Saturday, 23 May 2020 14:48

ቀጣዩን ምርጫ ለማካሄድ እስከ 13 ወራት ጊዜ ያስፈልጋል ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

  ተጨማሪ 2.5 ቢሊዮን ብር በጀት ያስፈልጋል

          በቀጣይ የኮሮና ወረርሽኝ መገታትን ተከትሎ 6ኛውን አገራዊ ምርጫ ለማከናወን ቢያንስ የ13 ወራት ጊዜና ተጨማሪ ከ2.5 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልገው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ፡፡
ባለፈው ሃሙስ በሸራተን አዲስ በተካሄደው በሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ላይ ተገኝተው በነሐሴ ወር ላይ ሊካሄድ ታቅዶ የነበረውን ምርጫ ለማስተላለፍ ውሳኔ ላይ የደረሱበትን ምክንያት ያብራሩት የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ት ብርቱካን፤ በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ የታጠፈውን 6ኛው አገራዊ ምርጫ መቼ ለማካሄድ እንዳቀዱ ተጠይቀው ሲመልሱ፤ ወረርሽኙ ከተገታና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተነሳ በኋላ እስከ 13 ወራት ጊዜ ያህል እንደሚያስፈልግ ባቀረቡት ባለሁለት ሴናርዮ ትንተና ተናግረዋል - ትክክለኛውን የጊዜ ሰሌዳ አሁን ላይ ለማወቅ አዳጋች መሆኑን በመጠቆም ዘንድሮ ምርጫው አለመካሄዱን ተከትሎም የምርጫ ማካሄጃ ወጪ ከፍ እንደሚል የገለፁት ወ/ት ብርቱካን፤  በአጠቃላይ 8 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
በቀጣይ ቦርዱ የተለያዩ የቢሆን ትንተናዎችን መነሻ በማድረግ፣ አስፈላጊ የሆኑ ቅድመ ዝግጅቶችን እያከናወነ እንደሚቆይ ገልፀዋል - ሰብሳቢዋ፡፡
ቦርዱ በነሐሴ 2012 ምርጫውን ለማከናወን ምን ያህል በቁርጠኝነት ሲንቀሳቀስ እንደነበር ሰብሳቢዋ ሪፖርት በማቅረብ ጭምር አስረድተዋል፡፡
በዚህ መሠረትም ቦርዱ በ30 ቀናት ውስጥ የመራጮች ምዝገባ በ14 ቀናት ውስጥ እጩዎች ምዝገባ፣ በ90 ቀናት ውስጥ የምረጡኝ ዘመቻ እንዲሁም ለ121 ቀናት ለመራጮች ትምህርት ለመስጠት ተዘጋጅቶ እንደነበር አስገንዝቧል፡፡
በአንድ የምርጫ ጣቢያም እስከ 1500 መራጮችን ለማስተናገድ አቅዶ እንደነበርና በአጠቃላይ በምርጫው በመላ አገሪቱ 50 ሚሊዮን ዜጎች የሚሳተፉበትን ዝግጅት እያከናወነ እንደነበር አስገንዝቧል፡፡
የምርጫ ቁሳቁሶችና ሰነዶችን በአምስት ቋንቋዎች ማለትም በአማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማሊኛና አፋርኛ ማዘጋጀቱን፣ ምርጫውን ለማካሄድ የሚያስችሉ 28 የተለያዩ መመሪያዎችን ማርቀቁን አስገንዝቧል - ቦርዱ፡፡
ለሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባኤው ቦርዱ ባቀረበው ዝርዝር መረጃ ላይ በቀጣይ ምርጫው ሊካሄድ የሚችልባቸውን ሁለት የቢሆን ግምቶችን መነሻ ያደረጉ የጊዜ ሰሌዳዎችንም አቅርቧል፡፡
በመጀመሪያው የቢሆን ግምታዊ ስሌት ምርጫውን ለማከናወን አጣዳፊ ስራዎችን በመስራትና ሌሎች ጊዜ የሚፈጁ ጉዳዮችን በመቀናነስ በ10 ወር ምርጫን ማካሄድ የሚቻልበት የቢሆን ግምት ሲሆን ሁለተኛውና ቦርዱ ትኩረት ያደረገበት ግን የተረጋጉ ተግባራትን በማከናወን ለሁነቶች ተጨማሪ ቀናትን በመስጠት የተዘጋጀውና 13 ወርን ታሳቢ ያደረገው የጊዜ ሰሌዳ ነው፡፡
በመጀመሪያው የቢሆን ትንተናና ግምት መሰረት ምርጫውን በ10 ወራት ውስጥ ለማካሄድ ተጨማሪ 139 ሚሊዮን 349 ሺህ ብር ያስፈልጋል የተባለ ሲሆን በሁለተኛው የቢሆን ግምታዊ ስሌት ግን ከ2.5 ቢሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ ባጀት ያስፈልጋል ብሏል - ለሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባኤ የቀረበው ሪፖርት፡፡
የምርጫ ማስፈፀሚያ በጀቱ ከፍ ሊል የሚችለውም በዋናነት በኮሮና ምክንያት በዓለም አቀፍ ደረጃ ካለው የግብነት ዳት ሰንሰለት መራዘም ጋር በተገናኘ የቁሳቁሶች የዋጋ ንረት ሊያጋጥም መቻሉ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
መድረኩ ላይ ማብራሪያ የሰጡት የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ፤ የቫይረሱ ስርጭት በዚህ ጊዜ ይገታል ብሎ ገደብ ማስቀመጥ እንደማይቻልና መድሃኒቱም እስካሁን እንዳልተገኘ አስረድተዋል፡፡
በመንግሥት የወጣው አስቸኳይ አዋጅና መመሪያዎች የቫይረሱን የስርጭት መጠን ለመቀነስ አስተዋፅኦ እያደረገ መሆኑን በመጠቆምም፣ ችግሩ እስኪቀረፍ ድረስ ሊቀጥል እንደሚገባውም በአጽንኦት ተናግረዋል - ሚኒስትሯ፡፡

Read 11824 times