Saturday, 23 May 2020 14:46

በህገ መንግስታዊ ትርጓሜ ሂደቱ ላይ ምሁራን ምን ይላሉ?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 በህገ መንግስቱ ትርጓሜ ላይ በህግ ባለሙያዎችና ህገመንግስቱን ባረቀቁ ግለሰቦች የተካሄደው ውይይትና የቀረበው ሙያዊ ትንተና ህገመንግስታዊነትና ህገመንግስታዊ ዲሞክራሲን የሚያጠናክር መሆኑን ለአዲስ አድማስ አስተያየታቸውን የሰጡ ምሁራን ገለፁ፡፡
ለህዝብ በቀጥታ የቴሌቪዥን ሥርጭት በተላለፈ የሶስት ቀናት የውይይት መድረክ፣ ምርጫ በማራዘምና የመንግስት ስርአቱን በማስቀጠል ጉዳይ የቀረቡ የህገ መንግስት ትርጉም  አስተያየቶች፣ ዜጐች ለህገመንግስትና ህገመንግስታዊነት ያላቸውን አመለካከትና ግንዛቤ የሚያጐለብት ነው ብለዋል ምሁራኑ፡፡
 በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፍልስፍና ምሁሩ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ፤ የውይይቱ ሂደት ዲሞክራሲያዊና አሳታፊ መሆኑን ጠቅሰው፣ ውይይቱ በመሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ወሳኝ ሆኖ አግኝቸዋለሁ ብለዋል፡፡
አንድ ህገመንግስት ህያው መሆን የሚችለው እንዲህ ያለ ግልጽ ትርጓሜ ሲሰጠው ነው ያሉት ዶ/ር ዳኛቸው፤ የሰሞኑ ውይይትም ህገመንግስቱን ህይወትና ቅቡልነት - ብለዋል፡፡
ውይይቱ ለሀገሪቱ ግንባታ እጅግ ጠቃሚ ነው ያሉት ዶ/ር ዳኛቸው፤ ህዝብም የውይይቱ አካል ሆኖ ጉዳዩን በእውቀትና በግንዛቤ እንዲረዳ እድል የከፈተ ሂደት ነው ብለዋል፡፡  አንጋፋው ፖለቲከኛ ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ በበኩላቸው፤ አሁን ኢትዮጵያ ላለችበት ፖለቲካዊ ሁኔታ፤ የህገ መንግስት ትርጉም የመስጠት ሂደት የተሻለው ተመራጭ መሆኑን ጠቁመው፤ በህገመንግስቱ ላይ በህግ ባለሙያዎች የቀረቡ ሃሳቦችና ትንተናዎች ብዙ እውቀት ያስጨብጣሉ ብለዋል፡፡ ውይይቱ በተጨማሪም ለህብረተሰቡ ስለ ህገመንግስት በቂ ግንዛቤ የሚሰጥ ሆኖ እንዳገኙትም ተናግረዋል፡፡
“አሁን በኢትዮጵያ ያለው መንግስት ጠንካራ ነው” ያሉት ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ፤ ኢ-ህገመንግስታዊ በሆነ መልኩ የሽግግር መንግስትን ለማቋቋም ማሰብ ሃገሪቱን ያልተገባ ዋጋ ያስከፍላታል ሲሉ አስጠንቅቀዋል - ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ የተሞከሩ የሽግግር መንግስታት እንዳልተሳኩ በመግለጽ፡፡
የህገመንግስታዊ ትርጓሜ ሂደቱ የሚያመጣውን ውጤት ተከትሎ አሁን ያለው መንግስት በጥንካሬ  ቀጥሎ ቀጣይ አገራዊ ምርጫ ፍፁም ነፃ፣ ዲሞክራሲያዊና ተዓማኒ እንዲሆን በትጋትና በፅናት መስራት - የተሻለ አማራጭ ነው ብለዋል - ፕ/ር በየነ፡፡
የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ሙሼ ሰሙ በበኩላቸው፤ ሃገሪቱ አሁን የገጠማትን ችግር ለማለፍ ህገመንግስታዊ ትርጓሜው አንዱ አማራጭ መሆኑን የገለፁ ሲሆን የህግ ባለሙያዎች በጉዳዩ ላይ ግልጽና አሳታፊ በሆነ መልኩ ሀሳባቸውን እንዲገልፁ የተደረገበት ሂደት በሀገሪቱ ተከውኖ የሚያውቅ፣ አዲስና ጠቃሚ ጅማሮ መሆኑን ተናግረዋል፡፡  “እውነቱን ለመናገር በኢትዮጵያ ታሪክ ከተለያየ የህይወት አቅጣጫ ህገመንግስቱን በዚህ ደረጃ ሲሞግቱት ሳይ የመጀመሪያዬ ነው” ያሉት አቶ ሙሼ፤ “ከዚህ በፊት የነበረውን የካድሬ ተኮር ውይይት ሙሉ በሙሉ የቀየረ አጋጣሚ ነው” ሲሉ መስክረዋል፡፡ ውይይቱም ከቁንጽል የህገመንግስቱ አንቀፆች ወጥቶ አጠቃላይ የህገመንግስቱን መንፈስ የፈተሸ መሆኑን አቶ ሙሼ ገልፀዋል፡፡ አካሄዱ አዲስና ድፍረት የተሞላበት ነው ያሉት አቶ ሙሼ፤ ባለፉት 27 አመታት በዚህ መሰል ሂደት ህገመንግስቱን ፈትሸነው ቢሆን ኖሮ፣ አሁን ያለንበት የፖለቲካ ማጥ ውስጥ ባልገባን ነበር ብለዋል - በቁጭት፡፡
በአሁኑ ወቅት የሽግግር መንግስት ማቋቋም የሚለው ሃሳብ ኢ- ህገ መንግስታዊ እንደሆነና  ከሀገሪቱ የፖለቲካ አሠላለፍና ነባራዊ እውነታ አንፃርም የማይቻል መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሙሼ፤ አሁን እንደተጀመረው በህገ መንግስት ትርጉም ያለውን መንግስት በተገደበ ስልጣንና ጊዜውን ማራዘም የተሻለ አማራጭ ነው ብለዋል፡፡  “ስልጣኑ በህግ ተገድቦ የሚራዘምለት መንግስትም ፓርላማውም የሚኒስትሮች ም/ቤትም ተጠናክሮ የሚቀጥልበት አይነት እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል” ብለዋል - አቶ ሙሼ በሰጡት አስተያየት፡፡  “በህገመንግስታዊ ትርጓሜ ስልጣን የሚራዘምለት መንግስት፤ በተጨማሪም እንደ ሽግግር መንግስት የማይታይ፣ የተገደበ ስልጣን ያለው፣ ሀገሪቱን አሁን ከገጠማት የወረረሽኝ ስጋት የሚያሻግር፣ ሃገሪቱን ለምርጫ የማዘጋጀት መሠረታዊ ተልእኮ ያለው፣ አስቸጋሪና አጣዳፊ ነገር ካልተፈጠረ በቀር ህግ ፈጽሞ የማያወጣ መሆን አለበት” ብለዋል፡፡
ይህ አይነቱ በህግ ትርጉም የሚመጣ መንግስት፤ ምክር ቤቶችን ይዞ የሚቀጥልና ተቋማትን የበለጠ የሚያጠናክር ሊሆን እንደሚገባውም አቶ ሙሼ አክለው ገልፀዋል፡፡


Read 11428 times