Saturday, 23 May 2020 14:42

ኢሰመጉ በታጣቂዎችና በመንግሥት የፀጥታ አካላት የሚፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች አሳስቦኛል አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

   
    በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ሀይሎችና የመንግሥት የፀጥታ አካላት መካከል በሚከሰቱ ግጭቶች ምክንያት አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየተፈፀሙ መሆኑ እንዳሳሰበው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሠመጉ) አስታወቀ፡፡
ተቋሙ ባካሄደው ማጣራት በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በደቡብና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ሀይሎች በዜጎች ላይ በተለይም በመንግሥት ሰራተኞችና ባለሃብቶች ላይ ግድያ እገታና፣ ዘረፋ እንደሚፈፀሙ ጠቁሞ፤ ታጣቂ ሃይሎቹን ለመቆጣጠር የሚሰማሩ የመንግሥት የፀጥታ ሀይሎች በሚወስዷቸው የአፀፋ እርምጃዎችም የንፁሃን ዜጎች ሕይወት ጭምር እየጠፋ መሆኑን አስገንዝቧል፡፡
በተለይ ከታህሳስ ወር 2011 ዓ.ም ወዲህ በኦሮሚያ ክልል በተለይም በቄለም ወለጋና ምዕራብ ወለጋ ዞኖች በሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ሀይሎችና በመንግሥት የፀጥታ አካላት መካከል በሚፈጠሩ ግጭቶች የአካባቢው ነዋሪዎች ለከፋ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተዳርገዋል ብሏል - ኢሰመጉ በሪፖርቱ፡፡
በላሎ አሳቢ፣ ገንጂና ሆማ ወረዳዎች የመንግሥት ሀይሎች “የኦነግ ሸኔ አባላትን አጋልጡ በሚል ነዋሪዎች እንዲሁም በወረዳና ቀበሌ አመራሮች ላይ የማሰር የመደብደብና የመግደል እርምጃ እየወሰዱ መሆኑን ተቋሙ ባገኘው መረጃ ማረጋገጡን ጠቅሷል፡፡ ታጣቂ ሀይሎች በበኩላቸው ከመንግሥት ጋር ይሠራሉ የሚሏቸውን ዜጎች እንደሚገድሉና የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሚፈጸምባቸው ሪፖርቱ አስታውቋል፡፡
በተመሳሳይ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን በሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ቡድኖች በዜጎች ላይ ግድያ እገታና ዘረፋ እየተፈፀመ መሆኑን የጠቆመው ኢሰመጉ፤ የመንግሥት የፀጥታ ሀይሎች በአንፃሩ ከታጣቂዎች ጋር ትተባበራላችሁ በማለት በዜጎች ላይ የተለያዩ በደሎችን እያደረሱ መሆኑን  አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡  
መንግሥት በአማራ ክልል ከሚንቀሳቀሰው ‹‹ፋኖ›› ጋር የጀመረውን እርቅና አብሮ የመስራት አካሄድ አስፍቶ እንዲቀጥልም ኢሠመጉ ሀሳብ አቅርቧል፡፡
በሌላ በኩል፤ በደቡብ ክልልና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ደግሞ ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት ጥቃት እየተፈፀመባቸውና ከቀዬአቸው እየተፈናቀሉ ነው ያለው ኢሰመጉ፤ መንግሥት ለእነዚህና ሌሎች ብሄር ተኮር ጥቃቶች በጥናት ላይ የተመሰረተ የመፍትሔ እርምጃዎች መውሰድ እንዳለበት ኢሠመጉ መክሯል፡፡

Read 2913 times