Sunday, 17 May 2020 00:00

ሻሞ! “274”

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 የሽግግር መንግሥት ጥያቄ ለሀገራችን ወቅታዊ፣ ጠቃሚና፣ ምትክ የለሽ መሆኑን የሚያሳይ  የቅድመ ምርጫ ግምትና ትንተና

1. መግቢያ

የኮሮና ቫይረስ ወደ ሀገራችን ከመግባቱ በፊት የዘንድሮ ምርጫ እንዲራዘምና፣ አንድ ሁሉን ዐቀፍ የሆነ የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም ስንጠይቅ እንደነበር ይታወቃል። በእኛ ጥረትና ትግል ሳይሆን በኮሮና ቫይረስ አስገዳጅነት፣ ሀገራችን ምናልባትም ህልውናዋን ሊፈታተን ይችል ከነበረው ከምርጫ 2012 ግርግር ለጊዜውም ቢሆን አምልጣለች ማለት ይቻላል። የኮሮና ቫይረስ ወደ ሀገራችን መግባት፣ ምርጫውን እንዲራዘም ከማድረጉ በተጨማሪ የሽግግር መንግሥት የማቋቋም ጥያቄያችንን የበለጠ አስፈላጊና ጥያቄውን ወደ ተግባር የመለወጡንም ዕድል ከቀድሞ በተሻለ ቀላል አድርጎታል። ይህንን የምንለውም በሚከተሉት ሁለት ምክንያቶች ነው።
የመጀመሪያዉ ምክንያት፥ እንደሚታወቀው ቀደም ሲል ምርጫው እንዲራዘምና የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም ስንጠይቅ የነበረው በዋናነት ሀገሪቷ ከምትገኝበት የፖለቲካ ውጥረት አኳያና “የለውጥ ሒደቱ” ስኬታማ ባልሆነበት ሁኔታ፣ የምናካሒደው ምርጫ በአንጻራዊነት ሰላማዊ፣ ነጻና ፍትሐዊ የመሆን ዕድል አይኖረውም በሚል ነው። እንዲያውም ሰላምና የሕግ የበላይነት ባልሰፈነበት ሁኔታ የምናካሒደው ምርጫ የሀገሪቷን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል ውጤት ሊያስከትል ይችላል ከሚል ስጋትም ጭምር ነው። ይህ የቀደመ ስጋታችን አሁንም መቀጠሉ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በኮሮናቫይረስ መከሰት ምክንያት ሀገራችን በአሁኑ ወቅት ከኅብረተሰብ የጤና ችግር በተጨማሪ በሐሳብ ለመገመት በማይቻል መጠን ለከፍተኛና ለተራዘመ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ተጋላጭ ሆናለች። ይህንን ከባድና ፈርጀ ብዙ የሆነ ሀገራዊ ችግር፣ እንኳንስ ከፋፋይ ወደሆነና የፖለቲካ ቀውስ ወደሚያስከትል ምርጫ ውስጥ ገብተን ቀርቶ፣ በሙሉ ትኩረትና ትብብር አንድ ላይ ቆመን ብንሠራም በቀላሉ ልንወጣው የምንችለው አይደለም። ስለዚህ በኮሮና ቫይረስ መከሰት ምክንያት የሽግግር መንግሥት የማቋቋም ጥያቄያችን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ለሀገራችን የፖለቲካ ችግር አስፈላጊና ምትክ የለሽ መፍትሔ መሆኑ ግልጽ እየሆነ መጥቷል።
ሁለተኛው ምክንያት፥ የምርጫውን መራዘምና የሽግግር መንግሥት መቋቋምን ቀደም ሲል ይቃወሙ የነበሩ አንዳንድ የፖለቲካ ኀይሎች ያቀርቡት የነበረው ብቸኛ መከራከሪያ “በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠውን የምርጫ ጊዜ ማራዘም የሚቻልበት ዕድል የለም” የሚል እንደነበር ይታወሳል። ይህ የክርክር ነጥብ ከፖለቲካ አንጻር ቀድሞውንም ተገቢ ያልነበረ ቢሆንም፣ አሁን ግን በኮሮናቫይረስ መምጣት ምክንያት ክርክሩ እንዳይመለስ ሆኖ ተዘግቷል። ከእንግዲህ በአሁኑ ወቅት እየታየ እንዳለው ዐይን ባወጣ ድርቅና ካልሆነ በስተቀር የሕግ አንቀጽና ትርጓሜን ጠቅሶ “ምርጫውን ማራዘም አይቻልም” ብሎ መከራከር የሚቻልበት ዕድል የለም።
በዚህም ምክንያት በአሁኑ ወቅት በሥልጣን ላይ የሚገኘው መንግሥት የሥልጣን ዘመኑ መስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ስለሚጠናቀቅና፣ የመንግሥትን የሥልጣን ዘመን ለአንድም ቀን ለማራዘም የሚያስችል ምንም ዓይነት ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ የሌለ በመሆኑ፣ ከመስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ ከመደበኛው የሕግ አሰራር ውጪ /Extra-Constitutional/ በሆነ የፖለቲካ ድርድር ሀገሪቷን እስከሚቀጥለው ምርጫ ድረስ ሊያስተዳድር የሚችል አንድ ሁሉን ዐቀፍ የሽግግር መንግሥት ማቋቋም ከፊታችን ያለ ምትክ የሌለው አማራጭ ሆኗል። ‘ሀገሪቷ የአንድ ገዥ ፓርቲ የግል ንብረት ናት’ ካልተባለ በስተቀርም፣ እንዲህ ዓይነቱ የፖለቲካ ውሳኔ ላይ ሊደረስ የሚገባው በገዥው ፓርቲ ውሳኔ ብቻ ሳይሆን ሁሉን ዐቀፍና አሳታፊ በሆነ ሀገራዊ የምክክር ሒደት /National Dialogue/ ነው። ስለሆነም የኮሮና ቫይረስ መከሰት ምርጫውን ለማራዘም የነበረውን የሕግ እንቅፋት በማስወገድ የሽግግር መንግሥት የማቋቋም ጥያቄን በቀላሉ የሚቻል አድርጎታል። ከእንግዲህ የሀገርን ጉዳይ ለማስቀደም፣ የሀገሪቷ የፖለቲካ ኀይሎች እንደተለመደው ቅንነትና የፖለቲካ ቁርጠኝነት ካላጣን በስተቀር፣ የሽግግር መንግሥት የማቋቋም ጥያቄን ላለመቀበል ሰበብ ወይም እንቅፋት የሚሆን የሕግ ድንጋጌ የለም።
ነገር ግን፣ ብልጽግና ፓርቲ በአሁኑ ወቅት እያሳየው ካለው የሀገርን ጥቅም ከማስቀደም ይልቅ፣ ለራስ የፖለቲካ ሥልጣን የበለጠ ቀናዒ ከሆነው ባህሪው አንጻር፣ በሕገ ወጥ መንገድ ሥልጣኑን ሊያራዝምና ምርጫውን ራሱ በፈለገው ጊዜና ሁኔታ እንዲካሔድ ሊወስን ይችላል። ገዥው ፓርቲም ወደዚህ ዓይነቱ ያልተገባ አቅጣጫ በመሄድ፣ (ምናልባትም የኮሮና ቫይረስ ችግር በቀጣዩ ጥቂት ወራቶች ከተወገደ) ምርጫውን እስከ 2013 ዓ.ም. አጋማሽ ባለው ጊዜ ውስጥ የማካሔድ ፍላጎት እንዳለው ከውስጥ አዋቂ ምንጮች እየሰማን ነው። ይህ መረጃ እውነትነት ኖሮት ወደ ተግባር ከተለወጠ፥ ይህ የገዥው ፓርቲ ውሳኔ በሀገራችን ህልውና ላይ ከፍተኛ አደጋ የሚያስከትል ታሪካዊ ስህተት እና ክስተት ይሆናል። ምክንያቱም የሀገራችን የወቅቱ የፖለቲካ ችግር በእውነተኛ የውይይትና የድርድር ሒደት እንጂ፣ ከእንግዲህ ወዲያ በተለመደው ዓይነት የይስሙላ ምርጫ የሚፈታ አይደለም። ውጤታማ በሆነና መዋቅራዊ ችግሮቻችንን ለመፍታት በሚያስችል የሽግግር ሒደት ባላለፍንበት ሁኔታ ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ ማካሔድም አይቻልም። የሆነ ሆኖ ገዥው ፓርቲ ወደዚህ ዓይነቱ የተሳሳተና ሕገ ወጥ ውሳኔ ሊገባ የሚችልበት ሰፊ ዕድል መኖሩን በመገንዘብና፣ ለሕዝብ ግንኙነት ተብለው በገዥው ፓርቲ በሚካሄዱ የታይታ ውይይቶች ሳይዘናጉ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሁለት ፈርጅ ያለው ትግል ማካሔድ ይኖርባቸዋል።
የመጀመሪው፥ በሥልጣን ላይ የሚገኘው መንግሥት ከመስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ በሕገ ወጥ መንገድ በሥልጣን ላይ እንዳይቀጥልና፣ ምርጫው የሚካሔድበትን ጊዜ ብቻውንና የራሱን መፃዒ ስልጣን በሚያረጋግጥ መንገድ እንዳይወስን የሚያደርግ ሰላማዊና ሕጋዊ ትግል ማድረግ ይኖርባቸዋል። ምክንያቱም፣ በተጭበረበረ ምርጫና በአፈና ድርጊት ለ29 ዓመታት በሥልጣን ላይ የቆየው ገዥው ፓርቲ፣ ከእንግዲህ በሌላ ማናቸውም አሳማኝ ያልሆነ ሰበብና ምክንያት በሥልጣን ላይ እንዲቀጥል ሊፈቀድለት አይገባም። በእንዲህ ዓይነቱ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነን ወደ ሀገራዊ ምርጫ የምንገባ ከሆነም፣ በምርጫው ግብጽን የመሰሉ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ካልሆኑ በስተቀር፣ የኢትዮጵያ ህዝብም ሆነ የትኛውም ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ኀይል አሸናፊ ወይም ተጠቃሚ ሊሆን እንደማይችል በመገንዘብ፣ እንዲህ ዓይነቱ ሀገራዊ አደጋ እንዳይከሰት ተቃዋሚው ጎራ ሕዝቡን በማስተባበር ጠንካራ ትግል ማድረግ ይጠበቅበታል። ገዥው ፓርቲ ራሱን ከውይይትና ከድርድር ሒደት አርቆ ሥልጣኑን በጉልበት የማራዘሙን ድርጊት የሚገፋበት ከሆነ፣ ተቃዋሚ ጎራው በአንድ ላይ መቆም ከቻለና ይህንን የገዥውን ፓርቲ ሕገ ወጥነት ለሕዝቡ በበቂ መጠን ማሳመን ከቻለ፥ የተቃዋሚው ጎራ በራሱ ተነሳሽነትና መንገድ የሽግግር መንግሥት እስከ ማቋቋም የሚደርስ ትግል ማድረግ ይኖርበታል። ከመስከረም 30፣ 2013 በኋላ ከገዥው ፓርቲ የተለየ ግብዣና መፍትሔ መጠበቅ ሙሉ በሙሉ መቆም ይኖርበታል።
ሁለተኛው፥ ተገቢውና ትክክለኛው መፍትሔ ከዚህ በላይ የተጠቀሰ ቢሆንም፣ መንግሥት በተለመደ አምባገነናዊ ባሕሪው በሕገ ወጥ መንገድ የራሱን ሥልጣን ማራዘም ከቻለና ምርጫው በአጭር ጊዜ እንዲካሔድ የሚወስን ከሆነ (የሚወስን ስለመሆኑ በእኔ በኩል ብዙም አልጠራጠርም)፣ ተቃዋሚው ጎራ በምርጫው ማግኘት የሚችለውን ከፍተኛ ውጤት አሟጦ ለማግኘት የሚያስችለውን ጥረትና ዝግጅት ከወዲሁ ማድረግ ይጠበቅበታል። ገዥው ፓርቲ የወቅቱን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሽፋን አድርጎና መንግሥታዊ መዋቅሩን ተጠቅሞ (ከላይ ለ6 ወራት ሥልጣኑን በማራዘም ዕቅዱ ላይ የሰማነውን ፍንጭ ታሳቢ በማድረግ) ውስጥ ውስጡን የራሱን የምርጫ ዝግጅት እያደረገ ነው። ተቃዋሚው ጎራ ይህንን ተገንዝቦ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በማይጻረር አግባብ የራሱን የምርጫ ዝግጅት ከወዲሁ ማድረግ ይኖርበታል። ይህንን ማድረግ ካልቻለና የኮሮና ችግር በተፈታ ማግስት ምርጫው እንዲካሔድ በገዥው ፓርቲ የሚወሰን ከሆነ ግን ተቃዋሚው ጎራ “ሠርገኛ መጣ” ዓይነት ችግር ውስጥ እንዳይገባ ከወዲሁ መዘጋጀት አለበት።
ከዚህ ግንዛቤ ጋር በተያያዘ፣ በአንድ በኩል አሁንም ምርጫው በቅርብ ጊዜ እንዲካሔድና የሽግግር መንግሥት የማቋቋሙ ጥያቄ ተቀባይነት እንዳያገኝ ለማድረግ እየጣሩ የሚገኙ የፖለቲካ ኀይሎች፣ ይህንን ለማድረግ ያስገደዳቸው ጠባብ የግልና የቡድን ፍላጎት ለሀገር ብቻ ሳይሆን ለራሳቸውም ፍላጎት የማይጠቅም መሆኑን ለማሳየት፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከፍ ሲል ለመጥቀስ በተሞከረው ምክንያት ምርጫው በቅርብ ጊዜ መካሔዱ የማይቀር ከሆነ ተቃዋሚው ጎራ በሀገሪቷ ያለውን የፖለቲካ የኀይል አሰላለፍ በአግባቡ ተገንዝቦ የራሱን ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ እንዲችል የቅድመ ምርጫ ውጤት ግምት ትንተና ከወዲሁ ማቅረብ አስፈላጊና ጠቃሚ ነው ብዬ አምናለሁ። ቀደም ሲል ስለ ‹‹የሽግግር መንግሥት መቋቋም አስፈላጊነት›› ባቀረብኩት ጽሑፍ ላይ እንደገለጽኩት፣ አሁን በምንገኝበት ነባራዊ የፖለቲካ ሁኔታ በአንጻራዊነት ሰላማዊ፣ ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ የማካሔድ ዕድላችን አንድ አምስተኛ ወይም ከ20% ያነሰ ነው። ይህ ዕድል በኮሮና ቫይረስ ወደ ሀገራችን መግባት ምክንያት የበለጠ ጠባብና ምናልባትም ወደ ዜሮ የተጠጋ ሆኗል። ይህ ግምት ከቅርቡ የዶ/ር ዐቢይ የከረረ የማስጠንቀቂያ ንግግርና መግለጫ በኋላ የበለጠ ተጠናክሯል።
ነገር ግን ምርጫው መካሔዱ የማይቀር ከሆነና በሆነ ተዐምራዊ ምክንያት በአንጻራዊነት ሰላማዊ፣ ነጻና ፍትሐዊ መሆን ቢችል፣ በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ካለው የፖለቲካ የኀይል አሰላለፍ አኳያ ምርጫውን የትኛው የፖለቲካ ፓርቲ ወይም ጎራ ሊያሸንፍ ይችላል? ለሚለው ጥያቄ ‹‹የቅድመ ምርጫ ውጤት ግምትና ትንተና›› መስጠት ጠቃሚ ይሆናል። ጠቃሚነቱም በሚከተሉት አምስት ዋና ዋና ምክንያቶች ላይ የተመሠረተ ይሆናል።
1. ምርጫው በቅርብ ጊዜ ከተካሔደ “እኛ የተሻለ የማሸነፍ ዕድል አለን” ብለው በማመን ምርጫው በቅርብ ጊዜ እንዲካሔድ ግፊት እያደረጉ የሚገኙ አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶች የሠሩት ሒሳብ ምን ያህል ጥቅማቸውን የማያስጠብቅና ከእውነት የራቀ ግምት እንደሆነ ቆም ብለው ማሰብ እንዲችሉ፤
2. የቅድመ ምርጫ ግምቱንም ሆነ በአጠቃላይ በሀገሪቱ ያለውን የፖለቲካ የኀይል አሰላለፍ በአግባቡ መረዳትም፥ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆኑ ዜጎች በተለያዩ ጉዳዮች ለሚይዟቸው አቋሞች እጅግ ጠቃሚ ግብዓት ሆነው ሊያገለግሉ የሚችሉ በመሆናቸው፤
3. ምርጫው የሚካሔድ ከሆነ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሀገሪቷ ያለውን የፖለቲካ የኀይል አሰላለፍ ሚዛን በአግባቡ ተገንዝበው በተናጠልም ሆነ በትብብር ማድረግ የሚገባቸውን ዝግጅት ከወዲሁ ለማድረግ እንዲችሉ፤
4. አንዳንድ ወገኖች እንደሚያስቡት መጪው ምርጫ በሆነ ተዐምራዊ ምክንያት ነጻና ፍትሐዊ ለመሆን ቢበቃ እንኳን፣ የምርጫው ውጤት በቀላሉ የሕዝብ መንግሥት ለማግኘት የሚያስችለን ሳይሆን፣ በእስካሁኑ የፖለቲካ ታሪካችን አይተነው የማናውቅና በበቂ ሁኔታ ያልተዘጋጀንበት አዲስ ዓይነት ውጤት ሊሆን እንደሚችል እንዲገነዘቡት ለማድረግ፤
5. እነዚህን ከዚህ በላይ የተጠቀሱትን ግንዛቤዎች በአግባቡ በመፍጠርም ሕዝቡ ከምርጫው በፊት ሀገራችን በቂ የዝግጅት ጊዜና የፖለቲካ ሒደት እንደሚያስፈልጋትና፣ ሁሉን ዐቀፍ የሆነ የእርቅና የአንድነት የሽግግር መንግሥት ማቋቋምም ምን ያህል ወቅታዊ፣ አስፈላጊና፣ ሊታለፍ የማይገባው ጥያቄ እንደሆነ የሚኖረውን ግንዛቤ የበለጠ ለማጠናከር ነው።
በአጠቃላይም እንዲህ ዓይነቱን የምርጫ ውጤት ቅድመ ግምትና ትንተና ማቅረቤ፣ ሀገራችን በድኅረ ምርጫ 97 ወቅት የገጠማት ዓይነት ወይም ከዛ የባሰ የህልውና ቀውስ ውስጥ እንዳትገባ የማገዝ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ይኖረዋል በሚል እምነት ነው።
በርግጥ፣ እንዲህ ዓይነቱን ‹‹የምርጫ ውጤት የቅድመ ግምትና ትንተና›› ከፓርቲ ጥቅም አኳያ ካየነው ለአንድ ፓርቲ ውስጣዊ ሥራ እንጂ ለሕዝብ በይፋ መቅረብ የሚገባው አልነበረም። ምክንያቱም እንዲህ ዓይነቱ ግምገማ ከምርጫ ስትራቴጂ ዝግጅት አንጻር ሌሎች ፓርቲዎች ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉበት መረጃ ሆኖ ሊያገለግል ይችላልና። ነገር ግን ጉዳዩ ከሀገር ደኅንነት ጋር የተያያዘና እንዲህ ዓይነቱን የሕዝብ ጉዳይም በውስጠ ፓርቲ መዋቅር ብቻ ገድቦ መወያየቱ፣ ኋላ ላይ ምን ያህል ያልተፈለገ ዋጋ ሊያስከፍል እንደሚችል ከ97ቱ ምርጫ ከተገኘው ልምድ በመነሳት ይህንን ሰነድ በዚህ መልክ ለሕዝብ ውይይት ይፋ ማድረጉ በቀና አመለካከት ላይ የተመሠረተ ተመራጭ መንገድ ነው ብዬ አምናለሁ።
በዚህ ጽሑፍ ላይ የተገለጸውን የምርጫ ውጤት ግምት ለመስጠት የተሞከረውም፣ እንዲሁ ከአንድ ግለሰብ ወይም ፓርቲ አመለካከት ጋር ከተያያዘ ጠባብ ግምገማ በመነጨ አይደለም። ይህ ግምገማ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ከተሰበሰበ ናሙና የመነጨ ባይሆንም፣ በአንዳንድ ክልሎች እስከ ወረዳ፣ በአንዳንድ ክልሎች ደግሞ ቢያንስ እስከ ዞን መዋቅር ድረስ ከሚገኙ የሀገሪቱ አካባቢዎችና ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ፣ በሀገሪቱ ውስጥ የተለያየ አመለካከት ካላቸው የፖለቲካ ድርጅት አመራሮችና አባላት መደበኛ ባልሆነ መንገድ የተሰበሰበ መረጃን መሠረት አድርጎ የቀረበ ግምትና ግምገማ ነው። ይህ የሆነውም በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ በፖለቲካ ዙሪያ የሚካሔድ ጥናት ግልጽና መደበኛ ከሆነ የጥናት አሠራር ይልቅ መደበኛ ባልሆነ የመረጃ አሰባሰብ ዘዴ ቢሠራ የተሻለ ውጤታማ እንደሚሆን በማመን ነው። ይህ የቅድመ ምርጫ ውጤት ግምትና ትንተና የተሰጠውም አሁን የምንገኝበትን ተጨባጭ ሁኔታ ብቻ ሳይሆን ወደፊት እስከ ምርጫው ዕለት ድረስ በሚኖረው ጊዜ፣ በተለይም በመጨረሻዎቹ ሁለት ወራት የሚካሄዱ የምርጫ ዘመቻዎችና የምረጡኝ ክርክር መድረኮች ሊያመጡ የሚችሉትን ከፍተኛ የኀይል አሰላለፍ ለውጥ ጭምር ግምት ውስጥ በማስገባት ነው።
በመጨረሻም፥ የ97 ምርጫን አስመልክቶ በወቅቱ በቅንጅት ውስጥ አቅርቤው የነበረው ተመሳሳይ ‹‹የቅድመ ምርጫ ውጤት ግምትና ትንተና›› ኋላ ላይ በምርጫው ከመጣው ውጤት ብዙም ርቀት ያልነበረው እንደነበር እዚህ ላይ አስታውሶ ማለፉ ጠቃሚ ይሆናል።


Read 2769 times