Print this page
Saturday, 16 May 2020 11:23

በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ ሆቴሎች በየወሩ 35 ሚ. ዶላር እያጡ ነው

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

    ብሔራዊ ባንክ የ3 ቢሊየን ብር ብድር ፈቅዷል
                          
             በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል አገልግሎት መስጠት ያቋረጡት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኙ ሆቴሎች በየወሩ 35 ሚሊየን ዶላር ገቢ እያጡ መሆናቸው ተገለፀ፡፡ ይህንኑ በሆቴሎቹ ላይ የደረሰውን ኪሳራ አስመልክቶ ብሔራዊ ባንክ በ5 በመቶ ወለድ 3 ቢሊዮን ብር ብድር ፈቅዷል፡፡
የአዲስ አበባ ሆቴል ባለቤቶች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ቢኒያም ብስራት እንደተናገሩት ማህበሩ ባለፈው መጋቢት ወር ላይ ባስጠናው ጥናት መሠረት ወረርሽኙ በዘርፉ ላይ ከባድ ጉዳት እያደረሰ መሆኑንና ሆቴሎቹ ከሚሰጧቸው አገልግሎቶች ያገኙ የነበረውን 35 ሚሊዮን ዶላር ወርሃዊ ገቢ እያጡ መሆኑ በጥናቱ መረጋገጡን ገልፀዋል:: እንደ ጥናቱ፤ በማህበሩ ውስጥ ከታቀፉት 130 ሆቴሎች ውስጥ 88 በመቶ የሚሆኑት ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ሥራ ለማቆም መወሰናቸውን አመልክቷል:: ከእነዚህ መካከል 56 በመቶዎቹ ሙሉ በሙሉ ለማቆም የወሰኑ ሲሆን 32 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ከሚሰጧቸው አገልግሎቶች መካከል ከፊሎቹን ለማቆም እንደሚገደዱ አስታውቀዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከውጪ አገር ለሚገቡ መንገደኞች አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙት ሆቴሎች 12 በመቶዎቹ ብቻ እንደሆኑም በዚሁ ጥናት ላይ ተመልክቷል፡፡
ሆቴሎቹ በገጠማቸው ከፍተኛ የስራ መቀዛቀዝና ኪሳራ ሳቢያ ሆቴሎቻቸውን በመዝጋት ሠራተኞቻቸውን ለመበተን እየተገደዱ እንደሆነም በመማጸን መንግሥት የሥራ ማስኬጃ ብድር እንዲሰጣቸው ጥያቄ ማቅረባቸውን የማህበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ቢኒያም ብስራት ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ ሆቴሎቹ ለአንድ ዓመት የሥራ ማስኬጃ የሚሆን ብድር ጠይቀው እንደነበር የገለፁት አቶ ቢኒያም ባንኩ የስድስት ወራት የስራ ማስኬጃ ብድር የፈቀደላቸው እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ ዘርፉ በደረሰበት ኪሳራ ብሔራዊ ባንክ ለሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ለሥራ ማስኬጃ የሚሆን የ3 ቢለየን ብር ብድር በ5 በመቶ ወለድ ለመስጠት መፍቀዱም ታውቋል፡፡
ባለፈው ማክሰኞ ግንቦት 4/2012 ብሔራዊ ባንክ ይህንኑ ጉዳይ ለባንኮች ሁሉ ማሳወቁ ተገልጿል፡፡ ይኸው ብድር በዘርፉ ውስጥ ለሚገኙ የሆቴልና የአስጐብኚ ድርጅቶች የሚሆን ነው ተብሏል፡፡ 89 በመቶ ሆቴሎች 11 በመቶ ደግሞ የአስጐብኚ ድርጅቶች የብድሩ ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሏል፡፡
የኦክስፎርድ ኢኮኖሚ ሪሰርች ያስጠናውን ጥናት ዋቢ አድርጐ የአዲስ አበባ ሆቴሎች ማህበር በጥናቱ ላይ እንደገለፀው ሆቴሎች በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ ከደረሰባቸው ኪሳራ አገግመው በ2019 ወደነበሩበት ሁኔታ ለመመለስ በርካታ አመታትን ይወስድባቸዋል ብሏል፡፡   


Read 938 times