Saturday, 30 May 2020 11:56

አምነስቲ ባለፈው ዓመት በአማራና ኦሮሚያ አካባቢዎች ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት ተፈጽሟል አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

  በግጭቶችና ጥቃቶችም ከ270 በላይ ሰዎች ተገድለዋል ብሏል

          ባለፈው አንድ አመት ጊዜ ውስጥ በኦሮሚያና አማራ ክልል የመንግስት የፀጥታ ሃይሎች፣ የየአካባቢው ባለስልጣናትና ኢ-መደበኛ የሆኑ አደረጃጀቶች በዜጐች ላይ ከፍተኛ ኢ-ሠብአዊ ድርጊት ሲፈጽሙ መቆየታቸውን የመብት ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል በጉዳዩ ላይ ጥልቅ ምርመራ አድርጐ፣ ትናንት ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ አስታውቋል፡፡
ለአንድ አመት ያህል በሁለቱ ክልሎች ጥልቅ ጥናት ሲያደርግ መቆየቱን የገለፀው አምነስቲ በዋናነት በየክልሉ ያሉ የፀጥታ ሃይሎች፣ የየአካባቢው ባለስልጣናትና ኢ-መደበኛ የሆኑ አደረጃጀቶች የተሳተፉበት የዜጐች ግድያ፣ ድብደባና እንግልቶች ተፈጽመዋል ብሏል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብና ምስራቅ ጉጂ ዞኖች እንዲሁም በአማራ ክልል ምዕራብና መካከለኛ ጐንደር ዞኖች በስፋት በዜጐች ላይ ጥቃት መፈፀሙንም ሪፖርቱ አትቷል፡፡
በጥር 2019 በምስራቅ ጉጂ ዞን በምትገኘው ጉሮ ዶላ ወረዳ እና በምዕራብ ዞን በምትገኘው ዱግዳ ዳዋ ወረዳ በጥቅሉ 39 ሰዎች በጥይት መገደላቸውን፤ ከእነዚህ ውስጥ 23 ያህሉ የጐሮ ዶላ፣ 16ቱ ደግሞ የዱግዳ ዳዋ ነዋሪዎች መሆናቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል” ተቋሙ፡፡
በተለያዩ ጊዜያትም የኦሮሚያ ልዩ ሃይልና የመከላከያ ሠራዊት የተሳተፉባቸው ግድያዎች መፈፀማቸውንም የገለፀው አምነስቲ፤ ከግድያ ባሻገርም ሰዎች ሰብአዊ መብታቸውን በሚገፍ መልኩ ለእስር ተዳርገዋል ብሏል፡፡ በፖሊስ ምርመራ ወቅትም ድብደባ፣ እንግልት እንዲሁም የአስገድዶ መድፈር ድርጊት ተፈጽሟል የሚል አቤቱታ እንደቀረበለትም የሰብአዊ መብት ተቋሙ ገልጿል፡፡
በሺዎች የሚቆጠሩም በግድ ከቀዬያቸው ተፈናቅለዋል ያለው አምነስቲ፤ በተለይ ከኦነግ (ሸኔ) ጋር በተያያዘ የሚደረጉ ዘመቻዎች የአካባቢውን ህዝብ ለሰብአዊ ቀውስ እየዳረገ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
በአማራ ክልል ደግሞ በምዕራብና መካከለኛው ጐንደር ዞኖች በሚገኙ የቅማንትና አማራ ህዝብ መካከል ግጭት ተፈጥሮ በርካቶች መጐዳታቸውን፣ ይህንንም የክልሉ ፀጥታ ሃይል በቸልታ መመልከቱን ተቋሙ በሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡
በጥር 2019 ዓ.ም በቋራ፣ በመተማና ጭልጋ ወረዳዎች በተፈፀሙ ጥቃቶች በ24 ሰአት ውስጥ 58 ሰዎች ተገድለው በጅምላ መቀበራቸውን ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡
በመስከረምና ጥቅምት 2019 ወራትም በጐንደር ከተማና ዙሪያዋ በተቀሰቀሰ ግጭት፣ 43 ሰዎች መሞታቸውን፣ 12 መቁሰላቸውን ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡
ጥር 10 ቀን 2019 ከሰዓት በኋላ በመተማ ዮሐንስ ከተማ በመቶዎች የሚቆጠሩ “የጐበዝ አለቃ” እና “ፋኖ” የተባሉ ኢ-መደበኛ አደረጃጀቶች፣ ቀበሌ ሶስት የሚባል መንደር በመግባትና ነዋሪዎችን በመክበብ በጠመንጃና በፈንጂ ጥቃት መፈፀማቸውን ያስታወቀው አምነስቲ፤ የመከላከያ ሠራዊት ጥቃቱን ለማስቆም የቻለው ከ1 ቀን ቆይታ በኋላ ነው ሲል ወቅሷል፡፡ በዚህ ጥቃትም 58 ሰዎች መገደላቸውንና በመተማ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን መቀበራቸውን ሪፖርቱ ያትታል፡፡
አምነስቲ የሳተላይት ምስሎችን በመጠቀም ስለ ጥቃቱ ማጣራት ማድረጉንና በዚህም የቅማንት ማህበረሰብ በሚኖርበት አካባቢ እሳትና ጭስ የሚያሳዩ ምስሎች መገኘታቸውንም አስታውቋል፡፡
በጐንደር ከተማ በስተሰሜን በሚገኙትና በብዛት የቅማንት ማህበረሰቦች ባሉባቸው አርባብን ወለቃ እና ሳይና ቀበሌዎች የበቀል ጥቃት በአማራ ማህበረሰብ ላይ መፈፀሙን በዚህም  ግጭት ቢያንስ 130 ሰዎች መገደላቸውን የገለፀው ሪፖርቱ፤ በዚህ ወቅትም የፀጥታ ሃይሎች ቸልተኝነት የጐላ እንደነበር ጠቁሟል፡፡
አምነስቲ ይህን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሪፖርት ሲያጠናቅር ከ80 በላይ ግለሰቦችን በአስረጅነት ማናገሩን፣ በጉዳዩ ላይም የተለያዩ የፌደራልና የክልል አስተዳደሮች ምላሽ እንዲሰጡበት ማድረጉንም የጠቆመው አምነስቲ፤
አጥፊዎች ለህግ እንደሚቀርቡና መንግስት አስተማሪ የሆነ እርምጃ እንደሚወስድ መገለፁን አስፍሯል፡፡
ጥቃቱ እንዲቆምና እንዳይደገም ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድም አጥፊዎችን በህግ እንዲቀጡና ለሁሉም የፀጥታ ሃይሎች እንዲህ መሰል ጥቃቶች እንዳይፈፀሙ የሚያደርግ ልዩ ትዕዛዝ ይሰጡ ዘንድም እንዲሰጡም አምነስቲ በሪፖርቱ ጠይቋል፡፡  

Read 10472 times