Print this page
Tuesday, 12 May 2020 00:00

በምርጫ፣ “አብዮት” እንዲፈነዳ ከጠበቅን፣ ለምርጫ አንመጥንም

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

  - የፖለቲካ ምርጫ ፋይዳ፤ “አብዮት”ን የሚያስቀር፣ ከለውጥ ማዕበል የሚገላግል ሲሆን ነው፡፡
    - ለሕግ የተገዛና በሕጋዊ ስርዓት የሚካሄድ፣… ሕግን አክብረው ለማስከበር የሚሰሩ ሰዎችን ለመምረጥ እስከሆነ ድረስ ነው - የፖለቲካ ምርጫ ፋይዳ
         የሚኖረው፡፡
     - በተቃራኒው፣ “በዚህኛው ምርጫ ጉድ ይፈላል፤ በዚያኛው ምርጫ ይለይለታል” ብለን ስንጠብቅስ?
     - አገር በምርጫ ትኩሳት ካልተንገበገበች፤ ምርጫ የተካሄደ አይመስለንም፡፡ በዚያ ላይ ‹‹የምርጫ ውጤት›› ማለት፣ ‹‹የንግስና ፈቃድ›› ሆኖ ይታየናል::
      ድንበር፣ ቅጥና ለከት የሌለው የዘፈቀደ ስልጣን፣ ከምርጫ ውስጥ እንደሚገኝ የሚያምኑ ሰዎች ሞልተዋል፡፡


          ምርጫ እንደ አልፋና ኦሜጋ የሚታየው፤ ‹‹በምርጫ ያሸነፈ፣ ማንኛውም ነገር ይፈቀድለታል›› በሚል ስሜት ነው፡፡ ‹‹ማንኛውም ነገር፣… ሕግ ማስከበርም፣ ሕግ መርገጥም ይፈቀድለታል - በምርጫ ላሸነፈ ፓርቲና ፖለቲከኛ፡፡ የተሸነፈ ደግሞ፣ ይረገጣል፤ ያልቅለታል›› እንደ ማለት ነው፡፡
ምናልባት በምርጫ ያሸነፈ ፓርቲና ፖለቲከኛ፣ ደግ ከሆነ፣ ለ5 ዓመት ሕግ አክብሮ፣ አገርንና ስርዓትን በሰላም ሊያቆይ ይችላል፡፡ በቀጣዩ ምርጫ የሚያሸንፍ ፖለቲከኛ፣ ክፋት የሚያሰኘው ከሆነስ? እንደሻው መሆን ይችላል? በሕዝብ እስከተመረጠ ድረስ፣ ሕግ አይገዛውም? ሕግና ስርዓትን መናድ፣ አገርንም ማፍረስ ይፈቀድለታል? የፖለቲካ ምርጫ እንዲህ ከሕግ በላይ ከሆነ፣ ከቁማርም በላይ አደገኛ ነው፡፡
ለመከባበርና ለመበላላት፣ ለእርጋታና ለግርግር፣ ‹‹እኩል›› እድል የምንሰጥበት የሞት ሽረት ቀጠሮ ሆነ ማለት ነው - የፖለቲካ ምርጫ፡፡
ለሕግ አክባሪና ለወንጀለኛ እኩል እድል መስጠት፣…. ወንጀልን ከመደገፍ ወይም ወንጀልን ከመጋበዝ አይለይም፡፡ እናም፣  
ህጋዊ ስርዓትና ስርዓት አልበኝነት፣ የአገር ህልውናና ትርምስ …ማንኛውም ነገር እንዲፈጠር የሚፈቅድና የሚያመቻች “የፖለቲካ ምርጫ” ማካሄድስ፤ ጥፋትን ከመጋበዝ በምን ይለያል? ለዚያውም በየ5 ዓመቱ እየደጋገምን? ከአላዋቂነትና ከኋላቀርነት የባሰ፣ በጣም የወረደ ክፉ የጥፋት ድግስ ይሆናል - የሞት ሽረት ምርጫ፡፡
የፖለቲካ ምርጫ፣ ጠቃሚ እንጂ አጥፊ ሊሆን አይገባውም ነበር፡፡ ጠቃሚ እንዲሆን ማድረግም ይቻላል፡፡ እንዴት? የፖለቲካ ምርጫ፣ ‹‹በሕግ የበላይነት›› ስርዓት ስር የሚካሄድ ሲሆን፤ የመከባበር እንጂ የመበላላት ድግስ አይሆንም፡፡ ወንጀልን የሚከለክልና ሕግ አክባሪነትን የሚያሰፍን የፖለቲካ ምርጫ ሊኖር የሚችለው ‹‹ለሕግና ሥርዓት›› ከተገዛ ብቻ ነው፡፡
ማንኛውም ተቋም፣ የሚያስከብራቸውና የሚከለክላቸው ነገሮች አሉት፡፡
መሰረታዊው የፖለቲካ ተቋም (አገርና መንግስት፤ ሕግና ሥርዓት)፣ ከሌሎች ተቋማት ሁሉ የሚለየው፤ ግዴታን የሚጨምር መሆኑ ነው፡፡
በአንድ በኩል፤ መንግሥት፣ የሚያስከብራቸውን ነገሮች፣ እንዳሰኘውና በዘፈቀደ ሳይሆን፣ ‹‹ህግን አክብሮ ስርዓትን ተከትሎ›› የማስከበር ግዴታ አለበት፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ፤ የተከለከሉ ነገሮችን የሚቆጣጠረው፣ በልመና ሳይሆን፣ ‹‹በህግና በአዋጅ፣ በፖሊስ ሀይልና በፍርድ ቤት ቅጣት›› በመሆኑ፣ ከሌሎች ተቋማት ይለያል፤ ‹‹መሰረታዊ የፖለቲካ ተቋም››፡፡  
ልዩነቱን ልብ በሉ፡፡ ማንኛውም ሰውና ተቋም፣ ህግና ስርዓትን የማክበር ግዴታ አለበት፡፡ መንግስት ግን፣ ህግና ሥርዓትን የማክበር ብቻ ሳይሆን ‹‹የማስከበር ግዴታም›› ይኖርበታል፡፡
ሁለተኛውን ልዩነት ተመልከቱ፡፡ ማንኛውም ሰውና ተቋም፣ ምንና ምንን እንደማይፈቀድ እየገለፀ፣ የተከለከሉ ነገሮችን ሊዘረዝር ይችላል፡፡ ነገር ግን፣ ራሱን ከአጣዳፊ ጥቃት ለመከላከል ካልሆነ በቀር፣ እንደ መንግስት፣ ወታደር ማዝመትና የጦር መሳሪያ መጠቀም፣ እንደ ፍርድ ቤት የሞት ወይም የእስር ቅጣት መፍረድ አይችልም፡፡
የፖሊስና የጦር ሃይል፤ የፍርድ ቅጣትና እስር፣ ለመሰረታዊ የፖለቲካ ተቋም ብቻ የሚፈቀዱ መሰረታዊ ባህርያት ናቸው፡፡ እንዲህ አይነት ከፍተኛ ስልጣን ‹‹ለመንግስተ - አገር›› ብቻ መፈቀዱ ተገቢ የመሆኑ ያህል (the monopoly of legal force እንዲሉ)፤ ያንን የሚመጥን ከፍተኛ ጥንቃቄ፣ ከሕግ ውጭ ውልፍት የማያስብል፣ እጅግ ጥብቅና ግልፅ ህጋዊ ስርዓት ያስፈልገዋል፡፡ አለበለዚያ፣ ነገሩ ይበላሻል፡፡
ህግና ሥርዓት ከሌለ፣ የመንግሥት ስልጣን፣ (የፖሊስ ሃይልና የፍ/ቤት ዳኝነት) ትርጉም ያጣል፤ አገር ይተራመሳል፡፡
ወይም ደግሞ፣ ሕግና ስርዓት የማይገዛው አምባገነንነት ይሰፍናል፡፡ አገርን ለመጠበቅ፣ ሕግን ለማስከበር መዋል የነበረበት የመንግሥት ስልጣን፣ የወንጀል ማሳለጫ ይሆንና፣ አገርን ሲዖል  ያደርጋታል፡፡
በሌላ አነጋገር ከአራቱ መሰረታዊ ገፅታዎች መካከል፤ ማለትም ከአገር፣ ከመንግስት፣ ከሕግ እና ከስርዓት መካከል፤ አንዱ ከሌለ፣ ሌሎቹ መና ይቀራሉ፡፡ የተፃፈም ሆነ ያልተፃፈ፣ አዲስም ሆነ ነባር፣ በዛም አነሰ፣ በተወሰደ ደረጃ ሕግና ስርዓት ከሌለ፣ ‹‹ወንጀል የሆነና ያልሆነ ተግባር›› እንደ እለቱ የአየር ፀባይ የሚለዋወጥ ከሆነ፤ ‹‹የሕግ አስከባሪና የዳኝነት ስልጣን፤ የክስና የይግባኝ እርከኑ፣ የተጠያቂነትና የሃላፊነት ሰንሰለቱ›› የማይታወቅ ከሆነ፣ ቢያንስ ቢያንስ ‹‹የንጉስና የወረዳ ገዥ የስልጣን ደረጃና ልክ›› ተለይቶ የማይታወቅ ከሆነ፣ መንግስትም አገርም አይኖሩም - የሽፍታ መንጋዎችና ጋራ ሸንተረሮች ግን ይኖራሉ፡፡
በአጭሩ፤ አገርና መንግስት፣ ሕግና ስርዓት፣ ለሌሎች ፖለቲካዊ ተቋማትና አሰራሮች ሁሉ የህልውና መሰረት ናቸው:: የፖለቲካ ተቋማት ሁለንታዊ መሰረትን ለመናድ የሚመጣ ሰው የለም ማለት አይደለም፡፡ ሞልቷል፡፡ የተግባራቸው መንስኤና ትርጉሙ ግን ሊለያይ ይችላል:: ምን ላይ እንደቆመ ሳይገባው፣ ከእግሩ ስር የረገጠውን መሬት የሚቦረቡር ሰው ይኖራል፡፡ ይሄ የአላዋቂ ስራ ነው፡፡
ከስር “እኔ ስሸረሽር፣ ያኛው ሰውዬ ከስር ከስር ይጠግናል” ብሎ የሚመኝ፤ ይህንንም እንደ ብልጣብልጥነት ብቻ ሳይሆን እንደ ብልሃት የሚቆጥር ቀሽም ፖለቲከኛም ሞልቷል፡፡ ጥበበኛ የሆነ ሊመስለው ይችላል:: ግን፣ የስንፍና፣ የሸፍጥና የሾላካነት አመል ነው የተጠናወተው፡፡
የተገነቡ ነገሮችን ከማፍረስ ውጭ ሌላ ምንም የማይታየው፣ ወለፈንድ (ናይህሊስት) ፖለቲከኛ ደግሞ አለ፡፡ ነገረ ስራው፣ በፖስት ሞደርኒዝም የተቃኘ አዲስ የጥፋት ፈጠራ ቢመስልም፤ ነባር የክፋት ተግባር ነው፡፡
በምርጫ ሰበብ፣ ሕግና ስርዓትን መሸርሸርስ?
ከአራቱ መሰረታዊ የፖለቲካ ገጽታዎችና ባህርያት አንፃር፣ የፖለቲካ ምርጫ የምንለው ክንውን፣ እንዲሁም “ዲሞክራሲ” የተሰኘው አሰራር፤ ትርጉማቸው፣ ድርሻቸውና ፋይዳቸው ምን እንደሆነ እንመልከት፡፡
ምርጫ፣ ቀዳሚና የበላይ አይደለም፡፡
አገርና መንግስት፣ ሕግና ስርዓት፣ …የፖለቲካ ምርጫ በሌለበት ዘመን፣ ህልውና ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ለብዙ ዘመናትም ህልውና ነበራቸው፡፡
የፖለቲካ ምርጫ የሚኖረው ግን፣ ‹‹ቅጣምባር›› ያለው አገር ሲኖር ብቻ ነው፡፡ የዜጎች መኖሪያ መሬት፣ ከሞላ ጎደል ከነ ዳር ድንበሩ የተከበረና ቅርፅ የያዘ አገር መኖር አለበት፡፡ አገር ከሌለ፤ እንደ መለማመጃ፤ ‹‹ለሕጻናት ፓርላማ›› እንኳ ምርጫ ማካሄድ አይቻልም፡፡
ይህም ብቻ አይደለም፡፡
አገር፣ ያለ ‹‹መላ›› ውሎ አያድርም:: ‹‹መላ ቅጡ›› የሚታወቅ አገር ሊኖር ይገባል - ከምርጫ በፊት፡፡ የአገር ሕልውና በምኞት አይቀናም፡፡ አገርን ከወረራና ከትርምስ የሚጠብቅ የመከላከያና የፖሊስ ሃይል፣ እንዲሁም ፍርድ ቤትና ምርጫ አስፈፃሚ፣ ገቢ የሚሰበስብና በጀት የሚመድብ መስሪያ ቤት …እነዚህና ሌሎች የመንግስት ተቋማት ሲኖሩ ነው፤ የአገር ሕልውና ሊሰነብት የሚችለው፤ የፖለቲካ ምርጫም የሚኖረው፡፡
ይህም ብቻ አይደለም፡፡
ከምርጫ በፊት፣ ‹‹ውጥንቅጥ›› ያለው ህግና ስርዓት ያስፈልጋል፡፡ ማለትም፣ ውሉ የሚታወቅ የሕግ ይዘት፣ እንዲሁም ከመነሻ እስከ መድረሻ የሕግ አፈጻጸም ሂደቱ የሚታወቅ ሕጋዊ ስርዓት ሲኖር ብቻ ነው፤ የፖለቲካ ምርጫ ሊኖር የሚችለው፡፡ አለበለዚያ፣ ከመነሻው ምርጫ እንዴት እንደሚካሄድ የማይታወቅ፤ ከዚያም በትክክል ስለመካሄዱ ለመዳኘት የማይቻል፣ ‹‹ውጥንቅጡ የወጣ›› ቅዠት ይሆናል - ሕግና ስርዓት በቅጡ ሳይኖር የሚከናወን የፖለቲካ ምርጫ፡፡
የፖለቲካ ምርጫ እንዲኖር የሚፈልጉ ሰዎችና ፖለቲከኞች፤ እነዚህን ነጥቦች መገንዘብ ያቅታቸዋል? የቆሙበትን መሰረት ማስተዋል አለባቸው፡፡ አገርንና መንግስትን፣ ሕግንና ስርዓትን የሚንድ ተግባር በግላጭ መፈፀምና ማበረታታት አይደለም፤ መፍቀድና በዝምታ ማለፍም የለባቸውም፡፡ መከላከል ነው የሚገባቸው፡፡
ለፖለቲካ ምርጫ ልዩ ፍቅር ቢያድርባቸው፣ ወይም አልፋና ኦሜጋ መስሎ ቢታያቸው እንኳ፣ እንዲያ አለቅጥ ያፈቀሩት “ምርጫ” እንዲካሄድ፤ ከዚያም “በ5 ዓመቱ ይድገመን” ለማለት ከፈለጉ፤ በቅድሚያ አገርና መንግስት፣ ሕግና ስርዓት መኖሩን ያረጋግጡ፡፡ እንዲዘልቅም ይትጉ፡፡
በፖለቲካ ምርጫ ምን ይገኛል? ስልጣን መያዝ ወይስ መንግሥት መሆን?
የፖለቲካ ምርጫ፤ በፖለቲካ ውስጥ ምን አይነትና ምን ያህል ድርሻ እንዳለው፣ በትክክል ማስተዋልና ማጤን ያስፈልጋል:: የፖለቲካ ምርጫ፤ እንደ አገር ሕልውና፣ ወይም እንደ መከላከያ ሀይልና እንደ ፍርድ ቤት፣ የእለት ተእለት ጉዳይ አይደለም፡፡ በአምስት አመት አንዴ ነው የሚካሄደው፡፡
የምርጫው ውጤት ድርሻስ፣ ምን ያህል ነው? አዎ፤ በምርጫ ያሸነፉ ፖለቲከኞችና ፓርቲዎች፣ “የመንግስት ስልጣን” ይይዛሉ፡፡ ነገር ግን፣ መንግሥት አይሆኑም፡፡ የተወሰነ የመንግሥት ስልጣን ብቻ ይኖራቸዋል፡፡ ልዩነቱ ምንድነው?
በምርጫ ያሸነፉ ፖለቲከኞች፣ ፓርላማ ውስጥ ብዙ ወንበር ይዘው፤ የተለያዩ ህጐችን የማውጣት፤ ጠቅላይ ሚኒስትርን የመሰየም፤ ሚኒስትሮችን፣ ኮሚሽነሮችና ምክትሎችን የመሾም ስልጣን ያገኛሉ፡፡
ነገር ግን፤ መንግሥት ማለት፣ ፓርላማና ጠቅላይ ሚኒስትር ማለት ብቻ አይደለም:: አብዛኛው የመንግስት ባለስልጣንና ሰራተኛ፤ በምርጫ ውጤት የምንሾመው የምንሽረው አይደለም፡፡ የምርጫ ውጤት እየታየ በሃላፊነት የሚመደብ አይደለም፡፡
የትኛውም ፓርቲና ፖለቲከኛ፣ ‹‹ምርጫ አሸነፍኩ›› ብሎ፤ እንዳሰኘው ዳኞችን መሻር አይችልም፡፡ የፖሊስ ሳጅንና ኢንስፔክተሮችን፣ የመከላከያ ሃይል ሻለቃና ኮሎኔሎችን እንዳሻው የመሾምና የመሻር ስልጣንም አይኖረውም፡፡ ነባር ፖሊስና ወታደሮችን በጅምላ አባርሮ፤ “የራሱ ፖሊሶችና ወታደሮችን” የመሰብሰብ ስልጣን አይኖረውም፡፡ አብዛኛው የመንግሥት ባለሥልጣንና ሰራተኛ፣ በምርጫ ድምፅ ሳይሆን፣ በሙያ ብቃት መመዘኛ እየተወዳደረ ነው ሃላፊነትና ደሞዝ ማግኘት ያለበት፡፡ በምርጫ ያሸነፈ ፓርቲና ፖለቲከኛ እንዳሰኘው መሾምና መሻር አይችልም፡፡
ሌላ ትልቅ ነጥብም አለ፡፡ የትኛውም ፓርቲና ፖለቲከኛ፣ ‹‹በምርጫ አሸነፍኩ›› ብሎ፤ አገሬውን ማፍረስና መበተን፤ ማስፋትና ማጥበብ፣ ክብ ወይም አራት ማዕዘን ቅርጽ ማስያዝ አይችልም፡፡
በተቃራኒው፤ በምርጫ ያሸነፈ ፖለቲከኛ፣ እንደማንኛውም ሰው፣ ነባሩን የአገር ድንበር የማክበር ግዴታ ብቻ ሳይሆን፤ ስልጣን ከያዘ በኋላ፣ የአገርን ድንበር የማስከበር ግዴታም ይታከልበታል፡፡
የምርጫ ውጤት፣ መረን የተለቀቀ ስልጣን አይደለም፡፡ የትኛውም ፓርቲ በምርጫ ቢያሸንፍ፣ ህግና ስርዓትን እንዳሻው የመቀየር ስልጣን አይኖረውም:: ከህገ መንግስት ጋር የሚጣጣም እንጂ የሚቃረን ህግ ማወጅ አይችልም፡፡
ህጐች፤ ከምርጫ ውጤት በላይ ናቸው፡፡        
እድሜያቸውም ከምርጫ ዘመን ባሻገር ይረዝማል፡፡ የወንጀለኛ መቅጫ፣ የፍትሐ ብሔርና የንግድ ህጐች፣ ከሞላ ጐደል፣ ያለ ብዙ ለውጥ ለስንት ዓመታት እንደዘለቁ፣ ስንት መንግስታትን እንደተሻገሩ አስቡት፡፡ እንዲያውም፤ መሰረታዊ ሕጎች ‹‹ዘላለማዊ ናቸው›› ማለት ይቻላል፡፡ ‹‹በሐሰት አትወንጅል፣ ሸፍጥም አትስራ፡፡ የሰውን ንብረት አትዝረፍ፣ የሰውን ሕይወትም አታጥቃ፡፡››… ዋና ዋናዎቹ ሕጎች ከእነዚህ ሀሳቦች የሚመዘዙ ዝርዝሮች ናቸው፡፡
መሠረታዊ ህጎች በምርጫ አማካኝነት የሚመጡና የሚባረሩ አይደሉም፡፡ በተቃራኒው፣ አትሸፍጥ፣ አትስረቅ፣ አትግደል የሚሉ ሕጎችን ለማስከበር ከሚያገለግሉ በርካታ አሰራሮች መካከል አንዱ ነው - የፖለቲካ ምርጫ፡፡  
‹‹በምርጫ አሸንፌያለሁ፤ ስልጣን ይዣለሁ›› የሚል ፓርቲ፣ ህገመንግስትን የመሻር፤ ሌሎች ህጐችንም እንዳሻው የመጣስ ስልጣን አይኖረውም ማለት ነው:: አንደኛ ነገር፣ በምርጫ ያሸነፈ ፓርቲም ሆነ ፖለቲከኛ፣… እንደማንኛውም ሰውና እንደማንኛውም ተቋም፤ ህግን ማክበር፣ ግዴታው ነው፡፡ የመንግስት ስልጣን ከያዘ ደግሞ፤ ህግን የማክበር ብቻ ሳይሆን፣ የማስከበር ግዴታ ይጨመርበታል፡፡
ይሄ፤ ወደ ሦስተኛውና ወደ ዋነኛው ነጥብ ያሸጋግረናል፡፡
‹‹ምን የምን›› የበላይ፣ ‹‹ምን የምን›› አገልጋይ እንደሆነ እንድናገዝብ ይረዳናል፡፡
‹‹የአገርና የመንግስት፣ የህግና የስርዓት›› ፋይዳ፣ የፖለቲካ ምርጫዎችን ለማካሄድ አይደለም፡፡
በተቃራኒው፤ የፖለቲካ ምርጫ የሚካሄደው፤ የአገርን ህልውናና ሰላም የሚያስጠብቁ የመንግስት ተቋማትን ለማገልገል፣ ለመከታተልና ለመቆጣጠር ስለሚጠቅም ነው፡፡ ህግንና ስርዓትን አክብረው ለማስከበር የሚሰሩ፤ ጥቂትና ጊዜያዊ ተቆጣጣሪዎችን ለመመደብ ያገለግላል - የፖለቲካ ምርጫ፡፡
በአጠቃላይ፤ በደረጃው፣ በድርሻውም ሆነ በፋይዳው፣ የፖለቲካ ምርጫ፣ የፖለቲካ አልፋና ኦሜጋ አይደለም፡፡ ቀዳሚና መሰረታዊ አይደለም፡፡ ዋናው አስኳል አይደለም፡፡ ወሳኝ አላማ አይደለም፡፡ አንድ ጠቃሚ አሰራር ነው፡፡
ይህንን እውነታ በውል ብንገነዘብ ኖሮ፤ የምርጫን ፋይዳና ድርሻ እንደ ተራራ ባናጋንን ኖሮ፣ ሕግን ማስከበርና ስርዓትን ማሟላት ከምርጫ የሚቀድሙና የሚልቁ መሆናቸውን ጠንቅቀን ብንረዳ ኖሮ፣ የምርጫ ጉዳይ የቀውስ ሰበብ አይሆንብንም ነበር፡፡ ለዘብ ያለ፣ ግርግር ያልበዛበት ምርጫ፤ በጣም በተረጋጋና በጥሞና፤ በዚህ አመት ማካሄድ አያቅትም ነበር ማለት ይቻላል፡፡
ሁሉም ሰው፣ ለመምረጥና ለመመረጥ ሲመዘገብ እጁን በሳሙና ታጥቦ፣ በሆይ ሆይታና በግርግር ሳይሆን፣ ቅስቀሳውንና የምርጫ ዘመቻውን አሁን እንደምናየው፣ ‹‹በኦን ላይን›› አካሂዶ፣ እያንዳንዱ ሰው ርቀቱን ጠብቆ፣ ራሱን ችሎ የምርጫ ድምፅ ቢሰጥ፣ ጥቅም እንጂ ጉዳት የለውም፡፡
‹‹ግርግሩና ጫጫታው ነው ምርጫን የሚያሳምረው›› ካልተባለ በቀር፤ የምርጫ ድምፅ፣ የግል ድምፅ ነው፡፡ ርቀትን መጠበቅም የግል ርቀትን ማክበር ስለሆነ፤ ሁካታ ቢቀርብን እንጂ፣ የምርጫ ድምፅ መስጠትን አይከለክልም፡፡
ደግሞም፣ ‹‹ከፖለቲካ ምርጫ የሚቀድሙና የሚልቁ መሰረታዊ ጉዳዮችን አሟልተናል›› የምንል ከሆነ፣ ማንም ቢመረጥ የዚያን ያህል የሚያስጨንቅ አይሆንብንም ነበር፡፡ ማንም ቢመረጥ፤ ሕግና ስርዓትን ከማክበርና ከማስከበር ውጭ፤ እንዳሻው አገሬውን በማዕበል የማናወጥ ስልጣን የማይኖረው ከሆነ፤ ምርጫውን ‹‹ማካበድ›› እና ማራዘም ባላስፈለገ ነበር፡፡
ችግሩ ምንድነው? የፖለቲካ ምርጫ፣ እንደ አልፋና ኦሜጋ ነው የሚታየው - በአብዛኛውም በኋላ ቀርነት ሳቢያ፡፡ አገሪቱ በምርጫ ትኩሳት ካልተንገበገበች፤ እንደ ጉድለት ነው የሚቆጠረው፡፡ እናም፣ ምርጫውን ማራዘም የግድ ሆነ:: የሚራዘመው በሕጋዊ መንገድ ብቻ ነው መባሉ ግን ጥሩ ነው፡፡ ከምርጫ በፊትና በላይ፣ ሕግና ስርዓት ይቀድማል፡፡ ይልቃል::
የፖለቲካ ምርጫ፣ በሁለት ወይም በአራትና አምስት ዓመት በመካሄዱ፣ አልያም ከመደበኛ ጊዜው ስድስት ወር ቀድሞ ወይም ዘግይቶ በመካሄዱ የሚገኝ ጥቅም ካለ፣ የትኛው እንደሚሻል ማመዛዘንና ሐሳብ መስጠት ክፋት የለውም፡፡
ሕግና ሥርዓትን የመከተልና የመጣስ፣ የማክበርና ያለማክበር ጉዳይ ግን፣ ጨርሶ ለሚዛንና ለምርጫ መቅረብ የለበትም፡፡ ‹‹ያኛውን ሕግ ማሻሻል፣ ያኛውን አሰራር መለወጥ››፣ ትርጉም የሚኖረው፤ ሕግና ሥርዓት የሚከበር ከሆነ ብቻ ነውና፡፡ የአገር ሕልውናን የማስጠበቅና የማፍረስ ጉዳይ፤ የእነ ፖሊስ የእነ ፍርድ ቤት እጣ ፈንታ ለውይይት፣ ማለትም መንግሥት አልባ መሆንና አለመሆን ለድርድር ወይም ለምርጫ መቅረብ የለበትም፡፡
አገር፣ ለዜጎች ህልውናና ነፃነት የምትመች እንድትሆን መመኘትና መጣር የሚቻለው፤ አገር ካለ ነው፡፡ የመንግሥት አስተዳደርን ማቃናትና በምርጫ መቀየር የሚቻለው፣ መንግሥት ያለው አገር ውስጥ ብቻ ነው፡፡    


Read 3436 times