Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 07 July 2012 12:15

የአንድ ታላቅ ሰው ታሪክ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ባለፈው ሳምንት በጅማ ዩኒቨርሲቲ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ በህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የቀረበ)

“ምን ችግር አለው የአምቦ ህዝብ ጠላ ይጠጣ የለ! እዛ ሄደን ቤት ተከራይቼ ጠላዬን እየሸጥኩ ትምህርትህን ትጨርሳለሃ!”

የዛሬው የእናንተ የምረቃ ቀን እጅግ ያማረና ታሪካዊ ይሆን ዘንድ፣ የእናንተን የድል ቀን ሊያደምቅላችሁ አንድ ታላቅ ሰው አትላንቲክን አቋርጦ፣ ከምድረ አሜሪካ ከፊት ለፊታችሁ ይገኛል፡፡ ይህ ሰው ሲወለድ የተሰጠው ስም “እደግ ተመንደግ” የሚል ትርጉም ነበረው፡፡ በስነ - አካሉ ግዝፈትም ሆነ በስነ-አዕምሮ ብቃቱ ጣራ የሚነካ ሊሆን እንደሚችል ተተንብዮሎት ኖሮ ስሙን ሆኖ ተገኘ፡፡

የዚህን ሰው የታሪክ ፍሰት ሙሉ የሚያደርገው አንዲት ሴት አብራ ስትጠቀስ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ 62 ኪሜ ራቅ ብሎ ኦሌንኮሚ በምትባል አነስተኛ ከተማ ነዋሪ የነበረች፣ ከጀምጀም ውሃ በጀርባዋ እየቀዳች፣ ጠላ ጠምቃ እና እንጀራ ጋግራ ትተዳደር የነበረችው ወ/ሮ ሙቱ አያነው፤ የመጀመሪያም የመጨረሻም ለሆነው ልጇ የህይወቱ መሐንዲስ ነበረች፡፡ ይህች ሴት ብቻዋን ሆና የእሷንና የልጇን የኑሮ ውጣ ውረድ ለማሸነፍ ከምታደርገው ትግል ባሻገር የልጇ የወደፊት የህይወት ሐዲድ በተቃና መልኩ እንዲዘረጋ ያልከፈለችው መስዋዕትነት አልነበረም፡፡ ቄስ ት/ቤት ባስገባችው ጊዜ አብረውት ይማሩ ከነበሩት ልጆች በመላቅ ያገኘውን ሁሉ ጥርግርግ አድርጐ ያነበንብ ነበር፡፡ በትንሿ ከተማ ውስጥ ግን ያኔ ዘመናዊ ትምህርት (አስኳላ) አልነበረም፡፡ ዘመድ ያለው ልጁን ወደየዘመዱ እየላከ ነበር የሚያስተምረው፡፡

ይህች እናት ታዲያ አንድያ ልጇን ከራሷ ነጥላ በመላክና ያለትምህርት እንዳይቀር በመስጋት አጣብቂኝ ውስጥ ገባች፡፡ በዚህ ጭንቀት ውስጥ እያለች ነበር አንድ ባለሀብት ልጆቻቸውን በግል ቤታቸው አስተማሪ ቀጥረው ማስተማር የጀመሩት፡፡ የእሳቸውን አርአያ በመከተል ሌሎችም ቤት ተከራይተውና አስተማሪዎች ቀጥረው ዘመናዊ ትምህርት እንዲጀመር አደረጉ፡፡ ይሄን ጊዜ ነው በሁኔታው የተደሰተው ብላቴና፤ እናቱ ትምህርት ቤት ታስገባው ዘንድ የጠየቃት፡፡ ልጇ ከባልንጀሮቹ ኋላ እንዳይቀርባት ትሻ የነበረችው እናት፤ የአቅም ነገር ግን እንቅፋት ሆነባት፡፡ ለካ ት/ቤቱ በክፍያ ነው የሚያስተምረው፡፡ በጠላ ንግድ የምትተዳደረው እናት ደግሞ ከሆዳቸውና ከላምባ የሚተርፍ ገንዘብ አልነበራትም፡፡ ልጇ ት/ቤት ገብቶ መማር የሚችለው እናት ከገቢዋ በቀን 0.67 ሣንቲም ካጠራቀመች ብቻ ነበር፡፡

የትምህርቱ የወር ክፍያ በወር ሁለት ብር ነበርና፡፡ ይሄን ደግሞ ማድረግ አልቻለችም፡፡ እናም በሃዘን ስሜት ተሞልታ “ታገሰኝ አሁን አልችልም” አለችው፡፡ የገዛ ጓደኞቹ ኤቢሲዲን ሲያነበንቡ የእሱ እጣ ፈንታ ከብት ማገድ ሆነ! እነዚህ ባልንጀሮቹ ከትምህርት በኋላ እኮ አብረውት ይጫወቱ ነበር፡፡ ሁለት ብር ለትምህርት ክፍያ አጥቶ የነበረው ሰው ይኸው ዛሬ በመሃከላችን አለ፡፡

ሚሊዮኖችን ከረሃብና ከቸነፈር ነፃ አውጥቶ የገዛ አህጉሩን የታደጋትና “የቁርጥ ቀን ሣይንቲስት” ተብሎ የአለም የምግብ ፕሮግራም ሽልማትን ከ250ሺ ዶላር ጋር የተሸለመው የዓለም ሎሬት ፕሮፌሰር ገቢሣ እጀታ የክብረ በዓላችን ፈርጥ በመሆን ከመካከላችን ተገኝቷል፡፡

ከ70 በላይ ለሆኑ ሀገር አቀፍና አለም አቀፍ ድርጅቶች በአማካሪነት የሚሰራው፣ ከ200 በላይ መፃሕፍትን ያሳተመው፣ ከአስራ ሰባት በላይ ታላላቅ ሽልማቶችን የተሸለመውና እውቀትን ከአላማ ጽናት ጋር አጣምሮ የሚተገብረው ሎሬት ገቢሣ እጀታ ነው የዛሬው ታላቁ እንግዳችን!

ገቢሳ እጀታ በኦሎንኮሚ ከተማ በ1958 ዓ.ም ነው የተወለደው፡፡ የስምንት አመት ልጅ ሳለ ወላጆቹ በመለያየታቸው እሱን የማሳደግ እጣ ፈንታ በእናቱ በወ/ሮ ሙቱ አያነው ላይ አረፈ፡፡ በሁለት ብር እጦት ወደ ትምህርት ቤት መሄድ ባለመቻሉ ሲቆጭ የነበረው ብላቴና፤ በመጨረሻ እናቱን አልቅሶና አስቸግሮ ት/ቤት እንድታስገባው ሲማፀናት ዝም ለማለት አንጀቷ አልቻለላትም፡፡ ት/ቤት በመሄድ ችግሩን አስረድታ የወር ክፍያው አንድ ብር እንዲሆንለት አስደረገች፡፡ እስከ ሰባተኛ ክፍል ከተማረ በኋላ ግን ለተጨማሪ ትምህርት ወደ ሌላ ከተማ መሄድ ነበረበት፡፡ ከቀዬው በ20 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው አዲስ አለም ከተማ ዘመድ ጋ ከሰኞ እስከ አርብ እየተቀመጠ እሁድ በየሣምንቱ 20 ኪ.ሜ በእግሩ በመመላለስ እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ በደረጃ እየቀደመ ትምህርቱን አጠናቀቀ፡፡ ይህን ሁሉ የትምህርት ዓመታት ያሳለፈው ከእናቱ በየሣምንቱ የሚቋጠርለትን ሙልሙል ዳቦ ለሣምንት እንድትበቃው በመከፋፈል እየበላ ነበር፡፡ በትምህርት ውጤቱ ሞራሏ የተነቃቃው እናቱ፤ የተቻላትን ድጋፍ ሁሉ እያደረገች ቀጣይ ትምህርቱን ማስቀጠል ነበረባት፡፡ በእርግጥ ቀጣዩን ትምህርቱን ለመማር ወደ አምቦ ከተማ መሄድ ነበረበትና እየተጨነቀ እናቱን አማከራት፡፡ “እዚህ ያለው እስከ ስምንተኛ ክፈል ብቻ ነው ከዚህ በላይ ለመማር የግድ አምቦ መሄድ አለብኝ፤ እዛ ደግሞ ዘመድ የለን… የትስ እቀመጣለሁ?” ይላታል፡፡ መለኛዋ እናት በአለም የድንቃድንቅ መዝገብ እንኳን ሊገኝ የማይችል በተፈጥሮ ብልህነት የተካነ ሁነኛ መላ አቀረበች፡፡

“ምን ችግር አለው የአምቦ ህዝብ ጠላ ይጠጣ የለ! እዛ ሄደን ቤት ተከራይቼ ጠላዬን እየሸጥኩ ትምህርትህን ትጨርሳለሃ!”

በጣም የሚገርም ነበር፡፡ የገቢሣ እጀታ መክሊቱ የሚቃናበት ጊዜ ኖሮ፣ ከቤተሰቡና ጓደኞቹ ጋር በተደረገ ምክክር በወቅቱ ከአክላሆማ ዩኒቨርስቲ ጋር በትብብር በተከፈተው የጅማ የእርሻ የቴክኒክ ት/ቤት በመግባቱ እፎይ አለች፡፡ ከት/ቤቱ በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቀው ገቢሣ፤ በመቀጠልም እ.ኤ.አ በ1973 ከሃረማያ ዩኒቨርሲቲ በፕላንት ሣይንስ በከፍተኛ ማዕረግ ተመረቀ፡፡

በሀረማያ ቆይታው በመለሎ ቁመቱ ከዩኒቨርሲቲው አልፎ የብሔራዊ የቅርጫት ኳስ ተጨዋች በመሆን ሁለገብ ክህሎቱን ማሳየትም ችሏል፡፡ ከዚያም ከፐርዱ ዩኒቨርሲቲ ባገኘው ስኮላርሺፕ እ.ኤ.አ በ1976 የማስተርስ፣ በ1978 የፒኤችዲ ትምህርቱን በፕላንት ብሪዲንግ እና በጄኔቲክ አግኝቷል፡፡

አሁን የወ/ሮ የሙቱ አየናው ተልዕኮ ተሳክቷል፡፡ እናም ታሪክ የመስራት ሪሌውን ተቀብሎ ወደ አለም መድረክ መጣ - ዶ/ር ሎሬት ገቢሳ እጀታ፡፡

የዶክትሬት ዲግሪውን ከፐርዱ ዩኒቨርሲቲ ከተቀበለ በኋላ ከአለም አቀፍ የአዝዕርት ምርምር ተቋማት ጋር የሰራው ሳይንቲስቱ፤ በተለይም ከፊል በረሃ በሆኑ የትሮፒካል አካባቢዎች ላይ ከሚሰራ የጥናት ኢንስቲትዩት ጋር በጋራ መስራትን ተያያዘው፡፡ ወደ አፍሪካ በመምጣትም፤ በአለማችን ከአምስቱ ዋና የአዝዕርት መደቦች ውስጥ የሚመደበውና የ500 ሚሊዮኖች ወሳኝ ምግብ የሆነው ማሽላ ላይ ምርምሩን ጀመረ፡፡ ጐረቤታችን ሱዳንም የወጣት ሣይንቲስቱ የምርምር ማሣ ሆነችለት፡፡ ማሽላ ድርቅን የመቋቋም እና አካባቢን የመልመድ ተፈጥሮአዊ አቅም ቢኖረውም በተለይም አፍሪካ ውስጥ ላሉ ሃገሮች ወገን የመታደግ ሚናውን በቅጡ እየተወጣ አልነበረም፡፡ እንግዲህ በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ እንዲሉ አፍሪካ ውስጥ በነበረው የእርስ በርስ ጦርነት፣ ድርቅ እና ማሀይምነት ላይ ተስፋዋ የሆነው ማሽላም እጐተራ እማይደርስ ከቋት የሚጨለፍ ጊዜያዊ ማስታገሻ ነበር፡፡ በዚህ ላይ በመልካም አስተዳደር እጦት አምራቹ ሃይል ቀዬውን ለቆ መሰደድና በተረጂ ድንኳን ተኮልኩሎ የሚሰፈርለትን ድርጐ ናፋቂ ከመሆን አላመለጠም፡፡ ለዚህ ነው የሀገራችንም ገበሬ ሲከፋው፣ ማሽላዬን ወማ በላው

እንኳን ወማ ይብላው ነጐዴ የሰው ነገር አትስማ ሆዴ…

ብሎ ያቀነቀነው፡፡ ለዚህ አህጉራዊ ችግር የቁርጥ ቀን ደራሽ መሆን የቻለው ወጣት ተመራማሪ፤ በአሳለፋቸው የአምስት አመት የምርምር ውጤት፤ የሱዳን በረሃን የአየር ንብረት መቋቋም የቻለ፣ አመርቂ የምርት ብቃት የታየበትንና የገበሬዎቹን ህይወት የቀየረ “ሃጂን ዶሮዋን” የተባለውን ድርቅ ተቋቋሚ ሃይብሪድ ማሽላን ያገኘ ሲሆን፣ ቀድሞ ከነበረው ከ150% እጥፍ በላይ ምርት በሀገሬው አምራቾች እንዲመረት አደረገ፡፡ ከዚያም ከUSAID በተገኘ ፈንድ፤ ብሔራዊ የዘር ማምረትና ማከፋፈል ዘዴ በመፍጠር፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ገበሬዎች በሚሊየን ሄክታር እንዲያመርቱና ይህንን ዘር በብዛት በማምረት የኮሜርሻል Seed Industry እንዲስፋፋ እንቅስቃሴውን ጀመረ፡፡

ቀጣዩ የሳይንቲስቱ ጥረት ደግሞ በተለየ መልኩ የማሽላ ጠላት በሆነው በእንግሊዝኛው አጠራር Striga ወይም “ሟርተኛው አረም” ተብሎ በሚጠራው ጠንቀኛ የማሽላ ጠላት ላይ ነበር፡፡ ይሄ ጠንቀኛ ጠላት ከከርሰ ማሣ ካልጠፋ የማሽላ ድርቅን የመቋቋም ችሎታ ብቻ ምርታማነቱን እንደማይጨምር የተገነዘበው እልኸኛው ተመራማሪ፤ በ”ሟርተኛው አረም” ላይ ዘመቻውን አፋፍሞ ቀጠለ፡፡

Striga ወይም “ሟርተኛው አረም” ተብሎ የሚጠራው ጥገኛ አረም፤ የላይ ገጽታውን በሚያምሩ ሃምራዊ አበባዎች አሣምሮ፣ የምድርን ምንጣፍ ለማድመቅ የመጣ ውብ ተክል መስሎ በመቅረብ፣ ውስጥ ለውስጥ በስሮቹ አማካኝነት ማሽላን አመንምኖ እና አጠውልጐ ከጥቅም ውጭ የሚያደርግ እውነትም ሟርተኛ አረም ነበር፡፡

እንግዲህ እዚህ ላይ ነው የሣይንቲስቱ ብቃት በከፍተኛ ሁኔታ የታየው፡፡ ይህ አረም አንድ ተክል ወርሮ 500,000 ዘሮችን የመበተን አቅም ያለውና ዘሩም ከ10-20 ዓመት በአፈር ውስጥ ሊቆይ የሚችል ነው፡፡ ዘሩ በዋናው ተክል ስር ውስጥ በመብቀል፣ የዋናውን ተክል ዘር ሙሉ በሙሉ በመውረር፣ የተክሉ ስር ከላይ ጠብቦ ከስር እየሰፋ የሚሄድ የደውል ቅርጽ አስመሰሎት፣ ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር ከጥቅም ውጭ የሚያደርግ የአረም አይነት ነው፡፡

ሳይንቲስቱ ይህንን አደገኛ አረም ለማጥፋት እንደገና ወደ ፐርዱ ዩኒቨርስቲ በመመለስ፣ በተለምዶ ይታወቅ የነበረውን አረሙን የማጥፋት ዘዴ በሣይንሳዊ መንገድ ድል ለመንሳት ከተመራማሪ ጓደኛው ጋር በመሆን ምርምሩን ቀጠለ፡፡ በዚህ ምርምሩም በStriga እና በማሽላ መካከል ያለውን ኬሚካላዊና መሠረታዊ ዝምድና በመለየት፣ ማሽላን ድርቅ ተቋቋሚ ብቻ ሣይሆን ለስትራይጋ የማይበገርና በአሸናፊነት የሚወጣ ለማድረግ የሚያስችል የተሳካ ውጤት አስገኝቷል፡፡ አለምን ያስደነቀ ምርጥ ዘር የፈጠረው ሳይንቲስቱ፤ ይሄ ምርጥ ዘር የአፍሪካን ማሳዎች በፍጥነት እንዲተዋወቅ አደረገ፡፡ እ.ኤ.አ በ1994 ከዩኤስኤይድ ጋር በተደረገ ትብብር፤ ስምንት ቶን ድርቅን ተቋቋሚና ለስትራይጋ የማይበገር የማሽላ ዘር ለ12 የአፍሪካ ሀገሮች እንዲደርስ በማድረግ የአህጉራችን የቁርጥ ቀን የወገን ደራሽነቱን አስመስክሯል፡፡

በየጊዜው ከኦሎንኮሚ እስከ አዲስ አለም 20 ኪ.ሜ የተመላለሱት እግሮች ዛሬ አለምን አዳርሰዋል፡፡

በወር ሁለት ብር ለት/ቤት አጥቶ የነበረው ብላቴና ዛሬ ለሚሊየኖች ተርፏል፡፡ የበርካታ የሳይንስና የፕሮግራም ሪቪው ፓናሎች የኮሚቴ አባል የሆነው ሳይንቲስቱ፤ አያሌ የምርምርና የልማት ድርጅቶችን ያማክራል፡፡ አለም አቀፍ የግብርና ምርምር ማዕከሎች አብረውት ይሠራሉ፡፡

የሮክፌለር ፋውንዴሽን፣ የምግብና የእርሻ ድርጅት (ፋኦ) እና የአሊያንስ ግሪን ሪቮሉሽን የክብር አባል ነው፡፡

ከሮክፌለርና ከጌትስ ፋውንዴሽን ጋር አብሮ ይሰራል፡፡ የሣይንስ ካውንስል፣ የሣሣካዎ ግሎባል የቦርድ አባል ነው፡፡ ሎሬት ፕሮፌሰር ገቢሣ፤ Association For the Advancement of science, A crop society of America, American Society of Agronomy የተባሉ ተቋማት ሁሉ ቤተኛ (Fellowship አባል) ነው፡፡

ፕሮፌሰሩ ባከናወናቸው ሥራዎች ብዙ ሜዳሊያዎችን አጥልቋል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የ209 የworld food prize ተሸላሚ መሆኑና ከክብር ፕሬዝዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ የብሔራዊ ጀግና ሽልማትን ማግኘቱ ይጠቀሳል፡፡ በፕሬዚዳንት ኦባማ “Board for International Food and Agriculture Developt.” (BIFAD) ፕሬዚዳንት እንዲሆን የተመረጠው የዛሬው እንግዳችን ፕሮፌሰር ገቢሣ እጀታ፤ ዛሬ ቀድሞ በተማረበት ሀገር በጅማ በ2ሺ 390 ተመራቂዎች፤ ከ3ሺ በላይ በሆኑ የተመራቂ ቤተሰቦችና በጅማ ዩኒቨርሲቲ የመማክርት አባላት መሐል የበዓላችን ፈርጥ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

በህብረተሰብ አቀፍ ፍልስፍናው የህብረተሰቡን ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎችን በመስራት፣ በማሰልጠንና አገልግሎት በመስጠት በሀገሪቱ ግንባር ቀደም፣ በአፍሪካ የታወቀና በአለም የተከበረ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ለመሆን ያለመው ጅማ ዩኒቨርሲቲ፤ የዚህን በምርምር ብቃቱ ሀገራችንን ያስጠራ፤ ለሚሊዮኖች ረሃብን የታደገ፤ ፈረንጆች “The voice of poor” የሚሉት፤ በሂላሪ ክሊንተን “በአንዲት የሙከራ ሁዳድ ላይ ሣይሆን በሚሊዮኖች ሄክታር ላይ ስራው የተፈተነ” ተብሎ የተወደሰ ምርጥ የዘመናችንን ሣይንቲስት ፕሮፌሰር ገቢሳ እጀታ ታላቅ አበርክቶት የአካዳሚካዊና ሣይንሳዊ ፈለግን ከመረመረ በኋላ ሰኔ 21 ቀን 2004 ዓ.ም የትምህርት ጉባኤ በወሰነው መሰረት በሣይንስ የክብር ዶክትሬት ከነሙሉ ክብሩና ግዴታው ጋር እንዲሰጥ ወስኗል፡፡

 

,=========================================================================

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዓርማ ለውጥ አደረገ

የቀድሞ ዓርማውን ባንኩ ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ ለ13 ዓመት ተጠቅሞበታል - ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ፡፡ ነገር ግን ዓርማው ውስብስብ ስለሆነ ለአሠራር አላመቸውም፡፡

ባንኩ ደግሞ አሠራሩን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመተካት የአገልግሎት ዓይነቶችን ለመጨመር፣ የሥራ አድማሱን ለማስፋፋት፣ ከሌሎች ጋር ለመሥራት፣ … ዝግጅቱን እያጠናቀቀ ነው፡፡

ስለዚህ የባንኩ የዲሬክተሮች ቦርድና የሥራ አመራር አባላት “ምን ይሻላል?” በማለት መከሩበት፡፡ የቀድሞውን ዓርማ ባይጠሉትም ለአሠራር እንዲያመቻቸው፤ ግልፅ ቀላልና፣  ዘመናዊ በሆነ አዲስ ዓርማ ለመተካት ተስማሙ፡፡

“የቀድሞው ዓርማ እንደ እስክሪብቶ ባሉ ትናንሽ ቁሶች ላይ ለማተም አይመችም፡፡ ቪዛ ካርድ ከሌሎች ጋር ለመጀመር አቅደናል፡፡ እዚያ ካርድ ላይ የእኛም ዓርማ መታተም አለበት፡፡ ሌሎችም ምክንያቶች አሉ፡፡ ስለዚህ ዓርማችንን ግልፅ፣ ቀላል፣ ዘመናዊና ለአሠራር ምቹ በሆነ አዲስ ዓርማ ተካን” ብለዋል የባንኩ ዲሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ታፈሰ ቦጋለ፡፡ አቶ ታፈሰ አያይዘውም፣ የኮር ባንኪንግ ሶሉሽን እጅግ ዘመናዊ በሆነ የመረጃ ቴክኖሎጂ አደራጅተው ባጠናቀቁበትና የተገልጋዮችን ፍላጐት ሙሉ በሙሉ ለማሟላት ከፍተኛ ጥረት ተደርጐ ምርጥ የባንኪንግ ሶፍትዌር በገዙበት ወቅት አዲሱ ብራንድ ከባንኩ ራዕይ፣ ተልዕኮና መሠረታዊ ዕሴቶች ጋር ሙሉ በሙሉ እንዲጣጣም ተደርጐ በመዘጋጀቱ ለተገልጋዮች ደረጃቸውን የጠበቁ አገልግሎቶች መስጠት እንደሚያስችላቸውና የታማኝነታቸው ማሳያ ቃል ኪዳን ማሰሪያ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ዓርማው ክብ ሆኖ ከላይ ቡናማ፣ ከታች ቢጫ ቀለማት ያሉት ሲሆን በየጊዜው የሚታየውን የኢኮኖሚና የምንዛሪ መዋዠቅ ለማሳየትና የባንኩን የመጀመሪያ የእንግሊዝኛ ፊደል ኤን ለማመልከት ሁለቱ ቀለማት በነጭ ዚግዛግ መስመር ተለይተዋል፡፡

ፈዘዝ ያለው ብርቱካናማ ቢጫ ቀለም የንብ የምርት የሆነውን የማር ቀለም የሚያመለክት ሲሆን በምዕራቡ ዓለም ይህ ቀለም ከምሁርነት፣ ከትኩስነት፣ ከደስታ፣ ከክብርና ከታማኝነት ጋር ያያያዛል፡፡

ቡናማው ቀለም ደግሞ አስተማማኝና የሁሉም ነገር መብቀያ የሆነውን ምድር የሚያመለክት ስለሆነ የባንኩ ኔትዎርክ ሁልጊዜ እያደገ መሆኑንና የቢዝነሱን ትክክለኛነት ይጠቁማል ብሏል - ዲዛይኑን የሠራው አቶ ያየህይራድ፡፡ ይህ በእንዲህ እያለ ንብ፣ አዋሽና ሕብረት ባንኮች በቅርቡ የካርድ ክፍያ፣ የኢንተርኔትና የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎት መስጠት የሚያስችላቸው ፕሪሚየር ስዊች ሶሉሽን የተባለ ኩባንያ ማቋቋማቸው ታውቋል፡፡ በአገሪቱ ካሉት 14 የግል ባንኮች አንዱ የሆነው ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ፤ በ1992 ዓ.ም በ27.6 ሚሊዮን የተከፈለ ካፒታል፣ በ150 ሚሊዮን የተፈቀደ ካፒታል፣ በ717 አባላትና በ28 ሠራተኞች የተቋቋመ ሲሆን፤ በተጠናቀቀው ሦስተኛ ሩብ ዓመት ሪፖርት መሠረት፤ ጠቅላላ ሀብት 9.87 ቢሊዮን፣ ጠቅላላ ተቀማጭ ብር 5.4 ቢሊዮን፣ ጠቅላላ ብድር ብር 3.64 ቢሊዮን፣ ጠቅላላ ካፒታል ብር 1.45  ቢሊዮን፣ የተከፈለ ካፒታል ብር 942.5 ሚሊዮን፣ የባለአክስዮን ብዛት 3,837 ሲሆን 2,063 ሠራተኞች እንዳሉት አመልክቷል፡፡

 

 

 

Read 5221 times Last modified on Saturday, 07 July 2012 12:23