጥፍ በላይ በማደግ ከ600 ያለፈ ሲሆን ቁጥሩ በቀጣይም በፍጥነት ያድጋል ተብሎ ተሰግቷል፡፡
በመላው አለም በቫይረሱ ከተጠቁ ሰዎች መካከል በአማካይ 7 በመቶ ያህሉ የጤና ባለሙያዎች መሆናቸውንም ምክር ቤቱ ባወጣው መግለጫ ማስታወቁን ዘገባው አመልክቷል፡፡

የፍሎይድ ሞት ተቃውሞ
እና የኮሮና ስጋት
በአሜሪካ ጆርጅ ፍሎይድ የተባለ ጥቁር በአንድ ፖሊስ በጭካኔ መገደሉን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች ተስፋፍቶ የቀጠለ ሲሆን፣ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በአንድ ላይ የሚያደርጉት ተቃውሞ የኮሮና ቫይረስን የበለጠ እንዳያስፋፋው ተሰግቷል፡፡ ምንም እንኳን አብዛኞቹ ሰልፈኞች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ቢያደርጉም፤ በርካታ ሰዎች አንድ ላይ መሰባሰባቸውና ንክኪዎች መኖራቸው ቫይረሱን ሊያስፋፋው እንደሚችል ባለሙያዎች አስጠንቅቀዋል።

ገደቦችን ማንሳትና ማላላቱ ቀጥሏል
የተለያዩ የአለማችን አገራት ኮሮናን ለመከላከል ያወጧቸውን የተለያዩ የእንቅስቃሴ ገደቦች ማንሳትና ማላላት የቀጠሉ ሲሆን፣ በአውሮፓ በኮሮና ክፉኛ የተጠቃችው ጣልያን ለ3 ወራት ያህል የዘጋቻቸውን ድንበሮቿን ከሰሞኑ ለአውሮፓ አገራት ቱሪስቶች ክፍት አድርጋለች።
ዱባይ ሁሉንም የገበያ አዳራሾችና የግል ሱቆች ባለፈው ረቡዕ የከፈተች ሲሆን፣ ኦስትሪያም ከሰባት ጎረቤት አገራት ጋር የሚያዋስኗትን ድንበሮች ከትናንት በስቲያ መልሳ መክፈቷ ተነግሯል፡፡ በእስራኤል በኮሮና ቫይረስ በተጠቃ አንድ መምህር ሳቢያ ወረርሽኙ በትምህርት ቤቶች መስፋፋቱን ተከትሎ፣ በአገሪቱ የተለያዩ ከተሞች የሚገኙ ከ40 በላይ ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውና 7 ሺህ ያህል ተማሪዎችና መምህራን ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ መደረጉ ተዘግቧል፡፡
በሳምንቱ ከፍተኛው የኮረሮና ቫይረስ ሞት የተመዘገበባትና ብዙ ጉዳት ይደርስባታል ተብሎ የተሰጋላት ብራዚል፣ የሚመጣውን ጥፋት ለመቀነስ ከመዘጋጀት ይልቅ የጣለቻቸውን ገደቦች ለማንሳት መዘጋጀቷን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡ ኮሮናን አቃልለው በማየት ህዝባቸውን እያስፈጁ ነው በሚል የሚተቹት የብራዚል ፕሬዚዳንት ጄር ቦልሶናሮ፤ በአገሪቱ ከ1 ሺህ 340 በላይ ሰዎች በሞቱበትና 28 ሺህ 548 አዳዲስ የቫይረሱ ተጠቂዎች በተመዘገቡበት ባለፈው ረቡዕ፣ በአደባባይ አፋቸውን ሞልተው የተናገሩት እንዲህ በማለት ነበር፡- “ሞት ለሁሉም ሰው የማይቀር ዕዳ ነው!...”
 
የአየር መንገዶች ኪሳራ
በጀርመን የስራ አጦች ቁጥር ባለፈው ወር ብቻ በ169 ሺህ ያህል በመጨመር አጠቃላይ የአገሪቱ ስራ አጦች ቁጥር 2.8 ሚሊዮን መድረሱ የተነገረ ሲሆን የአገሪቱ ግዙፍ አየር መንገድ ሉፍታንዛ፣ በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ በአመቱ የመጀመሪያው ሩብ አመት 2.35 ቢሊዮን ዶላር ያህል ገቢ ማጣቱን ብሉምበርግ ዘግቧል፡፡
ኤርካናዳ አየር መንገድ ግማሽ ያህሉን ሰራተኞቹን እንደሚቀንስ ከሰሞኑ ያስታወቀ ሲሆን፣ ብሪትሽ ኤርዌይስ በበኩሉ 12 ሺህ ያህል ሰራተኞችን እንደሚያሰናብት መነገሩን ኒውዮርክ ታይምስ ዘግቧል፡፡
አልጀዚራ በበኩሉ፤ ቻይና ከዚህ በፊት ወደ አገሪቱ ይበርሩ የነበሩና በወረርሽኙ ሳቢያ አገልግሎታቸውን ያቋረጡ 95 የውጭ አገራት አየር መንገዶች ዳግም ወደ ስራ ለመመለስ ከፈለጉ ማመልከቻ እንዲያስገቡ ጥሪ ማቅረቧን ከትናንት በስቲያ ባወጣው ዘገባ አስነብቧል:: ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ በአለማችን የቱሪስቶች ቁጥር በአመቱ በ78 በመቶ ያህል እንደሚቀንስ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ አስጠንቅቋል:: በህንድ ከ33 በመቶ በላይ አነስተኛ የንግድ ተቋማት ስራቸውን አቁመው መዘጋታቸውን የአለም የኢኮኖሚ ፎረም ከሰሞኑ ባወጣው መረጃ አመልክቷል፡፡

“2 ሜትር አይበቃም፤ ከዚያ
በላይ ተራራቁ”
ከኮሮና ቫይረስ ራስን ለመከላከል በባለሙያዎች ከሚሰጡ ምክሮች መካከል አንዱ ማህበራዊ ርቀትን መጠበቅ እንደሆነ ይታወቃል:: አንድ ሰው ከሌላው ሰው 2 ሜትር ያህል ቢርቅ ቫይረሱ እንደማያገኘው ተደጋግሞ ሲነገር ቆይቷል፡፡ ከሰሞኑ ግን ላሰንት የተባለ የሳይንስ ህትመት ውጤት ላይ ይፋ የተደረገ አንድ አዲስ የጥናት ውጤት “2 ሜትርም አይበቃም፤ አደጋ አለው” ሲል አስጠንቅቋል፡፡
በ170 የአለማችን አገራት የተሰራውን አንድ ጥናት ጠቅሶ ላሰንት እንዳስነበበው፣ ኮሮና ቫይረስ የመተላለፍ ዕድሉ በአንድ ሜትር ርቀት ላይ 3 በመቶ ያህል ሊደርስ፤ ከአንድ ሜትር በታች ርቀት ላይ ደግሞ 13 በመቶ ሊደርስ ይችላል፡፡ በሁለት ሰዎች መካከል ያለው ርቀት ወደ ሁለት ሜትር ከፍ ሲል ቫይረሱ ከአንደኛው ሰው ወደ ሌላኛው የመተላለፍ ዕድሉ ይቀንሳል እንጂ መተላለፉ አይቀርም፤ ስለዚህ ሰዎች ከ2 ሜትር በላይ ተራርቀው ቢቆሙ ይመከራል፤ ብሏል ጥናቱ፡፡

ከ127 በላይ ጋዜጠኞች
በኮሮና ሞተዋል
ባለፉት ሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ በመላው አለም ከ127 በላይ ጋዜጠኞች በኮሮና ቫይረስ ተጠቅተው ለሞት መዳረጋቸውን ተቀማጭነቱ በጄኔቫ የሆነው ፕሬስ ኢምብሊም ካምፔን የተባለ ተቋም ከሰሞኑ ባወጣው መረጃ አስታውቋል፡፡ ተቋሙ ባለፈው ማክሰኞ ያወጣውን መረጃ ጠቅሶ አናዶሎ ኤጀንሲ እንደዘገበው፣ ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑት ጋዜጠኞች በስራ ገበታቸው ላይ እያሉ በቫይረሱ የተያዙ ሲሆኑ አብዛኞቹ በቫይረሱ የተያዙትም በቂ መከላከያ ሳይኖራቸው ስራቸውን በሚያከናውኑበት ወቅት ነው፡፡
በርካታ ቁጥር ያላቸው ጋዜጠኞች በኮሮና ለሞት የተዳረጉት በላቲን አሜሪካ አገራት መሆኑንና በአገራቱ ለሞት የተዳረጉት ጋዜጠኞች 62 እንደሚደርሱ የጠቆመው ዘገባው፤ በአውሮፓ 23፣ በእስያ 17፣ በሰሜን አሜሪካ 13፣ በአፍሪካ 12 ጋዜጠኞች በቫይረሱ ህይወታቸውን ማጣታቸውም አክሎ ገልጧል፡፡



Read 4909 times
Administrator

Latest from Administrator