Print this page
Monday, 18 May 2020 00:00

ዘወትር ጎብኚ የማያጣው አስደናቂ ሰዓት

Written by  ታደለ ገድሌ ጸጋየ (ዶ/.ር)
Rate this item
(1 Vote)

    ሥነ ጠፈራዊ ሰዓቱ

 ፕራግ የቼክ ሪፐብሊክ ዋና ከተማ ናት:: በቼክ ውስጥ  ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኙ የተለያዩ የቱሪስት መስህቦች ሲኖሩ፤ ከእነዚህም ውስጥ  ‘ፕራግ ኦርሎጂ’ ተብሎ የሚጠራውና በሰሜናዊ ምዕራብ ጥንታዊ ከተማ የሚገኘው አስትሮኖሚያዊ ወይም ሥነ ጠፈራዊ ሰዓት ይገኝበታል፡፡ ብዙ መቶ ሺህ የዓለም ቱሪስቶች የሚጎበኙት ይሄ ሰዓት፤ ከትልቅ ካቴድራል አናት ላይ የሚገኝ ሲሆን ከሥር ሆኖ ወደ ላይ ከማንጋጠጥ ይልቅ ራቅ ብሎ ሲመለከቱት ውበቱና ሁሉ ነገር በእጅጉ ይማርካል፡፡ ነፍሱን ይማረውና በአስጎብኝዬ በዮሐንስ ታምሩ (የኤፍሬም ታምሩ ታላቅ ወንድም) አማካይነት ፕራግን በጎበኘኹበት ወቅት፣ ለሦስት ሰዓታት ያህል ፈዝዤና ተገርሜ የቆየሁት በየሰዓቱ በሚጮኸው ዶሮ፣ በየሰዓቱ ተራቸውን ጠብቀው በሰዓቱ ውስጥ እየታዩና  እጅ እየነሱ በሚያልፉት 12 ሐዋርያት እንዲሁም ዐፅም ብቻ ያለው ሰው በሚደውለው ደወልና ወቅትን በሚያመለክተው ካሌንደር ነው፡፡ በሰዓቱ ግራና ቀኝ የመለከት ድምጽ የሚያሰማ መልአክና መጽሐፍ ቅዱስን እያነበበ የሚሰብክ ሐዋርያ ይታያሉ፡፡
የሚያስፈራራ ገጽታ ያለውን ደወል ደዋይ አካል ስንመለከት፣ ሞት የማይቀርልንና አጠገባችን የደረሰ ያህል በማሰብ ክፉ ነገር ሁሉ ከመሥራት እንድንቆጠብ ያስታውሰናል፡፡ ዐፅሙ ብቻ ቀርቶ በአስፈሪ መልክ የሚታየው አስቀያሚ ነገር፣ በተምሳሌት ሞትን ያመለክታል:: ይኸውም  የሰው ልጅ በምድር ላይ ያለሁ ቢመስለውም ጠፊና ረጋፊ እንደሆነ፤ ሞትም ለሰው ልጅ ሁሉ  የማይቀርለት እዳው መሆኑን ይጠቁማል፡፡ ሰዓቱ በሰማይ ፀሐይን፣ ኮከብንና ጨረቃን፣ በምድር ደግሞ ሐዋርያትን ይወክላል፡፡ የየራሳቸው መልክና ቅርፅ ያላቸው ሐዋርያቱ፣ በየሰዓቱ  ዶሮ ሲጮህና ተንቀሳቅሰው ሲመጡ ስማቸው (ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስ፣ ዮሐንስ…) ከገጽታቸው ጋር ሲታይና እጅ ነስተው ሲያልፉ፤ ለሰው ልጅ ሁሉ ሰላምን፣ ፍቅርንና ደስታን…  ያጎናጽፋሉ፡፡
በየሰዓቱ እጅ እየነሡ በሰዓቱ ውስጥ ከሚያልፉት ሐዋርያት ጥቂቶቹ

በሀገሪቱ ባህላዊ እምነት መሠረት፣ ደወሉ በየሰዓቱ ካልተደወለ ሕዝብ ሁሉ ከችግርና ከመከራ ላይ ይወድቃል፤ የጥንቱ መንፈስም ይቆጣል ተብሎ ይታመናል:: እንደ ባህሉ ለከተማው ሕዝብ ተስፋ የሚፈነጥቀው፣ በአዲሱ ዓመት ሌሊት ወንድ ልጅ ሲወለድ ነው፡፡ ይህንን ወጥነት ያለውን አስትሮኖሚያዊ ሰዓት ለመጀመሪያ ጊዜ እ.ኤ.አ በ1410 ከረዳቱ ከዣን ሺንዴል ጋር ሆኖ የሠራውና በኋላም በሌላ ሀገር እንዳያስፋፋው በሚል በመንግሥት መገደሉ ወይም ዓይኑ እንዲጠፋ መደረጉ የሚነገረው የንጉሠ ነገሥቱ ሠዓት ሠሪ፣ ጥበበኛው ሚኩለሽ የካዳኙ ነው፡፡ ዣን ሺንዴል በንጉሠ ነገሥቱ ስም በተሰየመው በቻርለስ ዩኒቨርሲቲም የሒሳብና የአስትሮኖሚ ፕሮፌሰር ሆኖ አገልግሏል፡፡
በዓለም ላይ የገዘፈ ስምና ቦታ ያለው ይህ ሥነ ጠፈራዊ ሰዓት፣ በምድራችን ላይ ከሚገኙ ሦስት አስደናቂ የመካከለኛው ዘመን የአስትሮኖሚ ሰዓት ሥሪቶች ውስጥ ሦስተኛው ሲሆን እስከ ዛሬም ድረስ በአገልግሎት ላይ ነው፡፡ ከዚህም የተነሣ በታሪክ  ጭምር ተመዝግቦ የሚገኘው ጥንታዊው የኦርሎጂ አደባባይ ሰዓት ምንጊዜም ቢሆን በየቀኑ በሰው ግፊያና ትርምስ ተከብቦ ይውላል፡፡

የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች አስትሮኖሚያዊ ሰዓቱን ሲመለከቱ

የሰዓቱ ቅምር የተከናወነው ሦስት መሠረታዊ ነገሮችን መነሻ አድርጎ ነው:: እነርሱም ሰማይ ላይ የሚታዩት ፀሐይ፣ ጨረቃና ኮከብ፣ አስትሮኖሚያዊ ደወል፣ በምድር የተለያየ መልክና ቅርፅ ያላቸው ሐዋርያት ናቸው፡፡ ለ80 ዓመታት ያህል ምንም ሳይሆን የቆየውና ኦክቶበር 9 ቀን 14010 የተሠራው ግዙፉ  የኦርሎጂ ሰዓት፤ እ.ኤ.አ በ1490 ላይ በበለጠ በልዩ ልዩ ቅርፆች እንዲያምርና እንዲዋብ ተደርጓል:: እንደገና እ.ኤ.አ በ1555 ዣን ታቦርስ በመዳብና በብረት የተሠራውን የሐዋርያት ቅርፅ፤ በተዋበና በጠነከረ የእንጨት ቅርፅ ቀይሮ አድሶታል፡፡ በኋላም በወርቃማ ቅርፅ ይዘት ቀይሮታል፡፡ ጎረቤት ሀገር የሆነቺው ናዚ ጀርመን እ.ኤ.አ በሚያዚያ  9 ቀን 1945 የቼክ ሪፑበሊክን በወረረችበት ወቅት በኦርሎጂው  ሕንጻ ላይ ከባድ አደጋ ጥላ ቅርሱን ለጉዳት ዳርጋው ነበር፡፡ በኋላ በጠላት የተቃጠለውና የተደመሰሰው ቅርስ ማለትም ደወሉና ካሌንደሩ በጆሴፍ ማኔሳስ ከፍተኛ ጥረት ጥገና ሊደረግለት ችሏል፡፡
 
የሰዓት ዑደት መነሻ የሆነው ሕንጻ

 በዓለም ላይ እጅግ በተዋበና ሰዓትን በትክክል በሚለካ መንገድ በእንጨት ቅርፅ ተሠርቶ የነበረው የሐዋርያት ምስል ዳግም የተሠራው በሶርቲች ሱፐርዳ ሲሆን የአስትሮኖሚው ሰዓት ሙሉ ለሙሉ መሥራት የጀመረውም እ.ኤ.አ በ1948 ነበር::
600ኛ ዓመቱ  በከፍተኛ ድምቀት የተከበረለት ይህ የፕራግ ኦሎጂ ሰዓት በትክክል የሚያመለክተው  ቀኑ ፀሐይ ስትገባ የሚጀምረውን የጥንታዊት ቦሆሚያን የሰዓት አቆጣጠር፤ የመካከለኛው አውሮፓን የሰዓት ስሌትና በከዋክብት እንቅስቃሴ ላይ በተመሠረተው ከሶላር ሰዓት በሚያንሰው በኮከብ ሰዓት አቆጣጠር ሲሆን በዞዲያክ ካሌንደር ደወል አደዋወል ላይም ያተኩራል:: በዋነኛነት የፀሐይን፤ የጨረቃንና የኮከብን እንቅስቃሴ መሠረት ያደርጋል፡፡


_

Read 3134 times