Monday, 11 May 2020 00:00

አሁን የገጠመን የሕገ መንግሥት ቀውስ ሳይሆን የወረርሽኝ ቀውስ ነው››

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

    የሽግግር መንግስት ጥያቄ አገር የማጥፋት ዘመቻ ነው

         ቀጣይ ምርጫ የሚካሄድበት ሁኔታ የሕገ መንግሥት ትርጉም ይሰጥበት ሲል የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ወስኗል፡፡ የተለያዩ የፖለቲካ ሃይሎችም በዚህና ተያያዥ ጉዳዮች በተለያዩ አግባቦች ውይይቶች ክርክሮች እያካሄዱ ይገኛሉ፡፡ የሽግግር መንግሥት የሚል ሀሳብም በስፋት እየቀረበ ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ የመፍትሄ
ሀሳቦች እንዴት ሊታረቁ ይችላሉ? በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ አንጋፋው ፖለቲከኛ አቶ አስራት ጣሴ የራሳቸውን ምልከታና ምክረ ሀሳብ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ባደረጉት ተከታዩ ቆይታ ያጋራሉ፡፡


          አንዳንዶች የሕገ መንግሥት ቀውስ አጋጥሞናል የአገሪቱ እጣ ፈንታም አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል ሲሉ ይደመጣል እርስዎ ይሄን እንዴት ይመለከቱታል?
እኔ የሕገ መንግሥት ቀውስ አጋጥሞናል፤ አጣብቂኝ ውስጥ ገብተናል ብዬ አላምንም:: የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በዓለም ያልተጠበቀ፣ አዲስ ቫይረስ ነው፡፡ ይሄ ቫይረስ ደግሞ በባህሪው የሕዝብን መሰባሰብና መቀራረብ ይከለክላል፡፡ ርቀትን መጠበቅ ዋነኛ የመታገያ መሳሪያ ነው፡፡ ስለዚህ ሕዝብን በሰፊ ሁኔታ ሰብስቦ በአንድ ጉዳይ ላይ መምከር አይፈቅድም ማለት ነው፡፡ ምርጫ ደግሞ የሰዎች መሰባሰብን አደባባይ መውጣትን የሚጠይቅ ነው፡፡ ከመራጮች ምዝገባ ጀምሮ  ምርጫ አስፈፃሚዎችን ማሰልጠን ከመሳሰሉት ጀምሮ እስከ ቅስቀሳና ድምፅ  መስጠት ያሉ ሂደቶች በሙሉ የሕዝብ መሰባሰብን የሚጠይቁ ናቸው፡፡ ኮሮና ደግሞ የእነዚህ ሁሉ ድርጊቶች ተቃራኒ ነው:: ስለዚህ አሁን የገጠመን የሕገ መንግሥት ቀውስ ሳይሆን የወረርሽኝ ቀውስ ነው። መንግሥት ሆን ብሎ በስልጣን ላይ ለመቆየት አስቦ ወረርሽኙን አልፈጠረውም:: ጉዳዩ አለማቀፍ የሆነ ቀውስ ነው፡፡ አለምን አጣብቂኝ ውስጥ የከተተ ወረርሽኝ ነው። አንዳንድ ሰዎች የሚናገሩትን ስሰማ በጣም ነው የማዝነው፡፡ ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት፣ ኮሮናን ሽፋን በማድረግ ሥልጣኑን ለማራዘም እየሞከረ ነው ይላሉ:: እንደው አዕምሮ ያለው ሰው በአሁኑ ጊዜ ከ250 ሺህ በላይ ሰዎችን የገደለ፣ ከ3.5 ሚሊዮን በላይ ሕዝብን የመረዘ በሽታን እንዴት ሽፋን ነው ይላል? በጣም ነውረኝነት ነው፡፡ ይሄ የወረርሽኝ ቀውስ በኢትዮጵያ ላይ ብቻ የመጣ ሳይሆን የአለም ሀያላን አገራትንም የፈተነ ነው፡፡ በብዙ አገሮች ምርጫዎች፣ ሕዝበ ውሳኔዎች የተሰረዙበት ሁኔታን አስከትሏል፡፡ ታዲያ ኢትዮጵያ ጋ ሲደርስ እንዴት ጉዳዩ የሕገ መንግሥት ቀውስ የሚል ትርጉም ይሰጠዋል፡፡
የሽግግር መንግሥት እንዲመሰረት ጥያቄ የሚያቀርቡ ወገኖች አሉ ይሄን ሃሳብ እንዴት ይመለከቱታል?
የእነዚህን የሽግግር መንግስት ጠያቂዎች ማንነት ለይቼ ስለማውቅ፣ ይሄ የሽግግር መንግሥት ጥያቄ ለኢትዮጵያ ኮቪድ 19 ከሚያመጣው ቀውስ የጎላና የገዘፈ ችግር የሚያመጣ አደገኛ ጨዋታ መሆኑን እገነዘባለሁ፡፡ እነዚህ የሽግግር መንግሥት ጠያቂዎች በአንድ በኩል “ሕገ መንግሥት ይከበር” ይላሉ፡፡ ታዲያ ሕገ መንግሥቱ “የሽግግር መንግሥት ይመሰረታል” የሚል ድንጋጌ አለው እንዴ? የለውም፡፡ ነገር ግን በአንጻሩ፤ የሕገ መንግሥት ትርጓሜ የሚጠየቅበት አግባብ በሕገ መንግሥቱ አለ፡፡ ታዲያ ለምን እነዚህ ሀይሎች የተለየ ጩኸት ያሰማሉ ከተባለ፣ ቀጥተኛ አላማቸው ሥልጣንና ሥልጣን ብቻ ስለሆነ ነው፡፡ እነዚህ ሀይሎች ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላም አንድነትና መረጋጋት የሚያስቡ አይደሉም:: በፀዳ አዕምሮ ራሳችንን ስንፈትሽ የሽግግር መንግሥት በኢትዮጵያ ባለው ሁኔታ ፍፁም የጥፋት ዘመቻ ነው፡፡ ለኔ በአሁን ሰዓት የሚጠየቀው የሽግግር መንግሥት የአገር ማጥፋት ዘመቻ ነው፡፡ እንዴት ነው የሽግግር መንግሥት የሚቋቋመው? እነማን ናቸው ተሰባስበው የሚያቋቁሙት? አሁን ሰሞኑን አዳዲስ ቋንቋ እሰማለሁ፡፡ “ምርጫ ቦርድ ያስቀመጠውን መስፈርት የምናሟላ ሰርተፊኬት ያለን” ሲባል እሰማለሁ፡፡ ምርጫ ቦርድ ያስቀመጠውን መስፈርት ማሟላት ማለት፣ የሽግግር መንግሥት ለማቋቋም የእውቅና ሰርተፊኬት (ላይሰንስ) ሊሆን አይችልም፡፡ በሕዝብ ፊት ቀርቦ ፕሮግራምን አስረድቶ፣ በሕዝብ ለመመረጥ የሚቻልበትን ፈቃድ ነው የሚሰጠው እንጂ የሽግግር መንግሥት፣ ማቋቋሚያ ፍቃድ አይደለም፡፡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በጎ የሚያስቡ፣ ለራሳቸውም በጎ የሚያስቡ ሰዎች በዚህ ወቅት ይሄን አይነቱን ግራ የተጋባ ጥያቄ መጠየቅና ሕዝብን ማወናበድ የለባቸውም፡፡ በአንድና አንድ መንገድ ብቻ ነው ወደ ሥልጣን መመጣት ያለበት፡፡ በነፃ ፍትሃዊና ተአማኒነት ባለው ምርጫ ብቻ
ምርጫን ማራዘም የሚቻልበት ሁኔታ በሕገ መንግሥቱ አልተቀመጠም፤ ስለዚህ መፍትሄው ፖለቲካዊ መሆን አለበት፡፡ የፖለቲካ መፍትሄ ሆኖ የሽግግር መንግሥት ነው እየተቀነቀነ ያለው፡፡  እርስዎ ደግሞ የሽግግር መንግሥት ትርፉ ቀውስ ነው ብለዋል፡፡ ምን ይሻላል?
በመጀመሪያ ደረጃ ይሄን ሕገ መንግሥት እንፈትሽው ብንል፣ እኔም ብሆን  የኢትዮጵያ ሕዝብን የሚወክል ሕገ መንግሥት አድርጌ አላየውም፡፡ እራሴ ሕገ መንግሥቱን አልቀበለውም፡፡ ግን በግድ ስለተጫነብን ጊዜው ደርሶ እስከሚሻሻል እያልን ስንገዛበት ኖረናል፡፡ ነገር ግን አሁን ስለ ሕገ መንግሥት መጣስ የሚናገሩ ሰዎች ራሳቸው፣ ሕገ መንግሥቱን አክብረው የማያውቁ ናቸው። ሕወኃት 27 ዓመት ሙሉ ሕገ መንግሥቱን አክብሮ አያውቅም፡፡ አሁን ሁላችንም ጤናማ የሆነ ህሊናችንን እንጠቀምና ሕገ መንግሥቱ በሕገ መንግሥታዊ መንገድ ይለወጥ የሚለውን ሐሳብ አክብረን ማየት አለብን፡፡ እኔ ይሄን ሀሳብ በሚገባ አክብጄ አየዋለሁ፡፡ ሆኖም ግን የሽግግር መንግሥት በዚህን ወቅት ማሰብ፣ ይሄ በሕገ መንግሥታዊ መንገድ እንዲሻሻል እንዲለወጥ የሚፈለገውን አካሄድ ማበላሸት ነው፡፡ ትርፉ ቀውስ መፍጠር ነው የምለው ከዚህ መነሻ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ለረዥም ጊዜ ኖሬያለሁ በሕይወት ዘመኔ ከኢዴፓ እስከ ቅንጅት በኋላም ከአንድነት እስከ መድረክ ድረስ ለሁለት አስርት ዓመታት ገደማ በሃላፊነት ጭምር ሰርቻለሁ፡፡  የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ባህሪ ጠንቅቄ እረዳለሁ፡፡ በዚህ ታሪካቸው ውስጥ አንድም ጊዜ መግባባትና አገራዊ ስምምነት ላይ ደርሰው አያውቁም:: መድረክ ገብተን ስንወጣ፣ ቅንጅት ሲፈርስ፣ ሌላውም ሲፈርስ ነው የማውቀው:: የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሕይወት ውስጥ ያሉ ሰዎች ራሳቸውን መጠየቅ ያለባቸው “መጀመሪያ መቼ ነው አገራዊ መግባባት ተሞክሮ የሚያውቀው?” የሚለውን ነው:: እኔ ይሄ አገራዊ መግባባት የታየበትን አንድም ወቅት አላውቅም፡፡ ሁላችንም ተቀምጠን ተወያይተን፣ በአንድ አገራዊ ጉዳይ ላይ እንኳ በአግባቡ የተስማማንበትን ጊዜ አላስታውስም፡፡ ስለዚህ ዛሬ የሽግግር መንግሥት ሲባል እነዚህን ሁሉ ባላየ አይቶ የሥልጣን ጥያቄን ብቻ አንግቦ የተነሳ ነው፡፡ የሽግግር መንግሥት ጥያቄ፣ በአቋራጭ ወደ ፖለቲካ ሥልጣን ለመምጣት ያለመ ነው፡፡ ለዚያውም ተገቢ ስምምነት ላይ ሳይደረስ:: ከዚያም አገርን ለትርምስ የመዳረግ እቅድ ነው፡፡ በእኔ በኩል ወደ ሽግግር መንግሥት ሂደት የሚገባ ከሆነ፣ በጣም ነው የማዝነው ሀሳቡንም በጣም ነው የምጠላው፡፡ በማንኛውም ደረጃ ፊት ለፊት ወጥቼ የምቃወመው ሀሳብ ነው፡፡
በሌላ በኩል ህወሃት “በክልል ደረጃ ምርጫ አደርጋለሁ” እያለ ነው ይሄ አካሄድ ወዴት ያደርሰናል?
እያንዳንዱ ችግር በውስጡ የራሱ በጎ ነገር ሊኖረው ይችላል የሚባል አባባል አለ:: ይሄ ኮቪድ 19 ወረርሽኝ በዚያው ልክ በጎ ነገር ይዞ የመጣም ይመስላል:: በነበረውና ባልተረጋጋው የፖለቲካ ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ አንድ ክልል “የኔ ክልል ውስጥ አትገባም፤ ስብሰባ ማካሄድ አትችልም” እየተባለ በሚበተንበት ወቅት፣ የተለያዩ መፈናቀሎችና የአስተዳደር ችግሮች በነበሩበት ወቅት ጊዜውን ጠብቆ የሚካሄድ ቢሆን ኖሮ፣ ከባድ ቀውስና ውጣ ውረድ ነበር የሚከሰተው፡፡ ስለዚህ እንደውም ከመጥፎ አጋጣሚ መሃል በጎ ነገር ይወጣ ይሆናል የሚባለው ያጋጠመን ይመስለኛል:: እንደውም እዚህ አገር ብሄራዊ መግባባት ተፈጥሮ ጥሩና የተመሰከረለት ምርጫ ለማካሄድ እድል እየተመቻቸልን ሊሆን ይችላል፡፡ ሥልጣንን በሶስተኛና አራተኛ ደረጃ ነበር ማየት የሚገባን፡፡ ከራስ በላይ ንፈስ ቀርቶ፣ ከራስ በላይ አገርና ሕዝብ ነው ማለት የሚጠበቅብን፡፡ ይሄ ምርጫ በተሻለ መልኩ እንዲካሄድ ጊዜ መገኘቱ ለኔ በችግር ውስጥ የመጣ በጎ ነገር አድርጌ ነው የማየው:: በዚህ ረገድ ምርጫ ወይም ሞት ማለት በጣም አሳዛኝ ነው፡፡
እዚህ ጋ አንድ ነገር ባስታውስ ደስ ይለኛል፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 103 ላይ፤ የሕዝብ ቆጠራ በየ10 ዓመቱ ይካሄዳል ይላል፡፡ ከዚህ ውጪ የሚያቀርበው አማራጭ የለውም፡፡ ነገር ግን በ1997 ዓ.ም በምርጫ ምክንያት ምርጫና ሕዝብ ቆጠራ አንድ ላይ ሊካሄድ አይችልም በሚል ሰበብ እኮ ሳይካሄድ ተዘልሏል፡፡ ይሄን የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌ ጥሰው የዘለሉ ሰዎች  ናቸው ዛሬ “ምርጫ በተቀመጠለት ጊዜ ካልተካሄደ ሞተን እንገኛለን” የሚሉት:: ስለ ሕገ መንግሥት መከበር እየጮሁ የሚነግሩን እኮ እነዚህ ሰዎች ናቸው፡፡ ህወኃት መቼ ነው ሕገ መንግሥቱን አክብሮ የሚያውቀው?! እንደፈለገው ሲረግጠውና ሲጥሰው አይደለም እንዴ የኖረው! ታዲያ ዛሬ አለማቀፍ ወረርሽኝ አገራችን አጣብቂኝ ውስጥ በከተተበት ወቅት “ምርጫና ሕዝብ ቆጠራ አብሮ አይሄድም” ያሉ አንደበቶች፤ “እንዴት የኮቪድ 19 ወረርሽኝና ምርጫ አብሮ መሄድ ይችላል” የሚል አንደበት አገኙ? ምን ፈልገው ነው በዚህ መጠን ነገሩን የሚያከሩት? ይሄ እኮ ለሕዝብ ደንታ ቢስነታቸውን ነው የሚያሳየው:: ሕዝብ ለእነሱ ለሥልጣን መወጣጫ ብቻ እንደሚጠቀሙበት ነው የሚያሳየው:: “ዛሬ ምርጫ ካልተካሄደ ሞቼ ልደር” የሚለው የክፉ ሰዎች የክፋታቸው መገለጫ ሆኖ ነው የሚታየኝ፡፡ ለአገርና ለሕዝብ ደንታ ቢስ የሆኑ ክፉ ሰዎች እንደሆኑ ነው የሚያመላክተኝ፡፡
ፓርላማው፤ የሕገ መንግሥት ትርጉም ይሰጥበት የሚለውን የውሳኔ ሀሳብ አጽድቋል፡፡ እርስዎ ይሄን ሀሳብ እንዴት ያዩታል? የትኛው አማራጭስ ነው የበለጠ ለገጠመው ችግር መፍትሄ የሚሆነው?
አሁን ለተፈጠረው ችግር የምክር ቤቱን ጊዜ ማራዘም አስፈላጊ ነው፡፡ ይሄ ሲሆን ምንም ችግር የሌለው፣ ሁነኛ አማራጭ ነው ማለት አይደለም፤ አሁን ካለው ችግር አንፃር ግን የተሻለው አማራጭ ነው፡፡ የምክር ቤቱን ዕድሜ በአንድ ዓመት ወይም በሁለት ዓመት ማራዘም ከሁሉም የተሻለ መፍትሄ ነው የሚሆነው፡፡ ምርጫውን እንደርስበታለን፤ የትም አይሄድብንም፡፡ የምክር ቤቱን ሥልጣን አራዝሞ፣ የተሻለ መረጋጋት ተፈጥሮ ጽንፈኝነት ቀዝቅዞ፣ ሕዝብ ወደ ጤናማና መደበኛ የሕይወት እንቅስቀሴ፣ ወደ መደበኛ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ተመልሶ፣ ትምህርት ቤቶች ተከፍተው፣ ፋብሪካዎች እንደገና በሙሉ ጉልበታቸው መስራት ጀምረው፣ ኢኮኖሚው ተነቃቅቶ፣ ሕዝቡ እንደ ልቡ መንቀሳቀስ ጀምሮ ተረጋግቶ፣ ምርጫን ትልቅ አጀንዳ አድርጎ፣ በማያዳግም ሁኔታ በኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ነፃ ፍትሃዊና ተዓማኒነት ያለው ምርጫ አካሂዶ፣ አለማቀፍ ተቀባይነታችን ያረጋገጠ፣ ቆንጆ ምርጫ ብናካሂድ ተመራጭ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ የሽግግር መንግሥት እየተባለ የሚደረግ ሩጫ አገር ላይ መቀለድ ነው፤ አያዋጣም፡፡
እርስዎ በብዙ የፖለቲካ ሂደቶች ውስጥ ያለፉ እንደመሆንዎ፣ ለመንግሥትም ለፖለቲከኞችም የሚያቀርቡት ምክር ምንድን ነው?
መንግሥት አሁን የኮቪድ 19 ወረርሽኝን  ጥሩ እንቅስቃሴ እያካሄደ ነው፡፡ ፍፁምነት ከማንም አይጠበቅም፡፡ እንኳን ሁለት ዓመት ስልጣን ላይ የቆየ መንግሥት ይቅርና ለረዥም ጊዜ  በሥልጣን ላይ የኖሩ መንግሥታት፣ ጉዳዩ ምን ያህል እንደ ከበዳቸው ጀርመኖችን፣ እንግሊዞችና ሌሎችን አገራትን ማየት ይቻላል፡፡ በዚያው ልክ መንግሥት አሁንም በየመሥሪያ ቤቱ፣ በሕዝብ ዘንድ የተፈጠሩ ሮሮዎችን እየተከታተለ መፍትሄ እያበጀ እንዲሄድ እመክራለሁ፡፡ ለዚህ የተለየ ዘዴ መተግበር አለበት፡፡ በተረፈ ግን በአለማቀፍ ደረጃም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ እያደረገ ያለውን ሁለንተናዊ ጥረት በአክብሮት ነው የማየው:: ለፖለቲካ ፓርቲዎች ያለኝ ጥሪ፤ “እባካችሁ እዚህ አገር ለፖለቲካ ፓርቲ መመስረት ከተቻለ ጀምሮ ኖረናል፤ የደርግንም ሆነ የህወኃት/ ኢህአዴግን ምርጫ አይተናል:: በኢትዮጵያ ውስጥ ምርጫ በህወኃት ኢህአዴግ የይስሙላ ምርጫ ነው የውሸት ዴሞክራሲ ነበር፤ በየአምስት አመቱ ትያትር ነበር የሰራነው፡፡ ይሄን ደግሞ በሚገባ ውስጡን የምናውቅ ነን፤ ስለዚህ አሁን የተፈጠረውን መልካም ዕድል ተጠቅመን ትዕግሥት አድርገን ከውሸት ምርጫ እንውጣና ሁኔታውን ተጠቅመን ወደ ህሊናችን ተመልሰን፣ እየተነጋገርን አገራዊ መግባባት እየፈጠርን ረጋ ብለን የምናደርገው ምርጫ እውነተኛ  ሕዝብንና አገርን የሚታደግ ይሆናል፡፡ እባካችሁ ቀስ ብሎ መሄድ ጥሩ አሸናፊ ያደርገናል፤ ዝም ብሎ በችኮላ ከሆነ ግን ታሪካችንን የበለጠ እናበላሻለን፡፡ ግለሰቦችም በተለይ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ለረጅም ጊዜ የማውቃቸው ሰዎች ተለውጠውብኛል፡፡
ምን ነካን? ምንድን ነው የሆንነው? ይሄ ራሱ ሌላ ቫይረስ እኮ ነው የሆነብን? ምን ቫይረስ ነው የነካን? እንረጋጋ እንጂ! ስለ ሕዝብ ስለ አገር እናስብ እንጂ! አደራ የምለው “እባካችሁ እንብሰል፣ እንረጋጋ ነው፡፡ ያ ሁሉ መልካም ቋንቋችሁ፣ መልካም አካሄዳችሁ፣ ኢትዮጵያዊነት የምንለውን አገራዊ ስሜትን ምን አድርገን ነው አሁን ከመሬት ተነስቶ መንግሥትን ማጠልሸትና ቆሻሻ በሌለበት ሁኔታ ቆሻሻ ፍለጋ መማሰን? ምን ነክቶን ነው? ቆሻሻ በነበረበት ጊዜ እኮ ብዙዎች ብቅ አላሉም፡፡
ወዳጄ አንዷለም የሚለው አንድ አባባል አለ፡- “በነብሩ አደን ጊዜ ማንም ወደ ጫካው አልመጣም፤ ነብሩ ከሞተ በኋላ ግን በነብሩ ቆዳ ላይ የመፎከር ባህሪ አለ ይላል:: ከዚህ ባህሪ ለምን አንወጣም? እባካችሁ ሥልጣን ሃላፊነት ነው፤ ተረጋግቶ ሰክኖ በስሎ የሚደረስበት፤ ትከሻን የሚያጎብጥ ሃላፊነት ነው፤ ዝም ብሎ የሚሮጥበት ተራ ጨዋታ አይደለም፡፡ እባካችሁ ተረጋግተን ለዚህች አገር የሚሆን፣ በጎና የተረጋጋ ምርጫ እናካሂድ፡፡ እናንተም ረጋ ስትሉ ኢትዮጵያን የበለጠ ነው የምታገለግሏት:: ከዚህ በላይም በትውልድ የሚያስከብር አገልግሎት አይኖርም፡፡ እባካችሁ ተረጋጉ ስል ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡


Read 2588 times