Wednesday, 13 May 2020 00:00

ህወሓት ሆይ፤ በዴሞክራሲ ሂደት መሸነፍ የዓለም መጨረሻ አይደለም

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(1 Vote)

 ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝ የህወሓት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሚያዝያ 26 ቀን 2012 ዓ.ም የሰጠው መግለጫ ነው፡፡ በህወሓት መግለጫ ላይ ያለኝን አስተያየት ለመጻፍ የተነሳሳሁት የብልጽግና ፓርቲ አባል ወይም ደጋፊ ስለሆንኩ አይደለም፡፡ በህወሓት መግለጫ ላይ ለመጻፍ የተነሳሳሁት “ህወሃትን ስለምጠላ” አይደለም፡፡ ለጽሁፌ መነሻ የሆነኝ ህወሓት በገዢነትም በተቃዋሚነትም ሚናዋ የምታራምደው አቋም፤ ምን ያህል መርህ አልባና ኢ-ዴሞክራሲያዊ እንደሆነ ለማሳየት መሆኑን አስቀድሜ ለማስገንዘብ እወዳለሁ፡፡
የህወሓት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ለሦስት ቀናት ስብሰባ ያደረገ ሲሆን፤ በዚህ ወቅት በስፋት ከመከረባቸው ጉዳዮች ውስጥ ዋነኛው “ብልፅግና ፓርቲ እያካሄደው ያለውን ሕገ መንግስታዊ ስርዓትን የመናድ ዘመቻ” በተመለከተ መሆኑን በመግለጫው መግቢያ ላይ ጠቅሷል፡፡ መግለጫው አያይዞም “በአንድ ሰው የሚመራ አምባገነን ሥርዓትን ለመትከልና ከሕገ መንግስታዊ መንገድ ውጪ የሥልጣን ዕድሜን ለማራዘም የተጀመረውን ጥረት አጠናክሮ ቀጥሎበታል” በማለት ብልጽግና ፓርቲን ይከሳል፡፡ በመሰረቱ የብልጽግና ፓርቲና የህወሓት ክስና ውዝግብ የሚገርም ነገር አይደለም፡፡ አዲስ ነገርም አይደለም፡፡ እናም ይህንን እንለፈውና የመግለጫውን አምስት ነጥቦች እንመልከት፡፡
ከላይ በተጠቀሰው ቀን የህወሓት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ አምስት ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡ ተራ በተራ እንያቸው፡፡ የመጀመሪያው ነጥብ፤ “የብልፅግና ፓርቲ ሕገ-መንግስቱን ለመተርጐም በሚል ሰበብ የጀመረውን እንቅስቃሴ በአስቸኳይ ያቁም፡፡ ሕገ-መንግስታዊ ትርጓሜ የሚያስፈልገው ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓቱ ባስቀመጠው ግልፅ መስፈርት መሰረት አሻሚ ሆነው ለተገኙ አንቀፆች እንጂ የአንድን ስብስብ የሥልጣን ዕድሜ ከሕገ-መንግስታዊ ሥርዓት ውጭ ለማራዘም ሊሆን አይችልም፡፡ በመሆኑም ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓቱን ለማፍረስ እየተደረገ ያለው ጥድፊያ በአስቸኳይ ቆሞ… የኮሮናን ወረርሽኝ በተቀናጀ መልኩ ለመከላከልም ሆነ ሃገራዊ ምርጫን ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓቱ በሚፈቅደው ማእቀፍ ውስጥ በመሆን ለማከናወን በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ሁሉም ፓርቲዎች በሙሉ የባለቤትነት መንፈስ እንዲሳተፉ …” መድረክ እንዲመቻች ይጠይቃል - ህወሓት በመግለጫው፡የውይይት መድረክ መጠየቅ አግባብ ነው፡፡ ሃሳብን በሰለጠነ መንገድ አቅርቦ መከራከርም ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን በደፈናው “ህገ መንግስት የሚተረጎመው አንቀፆች አሻሚ ሆነው ሲገኙ ነው…” ማለት ትርጉም የለውም፡፡ ትዝብትም ላይ ይጥላል:: የህግ ምሁራንና ሊቃውንት እንደሚሉት ከሆነ፤ የህገ መንግስት አንቀፅ ብቻ ሳይሆን እንደ ሁኔታው ሌሎች ነገሮችም የሚተረጎምበት አግባብ አለ፡፡ “Abstract Review” (ድብቁን መፈተሽ) በሚለው የህግ ጽንሰ-ሃሳብና ተለምዷዊ አካሄድ መሰረት፤ ህገ መንግስቱ ግልጽ ባላደረጋቸው ጉዳዮች ላይ ትርጉም መስጠት ይቻላል፡፡ ይህ ዓይነቱ አሰራር በበርካታ ሀገራት ሥራ ላይ መዋሉንም ልንገነዘበው ይገባል፡፡
ህወሓት ስልጣን ላይ ብትሆን ኖሮ፣ አሁን የገጠመንን ችግር ህገ መንግስትን ከመተርጎም ውጪ መፍትሄ ልታገኝለት እንደማትችል በእርግጠኛነት መናገር ይቻላል፡፡ ህገ መንግስቱ የሚተረጎመው እኮ “የኮረናን ወረርሽኝ በተቀናጀ መልኩ ለመከላከልና ሃገራዊ ምርጫን ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓቱ በሚፈቅደው ማእቀፍ ውስጥ በመሆን ለማከናወን” በቂ ጊዜ ለማግኘት ከመሆን ውጪ ሌላ ምን ለማድረግ መስሏት ይሆን ህወሓት “ህገ መንግስቱ አይተርጎም” የምትለው? “ሌባ እናት ልጇን አታምንም” እንዲሉ፣ ይህ አባባል ህወሓት በብልጽግና ፓርቲ ቦታ ብትሆን ኖሮ ታደርገው የነበረውን እየነገረችን ከመሆን የዘለለ ትርጉም የለውም፡፡ እንደኔ፤ እንደኔ የብልጽግና ፓርቲ ዓላማ ስልጣን ላይ ለመቆየት ቢሆን ኖሮ፣ እንዲህ ዓይነት ውጣ ውረድ ውስጥ ምን አስገባው? ይህንን ለማድረግ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ይበቃው ነበር እኮ!
የህገ መንግስት መተርጎም ጉዳይ አወዛጋቢ በመሆኑ የህግ ባለሙያዎችን እይታ ሰፋ አድርጌ ለማቅረብ እወዳለሁ:: እንዲህ ይላሉ የህግ ባለሙያዎች፡- በሕገ መንግስቱ በአንቀጽ 58/3 ፤ላይ የተወካዮች ም/ቤት የሥራ ዘመን 5 ዓመት መሆኑና የሥራ ዘመኑ ከማብቃቱ ከአንድ ወር በፊት ምርጫ መካሄድ እንደሚገባ ተደንግጓል:: ነገር ግን ምርጫው ከዐቅም በላይ በሆነ/ባልሆነ ምክንያት በሰዓቱ ሳይደረግ ቢቀር ምን ይሆናል? ለሚለው ጥያቄ፤ ህገ መንግስቱ ግልፅ መልስ አላስቀመጠም። ከዚህ በተጨማሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የስራ ዘመኑ ካበቃ እንደፈረሰ ተቆጥሮ ሀገሪቱ መንግሥት አልባ ትሆናለች ማለት ነው? ወይንስ ጊዜው ቢያልፍም ምርጫ ተደርጎ አዲስ ምክር ቤት ስልጣን እስኪረከብ ድረስ ነባሩ ምክር ቤት ይቀጥላል? ለሚለው ጥያቄ ግልፅ መልስ የለውም - ህገ መንግስታችን። እናም ይህ ሁኔታ ትርጉም ያስፈልገዋል ይላሉ የህግ ባለሙያዎች።
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ሕገ መንግስቱ፣ ሀገር ያለ መንግሥት ለአንዲት ደቂቃ እንኳን እንድትቆይ እንደማይፈቅድ መገንዘብ ይቻላል። “የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚመረጠው ለ5 ዓመታት ነው” የሚለው አንቀጽ የተቀመጠው “የሥልጣን ዘመንን ለመገደብ” ነው እንጂ በተለያየ ምክንያት ምርጫ በሰዓቱ ሳይደረግ የቀረ እንደሆነ፤ “አዲሱ ምክር ቤት እስኪመረጥ ድረስ ነባሩ ምክር ቤት እንደፈረሰ እንዲቆጠርና አገሪቱም መንግሥት አልባ እንድትሆን ለማድረግ” ሊሆን አይችልም። በመሆኑም “በሀገሪቱ አዲስ ምርጫ ተደርጎ፣ አዲሶቹ ተወካዮች ሥራ እስኪጀምሩ ድረስ ነባሩ ምክር ቤት ከመስከረም ወር 2013 ዓ.ም የመጨረሻዋ ሰኞ በኋላም ቢሆን የመሥራት ሥልጣን ብቻ ሳይሆን ግዴታ አለበት” የሚል እምነታቸውን ይገልጻሉ የህግ ባለሙያዎች። ምክንያቱም “ነባሩ ምክር ቤት ህዝብ የሰጠውን ስልጣን ለማን አስረክቦ ነው የሚበተነው!? ምናልባት አርቃቂዎቹ ይህንን ነጥብ በግልፅ ያላነሱት መልሱ ግልፅ ስለሆነ ነው ብሎ መውሰድም ይቻላል” በማለት ይከራከራሉ - የህግ ባለሙያዎቹ።
በእኛ ሀገር ህገ መንግስት መሰረት፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስልጣን የሚያበቃው በሁለት ዓይነት መንገድ መሆኑን የህግ ባለሙያዎች ያስረዳሉ። ይኸውም፡- አንደኛው በመበተን ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በምርጫ በመተካት ነው። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚበተነው በአንቀጽ 60 መሰረት ነው። ይህም የሚሆነው አንድም አብላጫ ወንበር የያዙት ፓርቲዎች ጥምረታቸው ፈርሶ አብላጫ መቀመጫ መያዝ ያቃታቸው እንደሆነ፤ አሊያም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምክር ቤቱን አስፈቅዶ ራሱን ምክር ቤቱን የበተነው እንደሆነ ነው። ከዚህ ውጪ “የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በምርጫ አማካይነት በሌላ ምክር ቤት ይተካል እንጂ፤ ‘የስልጣን ዘመኑ አብቅቷል’ ተብሎ የሚበተን ስለመሆኑ በህገ መንግስቱ ላይ አልተደነገገም” የሚል መከራከሪያ ያቀርባሉ የህግ ባለሙያዎች። በሌላ አባባል፤ “የስልጣን ዘመን ማብቃት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን የመበተኛ ምክንያት ሆኖ አልተቀመጠም ማለት ነው። ስለዚህ የምክር ቤቱ የሥራ ዘመን ቢጠናቀቅም ምርጫ ተደርጎ የተመረጠው አዲስ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስልጣን እስከሚረከብ ድረስ ነባሩ ምክር ቤት ሥራውን መሥራት እንጂ አገሪቱን ምክር ቤት አልባና መንግሥት የለሽ አድርጎ መበተን አይገባውም፡፡ ይህንን ለማድረግ ህግ ብቻ ሳይሆን ሞራልም ሎጂክም አይፈቅድም” የሚል አስተያየት ይጨምራሉ - የህግ ባለሙያዎች።
የህወሓት መግለጫ ሁለተኛ ነጥብ ደግሞ በሀገሪቱ ህግ መሰረት የተቋቋመውን ምርጫ ቦርድ፤ “ነፃና ግልፅ ምርጫ የመምራት ምንም ዓይነት ሞራላዊ ብቃት የሌለው” በማለት ይወርፈዋል፡፡ ይህ ቦርድ እኮ ሰዎቹ ተቀየሩ እንጂ አምስት ምርጫዎችን በማስፈጸም ህወሓትን ለስልጣን ያበቃ አካል ነው፡፡ ዛሬ ምን ተፈጠረና ነው ቦርዱ እንዲህ የሚወገዘው? በሌላ በኩል፤ ቦርዱን ማውገዝ ከዚህ በፊት ቦርዱ ያከናወናቸውን ምርጫዎች እውቅና መንፈግ አይሆንም? ከዚሁ ጋር በማያያዝ ህወሓት “የሃገርን ሉዓላዊነትና ሰላም ለማስከበር በቂ ትኩረት በሰጠ መልኩ ምርጫውን ለማከናወን የሚያስችል ዝግጅት ይጀመር” በማለት የሰነዘረቺው ሃሳብ ደግሞ የሚገርም ነው:: አሁን ሀገሪቱ በወረርሺኝ ውስጥ ሆና፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በታወጀበት ሁኔታ፣ ህዝብ እንቅስቃሴው ተገትቶ ከቤቱ እንዳይወጣ ተከልክሎ እያለ፣ አትጨባበጡ፣ ተራራቁ ተብሎ ጧት ማታ በሚመከርበት ሁኔታ “ምርጫውን ለማከናወን የሚያስችል ዝግጅት” እንዴት ማድረግ ይቻላል? የመራጮችና የእጩዎች ምዝገባ፣ የምርጫ ቅስቀሳስ፣… እንዴት ማከናወን ይቻላል? ወይስ ህወሓቶች ውድድር የሌለው የምርጫ ድራማ ለማድረግ ነው የሚያስቡት? ይህ አባባላቸው ህወሓቶች ግራ መጋባታቸውን ከማረጋገጥ ውጪ ትርጉም ያለው ሆኖ አልታየኝም፡፡
ሦስተኛውን ነጥብ እንይ … “ብልፅግና ከመስከረም 25 በኋላ በሥልጣን ላይ ለመቆየት የሚያስችለው ዕድል የማይኖር በመሆኑ ሀገሪቱ ለመፍታት ወደሚከብድ ችግር የምትገባበት ዕድል መፈጠሩ የማይቀር ይሆናል፡፡ … [ስለሆነም] ክልላዊ ምርጫን… በትግራይ ክልል ደረጃ ለማድረግ ዝግጅት እንዲደረግ ወስነናል” ይላል የህወሓት መግለጫ፡፡ ህወሓቶች በአንድ በኩል፤ “ህገ መንግስታዊ ስርዓት መፍረስ የለበትም” በማለት ተገቢ ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ ብዙም ርቀት ሳይሄዱ ራሳቸው ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ፍርስርሱን የሚያወጣ ሃሳብ ሲያቀርቡ ይታያሉ፡፡ “በትግራይ ምርጫ እናካሂዳለን” ለማለት የደፈሩት በየትኛው ህገ መንግስታዊ አግባብ ነው? ምርጫ ቦርድ የማያውቀው ምርጫ ማካሄድስ ይቻላል? በክልል ደረጃ ምርጫ ቦርድ ማቋቋም የሚቻለውስ በየትኛው የህግ አግባብ ነው?
“የተወካዮች ምክር ቤት እና የፌደሬሽን ምክር ቤት አባላት ህልውናችሁን ያረጋገጠውን ህገ-መንግስታዊ ሥርዓት በጠራራ ፀሃይ ለማፍረስ የሚደረገውን እኩይ ተግባር በማስቆም ከታሪክ ተጠያቂነት ራሳችሁን አርቁ” የሚለውን የህወሓትን “አንዛኝ ቅቤ አንጓች” የሆነ፣ ፍሬ-ቢስ፣ መርህ አልባ ጥሪ እንለፈውና የመግለጫውን አምስተኛ (የመጨረሻ) ነጥብ እንቃኝ… እንዲህ ይላል፡- “በመጨረሻም ህወሓትም ሆነ የትግራይ ህዝብ ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓታችን ያረጋገጠውን ሕብረ ብሄራዊ ፌዴራላዊ ሥርዓት ለማዳን በሚደረገው ርብርብ፣ መሰል አጀንዳ ከሚያራምዱ ብሄር ብሄረሰቦችም ሆነ የፖለቲካ ሃይሎች ጋር ለመታገል ዝግጁ መሆናችንን ማረጋገጥ እንፈልጋለን” ይላል የህወሓት መግለጫ፡፡ ለመሆኑ ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓቱን አደጋ የጋረጠበት ማን ሆነና ነው ህወሓት “የህገ መንግስት ዋርድያ” ለመሆን ያሰበቺው? ነገሩ አስቂኝ ከመሆኑም በላይ አንድ ነገር አስታወሰኝ፡፡ የመርካቶ ጮሌ ዘንጋ ካለ ሰው ላይ አንዳች ነገር ሲመነትፍ ከተነቃበት “ሌባ ሌባ! ያዘው ያዘው!...” እያለ ራሱ አባራሪ፣ ራሱ ተባራሪ ሆኖ ይሮጣል፡፡ ህወሓትም እንደ መርካቶው ጮሌ እያደረገች መሆኑን ሳስብ ሳቄ ይመጣል…
የህወሓት የሰሞኑ መግለጫ በጥቅሉ ሲታይ፤ የተሸናፊነት ስነ ልቦና የወለደው እንጂ በተረጋጋ መንፈስ ታስቦበት የተጻፈ አይመስልም፡፡ ለዚህም ነው የጽሁፌን ርእስ “ህወሓት ሆይ፤ በዴሞክራሲ ሂደት መሸነፍ የዓለም መጨረሻ አይደለም” ያልኩት፡፡ እንደኔ እንደኔ፤ መሸነፍን የዓለም መጨረሻ የሚያደርገው ከተሸነፉ በኋላ ጓዝን ጠቅልሎ በአንድ ከተማ መመሸግና ክፉ ክፉ ነገር እያሰቡ በውስኪና በአረቄ መቆዘም ነው:: በዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሂደት መሸነፍም ሆነ ማሸነፍ የተለመዱ ውጤቶች ናቸው:: እናም ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ያላቸው፣ እምነትና ተጨባጭ እንቅስቃሴያቸውን በዚያ ስነ ልቦና ላይ ያዋቀሩ ግለሰቦችም ሆኑ የፖለቲካ ኃይሎች፤ በዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሂደት የሚያገኙትን ውጤት በፀጋ ከመቀበል ውጪ አንገታቸውን ደፍተው አያለቅሱም፤ አሊያም አየር ላይ እየተንሳፈፉ ጮቤ አይረግጡም፡፡
የህወሃትን መግለጫ እዚህ ላይ እናቁምና ከህሓት ጋር ተያያዥነት ያላቸው ሃሳቦችን እናንሳ፡፡ በቅድሚያ በፓርላማ ቆይታዬና የኢዴፓ ከፍተኛ አመራር አባል በነበርኩበት ጊዜ ያስተዋልኳቸውን ሁኔታዎች አሁን ህወሃት እያራመደቺው ካለው ሁኔታ ጋር በማነጻጸር ላቅርብ… በአሁኑ ወቅት ህወሓት ከምታሰማቸው “ጩኸቶች” አንዱ፤ “ገዢው ብልጽግና ፓርቲ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ብቻውን መወሰኑን ያቁም” የሚል መንፈስ አለው፡፡
ህወሓት መራሹ ኢህአዴግ በ27 ዓመታት የስልጣን ዘመኑ፤ (ህዝብንም ሆነ የትኛውንም ተቃዋሚ ፓርቲ ሳያማክርና ሳያሳትፍ) ቁልፍ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሀገርና ህዝብን የሚጎዱ፣ ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ውሳኔዎችን ያሳልፍ ነበር፡፡ ያኔ በተቃዋሚው ጎራ ጩኸት ይበረክታል፡፡ የተለያየ መግለጫ ይወጣል:: ተቃዋሚዎች “ድምጻችንን ስሙ፣ በጋራ ተመካክረን እንወስን…” በማለት ይጮሃሉ:: ጋዜጦች ጩኸቱን በማስተጋባት ወደ ህዝቡ ያደርሳሉ:: ህወሓት መራሹ ኢህአዴግ ግን እንኳን ሰምቶ የእርምት እርምጃ ሊወስድ ጩኸቱን ከቁም ነገር አይቆጥረውም፣ መልስም አይሰጥም ነበር::  በዚህ ዓይነት ሁኔታ ለምሣሌ እንደ የአልጀርስ ስምምነት ዓይነት የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ጥቅም አሳልፈው የሰጡ ውሳኔዎች ተወስነዋል፡፡ ዛሬ ህወሃት ተቃዋሚ ፓርቲ ሆና፣ ገዢው ፓርቲን በመክሰስና በመውቀስ፤ የተቃውሞ መግለጫ ማውጣቷን ሳይ የታሪክ ስላቅ ያስደምመኛ፡፡ ያኔ ያላስቀመጡት አሰራር ዛሬ ከየት ይምጣ!? ያኔ ለተቃዋሚዎቻቸው ያልሰጡት እድል እንዲሰጣቸው መጠየቅስ ለአንድ ጉዳይ ሁለት መለኪያ መጠቀም (Double Standard) አይሆንም? - ወደ ኅሊናችሁ ተመለሱ እንጂ ብጽዖት!
ፓርላማ እያለሁ ያየሁትን ተመሳሳይ ሁኔታ ልጨምር፡፡ በወቅቱ በፓርላማው ተቃዋሚዎች 180 ገደማ መቀመጫ ነበረን:: ነገር ግን ህወሓት ሁሉንም ነገር በአብላጫ ድምፅ ውድቅ ስለምታደርገው አጀንዳ እንኳ ማስያዝ አንችልም ነበር፡፡ እነሱ በሚያቀርቡት አጀንዳ ላይ እንጮሃለን፤ ህወሓት በሩን ሁሉ ስለምትጠረቅመው ሰሚ አልነበረም:: አማራጭ ሃሳቦች ይቀርባሉ፣ ጥቅምና ጉዳታቸው ሳይታይ በደፈናው በድምፅ ውድቅ ይደረጋሉ:: “እባካችሁ ድምጻችን ይሰማ” ስንላቸው “በዴሞክራሲያዊ አግባብ በአብላጫ ድምፅ የተወሰነውን ተቀበሉ” ይሉን ነበር:: ዛሬ ነገሩ ሁሉ የተገላቢጦሽ ሆነና፣ ህወሓት በዴሞክራሲያዊ አግባብ በአብላጫ ድምፅ የተወሰነውን መቀበል አቅቷት፣ ብዙዎችን ባስለቀሰቺበት የፓርላማ መድረክ፣ የለቅሶ ሂሳብ እያወራረደች ነው፡፡ “ቦ ጊዜ ለኩሉ!” አለ ጠቢቡ ሰለሞን! ጊዜ መስተዋት ነው - ሁሉንም እያሳየን ነው፡፡
ሌላ ጉዳይ ላንሳ… የትግራይ ፖለቲካ የሀገራችን ፖለቲካ የስህበት ማዕከል መሆኑን ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ በዚህም ምክንያት በሃያ ሰባቱ የኢህአዴግ/ህወሓት አስተዳደር፣ ህወሓት የሴራው ማእከል ሆና አገልግላለች:: ዶ/ር ገቢይ እንደ ኢትዮጵያ መሪ ጠንካራ አቋም ይዘው፣ ደፈር ያለ እርምጃ ባለመውሰዳቸው፣ መነቀል የሚገባው የሴራ አረም፣ ዛሬም በትግራይ ክልል ህይወት ዘርቶ በስፋት በቅሏል፡፡ አእምሯቸው መልካም ነገርን ማፍለቅ የማይችሉ ሴረኞች፣ 27 ዓመታት በሰሩት እኩይ ተግባር ሳይጸጸ፣ ዛሬም መቀሌ ከትመው ሴራ መጎንጎናቸውን ገፍተውበታል፡፡ በያዙት ሚዲያ ልማትና እድገትን፣ ፍቅርና አንድነትን ሳይሆን መርዘኛ አፍራሽ ፕሮፓጋንዳ ቀምመው መርጨት የእለት ተእለት ተግባራቸው ሆኗል፡፡ “ለመስራት ያልታደለ አእምሮ ለማፍረስ ተወዳዳሪ የለውም” እንዲሉ መቀሌ የመሸገው ኃይል ሀገር የመረበሽ አቅም እንዳለው የብዙዎች ግምት ነው፡፡
ሰሞኑን ህወሓት የሰጠቺውን ግትርነት የተሞላበት “የራሴን ክልላዊ ምርጫ አካሂዳለሁ” የሚል ኢ-ህገ መንግስታዊ መግለጫ፣ በርካታ የክልሉ ተወላጆችና የፖለቲካ ፓርቲዎች እያወገዙት ይገኛል፡፡ እዚህ ላይ አንድ ጥያቄ ለማንሳት ወደድሁ:: ጥያቄው “ህወሓትን በትግራይ ክልል ምርጫ አደርጋለሁ እንዲል ያስገደደው ነገር ምንድን ነው?” የሚል ነው። ተጨማሪ ጥያቄዎችንም ማስከተል ይቻላል:: እውነት የህጋዊነት መርህና ታማኝነት ነው ወይስ በክልሉ ያሉ ፓርቲዎች ከመስከረም በኋላ ህወሓት ክልሉን መምራት አትችልም ስላሉ? ወይስ ኮሮናን በክልሉ መቆጣጠር በመቻሉ ምርጫን ለማከናወን የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል? መልሱን ለህወሓት መተውን እመርጣለሁ፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት እንዲሰጠኝ የጠየቅኩት አንድ የትግራይ ክልል ተወላጅ የረዥም ዓመታት ወዳጄ፤ “ዛሬ ትግራይ ውስጥ እየተሸረበ ያለው ፀረ- ኢትዮጵያ ሴራ የሁሉም የህወሓት አባላት ፍላጎት አይመስለኝም፡፡ ከህወሓት አባላት ይልቅ ጀርባዋ ላይ የታዘሉት ይበልጥ ተደራጅተዋል:: ሚድያ፣ ገንዘብና የማይታይ አደረጃጀት አላቸው፡፡ ህዝቡን ብቻ ሳይሆን ህወሓትን ራሷን ለመሸበብ እንደቻሉ እያታዘብን ነው፡፡ እነዚህ ኃይሎች “ፀረ-አንድነት እና ፀረ-ኢትዮጵያዊነት” የሆነ ያረጀ፣ ያፈጀና የተሳሳተ አጀንዳን “አጀንዳቸው” አድርገው እየገፉበት ይመስላል፡፡ ይህ ከንቱ “የተገንጣይነት” አጀንዳ የሚያጋጫቸው ለሀገረ ኢትዮጵያ መፈጠር ምክንያት ከሆነው፤ ሀገራችንን ከውጪ ወራሪ ለመከላከል ውድ ህይወቱን ሲገብር ከኖረው የትግራይ ህዝብ ጋር ብቻ ሳይሆን ሀገራቸዉን ከሚወዱ የህወሓት ዓባላትም ጭምር ነው፡፡ እነዚህ ኃይሎች ቀዩን መስመር እያለፉ ነው:: ባሩድ እየሸተታቸው ነው፡፡ በእነሱ ፉከራ ቀጣዩ ምእራፍ የደምና የህይወት ጨዋታ ነው፡፡ ለነሱ የስልጣንና የጥቅም ቀጣይነት የሀገራችን ሁኔታ አደጋ ላይ መውደቅ የለበትም፡፡ የትግራይ ህዝብ ይህንን ጉዳይ ስለማይታገስ ግጭቱ የሚጀምረው ትግራይ ላይ ይሆናል፡፡ በትግራይ ግጭት የሚነሳ ከሆነ ደግሞ ግጭቱ የሚሆነው በቅድሚያ በክልሉ ተወላጆች መካከል ነው:: ማንም ኢትዮጵያን የሚወድና ለሀገሩ ቀናዒ የሆነ ዜጋ ትግራይ ውስጥ ህይወት እንዲጠፋ የሚመኝ ይኖራል ተብሎ ኣይገመትም፡፡ እዉነተኛ ኢትዮጵያዊ የሆኑ የህወሓት ዓባላት፣ በዚህ ወቅት ደግመው ደጋግመው በጽሞና ሊያስቡ ይገባል፡፡ የድርጅታቸውን አመራር መግራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ያዘሏቸውን ማራገፍ  ይኖርባቸዋል፡፡ የህወሓት ከፍተኛ አመራርና በጀርባዋ የታዘሉ ሃይሎች የሚያራምዱት ፖለቲካ፣ እውነተኛ ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ እንዳይወለድ ጋሬጣ ሆኗል” በማለት በኀዘንና በስጋት የተሞላ ምላሽ ሰጥቶኛል፡፡
የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ አባል የነበሩት ታጋይ ሴኩቱሬ ጌታቸው በበኩላቸው፣ ለትግራይ ሚዲያ ሃውስ (TMH) በሰጡት ቃለ ምልልስ ከላይ የተጠቀሰውን ሃሳብ የሚያጠናክር አስተያየት ሰንዝረዋል፡- “የትግራይ ሕዝብ ከማዕከል የሚደርስበት ተጽእኖ ተፈቷል ብሎ ሲያምን፣ ፊቱን ወደ ራሱ አመራር ማዞሩ አይቀርም” ብለዋል - ታጋይ ሴኮ፡፡ የትግራይ ሕዝብ ጥያቄ፣ አንዳንዶች መጠቀሚያ እያደረጉት እንዳለው መገንጠል ሳይሆን እንደ ማንኛዉም ኢትዮጵያዊ በእኩልነት ተከባብሮ መኖር እንደሆነ ግልጽ ነው። ከታጋይ ሴኮ ቃለ ምልልስ የምንረዳው ሌላው ቁም ነገር፤ የትግራይ ሕዝብ የሕወሃትን አንዳንድ አመራሮች አቋም ከወዲሁ መታገል ካልጀመረ በስተቀር በቀጣይ የሚያጠራው ትልቅ የቤት ስራ የሚጠብቀው መሆኑን ነው።
በመጨረሻም ማጠቃለያ ትሆን ዘንድ አንዲት የመውጫ ነጥብ ልጨምር:: ይህቺን ማስታወሻ በማዘጋጅበት ወቅት ያሰባሰብኳቸው መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ በአሁኑ ወቅት ሃምሳ የሚሆኑ ሀገሮች፣ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ምርጫ ማካሄድ ባለመቻላቸው፣ የምርጫ ጊዜያቸውን እንዳራዘሙ ይነገራል:: ኢትዮጵያ የዓለም አካል በመሆኗ ምርጫ ማራዘሟ የተለየ ተዓምራዊ ነገር ተደርጎ መታየት የለበትም፡፡ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው የህዝቡ ህልውናና የሀገሪቱ ቀጣይነት ነው:: በመሆኑም… ህወሓት/ኢህኣዴግ ለ27 ዓመታት በዘረጋቺው የጥርነፋና የግምገማ መረብ ተተብትቦ መስራት የሚገባውን ባለመስራቱ፣ ሲወቀስ የኖረውና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ የህወሓት ተወካዮች ተገቢም ተገቢ የማይመስሉም ሃሳቦችን በማንሳት ጩኸት የሚያሰሙበት የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት፤ “ህገ መንግስታዊ ትርጉም ያስፈልጋል” በሚለው ጉዳይ ላይ ተወያይቶ በአብላጫ ድምፅ ታሪካዊ ውሳኔ ወስኗል፡፡ እንደ ፖለቲካ ኃይል፣ የህወሓት ኃላፊነት ለብዙሃኑ ድምፅ ተገዢ በመሆን፤ እንደ ሰለጠነ ፖለቲከኛ የምክር ቤቱን ውሳኔ በመፈጸምና በማስፈጸም፣ ሀገራችንን ከገባችበት አጣብቂኝ እንድትሻገር ማድረግ መሆኑን ህወሓቶች ልብ ሊሉት ይገባል፡፡
ጸሐፊውን Email: ahayder2000@gmail.Error! Hyperlink reference not valid. ማግኘት ይቻላል፡፡Read 6327 times