Saturday, 09 May 2020 12:44

ልደቱና ጃዋር - “ተመሳሳይ ላባ ያላቸው ወፎች”

Written by  (ኩርኩራ ዋፎ - ከለገጣፎ)
Rate this item
(4 votes)

  ቅዳሜ ሚያዝያ 24 ቀን 2012 ዓ.ም ምሽት ላይ አቶ ልደቱ አያሌው እና አቶ ጃዋር ሙሐመድ በOMN ቴሌቪዥን የሰጡትን ቃለ ምልልስ በጽሞና
ነው የተከታተልኩት፡፡ እንደ ፖለቲከኛ አማራጭ ሃሳብ ማቅረባቸው ችግር የለውም፡፡ ችግር የሚሆነው ያቀረቡት አማራጭ ሃሳብ እጅና እግር የሌለው፣
መያዣ መጨበጫ ያልተደረገለት፣ አማራጭ ይሁን ማስፈራሪያ ያለየለት፣ ፍፁም ሀገር አፍራሽ ሃሳብ ማቅረባቸው ነው፡፡
               (ኩርኩራ ዋፎ - ከለገጣፎ)


                 በዚህ ወቅት ከኮሮና ቀጥሎ በመገናኛ ብዙሃን እየተነገረ ያለው ጉዳይ የምርጫ መራዘምና የሽግግር መንግስትን የተመለከተ ነው፡፡ በዚህ መጣጥፍ ትኩረት ለማድረግ ያሰብኩት አቶ ልደቱ አያሌው እና አቶ ጃዋር ሙሐመድ በOMN ቴሌቪዥን ያደረጉትን ውይይት ነው፡፡ ከዚሁ ጋር በማያያዝ በመንግስት የቀረቡትን አማራጮችና አንዳንድ አስተያየቶችን በማከል፣ የመፍትሄ ሀሳቦችን ለመሰንዘር እሞክራለሁ፡፡
ዶ/ር ዐቢይ ስልጣን ከያዙ ወዲህ ነጻ፣ ፍትሃዊና ተዓማኒነት ያለው ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችሉ እርምጃዎች በተከታታይ ተወስደዋል፡፡ የምርጫ ህጉ ተለውጧል:: የፓርቲዎች ማቋቋሚያ አዋጅ ተሻሽሏል፡፡ አዲስ የምርጫ አስፈጻሚ ቦርድ አባላት ተሰይመዋል፡፡ በሀገሪቱ ህገ መንግስት መሰረት ነሀሴ 23 ቀን 2012 ሀገራዊ ምርጫ ለማካሄድ የጊዜ መርሐ-ግብር ተዘጋጅቶም ነበር፡፡ ይሁን እንጂ፤ ዓለምን ያስጨነቀ “የኮሮና ቫይረስ - ኮቪድ 19” የተሰኘ ወረርሺኝ በመከሰቱ ምክንያት ምርጫ ማካሄድ አልተቻለም፡፡ እናም የምርጫውን ጊዜ ማሸጋገር ግድ ሆነ፡፡
የምርጫውን ጊዜ ማሸጋገር ግድ ቢሆንም አስቸጋሪ የህግ ማነቆ ገጥሞናል:: የምርጫውን ጊዜ የማራዘሙን ውሳኔ አስቸጋሪ ያደረገው ምርጫው መራዘሙ አይደለም፡፡ አንደኛ፤ ይህንን ማድረግ የሚችለው ማን ነው? የሚለው ጥያቄ ሲሆን፤ ሁለተኛ፤ አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት በመጪው መስከረም የስልጣን ዘመኑ የሚጠናቀቅና ህጋዊነቱ የሚያበቃ መሆኑ ነው፡፡ ይህም ችግር ላይሆን ይችላል፡፡ ችግሩ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ በሚያጋጥምበት ወቅት የምርጫ ጊዜ የሚራዘምበትም ሆነ የስልጣን ዘመኑ የተጠናቀቀ መንግስት ስልጣኑ የሚራዘምበትን ሁኔታ የሚደነግግ “የህግ አንቀጽ” በህገ መንግስቱ ውስጥ አለመቀመጡ ነው፡፡ ስለዚህ “ምርጫ እስከሚካሄድ ድረስ ሀገሪቱን የሚመራ መንግስት አንዴት ይኑረን?” የሚለው ወሳኝ ወቅታዊ ጥያቄ ነው፡፡
ይህንን በተመለከተ በመንግስት በኩል አራት አማራጭ የመፍትሄ ሃሳቦች ይፋ የተደረጉ ሲሆን፤ ፓርላማውም አንዱን መርጦ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ዜጎችም በጉዳዩ ላይ አስተያየት እየሰጡ ነው:: የምርጫውን ጊዜ በማራዘሙና ምርጫው እስከሚካሄድ ድረስ የመንግስት አስተዳደር ምን ይምሰል በሚለው ላይ በብዙዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና በገዢው ፓርቲ መካከል ልዩነት የለም ማለት ይቻላል:: አንዳንድ ተቃዋሚዎች ግን “የሽግግር መንግስት ይቋቋም” የሚል አጀንዳ በማራገብ ላይ ይገኛሉ፡፡
ገዢው የብልጽግና ፓርቲ፤ “… ከ100 በላይ የሚሆኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አንድ ሆነው መስራት አይችሉም፤ በዚያ ላይ ደካማ ናቸው፡፡ በዚህ በጭንቅ ወቅት ጠንካራ አመራር መስጠት አይችሉም፡፡ ህገ መንግስታዊ የሽግግር ዘመን እንዲኖር በአማራጮቹ ላይ አብረን እንወስን፡፡ የህገ መንግስት ትርጉም ይሰጥና ብልጽግና ፓርቲ የሽግግሩን ሂደት እንዲመራ ይደረግ” ይላል፡፡ አቶ ልደቱ አያሌው እና አቶ ጃዋር ሙሐመድ ግን ከሌሎች ተቃዋሚዎች ለየት ያለ አቋም አላቸው፡፡ “ከመስከረም በኋላ ገዢው ፓርቲ ሀገር የመምራት ህጋዊ መሰረት አይኖረውም፣ ከእኛ ልዩነት የለውም፡፡ ስለሆነም ህገ መንግስታዊ ትርጉም መስጠት አያስፈልግም፡፡ ከመስከረም በኋላ የገዢው ፓርቲ ህጋዊነት ስለሚያበቃ የሽግግር መንግስት ይቋቋም” ሲሉ ይደመጣሉ፡፡
የአቶ ልደቱ እና የአቶ ጃዋር ሃሳብ ከሌሎች ለየት ያለና በመንግስት ላይ የጊዜ ገደብ (Ultimatum) እስከ ማስቀመጥ የዘለቀ በመሆኑ ሰፋ አድርጌ ለማየት እወዳለሁ፡፡ ቅዳሜ ሚያዝያ 24 ቀን 2012 ዓ.ም ምሽት ላይ አቶ ልደቱ አያሌው እና አቶ ጃዋር ሙሐመድ በOMN ቴሌቪዥን የሰጡትን ቃለ ምልልስ በጽሞና ነው የተከታተልኩት፡፡ እንደ ፖለቲከኛ አማራጭ ሃሳብ ማቅረባቸው ችግር የለውም፡፡ ችግር የሚሆነው ያቀረቡት አማራጭ ሃሳብ እጅና እግር የሌለው፣ መያዣ መጨበጫ ያልተደረገለት፣ አማራጭ ይሁን ማስፈራሪያ ያለየለት፣ ፍፁም ሀገር አፍራሽ ሃሳብ ማቅረባቸው ነው፡፡
ሁለቱ “ጓዶች”፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አራት አማራጮችን አስጠንተው ባቀረቡ ማግስት ከያሉበት ጎራ ተጠራርተው ከምንጊዜው ተወያይተው፣ ከመቼው የጋራ አቋም ይዘው እንደመጡ መመራመር አያስፈልግም፡፡ ምክንያቱም ፈረንጆች “ተመሳሳይ ላባ ያላቸው ወፎች አንድ ላይ ይበራሉ” እንደሚሉት፣ ሁለቱ “ጓዶች” ተመሳሳይ ባህሪ፣ ስነ ምግባርና ተሞክሮ ያላቸው በመሆኑ ነው፡፡ አንዳንዶቹን ተመሳስሏቸውን እንያቸው፡፡
ልደቱ እና ጃዋር ሁለቱም ገጠር የተወለዱ ናቸው፡፡ ሁለቱም በመንግስት ቢሮክራሲ ውስጥ አልሰሩም፡፡ የመንግስትን አሰራር አያውቁም፡፡ ሁለቱም የተማሩ ናቸው፡፡ ሁለቱም በሰው ነፍስ ተጠያቂ ናቸው እየተባሉ ይታማሉ፡፡ ሁለቱም በሀገሪቱ ፖለቲካ የጎላ ሚና አላቸው:: አቶ ጃዋር በመኖሪያ ቤቴ “ተከበብኩ” ብሎ፤ አቶ ልደቱ (ከምርጫ 97 በኋላ) በቢሮዬ ታገትኩ ብሎ… ደጋፊዎቻቸውን አነሳስተዋል፡፡ በዚህም ሰዎች ተጎድተዋል፡፡ አቶ ልደቱ የመላው ዐማራ ሕዝብ ድርጅት (መዐህድ)፤ አቶ ጃዋር የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ፓርቲዎች አባል በመሆን የጎሳ ፖለቲካን እያወገዙ፣ የጎሳ ፖለቲካ አራማጅ ናቸው፡፡ አቶ ልደቱ ከፕሮፌሰር አስራት በተሰጠው አመራር ሽምቅ ውጊያ ለማድረግ ወደ ዓባይ በረሃ ወርዶ፣ ሁለት ሣምንት ተንከራቶ ተመልሷል፡፡ አቶ ጃዋር በአሜሪካ የኢንተርኔት ጫካ መሽጎ ተዋግቷል፡፡ ሁለቱም ጓዶች በሚረባውም በማይረባውም ጉዳይ ህዝብን ማነሳሳት ይወዳሉ፡፡ ሁለቱም “ጓዶች” መንግስትን መወጠር ይወዳሉ፡፡ ሁለቱም “ጓዶች” ዛሬ የተናገሩትን ነገ አይደግሙትም፡፡ ሁለቱም “ጓዶች” የስነ ልቦና ቀውስ የተጠናወታቸው መሆኑ ይነገራል… ስለ ሁለቱ “ጓዶች” ብዙ ብዙ ማለት ይቻላል፡፡ ህዝብ ጠንቅቆ የሚያውቃቸው በመሆኑ ከዚህ በላይ አልሄድም፡፡ ወደ OMN ቴሌቪዥን ውይይታቸው እንለፍ…
የሁለቱን “ጓዶች” የOMN ቴሌቪዥን ውይይት ከተመለከትኩ በኋላ ለአንድ የልደቱ የቀድሞ ወዳጅ ደወልኩና “ልደቱ ከመስከረም በኋላ እኔም ጃዋርም “ጠቅላይ ሚኒስትር ነኝ” ብለን ማወጅ እንችላለን ማለቱን ሰማህ ወይ?” ስለው፤ “አይግረምህ … አንድ ታሪክ ላስታውስህ… አፄ ቴዎድሮስ ዙፋኑን ያገኙት በጉልበታቸው በመሆኑ ሲሞቱ ለወራሻቸው ስልጣናቸውን ማሸጋገር አልቻሉም ነበር፡፡ … ቴዎድሮስ በመቅደላ ከተሰዋ በኋላ የተፈጠረውን ክፍተት አይተው፣ የትግራዩ ካሳ ምርጫ “አፄ ዮሐንስ 4ኛ” ነኝ አለ፡፡ የሸዋው ምኒልክም “አፄ” ብሎ ራሱን ሾመ፡፡ የላስታው ዋግ ሹም ጎበዜም የጎንደርን ቤተ መንግስት ተቆጣጠረና ራሱን “አፄ ተክለ ጊዮርጊስ” ብሎ አነገሰ:: እና… ልደቱም የላስታ ተወላጅ በመሆኑ የቅድመ አያቱን ፈለግ በመከተል ምናልባት የላስታዎችን የዛግዌ ስርዎ መንግስት የመመለስ ህልም ይኖረው ይሆናል” አለና በማላገጥ ሳቀ፡፡
አንድ ሃሳብ ልጨምር፡፡ “አይ ልደቱ!?” አሉ አንድ አስተያየት ሰጪ፤ ቀጥለውም “ከትናንት እስከ ዛሬ ወጥ በሆነ የፖለቲካ ቁመና የማይታይ፣ በገነገነ የሥልጣን ጥም የተለከፈ፣ በድሀ ልጆች ነብስ ቁማር መጫወት የለመደ… ከትናንት ለዛሬ መማር የማይችል ምን አይነት ሰው ነው ግን? ለነገሩ በኢትዮጵያዊነት ሰብእና መማር ቢሻ “ፖለቲካ በቃኝ” እስከ ማለት የደረሰበት ውጣ ውረድም ስንቅ በሆነው ነበር። የሠሞኑ ቅጣንባሩ የጠፋው፣ በእሣት የመጫወት የፖለቲካ መንገዱ፣ ከነበረበት ከፍታ እንደ ቱንቢ ወርውሮና አምዘግዝጎ ጉድጎድ ውስጥ የከተተው ነው። ይህንን ለማረጋገጥ በማህበራዊ ሚዲያ ብቻ ሣይሆን (ከOMN በስተቀር) በሜይን ስትሪም ሚዲያውም ምሁራን፣ የህግ ሙያተኞችና ፖለቲከኞች የሚያዘንቡትን ወቀሣ ማዳመጥ በቂ ነው… ከእንግዲህ በሚዛናዊ ትግሉ ቢረጋ?” ብለዋል።
ልደቱ መንግስት የደከመ ሲመስለው ውጥረት መፍጠር ልማዱ ነው፡፡ ይህንን በተመለከተ አንድ የኢዴፓ አባልና የልደቱ አፍቃሪ (#Henok_Hedato) በፌስቡክ ገጹ ላይ፡- “ልደቱ አያሌው በዚህ የሽግግር ወቅት አጨቃጫቂ ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች መልስ እንዲያገኙ ያለችውን ቀዳዳ ተጠቅሞ እየወጠረ ነው! ዓላማ ቢስ ተቃዋሚዎች እንደተለመደው ሊያደናቅፉት እየጣሩ ነው!” በማለት ጽፏል፡፡
ልደቱ ከጃዋር ጋር ሆኖ ባደረገው ውይይት ስለ ሽግግር መንግስት አስፈላጊነት በጥልቀት ሲነግረን ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ልደቱ ከኢ/ር ይልቃል ጌትነት ጋር ሆኖ በሰጠው ቃለ ምልልስ ደግሞ “በህይወቴ የምጠላው ነገር የሽግግር መንግስት የሚባል ነገር ነው፡፡ የሽግግር መንግስት የውድቀት መፍትሄ ነው” ካለ በኋላ፤ ይኸው “የውድቀት መፍትሄ” አስፈላጊ መሆኑን አስረግጦ ይነግረናል:: በአንድ ራስ ሁለት ምላስ (Double Standard) ይሏል ይሄ ነው! እንዲህ ያለ ነገር ከጤናማ አእምሮ ይፈልቃልን? ፍርዱን ለአንባቢ መተው እመርጣለሁ!
ስለ አቶ ልደቱ የሰማሁትን አስተያየት ጽፌ ስለ አቶ ጃዋር ዝም ብዬ ባልፍ ትርፉ ትዝብት ነው፡፡ ለአንድ የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ አክቲቪስት ወዳጄ ደውዬ፣ ስለ አቶ ጃዋር የOMN የውይይት ሃሳብ ነገርኩትና አስተያየት እንዲሰጠኝ ጠየቅኩት፡፡
“ጃዋር ሊገርምህ የሚገባው ይህንን ባይል ነው፡፡ ነገ ሌላ ነገር ሲናገርና ሲያደርግ ልታገኘው ትችላለህ… ከባድ የስነ ልቦና ቀውስ ያለበት አወዛጋቢ ሰው ነው:: ጃዋር ከልደቱ ጋር በOMN ቴሌቪዥን “የሽግግር መንግስት” የሚል ሃሳብ ሲናገር፤ የጃዋር ፓርቲ (የኦፌኮ) መሪ የሆኑት ዶ/ር መረራ ጉዲና በበኬላቸው፤ስለ ብሔራዊ መግባባትና ህገ መንግስታዊ መንገድን መከተል አስፈላጊነት ነው የተናገሩት፡፡ በአጠቃላይ ጃዋር በኦሮሞ ህዝብና በቄሮ ስም እየማለና እየተገዘተ ከሁከት ውስጥ ማትረፍ የሚፈልግ፤ ቀደም ሲል የሰራቸውን ስህተቶች ለመሸፋፈን የሚውተረተር፣ ራሱ እንደሚለው አወዛጋቢ ሰው ነው…” ነበር ያለኝ፡፡
ሌላ አስተያየት ሰጪ ደግሞ “… ሌላውን ላቆየው እና አሁን ጃዋር የሚባል “ሰው መሳይ፣ የሰይጣን ቁራጭ” እንኳን ለሀገር መሪነት ለጉርብትና የሚበቃ ነው? ደህና ጓደኛ አግኝቷል! ልደቱና ጃዋር ከቻላችሁ የስልጣንና የምርጫን ጥያቄ ለጊዜው ያዝ አድርጉት፤ እና ትንሽ ስለ ሃገር እና ህዝብ መቀጠል ጉዳይ አስቡ እና ተረጋጉ:: የOMN የልደቱ እና የጃዋር ውይይት፣ ከዚህ በፊት በጃዋር መሪነት የተፈጸመውን የህዝቦች መተራረድ እውቅና እንደ መስጠት የሚቆጠር ነው። የሁለቱ ፖለቲከኞች አብሮነት ደግሞ ነገ በሽግግር መንግስት ምክንያት ግርግር ለመፍጠርና ተከታዮቹ ተመሳሳይ ጥፋት እንዲፈጽሙ ምልክት መስጠት ይመስለኛል” ብለዋል።
እነ አቶ ልደቱና ጀዋር፣ በመንግስት የቀረበውን አራት አማራጭ፣ “ዶ/ር ዐቢይ የስልጣን ዘመናቸውን ለማራዘም እየተጠቀሙበት ነው” ብለው ካወገዙ በኋላ “የሽግግር መንግስት ይመስረት” የሚል ሀሳብ ማቅረባቸውን ያዳመጡ አንድ ጎምቱ የፖለቲካ ሰው በፌስቡክ ገጻቸው በጻፉት ማስታወሻ፤ “የሽግግር መንግስት ይመስረት ማለት ፖለቲካዊ ውሳኔ ነው ካሉ፤ አሁን ያለውን መንግስት የስልጣን ዘመን ማራዘምም ፖለቲካዊ ውሳኔ የማይሆንበት ምክንያት የለም። አለበለዚያ ልደቱና ጃዋር እያራመዱ ያሉት ነገር በአንድ ራስ ሁለት ምላስ (ደብል ስታንዳርድ) ነው” ብለዋል፡፡
አቶ ልደቱ እና አቶ ጃዋር “ይህ መንግስት ሰላም የማስፈን አቅም የለውም፡፡ … እየሟሟ የሚሄድ መንግስት ነው” ይሉናል፡፡ ይሁን እንጂ፤ እዚህም እዚያም እሳት እየጫሩ፣ ወቅት እየጠበቁ “ተነስ! መንገድ ዝጋ!” እያሉ፣ ራሳቸው ችግር እየፈጠሩ፣ መንግስትን ማማረርና “አቅመ ቢስ” እንደሆነ መተረክ ትክክለኛና አግባብነት ያለው አካሄድ አይደለም፡፡ ዛሬም እንደ ትናንትናው “ተነስ! ታጠቅ!” የሚል ጥሪያቸውን ሰምቶ አደባባይ የሚወጣ ይኖራል ብዬ አልገምትም፡፡ ትላንት እሱ ባይሞት፣ ወንድሞቹንና እኩዮቹን እንደ ዘበት ማጣቱን አይዘነጋውም - ለእነዚህ ጀብደኞች ሥልጣንና ዝና ሲባል፡፡ ዛሬ ግን ያለ ምክንያት መሞት የሚሻ ወጣት የለም:: ለምን ብሎ?
በመሰረቱ የዶ/ር ዐቢይ የሁለት ዓመታት ጉዞ፣ በሂደቱ “የተዋጣለት ስራ ሰርቷል” ማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ ይሁን እንጂ፤ አቶ ልደቱ እና አቶ ጃዋር እንደሚሉት፤ የዶ/ር ዐቢይ መንግስት ያን ያህል “ልፍስፍስ” ነው ማለት አይቻልም፡፡ ቄስና ሼህ ሳይቀር የፖለቲካ ተንታኝ በሆነበትና ክንዱን እስከ ብብቱ ድረስ ነክሮ ፖለቲካ በሚያቦካበትና በሚከካበት ሁኔታ፣ የዶ/ር ዐቢይ መንግስት ህዝብን አረጋግቶ ለመምራት እያደረገ ያለው ጥረት በደፈረሰ ባህር ውስጥ ዓሣ ለማጥመድ ከመዝመት የማይተናነስ መሆኑም ግንዛቤ ሊሰጠው ይገባል፡፡ እንደሚታወቀው የዶክተር ዐቢይ መንግስት በቀውስ ውስጥ ተፈጥሮ፣ ከቀውስ ወደ ቀውስ ብሎም ወደ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ እየተሸጋገረና በተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች እየተዋከበ የመጣ፤ በዚህም ራሱን እየፈተነ ጥንካሬን ለመፍጠር እየተፍጨረጨረ መሆኑ ይታያል፡፡ ይህንን መፍጨርጨር ያዩት ጃዋርና ልደቱ፤ “ሳይርቅ በቅርቡ፣ ሳይደርቅ በርጥቡ” እንዲሉ፤ “በሽግግር መንግስት” ሰበብ ለመበተን መፍጨርጨራቸው (የፖለቲካ ስልጣን ጨዋታ ነውና) የሚገርም አይሆንም፡፡
ባለፉት 30 ዓመታት በሀገራችን የተፈጠረው ቀውስ ሁሉንም ሰው ከጫፍ እስከ ጫፍ ነካክቷል፡፡ እናም ሁሉም ሰው ብሶት አለው፡፡ ፍላጎት አለው፡፡ ህልም አለው፡፡ የተለያየ ብሶት፣ ዘርፈ ብዙ ፍላጎትና የተዘበራረቀ ህልም ደግሞ አንድ ዓይነት መዳረሻ ሊኖረው አይችልም፡፡ እናም፤ መፍትሄው ችግርን በቅደም ተከተል (priority) አስቀምጦ መፍታት እንጂ ሁሉም ችግር በአንድ ሌሊት ካልተፈታ ብሎ መቃተት፣ ግጭትን ከመፍጠርና ችግርን ከማባባስ የዘለለ ትርጉምም ፋይዳም የለውም!
ይህንን ወቅት በተመለከተ አንዳንድ ሰዎች የየራሳቸውን የመፍትሄ ሀሳብ ሲያቀርቡ ከሶሻል ሚዲያና ከተለያዩ መድረኮች አስተውያለሁ፡፡ ማንም ለሀገሩ የሚያስብ ቅን ሰው በዚህ ወቅት ስለገጠመን ሁኔታ የራሱ የሆነ እይታና የመፍትሄ ሃሳብ ማቅረቡ ተገቢ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ እንደኔ እንደኔ፣ ሀገሪቱን የገጠማት ትልቅ የፖለቲካ ቅርቃር መሆኑን ሁሉም ሰው ሊገነዘበው ይገባል፡፡ እናም መፍትሄውን በመፈለጉ ረገድ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎችና ባለ ድርሻ አካላት፣ ስለ ምርጫ መራዘምም ይሁን ምርጫው እስከሚካሄድ ድረስ የሚኖረውን ጊዜ በተመለከተ በጋራ ተመካክረው ቢወስኑ ለአፈጻጸሙ ጭምር ይረዳል ብዬ አምናለሁ:: በሁለተኛ ደረጃ፣ ቢቻል ምርጫው እስከሚካሄድ ድረስ የሚኖረው አስተዳደር፣ በምርጫ በማይሳተፉ ገለልተኛ ወገኖች እንዲመራ ቢደረግ፣ በተለይም በምርጫው ውጤት የሚፈጠርን ውዝግብ ከወዲሁ ለማስቀረት ያግዛል ብዬ አስባለሁ፡፡
ጽሑፌን ከማጠቃለሌ በፊት ለአቶ ጃዋርና ለአቶ ልደቱ አንዳንድ ጥያቄዎችን ለማቅረብ እወዳለሁ፡፡ የአንድ ዜጋ ቀዳሚ ዜግነታዊ ኃላፊነት፣ ከሚያገኘው ገቢ ላይ ለሀገሩ ታክስና ግብር መክፈል ነው፡፡ በዚህ ረገድ እናንተ ይህንን ዜግነታዊ ኃላፊነታችሁን ምን ያህል ተወጥታችኋል? የግብር ከፋይ ቁጥር (TIN Number) አላችሁ? አንዳንዶቻችሁ ከውጪ ሀገር ገንዘብ (Remittance) እንደሚላክላችሁ ይታወቃል፡፡ እንደ አንድ ኃላፊነት የሚሰማው ዜጋ፣ ይህንን የውጪ ሀገር ገንዘብ በባንክ ነው የምትመነዝሩት ወይስ በጥቁር ገበያ? ሁለታችሁም ሀብት እንዳላችሁ ይታወቃል፡፡ በዚህ ወቅት የተከሰተውን የኮሮና ወረርሺኝ በመከላከል ረገድ ምን አስተዋጽዖ አደረጋችሁ? አንድ ሳኒታይዘር ገዝታችሁ ለአንድ የጎዳና ተዳዳሪ ሰጥታችኋል? ለመሆኑ “ስልጣን ስጠን፣ እንምራህ” ለምትሉት ኅብረተሰብ በእስካሁኑ ህይወታችሁ፣ በሙያችሁም ይሁን በሥራችሁ ምን አድርጋችሁለታል? ሁለታችሁም በመንግስት መስሪያ ቤት ተቀጥራችሁ እንዳልሰራችሁ ይታወቃል፡፡ ታዲያ በየትኛው የቢሮክራሲ እውቀታችሁ ነው ፖሊሲ ቀርጻችሁ፣ ፕሮግራም ነድፋችሁ፣ እቅድ አዘጋጅታችሁ… ሀገር የምትመሩት? ወይስ የቢሮክራሲ ግንዛቤ እንደሌለው እንደ አሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ልታወዛግቡን ነው?
ከአዘጋጁ፡- በጽሁፉ የተንጸባረቀው ሃሳብ ጸሐፊውን ብቻ የሚወክል መሆኑን እንገልጻለን፡፡ ጸሃፊውን በ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡Read 4481 times