Saturday, 09 May 2020 12:26

አረና፤ የትግራይ ክልል መንግስት ለኮሮና ትኩረት አልሰጠም አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

 በተጐራባች ክልል የኮሮና ተጠቂዎች መበራከት ስጋት ፈጥሯል

               የኮሮና መከሰትን ተከትሎ ከማንም ቀድሞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጀው የትግራይ ክልላዊ መንግስት፣ በአሁኑ ወቅት ለወረርሽኙ ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ አይደለም ከኮሮና ይልቅ ለምርጫና ስልጣን የበለጠ ትኩረት ሰጥቷል ሲል አረና ትግራይ ለዲሞክራሲና ሉአላዊነት ወቀሰ፡፡
በአሁኑ ወቅት የትግራይ ክልልን በሚጐራበተው አፋር ክልል፣ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች እየተበራከቱ መምጣታቸውን የጠቀሱት የአረና ቃል አቀባይ አቶ አምዶም ገብረስላሴ፤ ‹‹በትግራይ መንግስት ከሚታየው መዘናጋት አንፃር፣ ኮሮና ለትግራይ በጣም ያሠጋል፤ ትኩረትም እየተደረገ አይደለም›› ብለዋል፡፡
ከአፋር ባሻገር በሱዳን በኩልም የቫይረሱ ስርጭት ስጋት እንዳለ ጠቁመው፤ የክልሉ መንግስት ተገቢውን የጥንቃቄ እርምጃዎች በመውሰድ ረገድ መዘናጋት እንደሚስተዋልበት ይገልጻሉ - የአረና ቃል አቀባይ፡፡
በክልሉ ካለው የመመርመሪያ መሣሪያ እጥረት እንዲሁም የክልሉ መንግስት ትኩረቱን ሙሉ ለሙሉ ወረርሽኙን በመከላከል ላይ አለማድረጉ ስጋቱን እንደሚያባብስው የአረና መግለጫ ጠቁሟል፡፡
በመጀመሪያ የክልሉ መንግስት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጀው ተቻኩሎና ቅድመ ዝግጅት ሳያደርግ መሆኑን የጠቆሙት አቶ አምዶም፤ በዚህም ሳቢያ ህብረተሰቡ ለኢኮኖሚያዊ ችግርና ለሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተዳርጓል ብለዋል፡፡
በክልሉ አብያተ ክርስቲያናትና ት/ቤቶች ተዘግተው ባሉበት ህወኃት በየወረዳው የካድሬዎች ስብሰባ እያደረገ መሆኑን የገለፁት የአረና ቃል አቀባይ፤ ይህ ሁኔታም በክልሉ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ሊያስፋፋ ይችላል የሚል ስጋት አሳድሮብናል፤ የክልሉ መንግስትም የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የወጡ  መመሪያዎችን ሊያከብር ይገባል - አቶ አምዶም ብለዋል፡፡
‹‹በክልሉ አንድም ሰው በኮሮና ቫይረስ እንዲሞት አንፈልግም›› የሉት አቶ አምዶም፤ የክልሉ መንግስት በአሁኑ ወቅት ለአለምም ለሀገሪቱም ስጋት በሆነው በኮሮና ወረርሽኝ ስጋት ላይ ሙሉ ትኩረቱን አድርጐ እንዲሠራ አሳስበዋል፡፡
የምርጫ ጉዳይም በመጀመሪያ በህብረተሰቡ ላይ የተጋረጠውን የአደጋ ስጋት መከላከል ከተቻለና ይህንንም ስለማከናወናችን ከተረጋገጠ በኋላ የሚደርስ ነው የሚሉት የአረና ቃል አቀባይ፤ በአሁኑ ጊዜ የክልሉ ገዥ ፓርቲ ምርጫ የማካሄድ ሃሳብ ማንሳቱም ከፕሮፓጋንዳ ያለፈ በመሬት ላይ ፈጽሞ የማይተገበር ጉዳይ ነው ብሏል - አረና፡፡  

Read 11065 times Last modified on Saturday, 09 May 2020 16:41