Saturday, 23 May 2020 14:50

በኮሮና ከ9 ሚ. በላይ ኢትዮጵያውያን ለምግብ እጥረት ሊጋለጡ ይችላሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

  በኮሮና ወረርሽኝ  ምክንያት በኢትዮጵያ ከተሞች ውስጥ የሚገኙ መደበኛ ባልሆኑ ስራዎች ላይ የተሰማሩ ከ9 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለምግብ እጥረት ሊጋለጡ እንደሚችሉ የአለም ምግብ ፕሮግራም አስታውቋል፡፡
የአለም የምግብ ድርጅት ሪፖርት ይፋ ባደረገው ጥናት፤ በርካታ የእለት ገቢ የሚያስገኙ የግል የሥራ ዘርፎች በኮሮና ወረርሽኝ ስጋት ሳቢያ በትንሹ ለቀጣይ ሶስት ወራት ዝግ ሆነው ሊቆዩ በመቻላቸው ሚሊዮኖች የሰው እጅ ጠባቂ ይሆናሉ ብሏል፡፡
የኢፌዲሪ የሥራ ፈጠራ ኮሚሽንን ሪፖርት የጠቀሰው ጥናቱ፤ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የተለያዩ ከተሞች ወደ 1.9 ሚሊዮን የሚደርሱ የእለት ገቢ የሚያስገኙ ሥራዎች እንዳሉ ጠቁሞ ከእነዚህ መካከል በቀጣዮች 3 ወራት 750 ሺህ ያህል ገቢ የሚያስገኙ ይቆማሉ ብሏል፡፡
ይሄን ተከትሎም በከተሞች የሚኖሩ ከ9 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በቀጣይ ለከፋ የምግብ እጥረት ሊጋለጡ እንደሚችሉ የአለም የምግብ ፕሮግራም አስታውቋል፡፡
በአሁን ወቅት ኢትዮጵያን ጨምሮ በዘጠኝ የምሥራቅ አፍሪካ አገራት ከ20 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በኮሮና ምክንያት ለምግብ እጥረት እስከ መጪው ሐምሌ ባለው ጊዜ ውስጥ ይህ አሃዝ ወደ 43 ሚሊዮን ከፍ እንደሚል ተመልክቷል፡፡
የዓለም የምግብ ፕሮግራም፣ በኮሮና ስጋት ሳቢያ እጥረት ይገባሉ ብሎ በሪፖርቱ ያካተታቸው የአፍሪካ አገራት ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኤርትራ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ኡጋንዳ፣ ሩዋንዳ፣ ቡሩንዲና ጅቡቲ ናቸው:: በእነዚህ አገራት ውስጥ የሚገኙ 3.3 ሚሊዮን ስደተኞችም ለከፋ የምግብ እጥረት ይጋለጣሉ ያለው ሪፖርቱ፤ ከወዲሁ አስፈላጊው ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳስቧል፡፡  

Read 11372 times