Saturday, 23 May 2020 16:31

ትዳር

Written by  ዮናስ ብርሃኔ
Rate this item
(1 Vote)

  ትዕግስቱ ከንፈሮቹን ገጥሞ እያንጎራገረ ነው የኮንዶሚኒየሙን ደረጃ የወጣው፡፡ ቤቱ በር ላይ እንደ ደረሰ ጣቱ ላይ ሰክቶ እያሽከረከረ በነበረው የመኪናው ቁልፍ በሩን ቆረቆረ፡፡ እጁ ከበሩ ላይ ሳይነሳ እዚያው ደገፍ እንዳለ እንደገና በስሱ ማንጎራጎር ጀመረ፡፡ ውጪ ውጪውን እያየ በሆዱ ሲያዜም፣ እጁም በሩን እየነካካ በድምጽ ሲያጅበው ነበር፡፡ የበሩ ቁልፍ ከውስጥ መዞር ሲጀምር ነው፣ እጁ ከበሩ ላይ የተነሳውና ዜማው የቆመው፡፡
"እሺ እንዴት አመሻችሁ?" አለ እግሩ እንደገባ፡፡
"መስታወቱን ልትሰብረው ነው እንዴ? አንዴ ካንኳኳህ አይበቃም?" አለችው ሚስቱ። ድምጿ ሾሎበታል፡፡ ፊቷን ከስክሳዋለች፡፡
"ምነው ረበሽኩ እንዴ?" አላት ቆሞ ትክ ብሎ እያያት፡፡ የቁጣዋ ሰበብ አልገባውም፡፡ አይኑን ከፍቅር ላይ አነሳና የከፈተችለትን በር ዘግታ ወደ ማዕድ ቤቷ እየተመለሰች የነበረችውን ተዋቡን ቃኘት አደረገ። ተዋበች ከገጠር የመጣች የፍቅር ዘመድ ናት፡፡ አንጀት የምትበላ ቅጥንጥን ያለች፣ ስስ ፍጡር ነች፡፡ ታሳዝነዋለች፡፡  
"እኔ’ንጃ ምናልባት ሳላውቅ ይሆናል፤ ሶሪ!" በሩን በቁልፉ እያንቋቋ ሲያዜም እንደነበር ትዝ ያለው መሃል ላይ ነው፡፡
"እንዴት ነሽልኝ ግን ለማንኛውም?" ወደ ሚስቱ ቀርቦ ከንፈሩን አሞጠሞጠ፡፡ እንደ ባዳ ጉንጯን አቀበለችው፡፡
"ሳላስበው የምትለው ልብህን የት ጥለህ ነው? ይህን ያህል ያስመሸህስ ምንድን ነው?"
"አሃ! ታዬ እና ሚስቱን እያስታረቅን እንደነበር ‘ላይቭ’ አይደል እንዴ የዘገብኩልሽ!?" አለ ሶፋው ላይ ራሱን እያመቻቸ፡፡
"የራስን ቤት ጥሎ ነው እንዴ ታዲያ?"
 ሚስቱ ነገር ነገር እንዳላት አልጠፋውም፡፡
"እንዴት ሆኑ ቢቀድም አይሻልም ሆዴ?"
"የራስን ትዳር ማቅናት ይበልጣል ብዬ ነው፡፡ ተሳሳትኩ!?"
"አሁን ያን ያህል የሚያባብል ነገር ነው ፍቅር?"
"ዛሬ ብቻ አናስመስለዋ! ከሶስትና አራት ሰዓት በፊት መች መጥተህ ታውቃለህ?!"
"እንዴ ፍቅር አመረርሽ እኮ! ቀለል አድርጊው እንጂ!"
"ምንድን ነው ቀለል አድርጊው ብሎ ቋንቋ፤ ትዳር መስሎኝ የያዝነው!?"
"እሺ በቃ! አሁን እንርሳው። እራት በላሽ እንዴ?" ወደ ምግብ ጠረጴዛው እየቃኘ፡፡
"አላሰኘኝም፡፡ ምነው ፌሽታ ላይ አልነበርክም እንዴ?"
"አአይ ትጠብቂኛለሽ ብዬ አልበላሁም፡፡ አንድ ሁለቴ ብቻ ነው ያጎረሱኝ፡፡
በነገራችን ላይ አስማማናቸው፤ ታረቁ፡፡"
"ኧረ ባክህ!" አለች ለማስመሰል እየሞከረች፡፡  
"አዎ! ለነገሩ መጀመሪያውኑም እዚያ ደረጃ የሚያደርስ አልነበረም፡፡ ዝም ብለው ነው፡። ኬዙን ነግሬሽ የለ? አንዳንድ ሰዎች የሚጣሉበት ነገር ግን ያስቃል" አለና ሳቁን ብልጭ አደረገ፡፡   
"ይሄኔ እሷ ስንቱን በውስጧ ችላው ይሆናል!? እሱ እንደሆነ የለየለት ጠጪ ነው፡፡"
"ኧረ እባክሽ ፍቅር … ዝም ብለሽ የሰው ሰው እንደዚያ አትበይ፡፡ ዋናው የተጣሉበት ምክንያት እኮ…" ብሎ የጀመረውን ሳይጨርስ አቋረጠችው፡፡
"ምንድን ነው ዝም ብዬ? ዳሩ አንተም ያው አይደለህ!"
"ኧረ እንደው በፈጠረሽ! አሁን እኔ  ጠጪ የምባል ሰው ነኝ? በሳምንት ሁለት፣ ሶስት ቀን ያውም ሶስት ቢራ ወይም ቢበዛ አራት ብጠጣ ነው። በዚያ ላይ የእኛ ስራ እንደምታውቂው በኮኔክሽን ነው፡፡ ከሰዎች ጋር አንድ ሁለት ማለት አለብሽ፡፡"
"አሃ! መሸታውንም ስራህ ያደረግከው ለዚያ ነዋ ለካ!"
"እንደዚያ ሳይሆን" አለና አፉን በእጆቹ ሸፍኖ ጋዙን አስወጥቶ ቀጠለ፡፡ "ያም አለ ለማለት ያህል ነው፡፡ እንዳንዴ ደግሞ እኮ ምንም አይደል ፍቅር፡፡ ያው አንቺ እንደዛ አይነት ነገር ማየትና መስማት አልፈልግም ስለምታይ ነው እንጂ አልፎ፣ አልፎ ያስፈልጋል፡፡ የሱም ሚስት ብትሆን አንዳንዴ ከእኛ ጋር ዘና ትላለች እኮ፡፡ እስኪ አንቺም አንዳንዴ እንኳ ወጣ ብለሽ ፈታ እንበል፡፡ ኧረ እንደውም ሳልነግርሽ፤ የእነ የማነ የአራተኛ አመት ‹አኒቨርሳሪ› ቅዳሜ ነው፡፡ ጠርተውሻል"
"ማን እኔ! ሥራ አላጣሁም!" ፍርጥም ብላ መለሰችለት፡፡
ለማሳመን ወይም ለመከራከር አልሞከረም፡፡  
"ትዳር እንደዛ እየተባለ የሚሆን ይመስልሃል?"
"አአይ እንደዚያ ሳይሆን ሁሌ በአንድ አጥር ውስጥ ተጠርንፎ ከመኖር የሆነ ለየት ያለ ሙድ መፍጠር ግድ ይላል ለማለት ያህል ነው፡፡"
"ሙድ የምትፈጥረው መሸታ ቤት ነው?"
"ኧረ ባክሽ፣ ባክሽ" አለና ሳቅ አለ፡፡ "አንዳንዴ ሳስበው የምትጨቃጨቁት ‘ሮማንቲክ’ ጨዋታ ካለመቻል ይመስለኛል፤ስለዚህ እንደ ፍቅር መግለጫ ብወስደው ሳይሻል አይቀርም"
"ምን ለማለት ነው?" ጠየቀችው፤ኮስተር ባለ ቅላጼ፡፡
"እስኪ አሁን የፍቅር ጨዋታ አምጪ!"
"አንተ ሞቅ ብሎህ ስትመጣ ነው ጨዋታ የሚታይህ? ያለዚያማ ለትዳርህ ጊዜ ትሰጥ ነበር"
"የጠፋው ሮማንቲክ ጨዋታው እንጂ ጊዜው መች ጠፋ እናቴ!"
"አሃ መሸታ ቤት ሄደን ነው ሮማንሱን የምናመጣው?"
" ነገሩን ወዴት፣ ወዴት ነው የምትወስጂው?"
"እራት ላቅርብ?" አለች ተዋቡ፡፡ ለሁለቱም ነው ጥያቄዋ፡፡  
"እኔ አልፈልግም፡፡" አለች ፍቅር፤አቀማመጧን ቀይራ እየተደላደለች፡፡
"እኔም ይቅርብኝ" አለ ትዕግስቱ፡፡
"በቃ እቃዎቹን አጣጥቢና ወደ መኝታሽ!" አለቻት ፍቅር፤ትህትና በራቀው ድምጸት፡፡   
"አልበላሁም ስትል አልነበር?" ወደሱ ደግሞ ዞረች፡፡
"አይ አንቺም የምትበይ መስሎኝ ነበር፡፡ ብትበይ ኖሮ እኔም እሞክር ነበር፡፡"
"እንደሱ የሚያስብማ  በጊዜ ይመጣል፡፡"
"በናትሽ ፍቅር በቃሽ!" አለና ከተቀመጠበት ተስፈንጥሮ ተነሳ፡፡
ትዕግስቱ ሽንት ቤት ደርሶ ሲመለስ የቲቪው ‹ቻናል› ተቀይሯል፡፡ ‹‹Life is Beautiful›› እየታየ ነበር፡፡ ተመቻችቶ ተቀመጠና ፊልሙ ላይ አተኮረ፡፡
"በጣም የሚገርም ፊልም ነው፡፡ አይተሽዋል ፍቅር?"
"እኔ ስለ ትዳር አወራሃለሁ፤ አንተ ስለ ፊልም ታወራለህ አይደል?"  
"ኡኡኡ --- ፍቅር በናትሽ!" ለመናት በምሬት፡፡
"ሆ ! ጭራሽ ሮማንስ ምናምን ይለኛል እንዴ?"
ውስጡ ቢበግንም፣ ሳቅ አለ ትዕግስቱ፡፡
"አንተማ ምን አለብህ! ቢራህን ተግተህ እየመጣህ ሳቅብኝ እንጂ!"
"ኧረ በፈጠረሽ፤ በቃ ‹ሶሪ› ብያለሁ! እስኪ አንዳንዴ እንኳን ነገሮችን ቀለል አርገሽ ማለፍ ልመጂ፡፡" አለ ራሱን ለመቆጣጠር  እየሞከረ፡፡  
"ምኑን ነው ቀለል የማደርገው? ትዳር መስሎኝ የያዝነው!?"
"ትዳር ማለት እኮ እቤት በጊዜ ገብቶ መጨቃጨቅ አይደለም፡፡"
 "ወይኔ ፍቅር ጉድሽ! ባንተ ብሶ እኔን ጨቅጫቃ አልከኝ!"
ትዕግስቱ ተሟጥጦ፣ ንዴቱ እየፈላበት ቢሆንም ዝምታን መረጠ፡፡  
"ወቸ ጉድ! ጭራሽ ጥፋተኛዋ እኔው ሆንኩና አረፍኩ!" ቀጠለች፤ፍቅር፡፡
ትዕግስቱ ትኩረቱን ፊልሙ ላይ ለማድረግ ሞከረ፡፡ ግን ዕድል አልሰጠችውም፡፡
"ትዳራችንን ጭቅጭቅ አደረግሽው ነው ያልከኝ!?"
ውስጡ በንዴት ሲንጨረጨር ይሰማዋል፡፡
"ንገረኝ እንጂ!?" ሚስቱ ተፈታተነችው፡፡
እሱ ግን በዝምታ አደባ፡፡ ግን እያበጠ እያበጠ ድብ አክሏል፡፡
"ምንም ሳታደርግ ዝም ብዬ ነው የምጨቃጨቅህ ማለት ነው?"
ደሙ ተንተከተከ፡፡ ጸጉሩ ቆመ፡፡ ሥሮቹ ተወጣጠሩ፡፡ ሁለመናው አባበጠ፡፡
ፍቅር ሁኔታው አላማራትም፡፡ ከመቅጽበት ኩምሽሽ ብላ በዝምታ ተዋጠች፡፡ ድንገት ተቀያየረባት፡፡ የተቆጣ አንበሳ መስሎ ታያት፡፡ አልተሳሳተችም፡፡ ድንገት ተወርውሮ ነው እላይዋ ላይ የሰፈረው፡፡  

Read 1889 times