Sunday, 31 May 2020 17:22

የ65 ዓመቷ ኢትዮጵያዊት ማርገዛቸውን ሳያውቁ ወንድ ልጅ በምጥ ተገላገሉ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

የ65 ዓመቷ ኢትዮጵያዊት ማርገዛቸውን ሳያውቁ ወንድ ልጅ በምጥ ተገላገሉ

ነብሰጡር መሆናቸውን እስከወለዱበት ቀን ድረስ ያላወቁት የዚህ አስገራሚ ክስተት ባለቤት የ65 ዓመት ዕድሜ ባለፀጋዋ ወይዘሮ ስንዱ ሰውነት የአዲስ አበባ ነዋሪ ናቸው።

የወይዘሮ ስንዱ ሰውነት "ወንድ ልጅ ከነቃጭሉ ተገላገሉ" መባል የአራሷን ጎረቤቶችና የገርጂ አካባቢ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ጀርባ አካባቢ ነዋሪዎችንም አስደንቋል በደስታም አስፈንድቋል።

 ወይዘሮዋ በጠላና በአነስተኛ ጉልት አትክልቶችን በመሸጥ የሚተዳደሩ ናቸው፤ ከብዙ ዓመታት በፊት ባጋጠማቸው ውርጃ ሳቢያ ልጅ ወልደው ለመሳም ሳይታደሉ ዕድሜያቸው መግፋቱን ይናገራሉ።

 ልጅ ወልዶ ለመሳም ባለመታደላቸው ፈጣሪያቸው ልጅ እንዲሰጣቸው ሌት ተቀን ሲማፀኑ መኖራቸውንና በኋላም ተስፋ መቁረጣቸውን የሚናገሩት ወይዘሮ ስንዱ 'የወር አበባ ማየት ካቆምኩኝ ረጅም ጊዜ ተቆጥሯል' ይላሉ።

 ነገሩ እንዲህ ነው ግንቦት 16 ቀን 2012 ዓ.ም ወይዘሮ ስንዱ ሆዴን አሞኛል፣ ይቆርጠኛል ሲሉ ወደስራቸው ለሄዱት ባለቤታቸው በስልክ ይናገራሉ፤ ባለቤታቸው የተለመደ የጨጓራ ህመም እንዳለባቸው የሚያውቁት አባወራ "ፈሳሽ ነገርም አየሁ" ማለታቸው ቢያሰጋቸው ጎረቤቶቻቸው ወደ ጤና ጣቢያ እንዲወስዷቸው ያሳስባሉ።

 ጎረቤቶችም ወይዘሮ ስንዱን ገርጂ አካባቢ ወደሚገኘው ድል ፍሬ ጤና ጣቢያ ይወስዷቸዋል።

 ምርመራ ያደረጉላቸው ሐኪሞች ወይዘሮዋ ነፍሰ ጡር እንደሆኑና ህመሙም ምጥ እንደሆነ በማስረዳት ዘጠኝ ወር ሙሉ ለምን የሕክምና ክትትል እንዳላደረጉ ይጠይቃሉ የወይዘሮዋ ምላሽ "ነብሰ ጡር መሆኔን አላውቅም" ነበር።

 በዚህ ጊዜ የድል ፍሬ ጤና ጣቢያ ወደ ዘውዲቱ ሆስፒታል የላካቸው ወይዘሮ ስንዱ በሆስፒታሉ ማዋለጃ ክፍል ወንድ ልጅ በምጥ ይገላገላሉ።

 ይሄኔ የወይዘሮ ስንዱን ነብሰ ጡርነት ብሎም በዚህ ዕድሜያቸው መውለድ ግርምት የፈጠረባቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ሁኔታውን በስልክ ይገልጻሉ፤ የኢዜአ ሪፖርተር በስፍራው ሲደርስም የ65 ዓመቷን አራስና "እንኳን ማርያም ማረችሽ" የሚሉ ጎረቤቶቻቸውን በማግኘት እውነታውን ተመልክቷል።

 በአራስ ቤት ወንድ ልጃቸውን የታቀፉት ወይዘሮ ስንዱ ስለ ነብሰጡርነታቸው የሚያውቁት ነገር እንዳልነበረና በአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ የሚኖሩ በመሆኑ እስከወለዱበት ዕለት ድረስ ከባድ ስራዎችን ይሰሩ እንደነበር ነው የተናገሩት።

ስለ ባለቤታቸው እርግዝና የሚያውቁት ነገር እንዳልነበረ የገለጹት ባለቤታቸው አቶ ሀብታሙ ገላን ሳያስቡት አባት በመሆናቸው ደስታቸውን ገልጸዋል።

 የተወለደው ልጅ በሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኝም ልጃቸውን በስስት እየተመለከቱ ነው የተናገሩት።

የእኚህ ሴት ልጅ የማግኘት ጉጉት የጎረቤቶቻቸውን ልጆች እንደራሳቸው ልጆች እንዲንከባከቡ አድርጓቸዋል። ከልጆች ጋር ያላቸው ቅርበትም የልጆቹን ልዩ ፍቅር አስገኝቶላቸዋል፤ ለዚህ ጎረቤቶቻቸውም ምስክሮች ናቸው።

 ጎረቤቶቻቸው ወይዘሮ የሺ ጌታቸው እና አቶ ንጉሴ መኮንን ልጅ በጣም ይፈልጉና ይጓጉ ለነበሩት ወይዘሮ ስንዱ ፈጣሪ በመስተመጨረሻ ስለሰጣቸው በእጅጉ መደሰታቸውን ነው የተናገሩት።

ወይዘሮ ስንዱ የእርሳቸው የዕድሜ እኩያ መሆናቸውን የገለጹት የ64 ዓመቱ ተስፋ ሊቃውንት ተስፋ

መስፍን ደግሞ በዚህ ዕድሜያቸው መውለዳቸውን "የፈጣሪ ድንቅ ስጦታ ነው" ብለውታል።

 ኢዜአ ወይዘሮ ስንዱን ያዋለዱ የዘውዲቱ ሆስፒታል የሕክምና ባለሙያዎችን ለማግኘት ያደረገው ተደጋጋሚ ጥረት በባለሙያዎቹ የስራ ጫና ምክንያት አልተሳካም።

 የሴት ልጅ ዕድሜ የመውለድ ዕድልን የሚወስን አንድ መስፈርት ስለመሆኑ የሕክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ።

 የሴቶች ከፍተኛ የመውለድ ዕድል በአሥራዎቹ መጨረሻና በ20ዎቹ መገባደጃ መካከል ሲሆን በ30ዎቹ ዕድሜ ላይ የመራባት ወይንም የማርገዝ ዕድል ማሽቆልቆል እንደሚጀምር ይጠቅሳሉ።

 በ45 ዓመት ዕድሜያቸው የመራባት ችሎታ በጣም እየቀነሰ የሚመጣ በመሆኑም ለአብዛኞቹ ሴቶች ማርገዝና መውለድ የማይቻል እንደሆነም ጥናቶች ያሳያሉ።

 ይሁን እንጂ ከመቶ አንድ የሚሆን እርግዝና በ50 እና ከዚያ በላይ የዕድሜ ክልል ባሉ ሴቶች ሊያጋጥም እንደሚችልም ነው ጥናቶች የሚጠቁሙት።

 በቅርቡ ሕንዳዊቷ የ73 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ መንታ ልጆችን መውለዳቸው፤ በናይጄሪያም የ68 ዓመት ሴት በተመሳሳይ መንታ ልጆችን መገላገላቸው ዓለምን ያስደመሙ ዜናዎች ነበሩ።

Ethiopian News Agency

Read 3291 times