Print this page
Saturday, 16 May 2020 11:49

በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ያለው አለመግባባት እንዲፈታ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪ አቀረበ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

 በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል እየታየ ያለው አለመግባባትና የቃላት ጦርነት ተጨማሪ ሀገራዊ ቀውስ ከማስከተሉ በፊት በአጭሩ እንዲገታ የቤተ ክርስቲያኒቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪ አቀረበ፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ከግንቦት 4 እስከ 6 ቀን 2012 ዓ.ም ለ3 ቀናት ያካሄደውን መደበኛ ጉባኤው ሲያጠናቅቅ ባወጣው መግለጫ፣ አሁን ሀገሪቱ እየገጠሟት ያሉ ፈታኝ ሁኔታዎችን በጋራ መግባባትና ስምምነት፣ በአንድነት ቆሞ መቋቋም እንደሚገባ በአጽንኦት አሳስቧል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ በባለ 6 ነጥቡ ጋዜጣዊ መግለጫው ትኩረት ካደረገባቸው መካከል የህዳሴ ግድብ፣ የኮሮና ወረርሽኝና የፖለቲካ ፓርቲዎች አለመግባባት ዋንኞቹ ናቸው፡፡
ሀገር ተጠናክራ ልትቀጥል የምትችለው በሁሉም ዜጐች ዘንድ ሰላም፣ አንድነትና መግባባት ሲኖር ነው ያለው ቅዱስ ሲኖዶስ፤ በአሁኑ ጊዜ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚታየው አለመግባባትና መካረር አሳሳቢ ነው ብሏል፡፡
ይህ አለመግባባትና መካረር በጊዜ በውይይት ካልተገታና መፍትሔ ካልተበጀለት ሀገራዊ ቀውስ ሊፈጥር ይችላል ያለው ቅዱስ ሲኖዶስ፤ ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች ከምንም በላይ ለሀገራዊ አንድነት በመቆም በሀገሪቱ ላይ የተጋረጡ አደጋዎችን በጋራ ለመመከት እንዲሰባሰቡ ጥሪውን አቅርቧል፡፡
የህዳሴው ግድብ ወደመጠናቀቁ እየሄደ መሆኑን በአድናቆት እንደሚመለከተው በመግለፅም፣ በቀጣይም በግድቡ ዙሪያ የበለጠ ብሔራዊ መግባባት በመፍጠር ያለ አንዳች መሠናክል ከፍፃሜ ማድረስ እንደሚገባ መክሯል፡፡
የኮሮና ወረርሽኝን በተመለከተም አብያተ ክርስቲያናትም ሆኑ ምዕመናን ፀሎታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉና የመንግስትን መመሪያ አጥብቀው እንዲፈጽሙ ያሳሰበው ቅዱስ ሲኖዶስ፤ ምዕመናን ከቤተ ክርስቲያን ተለይተው መኖር ስለማይችሉ የሚሰጠው መንፈሳዊ አገልግሎት በየአጥቢያው በተመደቡ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች አስተናጋጅነት በጥንቃቄ እንዲከናወን  አዟል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ ከመንግስት ጋር ተጨማሪ ምክክር እንደሚደረግም ቅዱስ ሲኖዶስ አስታውቋል፡፡

Read 11845 times