Saturday, 16 May 2020 11:39

በኢትዮጵያ በኮሮና ምክንያት ትምህርት ያቋረጡ ከ 5 መቶ በላይ ህፃናት ሴቶች ከታቀደላቸው ያለ እድሜ ጋብቻ ተርፈዋል ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

በኮሮና ምክንያት ትምህርት አቋርጠው ቤት የዋሉ ከ5 መቶ በላይ ህፃናትን ከታቀደላቸው ያለ እድሜ ጋብቻ እንደታደጋቸው የአማራ ክልል የሴቶች፣ ህፃናት እና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ አስታውቋል፡፡  
ሮይተርስ የክልሉን የሴቶች ህፃናት እና ወጣቶች ቢሮ ኃላፊ አነጋግሮ በሠራው ዘገባ  በኮሮና ምክንያት ት/ቤቶች መዘጋታቸውን ተከትሎ፣ በእረፍት ላይ የነበሩ 540 ያህል ሴት ህፃናት በቤተሰቦቻቸው ጫና ጋብቻ ለመፈፀም በዝግጅት እንደነበሩ አመልክቷል፡፡ ታዳጊ ህፃናቱም ገና 18 አመት ያልሞላቸው እንደሆኑ ተጠቁሟል፡፡
“ከተለያዩ አካባቢዎች ህፃናቱ ጋብቻ ሊፈጽሙ መሆናቸውን በመስማታችን በጉዳዩ ጣልቃ ገብተን ሂደቱን ማስቆም ችለናል” የሚሉት የክልሉ ሴቶች ህፃናት እና ወጣቶች ጉዳይ የሥራ ኃላፊ ወ/ሮ አስናቁ ድረስ፤ “በኮሮና ስጋት ምክንያት ት/ቤቶች መዘጋታቸውን ተከትሎ ህፃናትን ለጋብቻ አስገድዶ የማጨት ድርጊት እየተበራከተ መጥቷል” ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የህፃናት ጋብቻ እንዳይፈፀም በማድረግ በኩል ቢሮው የሚደርሱትን ጥቆማዎች ብቻ መነሻ አድርጐ እየሠራ መሆኑንና ጥቆማ ሳይቀርብባቸው የተፈፀሙ ጋብቻዎች ሊኖሩ እንደሚችሉም ተገምቷል፡፡
እ.ኤ.አ በ2005 ዩኒሴፍ ባወጣው መረጃ መሠረት፤ በኢትዮጵያ ከ10 ህፃናት ስድስቱ 18 አመት ሳይሞላቸው ትምህርታቸውን አቋርጠው ጋብቻ ይፈጽሙ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ግን ከ10 ህፃናት ሴቶች 4 ያህሉ ብቻ ናቸው ጋብቻ የሚፈጽሙት ተብሏል፡፡ አሁን ግን በኮሮና ምክንያት ት/ቤት ተዘግቶ ልጆች ቤት መዋላቸውን ተከትሎ የህፃናት ጋብቻ በድጋሚ  እየተስፋፋ መምጣቱ አሳሳቢ እንደሆነ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ከዚህ ቀደም ህፃናት ጋብቻ እንዳይፈጽሙ ለመከላከል ት/ቤቶችን እንደ መረጃ ምንጭ ይጠቀም እንደነበር የጠቆመው የአማራ ክልል የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ቢሮ፤ አሁን ት/ቤቶች ዝግ በመሆናቸው መረጃ ለማግኘት መቸገሩን ይገልፃል፡፡
በአማራ ክልል ከሚፈፀሙ ጋብቻዎች በአማካይ ሴቶች 15 አመት ሳይሞላቸው ጋብቻ እንደሚፈጽሙም ዘገባው ያመለክታል፡፡
በኢትዮጵያ  በአጠቃላይ 15 ሚሊዮን የሚሆኑ እድሜያቸው ለጋብቻ ያልደረሱ ህፃናት ሴቶች ጋብቻ ፈጽመው እንደሚኖሩ የተባበሩት መንግስታት መረጃ የሚያመለክት ሲሆን፤ ሀገሪቱም ያለ እድሜ ጋብቻን ለማስቀረት የተለያዩ ስልቶችን ነድፋ እየተንቀሳቀሰች መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን ተከትሎ፣ አብዛኛው ሰው ቤት ከመዋሉ የተነሳ በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች እየተበራከቱ መምጣታቸው የተዘገበ ሲሆን ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድም በቤት ውስጥ መዋልን ተከትሎ በሴቶች ላይ ጥቃት እንዳይፈፀም ጥሪ ማቅረባቸው አይዘነጋም፡፡


Read 1947 times