Saturday, 30 May 2020 14:08

የተሾመ ግጥሞች-- አገራዊ ቁጭት!

Written by  (ደ.በ)
Rate this item
(0 votes)


                 “ተገረሚ ልጄ
ፍቅርና ጥበብ--ለሁሉ የቸርን፣
የዓለም ስልጣኔ ምሰሶ ነበርን!
ነበርን ውቅያኖስ--ነበርን የሳት ቋያ፣
አሀዱ ለምድር --የሰው ዘር መብቀያ፣-”
ማርክሲስቶች፤ ግለሰቦች የሚጽፉትን ግጥም ካፒታሊስታዊ ግጥም እያሉ፣ የቀደመውንና ጥርሱን የነቀለበትን የቡድን አካሄድ ቢናፍቁም፣ እኛ ግን ዛሬም ግጥም በደቦ ብቻ ሳይሆን በግል በመብሰልሰል የተሻለ ሃሳብ ለማመንጨት ውበትን አምጦ ለመውለድ ይጠቅማል ብለን እናምናለን:: በእነ ሼክስፒር ዘመን የገዢዎችን ቤት አንሶላ አንጥፏል፣ አሸርግዷል፡፡›› ብለን ወደ ኋላ አንሄድም፡፡ ሰባኪ ይሆኑ ዘንድም አንቃትትም፡፡
ዛሬ ከገጣሚ ተሾመ ብርሃኑ ‹‹ኮብላይ ዘመን›› የተሰኘ መጽሐፍ ውስጥ አንድ ግጥም ይዤ የተነሳሁትም በዚህ መንፈስ ነው፡፡ ሀገር በቡድን ብቻ ሳይሆን በአንድ ልብ ውስጥ ነግሳ ይታሰብላታል፤ ይለቀስላታል፤ የተስፋ ሰንደል ይለኮስላታል፤ ሊብከነከኑላትም እልፍኝ ይቀመጣሉ፡፡
ጋዜጠኛ ተሾመ ብርሃኑም የቁጭቱ ሕመም ስለሚያም ነው ዐመዱን ሳይሆን ነበልባሉን ይዤ ብቅ ያልኩት፡፡ ገጣሚው በገጸ ሰቡ በኩል ለአንዲት እንስት የሚያወራው ‹‹ነበርን›› እያለ ነው፡፡ አሁን እዚያ ክብር ላይ፣ አሁን የምንከበርበት ማማ ላይ አይደለንም፤ የዛሬውን አያድርገውና እንዲህና እንዲያ አልነበርንም፤ እያለ በስንኞቹ ውስጥ ከንፈሩን ይነክሳል፡፡ ዘመኑን ይጠቅሳል፡፡ ምናልባትም ዐይኖቹ በእንባ የተነከሩ፣ በቁጭት ስንጥር የሚሰባብር ገጸ ሰብ ይታየናል፡፡ አንድ ሙሉ ግጥም በጸጸት ነበልባል እየነደደ፣ እንደ ሻማ እየቀለጠ ይመስላል፡፡
ይኸው፡-
ይኸውልሽ ልጄ
ያልኩት፡፡
ገጣሚው በገጸ ሰቡ በኩል ለአንዲት እንስት የሚያወራው ‹‹ነበርን›› እያለ ነው፡፡ አሁን እዚያ ክብር ላይ፣ አሁን የምንከበርበት ማማ ላይ አይደለንም፤ የዛሬውን አያድርገውና እንዲህና እንዲያ አልነበርንም፤ እያለ በስንኞቹ ውስጥ ከንፈሩን ይነክሳል:: ዘመኑን ይጠቅሳል፡፡ ምናልባትም ዐይኖቹ በእንባ የተነከሩ፣ በቁጭት ስንጥር የሚሰባብር ገጸ ሰብ ይታየናል፡፡ አንድ ሙሉ ግጥም በጸጸት ነበልባል እየነደደ፣ እንደ ሻማ እየቀለጠ ይመስላል፡፡
ይኸው፡-
ይኸውልሽ ልጄ
እናኮ ነበርን፣
ነበርን፡፡(አጽንኦቱን ልብ እንበል)
እንደ ድር ያበርን፣
ፍቅር እንደ ነዶ--ጠምዘን ያሰርን!
ነበርን ባይገርምሽ፣
ዛሬ በየሰፈር ስንባላ እንዲህ የተፈጠርን፣ እንዲህ የኖርን እንዳይመስልሽ፤ ፍቅር አርሰን አጭደን፣ አርመን ኮትኩተን፣ ጠግበን ተካፍለን ስናበቃ ከእርሻችን ላይ አጭደን ነዶ የምንከምርና አስረን ለጎተራ የሚተርፈን ነበርን፡፡›› ይላታል፡፡ ዛሬ ዘር ቖጠራ እንደገባነው፣ ዛሬ ወንድሞቻችንን ክደን፣ ለከርስ ሀገር እንደምንሸጥ አይምሰልሽ፤ አብረን በልተን፣ አብረን ጠጥተን በዘርና በሐይማኖት ጠርዝ ሳንሰራ ኖረን ለዐለም የፍቅር ተምሳሌት ነበርን፡፡
ነገሩ አሁን ሲታይ እውነት ባይመስልም፣ በተለይ ላንቺ ዘመን ትውልድ ቅዠት ያህል ቢሆንም፣ ነገሩ እውነት ነው ለማለት አጽንኦት ሲሠጥ እንዲህ ነው፡፡--
እውነት---እውነት--እውነት
ነበርን እንደ ዐለት፣
ለወቀረን ሁሉ የማንፈነከት፡፡
ሊለያዩን ለሚመጡ ሁሉ በር የማንከፍት፣ ጥላችንን እንኳ ደብቀን ጠላት ሲመጣ አንድ የምንሆን ነበርን፡፡ እንዳሁን በሸቀጥ አንሸጥም ነበር፡፡ ለስልጣን ሙሉ ሀገር አንከዳም፡፡ የሚል ይመስላል፡፡ ቁጭቱ ያስታውቃል፤ ምሬቱ ያበሳጫል፡፡
ይሁንና ለልጁ በተለያየ መንገድና ምሳሌ ሊያስረዳት ይሞክራል፡፡ ውስጧ የገባውን መርዝ ለመንቀል፣ በሀውልትና በሚዲያ የተዘራባትን ዘር ለመንቀል ብዙ ጥበብ ያስፈልጋል፡፡
ነበርን እንደ ንብ
ያንዲት ጥግ ጥቃት እኩል የሚያስቆጣን፣
እንደ ሃዋርያቱ
የቃል ኪዳኑን ወይን --ባንድ ዋንጫ የጠጣን፡፡  
አንዳችን ላንዳችን ቀየ እንሞት ነበር፤ ክልሌ ካልተነካ ሰፈሬ ካልተደፈረ አንልም ነበር፡፡ ለዚህ ደግሞ ኪዳን አለን፤ የጨበጥነው ቃል፣ ያነሳነው ጽዋ አለ፡፡ ሃዋርያቱ ከጌታቸው ጋር እስከ ሞት ታማኝ ሆነው የኖሩለትና የሞቱለት ዐይነት ኪዳን ነበረን፤ እያለ ነው፡፡ ኦሮሞ-- ለኦሮሞ ብቻ አይሞትም፡፡ ኦሮሞው ለአማራው ይሞታል፤ ኀይለማርያም ማሞ ለተሰማ እርገጤ፣ መስፍን ስለሺ ለአበበ አረጋይ ይሞታል፡፡ በርሄ ለኀይለማርያም ማሞ!!
ስንነሳ ተበታትነን ሳይሆን፣ እንደ ንብ እንተምም ነበረ፡፡ ታሪካችን የተበጣጠሰ፣ ቡትቶ አልነበረም፤ በቀበሌ ለመተራረድ ቢላ አንስልም ነበር፡፡
ነበርን እንደ ዋርካ
ነበርን ውብ አደይ፣
ለኩራት ሚጠሩን --ለብርቅ የምንታይ፣
የልባሞች አድባር--የጥቁር ዓለም አዋይ፣
የተስፈኞች ገነት--የምድረኞች ንዋይ፡፡
ነበርን ባይገርምሽ
ለራሳችን ብቻ ሳይሆን ለሌሎች የተረፍን፣ ሃሩር ላጠቃቸው፣ አጋር ላነሳቸው አለኝታ ነበርን፡፡ ብዙዎች በኛ ተጠልለዋል፤ በማንነታችን በታሪካችን ክብር የሚኮራብን ነበርን፡፡ ድንበራችንን አላስነካ ያልን ግስላዎች ስለነበርን ጥቁሮችን አኩርተናል፤ የተስፈኞች መንገድ ቀያሽ፣ የደካሞች ጉልበት ነበርን፡፡ ግብጽና ቱርክን ከማጥ ውስጥ አውጥተን፣ አጅበን እስከ ምጽዋ አድርሰናል፡፡ ለኮሪያ ተዋግተናል፣ ለኮንጎ ዘምተናል፡፡ ጀግንነታችን የዐለም ትኩረት ስቧል፡፡ ‹‹እንደዚያ ነበርን!!››
አሁን እንደምታዪው የገዛ ሀገራቸውን ለማፍረስ የሚሮጡ ሰነፎች አልበዙም፡፡ ባንዶች ቢኖሩም ይቀጡ ነበር፡፡
ተገረሚ ልጄ
ፍቅርና ጥበብ--ለሁሉ የቸርን፣
የዓለም ስልጣኔ ምሰሶ ነበርን!
ነበርን ውቅያኖስ--ነበርን የሳት ቋያ፣
አሀዱ ለምድር --የሰው ዘር መብቀያ፣
አክሱምና ላሊበላን የሰራው እጅ እንደ ዛሬው ወንድሙን ለማረድ ሰይፍ የሚጨብጥ አልነበረም፡፡ ጥበብ ከራሳችን ቤት አልፎ ለዐለም መንዝረናል፤ የስልጣኔ ቁንጮ ነበርን፡፡ በአክሱም ስልጣኔ ብዙዎችን የጋበዝን ከሺህ ዐመታት በፊት ገንዘብ አሳትመን ገበያ የቆምን!! ነበርን---ነበርን---ነበርን!
ተገረሚ ልጄ--ተገረሚ በጣም
ዛሬ ቁልቁል ወርደን፣
ኩሬ አከልን እንጂ
ከዚህና ከዚያ እየተቆፈርን፣ እየተቋርን፣
ይገርምሻል ልጄ መሆንስ ነበርን!
ዋናው ቁጭቱ እዚህ ላይ ነው፡፡ ውቅያኖስ ሆነን፣ የተጠሙ የጠጡብን ዛሬ ኩሬ አክለን በሰፈር ጠብበናል፤ እያለ ነው:: ያሳዝናል፤ያስለቅሳል፡፡ ቁልቁል መውረድ!! ግን አሁንም ዕድል አለ፡፡ የሰማቸው ልጅ ቁጭቷን ትወጣለች፡፡ ተስፋ ታመነጫለች፤ እንባችንን ትጠርጋለች፡፡ የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ፡፡ ሀገሬ ታላቅ ነበረች፤ በተረት የተፈጠረች ሳትሆን በጀግንነቷና በአልደፈር ባይነቷ ባንዲራዋን በዐገራት ያባዛች፣ ቃል ሳይሆን ስራዋ የሚናገርላት ናት፡፡ ዛሬም ኢትዮጵያ ዳግም ታብባለች፤ ተሾመም የሚለው ይህንኑ ነው፡፡ ያገሬ ልጆች ስሙ፡፡

Read 2009 times