Print this page
Saturday, 23 May 2020 16:40

የትውልድ ነጋሪት

Written by  ታደለ ገድሌ (ዶ/ር)
Rate this item
(0 votes)

‘እጎዘጉዛለሁ ሣርና ቄጠማ፤
ለሕዳሴው ግድብ ለዓባይ ዳር ከተማ፡’
እያለ እሚያዜመው ያገር ቤት ወገኔ፤
ተስፋ ስለአየ ነው በዓባይ ሥልጣኔ፡፡
ሣርና ቄጠማው ሲቀርብ  ለውዳሴ፤
ስመኘው እንደ አሮን፣ መለስ እንደ ሙሴ፤
ዓቢይ እንደ ኢያሱ፣ ገባኦን ተራራ፤
ለነጻነት መንገድ ጨለማ እየገራ፤
የቀዘቀዘውን ሞተር እየሠራ፤
ለኢትዮጵያ ሕዳሴ ብርሃን የሚያበራ፡፡
ዓባይ ነጻ ወጣ ከባርነት ግብሩ፤
ከነዓን ኢትዮጵያ ገባ ወደ አገሩ፡፡
እንግዲህ ወገኔ ጠፍቶለት አባዜ፤
በመርከብ በጀልባ ሊጓዝ ነው ሁል ጊዜ፤
በሰው ሠራሹ ዓባይ በባሕረ ተከዜ፡፡
 ጥቅም የሚገኘው ስንፋቀርና ስንዋደድ እንጂ፤
መጣላት መኳረፍ ለምንም አይበጂ፡፡
ለእኛ ብቻ ካሉ ዓባይ ለግላቸው፤
ውኃማ ለግብጾች ጥንትም ጠላታቸው፤
ልክፍታቸው እንጂ አይደለም ገዳቸው፤
ስለ ሰመጠበት ገብቶ ፈርዖናቸው፡፡
ዓባይ ወደ አገሩ ከግብጽ ተጠራ፤
ቤቱ ተሠርቶለት እንደ ዲያስፖራ፡፡
ጠረፍ እስከ ጠረፍ ኢትዮጵያውያን ሁሉ፤
በጸሎተ ሙሴ ንሴብሖ እያሉ፤
አላህ አክበር ብለው  በዱአ እየጦለሉ፤
ዓባይን በዜማ በአንድነት ባረኩት፤
ጨለማውን ዘመን በብርሃን አፈኩት፡፡
የኢትዮጵያ ልጆች እየተቀናጁ፤
ባላደራ ሆነው ጊዜውን ሲዋጁ፤
ምነው በዚህ ዘመን ቶሎ ባላረጁ፡፡
የሕዳሴው ፈረስ ቀድሞ ገሰገሰ፤
ወደ ኋላ አይልም ከፊት ከአልደረሰ፡፡
ውኃም እንደ ሰው ልጅ ሕዝብ ሊያረጋጋ፤
ቀኑን እየዋለ ሌቱን እያነጋ፤
ይኸው ዘብ ቆመለት በጉባ ጠረፍ፤
በኢትዮጵያ ልጆች ቅን አሰላለፍ፡፡
የሕዳሴው ግድብ በኅብረት ተሠራ፤
የዓፄ ዳዊት ምኞት መልካም ፍሬ አፈራ፡፡
ግብጾች ብንላችሁ ያላንዳች ሽንገላ፤
ከእኛ ጋር መጣላት ለምን ፈለጋችሁ፤
እኛ ስንገነባ ሲሆን በረዳችሁ፡፡
ለእኔ ለእኔ አትበሉ ጊዜው ተለውጧል፤
ብቻውን የበላ ብቻውን ይሞታል፡፡
ክፉ ካሰባችሁ  ጦር ብትነቀንቁ፤
ከኢትዮጵያ ጋር ነው እግዜሩም እወቁ፡፡
በተፈጥሮ ግዳጅ እኛን ሳትጠይቁ፡፡”
 እኛ እምንመኘው ታሪክ ተቀይሮ
ሰላም እንዲሆን ነው ከዚህ እስከ ካይሮ፡፡
የሕዳሴው ግድብ ሲሠራ  ቤታቸው፤
ለግብጽና ሱዳን ዛሬም ሕይወታቸው፤
የጋራ ልማት ነው ቅርም አይላቸው፡፡
የሕዳሴው ግድብ  ታላቅ ባለሟሉ፤
ዕፀ በለስ ቀምሰው ለታመሙት ሁሉ፤
ፈዋሴ ዱያን ነው ልክ እንደ ጸበሉ፡፡
የምን በረሀነት የምንስ ቃጠሎ፤
የምንስ ድህነት  አንገት አዘንብሎ፤
ጠልና ደመና በላያችን ውሎ፡፡
ሀገረ ኢትዮጵያ በውኃ ታጥራለች፤
ጠላት አይደፍራትም ታስደነግጣለች፡፡
የሕዳሴው ግድብ ፈክቶ ሲጎመራ፤
ክበበ ፀሐይ ነው የፀደይ ሙሽራ፤
የዘለዓለም ብርሃን የዘለዓለም ጮራ፤
እስከ ዓለም ዳርቻ ደምቆ የሚያበራ፤
የልማት አውታር ነው የመክሊት ጎተራ፤
የነጻነት ችቦ የአንድነት ደመራ፤
የትውልድ ነጋሪት ጸናጽል ዕንዚራ፡፡
በሕዳሴው መንደር በሕዳሴው አምባ፤
የትውልድ ነጋሪት ድምፁ ሲያስተጋባ ፤
እንኳንስ በሕይወት ቆመው ያስተዋሉ፤
በመቃብር ዓለም በእንቅልፍ ላይ ያሉ፤
ለኢትዮጵያ ትንሣኤ ቆመናል እያሉ፤
የምጽዓት ዘመን ነው ሁሉም ይነሣሉ፡፡

Read 1637 times