Tuesday, 02 June 2020 00:00

"የቤተዘመዱ - ይታያል ጉዱ!" ".ኢትዮጵያን ያላችሁ፣ እስቲ እንያችሁ!"

Written by  በተስፋዬ ድረሴ
Rate this item
(2 votes)


    ለዚህ ጥሪ እያጨበጨብክ መልስ ያልሰጠህ፤ ወደ ጭፈራው፣ ወደ ሽብሸባው አውድ ያልገባህ ዜጋ፤ ከወራት በኋላ ምንም ብትል አልሰማህም፡፡ አልኩህ በቃ፤ "አልሰማህም!" አንተም ብትሆን አትስማኝ! "የቤተዘመዱ፣ ይታያል ጉዱ!" እንዲል የሰርግ ቤት አቀንቃኝ፤ "ጥበበኛ ነኝ፣" "ልዩ ክህሎት፣ ልዩ እውቀት፣ ልዩ ተሰጥዖ ... አስማት፣ ምትሃት ... ወዘተ አለኝ"   የምትል ሁሉ "ያለህን"ለማሳየት ጊዜው አሁን ነውና ፍጠን፡፡  ይሄ ነው የወቅቱ ጥሪ፡፡ የዚህ ጽሁፍ ዋና ጭብጥ!አገርህ ትፈልግሃለች፤ መቼ? ዛሬ! ከዛሬም አሁን!  እና ... ፍጠና! ተናገር! እጅህ ከምን? ሰርጉ ሊጠናቀቅ፣ ሙሽሮች፤ ባዳ ዘመድ ሳይለዩ፤ የሰርጋቸውን ታዳሚዎች ሊሰናበቱ ጥቂት ደቂቃዎች ብቻ ሲቀሩ፣የሰርግ ቤት አቀንቃኝ፤ “የቤተ ዘመዱ፣  ይታያል ጉዱ! ... ሙሽራን ያላችሁ እስቲ እንያችሁ፤ ሙሽሪትን ያላችሁ፤ እስቲ እንያችሁ!“ እያለ የሚያስብለው ወድዶ አይደለም፡፡ የሙሽራው አሊያም  የሙሽሪት ዘመድ ነኝ የሚል ሁሉ፣ ሰርጉን ለማድመቅ አለኝ የሚለውን ችሎታ የመጠቀም እድሉ እንዳያመልጠው እንዲፈጥን ለማበረታታት ነው፡፡ ይህ ዘፈን  ሲዘፈን ትከሻውን ለእስክስታ፣ ሽንጡን፣ አንገቱን ወዘተ ለጭፈራ ያልተጠቀመ ሰው፣ ሰርጉ ካለፈ በኋላ ሰበብ ቢያቀርብ የሚሰማው ሰው አይኖርም፡፡ ለምን?  ወሳኝ በሆነው ሰዓት ጥሪ ተደርጎለታላ፡፡
"እስክስታ ስመታ አጥንት ያለኝ አልመስልም" ያለ ወይም ሲል የኖረ ሰው ከወንበሩ ሲነሳ፣ ወደ ጭፈራው አውድ፤ ማለት ወደ መሃል እንዲዘልቅ መንገድ ይለቀቅለታል፡፡ ወኔው ቱግ ያለ ተሳታፊ፤ ሰውን ገለል፣ ገለል አድርጎ የሚያስገባው ቢያጣ  እንኳ(እንደ አሁን ጊዜ ከሆነ፤ ሞባይሉን ጠበቅ አድርጎ ይዞ) እንደምንም እየተጋፋ ራሱን ወደ መሃል ለማሰማራት ጥረት ያደርጋል፤ እንጂ ወደ ኋላ አያፈገፍግም፡፡ "አላስገባ አሉኝ" ብሎ ነገር የለም፡፡በነገራችን ላይ ጭብጨባ፣ ሰርግን በማሞቅ ረገድ ትልቅ ድርሻ ነው ያለው፡፡ እስክስታ መውረድ፣ መውረግረግ ... ወዘተ ያልቻለ ወይም ያልፈለገ ሰው፤ ቢያንስ ቢያንስ በማጨብጨብ ሰርጉን ያሞቃል፡፡
"ይታያል ጉዱ!" የሚለው ሀረግ የሚያመለክተው፣ "እችላለሁ" ሲል የኖረን ሰው ችሎታውን በእማኝ፣ በታዛቢ ፊት እንዲያሳይ ለማፋጠጥም ይመስላል፡፡ "ለመሆኑ፣ የሙሽሪት/ሙሽራ ወገን ጭፈራ፣ ዘፈን ይችላልን?“ እያሉ ማወዳደሪያም ነው፡፡  ኢትዮጵያችን አሁን ያለችበት ሁኔታ ይህን ዘፈን ስለሚያስታውሰኝ ነው፤ የንባብ ማማሟቂያ ያደረኩላችሁ፡፡ አቀንቃኝ(ዘፈን አውጪ ሰው) የቤተ-ዘመዱ" ሲል፣  ተቀባዮች "ይታያል ጉዱ" የሚል ምላሽ እንደሚሰጡት  ሁሉ፤ መንግሥት፣ በ"ቤተ-ዘመዱ" ፈንታ የተለያዩ የሙያ ዘርፎችን፣ ተቋማትን ወዘተ ተራ በተራ፣  እየጠራ ... "የቤተ-ዘመዱ.." እያለና "ይታያል ጉዱ!" እያስባለ ያለ ነው የሚመስለኝ፡፡  መንግሥት እየተጣራ ነው፤ ተራ በተራ፡፡ ".... ሀኪም ነን ያላችሁ፤ ... እስቲ እንያችሁ!" አስብሏል፤ ተሳክቶለታል፡፡ "ሀብታም ነን ያላችሁ፤ እስቲ  እንያችሁ/ምናል ከእጃችሁ" ... አስብሏል፤ ተሳክቶለታል፡፡ "የህግ ባለሙያ ነን፣ ዳኛ ነን ... ያላችሁ፤ ... እስቲ እንያችሁ“ እያስባለ ነው፡፡ ወታደሩ፣ ፖሊሱ፣ የደን  ባለሙያው ... ሙዚቀኛው፣ ጸሀፊ/ገጣሚው፣... ባለቅኔው፣ አሳቢው፣ ተፈላሳፊው ... የታሪክ ሊቁ ... ያልተጠራ የለም፡፡ የተጠራ ሁሉ እያጨበጨበ ወደ መሃል  እየገባ ነው፡፡ ማንም ሳያውቃቸው፣ በድንገት፣ ተንደርድረው፣ ከጭፈራ መሃል ገብተው በልዩ የእስክስታ ጭፈራ ችሎታ ታዳሚውን ከያለበት እንዲያንጋጥጥ፣  እንዲንጠራራ፣ እጁ እስኪግል እንዲያጨበጭብ የሚያደርጉ ግለሰቦች ከታዳሚዎች መካከል (ብዙውን ጊዜ ከኋላ ወንበር ረድፍ) እንደሚከሰቱት ሁሉ፤ የፈጠራ  ሰዎች ብቅ ብቅ እያሉ ነው፤ ለጭፈራ ሳይጠሩ፡፡ ኢትዮጵያችን ስትጠማ የኖረችውን የፈጠራ ሥራ ዜና እያስጎነጯት ነው፤ ከኋላ ወንበር የተነሱ ልጆቿ፡፡ ግለሰብ  የፈጠራ ሰዎች፣ ራሳቸውን ንቁ ተሳታፊ በማድረጋቸው፣ በቅርቡ መንግሥት "የፈጠራ ችሎታ አለን ያላችሁ ... አርቲስት ነን ያላችሁ ... እስቲ እንያችሁ!" ብሎ  ጥሪ አስተላልፏል፡፡ አሁን ነው ጉዱ! የምንለውን ያህል ገጣሚያን፣ ባለቅኔዎች ነን? ይታያል!
አቀንቃኝ የሰርጉን ተሳታፊዎች በቡድን ከፋፍሎ ተራ በተራ እየጠራ፤ "ሚዜ ነን ያላችሁ ... ዘመድ ነን ያላችሁ፣ ጓደኛ (ነን) ያላችሁ..." ሲል ታዳሚው እያጨበጨበ፣ ለጭፈራም ቦታ እያመቻቸ፤ "እስቲ እንያችሁ" በማለት ምላሽ እንደሚሰጠው ሁሉ፤ መንግሥትም፤ የጥሪውን አድማስ እያሰፋ፣ የሚያበረታታ ተሳትፎ እያስተዋለ ነው፤ ከዜጎች፡፡ ደስ የሚል ነገር አለ፡፡ እናንተዬ፤ጠርጥሩ፡- ይህቺ አገር፤ በኮሮና ተገፍታ አንድ ሁለት የአዋቂ እርምጃ ወደ ፊት ሳትቀድም አልቀረችም፡፡  በአሁኑ ወቅት ራሱን ያልገለጠ ተቋም፣ ግለሰብ፣ ወዘተ ነገ ማን ይሰማዋል? ማንም! በበኩሌ "አልሰማህም!" ነው የምለው፡፡ ልድገመው፡- ኢትዮጵያ ሰው  ትፈልጋለች፡፡ ጥቅም ላይ ሊውል የማይችል እውቀት፣ ጉልበት ወዘተ አይኖርም፡፡ እያንዳንዱ ዜጋ ሚና ይኖረዋል፡፡ ብቻ ሲጠራ እያጨበጨበ (በደስታ) ወደ  ተሳትፎ አውድ ብቅ ይበል፡፡ ዛሬ አገርን ከበሽታ፣ ከወንጀለኛና ከመሳሰሉት ለመታደግ በነፃ የስልክ መስመር ደውሎ ወይም አስደውሎ መረጃ መስጠት ይቻላል  - ሌላ ሌላው ቢቀር፡፡ ለነገሩ፤ በዚህ ወቅት፣ መረጃን ያህል ምን አለ? "የአንዳንዱ" የእውነት ታይቷል ጉዱ፡፡ "እንዴት ያገሳ ይሆን ብለው የጠበቁት በሬ "እምቧ" አለ እንዲል ተረቱ፣ በሶሻል ሳይንሱ ዘርፍ ተሰማርተው የሚገኙና  ለክፉ ቀን ይበጁናል፣ ግጭት ፈቺዎች ይሆኑልናል ብለን የጠበቅናቸው (ግለሰቦች) ግጭት-አስኪያጆች ሆነው ሲያስደነግጡን ሰንብተዋል - የከረሙትን  ሳንጨምር፡፡ "ፍቅር አዋቂ፣ እንግዳ ተቀባይ ... ነን" ስንል የኖርን መደዳ ዜጎችም ከራሳችን ተጣልተን፣ ለራሳችንም ሳይቀር እንግዳ ሆነን ስንምታታ ቆይተናል፡፡ አሁን ሌላ ሰዓት ነው! ለማንኛውም ጥሪው ይቀጥላል፡፡ መቼም ዘንድሮ የማይፈተሽ አቅም አይኖርም፡፡መፍትሔ ፍለጋ ድምጽ ወዳጠፉ "ጠቢባንም"  እንመልከት፡፡
እስቲ እዚያ ጋ ...! "ፈዋሽ ነን" ያላችሁ ... እስቲ እንያችሁ!“ ከዚህ በላይ ምን አይነት በሽታ እስኪመጣ ትጠብቃላችሁ? ካስፈለገ መንግሥት ካሳ ከፍሎ አንዱን ቀበሌ ጥርግ፣ ድምጥ አድርጎ ሜዳ ይዘጋጅላችኋል፡፡  "መስተፋቅር፣ መስተዋድድ አለን" ያላችሁ - እስቲ እንያችሁ!“ካላችሁ፤ እያጨበጨባችሁ ወደ መፍትሔው አውድ ብቅ በሉ፡፡ ኑ፡፡ ከምን ጊዜውም በላይ ፍቅር  ያስፈልገናል፡፡ በጀት ይመደብላችሁና መስተ-ፍቅር ድረሱ፡፡ መቼም ህዝብ ከህዝብ አይጣላም፤ የተጣሉ ፓርቲዎችን አስታርቁ - አዋድዱ፡፡ ቂም ማርከሻ፣ በቀል  ማስረሻ አትደግሙ ይሆን? ከሆነ ድገሙልና! የአገር ልጆች የበቀል ጥምየይርጋ ጊዜ (ኤክስፓይሪ ዴት በሉት በፋርማሲኛ) ገደብ ጠፍቶታልና የናንተን ጥበብ  ሞክሩ፡፡ መንግሥት ለክታብ መሥሪያ በቂ ገንዘብ ይሰጣችኋል፡፡ካስፈለጋችሁ፣ ከኢንዱስትሪ ፓርኮቻችን የተወሰኑትን ልትጠቀሙ ትችላላችሁ፡፡ “ጠንቋይ ነን ያላችሁ - ኑ እንያችሁ፡፡“ፍጠኑ፡፡ የኢትዮጵያ ጠላቶች ከወዴት አቅጣጫ? መቼ? ምን ይዘው? በእነማን ታግዘው...እንደሚመጡ (አይመጡም  ከሆነ) ንገሩን፡፡ በተለይ በተለይ፣ የውጭ ጠላት በአገር ውስጥ መንገድ መሪ፣ ሚስጢር አጋሪ፤ ማለት፣  በባንዳ፤  ካልታገዘ የትም ሊደርስ አይችልምና እነማን  በባንዳነት እያገለገሉ እንደሆነ ጥቆማ ስጡ፡፡ ኢንሳን አግዙት፡፡ አገራችን ዳርድንበሯንና አንድነቷን እንደያዘች ትቀጥል አትቀጥል እንደሆነም ረገጥ አድርጋችሁ  ተናገሩ፡፡ ለዚህ ወሳኝ ውለታችሁ፣ አይደለምጥቁር፣ ገብስማ፣ ወሰራ፣ ወዘተ... ዶሮ፤ እና በግ፤ ከእነቀለምና መሰል ዝርዝሩ፣ ሰንጋም ይጣልላችኋል፡፡ የሥራ  ማስኬጃ ገንዘብም ቢሆን፣ ከ30 በመቶ ያላነሰ ቅድሚያ ክፍያ ባላችሁበት ይላክላችኋል፡፡አይዟችሁ፣ የእጅበጅ የገንዘብ ንክኪ አያሰጋችሁም፡፡ ለእናንተም  ቢሆን፣ ተራ ነገር እየጠነቆላችሁ ከደሃ ላይ ሁለት መቶ፣ አምስት መቶ ብርና ጥቂት ግራም ወርቆችን ከምትለቅሙ፣ የአገርን ችግር መፍቻ መረጃ ስጡናብዙ ብር  ታቀፉ፡፡ በዚያ ላይ፤ ያው እናንተ "ብርን የማባዛት አቅም አለን" ትሉ የለ? ገንዘቡን ወደምትፈልጉት መጠን ታበዙታላችሁ፤ ካስፈለገም ወደ ዶላርነት  ትለውጡታላችሁ፡፡ እግረመንገዳችሁን፤ አሁን አገራችንን እያጨናነቀ የሚገኘው በሽታ በየትኛው (የድንበር) በር እንደሚገባ፤ ቫይረሱ ኖሮባቸው አውቀውትም  ይሁን ሳያሳውቁ ከማህበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው የሚገኙ ዜጎች የት የት እንደሚገኙ ጠቁሙ፡፡ በየአካባቢዎቻቸሁ የሚገኙ ቢሮዎችን አቅጣጫ ለማወቅ እንደሆነ  እንደኛ ጎግል አትጎረጉሩ፣ ጂፒኤስ አያስፈልጋችሁ፣ ዋይ ፋይ ጠፋ በራ አያሳስባችሁም፡፡ ጠንቆል አድርጎ ሂድት ማለት ነው፤ ወደ ምትፈልጉት ጽ/ቤት፡፡ ይህም  አይረሳ፤ ብቸኛዋ ሳተላይታችን ደመና በሌለው ሰማይ ላይ ተንከራትታ የምትልከውን መረጃ የሚያግዝ ጥቆማ ለህዋ ሳይንስ ባለሙያዎችስጡ፡፡ ኢትዮጵያችን  ምን አይነት ማዕድኖች፣ የት የት ነው ያላት? የተፈጥሮ ጋዝ/ቤንዚንስ የት ነው የሚገኘው፤ ጠንቁሉ፡፡ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ገንዘብ ያስፈልገናል፣ በርቱልን፡፡  በዚህ ወቅት ወገንተኛነቱን ያላሳየ ጠንቋይ ... እንደኔ፣ እንደኔ፤ በህግ መዳፍ ውዝዋዜ ... ቻዎ፣ ቻዎ - አዎ፤ ... ባይ፣ ባይ! ባይ! እግረመንገድ ጠቁሞ ለማለፍ  ያህል፤ መንግሥት ካይዘንን በመጠቀም ጥቅማቸው ያልታየ ተቋማትን፣ አሰራሮችን ወዘተ ማስወገድ አለበት፡፡ ካይዘን ፀረ - ኮተታ ኮተት ነው፤ በአጭሩ፡፡  ሲፈለግ ያልተገኘ ዕቃ እንዳለ አይቆጠርም፡፡ ጥሪው ይቀጥላል፡- የሙት መንፈስ የማናገር ችሎታ/ጥበብ አለን፤ የምትሉ ሁሉ፤ አንደኛ፣ ከታሪክ ምሁራን ጋር በመተባበር የቀደሙ መሪዎቻችንን፣ የጦር አበጋዞቻቸውን ወዘተ  ከያሉበት በመጥራት (በቴሌ/ቪዲዮ ኮንፍረንስ ሞድ) አወያዩልን፡፡ በኢትዮጵያ ጉዳይ ምን ይሉ ይሆን? ጠይቋቸው፡፡ የአገራችን ታሪክ እንዲህ ወጣ ገባ፣ ቡራ ቡሬ እንዳይሆን እርዱን፡፡ ገዳያቸው ሳይታወቅ ተቀብረው የነበሩ ሰዎች፤ ቃላቸውን ይስጧችሁ፡፡ የአገር ጎብኚዎችን ቁንጽል ማስታወሻ እያነበብን፣ በገዛ  አገራችን ታሪክ እንዳንወዛገብ መላ ምቱልን፡፡ ሁለተኛ፣ የአገር ባህል መድሃኒተኛ የነበሩ ሙታንን አለፍ፣ አለፍ እያላችሁ ቀስቅሱና (መንፈሳቸውን) ቃላቸውን ተቀበሉ፡፡ ለወቅቱ በሽታ ሊሆን የሚችል መድሀኒት ካላቸው ይጠየቁ፡፡ የውጭ ምንዛሪ ያስፈልገናል - መድሃኒት ወደ ውጭ አገር ገበያ እንላክበት፡፡
ጅብ ከተማ እንዳይገባ እንገዝታለን፣ በድግምት እናግዳለን፤ የምትሉ ሰዎች ዛሬ ነገ ሳትሉ ወደ መከላከያ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ደውሉና የአገር አለኝታ ነን በሉ፡፡ የአገራችንን ድንበር ማንም እንዳይሻገር ከልክሉ - የጠላትን እግር በቆመበት ቀጥ እንዲል (ፍሪዝ) አድርጉት፡፡ የኮንትሮባንድ ንብረት አስራጊዎችንም በያሉበት አቁሟቸው፡፡ በረዶ እንዳይዘንብ ለማድረግ እንችላለን፤ በረዶ አቅጣጫ እንዲቀይር (ጨርሶም፣ እንደ አድማ በታኝ ደመናውን ብትንትኑን አውጥተን ወደ ንፋስነት መለወጥ)  እንችላለን፤ የምትሉ፤ ችሎታችሁን ከአየር መቃወሚያ፣ ፀረ ሚሳዔል፣  ...፡፡ ብቻ ልታደርጉ የምትችሉትን አሳወቁ! በድግምት/አስማት፣ ጠጠር ከመሬት ላይ አስነስተን የሰውን ቤት ጣሪያ ለመቀጥቀጥ እንችላለን (አንደርቢ)፣ የመሬት ስበት ህግን የምንዘልበት ዘዴ አለን የምትሉ ሰዎችም፤
ችሎታችሁን ለፀብ ማስኬጃነት ብቻ ከመጠቀም፣ እቃ ከቦታ ቦታ ለማንቀሳቀሻነትም አውሉት፡፡በድግምት ኃይል፣መጫኛን እንደ ኤሌክትሪክ ፖል ቀጥ አድርገን የማሳየት ብቃት አለን የምትሉ ሰዎችም፤ መጫኛን ያለ ግብሩ ከምትገትሩት፣ መሬት ላይ ተጋድመው ከቀሩ የአክሱም ሀውልቶች አንድ ሁለቱን ቀጥ አድርጉልን፡፡ ከላይ ከጠቀስኳቸው ባለችሎታዎች ጋር ተጣምራችሁ ሰርከስ ብጤ በማዘጋጀትም፣ ለአበሻ ለፈረንጁ ትርዒት አሳዩትና አገራችን ገቢ ታግኝ፡፡
በመጨረሻም፤ “የወገን ወዳዱ፣ ይታያል ጉዱ! ... ኢትዮጵያን ያላችሁ፣ እስቲ እንያችሁ!” ይህ አጠቃላይ ጥሪ ነው፡፡ ምርት እንዳይወድቅ፣ ዜጎች ለረሀብ እንዳይጋለጡ፣ ሥራ/ገቢ እንዳያጡ፣ በበሽታ እንዳይጠቁ፣ በውሃ፣ በመብራት፣ በመንገድ፣ ወዘተ ችግር እንዳይጎሳቆሉ ... ማህበራዊ አገልግሎቶች እንዲሳለጡ፣ ሁሉም ባለሙያ፣ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ያድርግ፡፡ ከማንኛውም ጊዜ ይበልጥ በየሙያዎችን፣ በየተሰማራንበት የሥራ ዘርፍ ሁሉ፣ ከሚጠበቅብን በላይ ውጤታማ ሥራ ለመስራት እንትጋ፡፡ "ጸሀፊ ነን ያላችሁ - እስቲ እንያችሁ!” ቸብ! ቸብ! ቸብ! የነገ ሰው ይበለን!


Read 8305 times