Saturday, 07 July 2012 11:22

“ያልተነገረለት የሐገር ባለውለታ” ነገ ይመረቃል

Written by  መልካሙ ተክሌ (melkamutekele@gmail.com)
Rate this item
(0 votes)

የቦክሰኛ በቀለ አለሙ (ጋንች) ሕይወት ዙሪያ የተፃፈው “ያልተነገረለት የሀገር ባለውለታ” መጽሐፍ ነገ ከቀኑ 8፡30 አትክልት ተራ አካባቢ በሚገኘው ሃይካን ሆቴል ይመረቃል፡፡ በወይዘሮ ይድነቃቸው አሰፋ የተዘጋጀው ባለ 243 ገጽ መጽሐፍ፤ ባለ ስድስት ክፍል ሲሆን ዋጋውም ለሐገር ውስጥ 40 ብር፣ ለውጭ ሀገራት 10 ዶላር ነው፡፡ ይህ በዚህ እንዳለ “ቁምነገር የጋዜጠኞች ማሠልጠኛ” ሦስተኛ ዙር ተማሪዎችን ትናንት አስመረቀ፡፡ ካዛንቺስ በሚገኘው የት/ቤቱ ቅጽር ግቢ የተረመቁት ተማሪዎች በመሠረታዊ የጋዜጠኝነት ጽንሰሀሳብ፣ የፕሬስ ሕግ፣ የዜናና አርቲክል አፃፃፍ፣ በሬዲዮና ቴሌቪዥን ፕሮዳክሽን፣ በቃለመጠይቅ (interview) ቴክኒክ እና ተያያዥ ጉዳዮች ለሦስት ወራት በተግባር የታገዘ ሥልጠና ወስደዋል፡፡

አንጋፋና ወጣት ጋዜጠኞችም ለተማሪዎቹ ልምድ ማጋራታቸውንና አራተኛ ዙር ሥልጠና ከአዲስ አበባ ወጣቶች ጋር በመተባበር በቅርቡ እንደሚጀመር ትምህርት ቤቱ ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡ በሌላም በኩል የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር ጐንደር ከተማ ቅርንጫፍ መስራችና ሰብሳቢ የሆኑት ኤልያስ መንግስቱ ያዘጋጁት “የማይናወጥ ድምጽ” የግጥም መድበል ትናንት ምሽት በጐንደር ቋራ ሆቴል ተመረቀ፡፡ የጐንደር ዩኒቨርሲቲ የዘንድሮ የሳይኮሎጂ ምሩቅ የሆኑት ገጣሚው፤ ካሁን ቀደም “ሃጉረንደር” የሚል የግጥም መድበል አስመርቀዋል፡፡ 68 ገፆች ያሉት “የማይናወጥ ድምጽ” በ15 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡

 

 

 

Read 895 times Last modified on Saturday, 07 July 2012 11:27