Print this page
Tuesday, 19 May 2020 00:00

ወረርሽኝን እየተቆጣጠርን፤ ኑሮን ወደመጠገን ኢኮኖሚን ወደማዳን እንሸጋገር!

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

 - ጊዜያዊ መፍትሔ፤ “ኢኮኖሚን የማይንድ፣ ከወረርሽኝ የሚያድን” ሆኖ፣ ጥንቃቄ ላይ ያተኮረና ቅድመ ዝግጅቶችን ለማከናወን ትንሽ ፋታ የሚሰጥ ነው -    የእስከ ዛሬው ቀዳሚ ምዕራፍ፡፡
    - መሸጋገሪያ መፍትሔ፤ “ወረርሽኝን ለመቆጣጠርና ኢኮኖሚን ለመጠገን” የሚጠቅሙ ዘዴዎችን ላይ ያተኩራል፡፡ በሽታው ከቁጥጥር ውጭ እንዳያመልጥ  የሚገቱ መላዎችን በመፍጠር፣ የምርትና የንግድ ስራዎች እንዲያገግሙ መትጋት፤ መሸጋገሪያ ምዕራፍ ይሆናል፡፡
    - የግስጋሴ መፍትሔ፤ “ወረርሽኝን በማሸነፍ ኢኮኖሚን ለማሳደግ” የሚያስችል ምዕራፍ ነው፡፡ ለኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ የመዝጊያ ምዕራፍ፤ ለዋናው የኑሮ       አላማ… ደግሞ ኑሮን የማሻሻል ጉዞ፣ በአዲስ መንፈስ የሚነቃቃበት የመክፈቻ ምዕራፍ ይሆናል፡፡

                 ያለፈውን መርምሮ፣ የወደፊቱን ትልም የማደስ ጊዜው አሁን ነው፡፡
ወረርሽኝን የመከላከል የኮሮና ቫይረስ ጉዳይ፣ እንዲሁም ኢኮኖሚን የማንቀሳቀስ የኑሮ ጉዳይ፣ ዋናዎቹ የጊዜያችን ገፅታዎች ናቸው፡፡ እናም ነጣጥለን ሳይሆን፤ ሁለቱንም ገፅታዎች አዋህደንና አቀናብረን ልናገናዝባቸው ይገባል - አንድ ላይ ደምረን፡፡
ወረርሽኝን 1) የሚከላከል፣ 2) የሚቆጣጠርና 3) የሚያሸንፍ ነው አንዱ ገፅታ፡፡
ኢኮኖሚን 1) የማይንድ፣ 2) የሚጠግንና 3) የሚያሳድግ!... ነው ሁለተኛው ገፅታ፡፡
ምዕራፍ አንድ፣ አፈግፍጐ የመዘጋጀት ምዕራፍ፡፡
የወረርሽኝ ማዕበል ድንገት ሳይደርስብን በፊት፣ አጭር የዝግጅት ጊዜ እንድናገኝ የሚረዳ፣ ‹‹ጊዜያዊ መፍትሔ››፣ ምን እንደሚመስል፣ ባለፉት ሁለትና ሦስት ወራት፤ አይተናል፡፡ ማፈግፈግና መታቀብ ያመዘነበት፣ አጣዳፊ የጥንቃቄና የዝግጅት ምዕራፍ ነበር ማለት ይቻላል፡፡
“ማፈግፈግ” ማለት ግን፣ መሸሽ ማለት አይደለም፡፡ በደራሽ ጎርፍ ሳንጥለቀለቅ፣ ለበሽታ ወረርሽኝ ሳንጋለጥ፤ አስተማማኝ የመከላከያ ቦታ ለመያዝ፤ ዙሪያ ገባውን ለማስተዋል፣ ለተወሰነ ጊዜ፣ ትንሽ ማፈግፈግ ብልህነት ነው፡፡ ምክንያቱም፣ በዚህችው አጭር የማፈግፈግ ምዕራፍ፤ ፈተናውን የሚመጥን አቅም ለማሟላት፣ በጥንቃቄና በፍጥነት ለመዘጋጀት በብርቱ መትጋት ይቻላል፡፡  
የመጀመሪያው ምዕራፍ፣ በአንድ በኩል መደበኛ እንቅስቃሴዎችን የምናለዝብበት “የፋታ ጊዜ” ቢሆንም፣ በሌላ በኩል ግን፣ መንቀሳቀሻ መላ ለማበጀት ቀድመን የምንዘጋጅበት የጥድፊያ ጊዜም ነው፡፡ “እንቅስቃሴን ማለዘብ” ማለት አገርን ዘጋግቶ፣ ኑሮን አቋርጦ፣ ኢኮኖሚን ቆላልፎ መቀመጥ ማለት አይደለም፡፡ “ለዝግጅት መጣደፍ” ማለትም፣ መደናበር ማለት አይደለም፡፡ “ኢኮኖሚ ሳይንኮታኮት፣ የበሽታ ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያስችል” የጥንቃቄና የዝግጅት ጊዜ ነው - የመጀመሪያው ምዕራፍ፡፡
በዚህ መነጽር፣ እስከዛሬ የተከናወኑ ዋና ዋና የጥንቃቄና የዝግጅት ተግባራትን፣ ስንዳኛቸውና ስንመዝናቸው፣ ከሞላ ጎደል፤ ትክክለኛ ውሳኔዎችና ተገቢ ተግባራት እንደነበሩ፣ አሁን ሳይሆን፣ ያኔውኑም ማወቅ ይቻል ነበር፡፡
ጥቂት የመፋለስና የመዝረክረክ ስህተቶች አልነበሩም አይባልም፡፡ ነገር ግን፣ አብዛኞቹ ዋና ዋና ውሳኔዎችና ተግባራት፣ በአመዛኙ በትክክል የተቀናበሩ፣ የአገርን አቅም ያገናዘቡና የሚያዋጡ፣ የወደፊቱን ተስፋ ሳያጨልሙ ለዘለቄታው የሚፈይዱ በመሆናቸው፤ ለውጤት በቅተዋል፤ ስኬታማ ሆነዋል፡፡
በአጭሩ፣ ‹‹ከደራሽ ወረርሽኝ ያዳኑ፣ ኢኮኖሚን ያልናዱ›› ናቸው- የእስከ ዛሬዎቹ የጥንቃቄና የዝግጅት ጥረቶች፡፡ በአንድ በኩል፤ ለወረርሽኝ በእጅጉ የሚያጋልጡ፣ ስብሰባዎችና የመዝናኛ ድግሶች፣ መደበኛ የትምህርትና የሃይማኖት ሥነ ሥርዓቶች፣ ለጊዜው እንዲቋረጡ መደረጋቸው፤ ተገቢ ነው፡፡ አንዳንዶቹም ከፍተኛ ጥረትን ጠይቀዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፣ የምርት እንቅስቃሴዎች፣ በተቻለ መጠን እንዳይስተጓጎሉ ጥንቃቄና ጥረት ተደርጓል - ኢኮኖሚው እንዳይንኮታኮት፡፡
በእርግጥ የአገር ኢኮኖሚ፣ መቁሰሉ አልቀረም፡፡ የሰዎች ሥራና ኑሮም፣ ከጉዳት አላመለጠም፡፡ ተጎድቷል፡፡ ነገር ግን፣ የአገር ኢኮኖሚ አልተናደም፡፡ የሰዎች ኑሮ፣ እጅጉን ቢናጋም ለይቶለት አልፈራረሰም፡፡ ይሄ፣ ቀላል ውጤት ከመሰለን ተሳስተናል፡፡
“መንግስት፣ የሌሎች አገራትን ውሳኔ በጭፍን ቢኮርጅ ኖሮ ምን ሊፈጠር ይችል ነበር?” ብለን ራሳችንን እንጠይቅ፡፡  አገር ምድሩን ዘጋግተን፣ ስራና ንግዱን ቆላልፈን እንድንቀመጥ መንግስት ቢወስን ኖሮ አስቡት!
‹‹ይዘጋ፣ ይከርቸም››… እያሉ የቀሰቀሱና ሆይ ሆታ የፈጠሩ የአገራችን አላዋቂዎች ጥቂት አይደሉም፡፡ በጭፍን እየተደናበርን፣ ‹‹እንዝጋው›› ‹‹እንቆልፈው›› ብንል ኖሮ፣ በገዛ እጃችን፣ አዲስ ተጨማሪ ቀውስ ጐትተን እናመጣ ነበር፡፡ ለወትሮው፣ ከእጅ ወደ አፍ የሆነው የብዙ ሚሊዮኖች ኑሮ፣ የእለት ጉርስ ርቆት፤ በአማራጭ እጦት፣ ወደ አደገኛ ቀውስ ሲያመራ ይታያችሁ፡፡  ስንዝር የማያወላዳው የአገራችን ኢኮኖሚ፣ ምንኛ እንደሚንኮታኮትም አስቡት፡፡ ሌላ ተጨማሪ በሽታ ይሆንብን ነበር፡፡
እናም፣ የእስከ ዛሬዎቹ የጥንቃቄና የዝግጅት ጥረቶች (የምዕራፍ አንድ ጊዜያዊ መፍትሔዎች)፣ ‹‹ኢኮኖሚን ያልገደሉ፣ አገሬውን ከደራሽ ወረርሽኝ የታደጉ›› ናቸው ማለት ይቻላል፡፡
የመሸጋገሪያ ምዕራፍ - ኢኮኖሚንና ኑሮን ለመጠገን መትጋት፡፡
“የትናንት ተግባራት ስኬታማ ናቸው” ሲባል፤ ‹‹ዛሬም ያለ ሀሳብ የትናንቱን እንድገም፣ ነገም እንደዚያው ያለሀሳብ እንቀጥል›› ማለት አይደለም፡፡
‹‹የዝግጅት ምዕራፍ›› እና “ጊዜያዊ መፍትሔ” ለዘላለም ሊቀጥሉ አይችሉም፡፡ ለጥንቃቄ አፈግፍገን፣ እዚያው ከቀረን፣ ኪሳራ ነው፡፡
የኑሮ እንቅስቃሴን የሚቀንሱ የጥንቃቄ ተግባራትና የቅድመ ዝግጅት ጥረቶች፤… ጊዜያዊ መፍትሔዎች ናቸው፡፡ ኑሮንና ስራን መቀነስ፣ ለበርካታ ወራትና አመታት፣ ዋና የኑሮ አላማና ዋና ሥራ ሆነው ሊቀጥሉ አይችሉም፡፡ እንደ አይነታቸውና እንደ ባሕርያቸው፤ የየራሳቸው ደረጃና ልክ ሊበጅላቸው ይገባል፡፡
‹‹እጅን አዘውትሮ የመታጠብ ጥንቃቄ››፣ ደራሽ ወረርሽኝን ለመከላከል ብቻ ሳይሆን፤  ወረርሽኝን ለመቆጣጠርና ለዘወትር ጤንነትም ስለሚበጅ፣ በልኩ የስልጡን አኗኗር አንድ ገጽታ እንዲሆን ማድረግ ይቻላል፡፡ ግን፣ ተስማሚና ቀላል ዘዴ ሊፈጠርለት ይገባል፡፡
ሰው በሚበዛበት አካባቢ፤ በተለይም ተሳፋሪዎች፣ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ እንዲጠቀሙ መደረጉ፤ ወረርሽኙን እየተከላከልንና እየተቆጣጠርን፤ ለምርትና ለንግድ ስራ እንድንንቀሳቀስ ይረዳል፡፡ ዋና ዋናዎቹ የመሸጋገሪያ ምዕራፍ ትኩረቶች ግን፤ ከዚህም ያለፉ ናቸው፡፡
በአንድ በኩል፤ ወረርሽኙን ከመከላከል በተጨማሪ፣ በየጊዜውና በየአካባቢው የሚፈጠሩ የቫይረስ ስርጭቶችን በፍጥነት ለማወቅ፣ እንዲሁም በምርመራ፣ በለይቶ ማቆያና በህክምና የቫይረሱን ስርጭት በብቃት ለመገደብ የሚያስችሉ የወረርሽኝ መቆጣጠሪያ አሰራሮችን ይበልጥ ማጠናከር፤ የመሸጋገሪያ ምዕራፍ አንድ ትልቅ ትኩረት ነው፡፡
ሌላኛው ትልቅ ትኩረት፤ የኢኮኖሚና የኑሮ ጉዳይ ነው፡፡ ለምሳሌ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚስፋፋበት መላ መፍጠር የግድ ነው፡፡ ዜጐች፣ “ሚኒ ባስ” መኪኖችን ገዝተው በታክሲ ስራ ላይ እንዲሰማሩ የመንግስት ማበረታቻ ያስፈልጋል ማለቴ አይደለም፡፡ መንግስት ባለፉት በርካታ አመታት፣ በላይ በላይ እየደረበ ሲከምራቸው የነበሩ እንቅፋቶችን ካስወገደ፤ የራሱን ሃላፊነት በብቃት እንደተወጣ ይቆጠራል፡፡ ቀሪው ኃላፊነት የእያንዳንዱ ዜጋ ነው - አቅም ያላቸው ሰዎች፣ ከፊሎቹ በገንዘብ፣ አንዳንዶቹ በሹፌርነትና በጥገና ሙያ የታክሲ አገልግሎት ላይ መሰማራት ይችላሉ ማለት ነው፡፡
እስከዚያው፤ መንግስት በእጁ ውስጥ ከሚገኙ ሚኒባሶች እና አውቶብሶች መካከል አንዳንዶቹን መሸጥ ይችላል፡፡
ትራንስፖርት ማሳለጥን ጨምሮ፣ ኢኮኖሚንና ኑሮን በስራ ለመጠገን የሚያስችሉ ዘዴዎችን መፍጠር፣ ቀዳሚው የመሸጋገሪያ ምዕራፍ ትኩረት ነው፡፡
በሌላ አነጋገር፤ የስራ እንቅስቃሴን በሩብ ወይም በግማሽ የሚቀንስ ጊዜያዊ የጥንቃቄና የማፈግፈግ ውሳኔ፣ በጊዜ ወደ ትክክለኛ እልባት እንዲደርስ፣ ወደ ተሻለ ደረጃም እንዲሸጋገር፣ ሊታሰብበት ይገባል፡፡


Read 7982 times