Saturday, 30 May 2020 13:40

ችኩል ሰው በሬ ያልባል!

Written by 
Rate this item
(7 votes)

    ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ነፍስ አባት የነፍስ ልጃቸው ቤት ጎራ ይላሉ፡፡ የነፍስ ልጃቸውም፤
“ውይ አባቴ፤ እንኳን ደህና መጡ! መቼም ማሰብ አያስመሰግንም እንጂ ሳስብዎት ነው የመጡት!”
ነፍስ - አባትየውም፤
“መቼም በደጃፍዎ ሳልፍ ዝም ብዬ ብሄድ አምላክዎ ያየኛል ብየ ገባሁ!”
“እንደው ወዳጄ ሚካኤል አይለመነኝ ክፉ ነበር የምቀየምዎት… አልፈው ቢሄዱ! በሉ ትንሽ ጉሽነት ቢኖረውም ፉት ይበሉት፡፡ እንኳን ደህና መጡ!” አሏቸውና ከጉሹ ቀምሰው አቀረቡላቸው፡፡ ብዙም ሳይቆዩ ተመለሱና፤
“በሉ እስቲ ይቺን ይሞክሩ፡፡ የአልጫ ፍትፍት ናት፡፡ ቅንጨው ብዙም ባይሆን ለአይነቱ ያህል ይጠቅማል፡፡ ጥብሱ እየደረሰ ነው፡፡ ጎድኑም ወደ መጨረሻ ሳይበርድ አመጣለሁ!”
“ኧረ ይህ ሁሉ አያስፈልግም ነበር’ኮ እመቴ” አሉ፡፡
 የነፍስ አባትየው እየበሉ ሳሉ እመቴ ጉድ ጉድ ይላሉ፡፡ ወዲያው ሁሉም ምግብ ገበታውን ሞላውና አብረው መብላት ቀጠሉ፡፡
“ምነው ቤተስኪያን አላየሁዎትም ታዲያ?”
“ኧረ እዚያው ነበርኩ፤ ከሰዓት በኋላ ማ’በር አለብኝ፡፡ አንዳንዶቹ ማ’በርተኞቼ፤ በጊዜ መጥቸ የማቀራርብላቸውን ላመቻች ብዬ ነው ከቤተስኪያን ቸኩየ የመጣሁት”
የነፍስ አባትዬውም “ደግ አድርገዋል፡፡ በጊዜ ፀበሉን ልርጭና ባርኬለዎት እሄዳለሁ፡፡ አንድ ሁለት ጥሪ አለብኝ፤ የሚካኤል ተሳላሚዎች እንዳይቀየሙኝ ደረስ ደረስ ልበልላቸው፤ ደግሞ ያመቱ እኮ ነው ዛሬ!”
እሜቴም፤ “አዎን አባቴ፣ በእለቱ ለኔ ሲል ደጀ ጣለዎ! እሰይ እሰይ! ሚካኤል ነው ያመጣዎት! በሏ ለማህበርተኞቼ ይቅመሱላቸው፡፡ መምጣትዎንም፤ ፀበል መርጨትዎንም እነግራቸዋለሁ፡፡ መቼም አስቤ አልጠራሁዎትምና እንደው ቤት ያፈራውን ቀምሰው ነው የሚሄዱት፡፡ እንደው ይኼው ሚካኤል ምስክሬ ነው ሌላ ቀን ሲመጡ በደንብ አርጌ ነው የምጋብዝዎት!”
የነፍስ አባትየውም፤
“ከሄድኩማ አዎ!” አሉ ይባላል፡፡
*     *    *  
“መልካም መስተንግዶ እንግዳን ከመሄድ ያዘገያል” ይባላል፡፡ በአቅምም ሆነ ያለ አቅም፣ እንግዳው አቀባበል ከተመቸውና ቆይታው ያማረ ከሆነለት፣ እንግድነቱን ረስቶ ቤተኛ መሆን የሚቃጣው ደረጃ ያደርሰዋል፡፡ በእርግጥ ዛሬ ዛሬ፣ ይኼ የእንግዳ ተቀባይነታችንን ባህል ከጥያቄ ውጭ የሚያደርገው ሁኔታ እየመጣ ይመስላል፡፡
የኮሮና በሽታ ስጋት ማንንም ወደ ማያምንበት ክፉ ጊዜ ላይ ጥሎናል! እንደሚታወቀው አገራችን በፖለቲካም፣ በኢኮኖሚም፣ በባህልም ስታስተናግድ የኖረችው አባዜ በርካታ ነው:: ከሁሉም በላይ ደግሞ የማያቋርጥ እንድገትን እየቋመጥን የማያቋርጥ ድህነትን ታቅፈን፤ “ሞት ሳይሞቱት ነው እሚለመድ” ያለውን የሎሬት ፀጋየ ገ/መድህን ጥቅስ መሪ መፈክር ካደረግን እያለ አመታት ዘለቁን፡፡ አሁን ደግሞ ከድጡ ወደ ማጡ ወይም እንደ ፈረንጆቹ አባባል ‹From the fire – pan to the fire› ሆነና ሁሉንም በጠቅላይ አዛዥነት የሚመራ የሚመስለው ኮሮና መጣ! እንደ ወትሮው “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” ወይም እንደ ፈረንሳይኛው ብሂል፤ “apres moi le dituge” ብለን የምናልፈው አይሆንም፡፡ ይልቁንም ጨክነን፤ ከሼክ ስፒር ጋር “መሆን ወይስ አለመሆን?” መጠንቀቅ ወይስ አለመጠንቀቅ? መታጠብ ወይስ አለመታጠብ? መኖር ወይስ አለመኖር? ምናልባት አስራ አንደኛው ሰዓት ላይ መሆናችንን መገንዘቢያችን ሰዓት ነው፡-
አሰሪው ለጸሐፊው አንድ የሚጻፍ ጽሑፍ ሥራ ይሰጣታል፡፡ ፀሐፊውም፤
“ይኼ ሥራ ለመቼ እንዲያልቅ ነው የምትፈልገው?” ስትል ጠየቀችው፡፡ (“How do you want it done – sir?”)
አለቅየውም፤
“ከተቻለ ለትናንት አድርሽልኝ!”
(If possible Yesterday!) አላት ይባላል፡፡ ሥራን በአግባቡና በሰዓቱ ማጠናቀቅ ያለብን ወቅት ላይ ነን፡፡ ይኼ መርሆ ለማናቸውም ጊዜ የሚሰራ ነው!
ያም ሆኖ አለቃ የበዛባትና የሥራ ድካም ያጎበጣት መከረኛ ሴት እንዳለችው፡- (… በመቶ አምሳ ጌታ
ስታጠቅ ስፈታ
ነጠላየ፤
አለቀ በላየ!...) እስከ ማለት ልንደርስ አይገባም፡፡
ጥድፊያ ጊዜን አቅምንና ቦታን ያገናዘበ ሊሆን ይገባል፡፡ በመጣደፍ የተሻለ ሪኮርድ እናስመዘግባለን ብለን “የቸኮለች አፍሳ ለቀመችን” ከረሳን፣ ከጥቅሙ ጉዳቱ የሚያመዝን ሁኔታ ውስጥ እንወድቃለን! ይህንን ካላመዛዝንን “ችኩል በሬ ያልባል” የተባለው ተረት በኛ ላይ ይተረታል! ከዚህ ይሰውረን!!  
የሚያስችኩልና የማያስቸኩለውን እንለይ!
በጊዜ እናቅድ፡፡ ጊዜ ሳንፈጅ እንጨርስ!
በጥናት ላይ የተመሰረተ እቅድ ለመልካም ፍሬ እንደሚያበቃን እንወቅ!!
ዛሬ መኖር ያለብን እንደ ራሳችን፣ እንደ ጎረቤታችን፣ እንደ ህብረተሰባችንም፣ እንደ አለምም ነው!
ዓለም “ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር” እንደ ተባለው፣ ሁሉም ኮሮናን ወደ ማሸነፍ እንበል!
የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ፤ አያሌ በሽታዎች እንደተሸነፉት ሁሉ ኮሮናም ይሸነፋል!
እንጠንቀቅ!
እንታገስ!
እንመርመር!
በእርጋታ እየተጓዝን “በሬ ከማለብ” እንገታ!!

Read 14293 times