Saturday, 09 May 2020 12:21

የዓለም ስፖርት የቨርችዋል፤ ዲጂታልና ሞባይል ቴክኖሎጂዎች ጥገኛ ሆኗል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

  • እግር ኳስ፤ ሜዳ ቴኒስ፤ ፈረስ ውድድር ፤ መኪና ሽቅድምድም፤ ብስክሌትና ቅርጫት ኳስ በስፖርት ጌሞችና ውርርዶች ቀጥለዋል

                  የኮሮና ወረርሽኝ ከመጣ ወዲህ የኢ-ስፖርትና የስፖርት ውርርድ ኢንዱስትሪዎች ከነበሩበት ደረጃ  በ3 እጥፍ እድገት እያሳዩ ናቸው፡፡ ኢ-ስፖርት የትክክለኛውን ስፖርት ደረጃና ክብር የሚቀንስ በሚል ሲተች ቢቆይም፤ በዓለም ዙርያ የስፖርት ውድድሮች ከቆሙ በኋላ ብቸኛው የስፖርት መዝናኛ አማራጭ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ቴክኖሎጂው የስፖርቱን ዓለም ደህነነት አስጠብቆ የሚቆይ፤ በፉክክር ሚዛናዊነት ያለውና ተከታታይነትን የሚያበዛ መሆኑም ተስተውሏል፡፡ በሌላ በኩል የኤሌክትሮኒክ ስፖርት ተፈላጊነት መጨመሩ   የስፖርት ውርርድና ቁማር ያለ ስፖርት ውድድሮችም ተፋፍሞ እንዲቀጥል ምክንያት ሆኗል፡፡ የኮሮና ወረርሽኝ የስፖርቱን ዓለም ማመስ ሲጀምር በስፖርት ውርርድ ላይ የሚሰሩ ተቋማት ስጋት ነበራቸው፡፡ በእውን የሚደረጉ ስፖርት ውድድሮች ባለመኖራቸው ውርርድ በማሳጣት የከፋ አደጋ ውስጥ እንደሚከታቸው ጠብቀዋል፡፡ ያለፉትን 3 ወራትም የተለያዩ አማራጮችን በመፈተሽ መፍትሄውን ሲያፈላልጉ ቆይተዋል፡፡ በመጨረሻም ዋንኛው መፍትሄ  ከኢ ስፖርት ወይንም ከኤሌክትሮኒክ ስፖርት የሚገናኝ ሆኗል፡፡
በቨርችዋል ቴክኖሎጂ አማካኝነት የኢ ስፖርት እና የስፖርት ውርርድ ኢንዱስትሪዎች ተጣምረዋል፡፡ የእግር ኳስ፤ የሜዳ ቴኒስ፤ የፈረስ ውድድር ፤ የመኪና ሽቅድምድም፤ የብስክሌት፤ የቅርጫት ኳስ ስፖርቶች በኢንተርኔት ጌሞች እና ውርርዶች ህልውናቸውን እየጠበቁ ናቸው::  የNascar ሽቅድምድም በቨርችዋል ቴክኖሎጂ  በቲቪ ሲቀርብ  1.3 ሚሊዮን ተመልካች ነበረው::  All-star የፍፃሜ ውድድር 12 ሚሊዮን ደቂቃዎችን በቀጥታ ስርጭት ሲተላለፍ ከ30ሺ በላይ አስተያቶች ተሰጥተውበታል፡፡ በፎርሙላ 1 እውቅ የሞተር ስፖርት ተወዳዳሪዎች የተሳተፉበት Grand-prix ተከታታዮቹን በ3 እጥፍ ማሳደግ የቻለ ሲሆን፤  በዩቲውብ ቀጥታ ስርጭት 1.7 ሚሊዮን ተመልካች አግኝቷል:: በሞተር ሽቅድምድም ላይ የተሰራው አዲስ የኤሌክትሮኒክ ስፖርት MOTOGP በኦንላይን ብቻ ሳይሆን በቀጥታ የቴሌቭዥን ስርጭት በመላው ዓለም ባገኘው ሽፋን ከ2 ሚሊዮን በላይ ተመልካች አግኝቷል፡፡የአሜሪካ ቅርጫት ኳስ  ደግሞ NBA 2k20 በተባለ ጌም እውቅ ስፖርተኞችን በዲጂታል ገፀባህርይ ቀርፆ የስፖርት አፍቃሪዎቹን እያሰባሰ ሲሆን ፤ በዚያው በአሜሪካ በሚገኝ ኩባንያ የተሰራ የስፖርት አፕሊኬሽን የቅርጫት ኳስ ውድድሮችን በስምንት የተለያዩ ስክሪኖች በሚያሳይበት ቴክኖሎጂው ደንበኞችን እያፈራበት ነው፡፡ በመላው ዓለም ከ128 በላይ ፕሮሼስናል ጌም ተጨዋቾች ያፈራው FIFA 20 በዚሁ ወቅት ከፍተኛ እውቅና ካገኙ የኤሌክትሮኒክ ስፖርቶች ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ በዚሁ ጌም አማካኝነት በስፔን ላሊጋ የተከናወነውን መልካም ተመክሮ ማንሳት ይቻላል፡፡ ከሳምንታት በፊት ስፓንያርዶችን ብቻ በሚያሳትፍ የፊፋ የእግር ኳስ ጌም የሪያል ማድሪዱ ማርኮ አሴንስዮ ክለቡን ለሻምፒዮናንነት ሲያበቃ በቀጥታ ስርጭት የተከታተለው ከ170ሺ በላይ ነው፡፡ ፎርብስ መፅሄት እንደተነበየው FIFA 20  በዚህ ዓመት እስከ 3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚኖረው ነው፡፡ በጃፓን የቤዝቦል ስፖርተኞች በቨርችዋል ቴክኖሎጂ ታግዘው ልምምዳቸውን  ሲሰሩ 3 ዓመታት ያሳለፉ ሲሆን ይህ ተመክሮ አሁን ዓለም እያስተዋለው ነው፡፡ በስፔን በአንደኛ ዲቪዝዮን የሚሳተፍ አንድ ክለብ በኮሮና ወረርሽኝ ውድድሮች መቋረጣቸውን ተከትሎ ተጨዋቾቹ በተለያዩ የጌም ጨዋታዎች እንዲጠመዱ በማነሳሳት ሰርቷል፡፡ በአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች ውድድሮች ከመቋረጣቸው ጋር በተገናኘ ኮከብ ተጨዋቾች በየማህበራዊ ሚዲያቸው ከስፖርት አፍቃሪው እና ከደጋፊዎቻቸው ጋር ቀልጣፋ ግንኙነት ላይ መቆየታቸው ሌላው ሁኔታ ነው:: በቨርችዋል ቴክኖሎጂ አማካኝነት አገራጭ አቋራጭ የብስክሌት ውድድር በዓለም አቀፉ የብስክሌት ስፖርት የግንኙነት መረብ የተጀመረ ሲሆን IRONMAN VR PRO በሚል ጌም ታዋቂ ኦሎምፒያኖች ከያሉበት የዓለም ክፍል ሆነው የትራያትሎን ውድድር እያካሄዱ ናቸው:: እነ አንዲ ሙራይና ራፋኤል ናዳንን ለዓመታት ሲያቀናቅን የቆየው የማድሪድ ኦፕን የሜዳ ቴኒስ ውድድር በኦንላይን የሚሰራጭ ጌም ሆኖ ተቀርፆ በሁለቱም ፆታዎች ለሚያሸንፉት እስከ 150ሺ ዩሮ የሽልማት ገንዘብ የቀረበበት ነው፡፡
ቨርችዋል ቴክኖሎጂ በዋናነት በኢ ስፖርት ላይ ተግበራዊ የሆነ ፈጠራ ነው፡፡ በኤሌክትሮኒክ የጌም ጨዋታዎች   ነባራዊውን የስፖርት ዓለም በዲጂታል ምስሎች አዋህዶ ለማቅረብ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ከ59 ዓመታት በፊት በአይቢኤም አማካኝነት በቤዝቦል ስፖርት ነው የተጀመረው፡፡ ዛሬ ዓለም በሚገለገልባቸው ስማርት ሞባይሎችና ዘመናዊ ኮምፒውተሮች ዲጅታል ስክሪኖች ላይ  እውነተኛ የሚመስሉ የስፖርት ውድድሮችን በአኒሜሽን ማቅረብ ተችሏል፡፡ ይህ ሁኔታም በስፖርቱ የተመናመነውን የገቢ ምንጭ ተስፋ የሚሰጥ አቅጣጫ ውስጥ ከቶታል:: የሶፍትዌር ቴክኖሎጂዎን ፈጣን የፈጠራ ሂደት ከማምጣቱም በላይ የስፖርት ውርርድን ለሚያካሂዱ ተቋማት ውድድሮች በነባራዊ ዓለም እየተካሄዱ ባይሆንም በኮምፒውተር የጌም ጨዋታዎች ላይ እንዲሰሩ አድርጓቸዋል፡፡
At Kearney በሰራው ጥናት የዓለም የስፖርት ገበያ ከ480 እስከ 620 ቢሊዮን ዶላር ይንቀሳቀስበታል፡፡  ዋንኛ የገቢ ምንጮች በነባራዊው ዓለም በቀጥታ ከሚካሄዱ የስፖርት ውድድሮች፤ በውድድር ቦታዎች የሚከናወኑ የምግብና ለስላሳ መጠጥ ሽያጮች፤ ከሚዲያ የስፖንሰርሺፕ መብት ውሎች፤ ከስፖርት እቃዎች እና ቴክኖሎጂዎች ንግድ ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ በኤሌክትሮኒክ ስፖርት እና በቨርችዋል ቴክኖሎጂ እነዚህን የገቢ ምንጮችን መፍጠር እንደሚቻል መታመኑ ተስፋ የሰጣቸው በርካታ የስፖርት አይነቶች ናቸው፡፡  በቨርችዋል ቴክኖሎጂ አማካኝነት ኢ ስፖርት ለሁሉም ስፖርት አፍቃሪዎች የተሻለ ተደራሽነት ማግኘቱ፤ ውድድሮችን በቀጥታ ለመከታተልና ውጤቶችን በትኩሱ ለማግኘት በየትኛውም ሁኔታ ላይ የሚቻል መሆኑ ከፍተኛውን ትኩረት አስገኝቷል፡፡ ኒውዙ የተባለ ተቋም በሰራው ጥናት ኢ-ስፖርት  በየዓመቱ ከ15%  በላይ፤  በጃፓን 39% በፈረንሳይ እና በእንግሊዝ 34%  በጀርመን 30% እንዲሁም በአሜሪካ 29% እድገት እያሳየ ነው፡፡ ከዓለም ህዝብ ከ1.57 ቢሊዮን ስለ ኢስፖርት እና ቨርችዋል ቴክኖሎጂው  ግንዛቤ አላቸው፡፡
በሌላ በኩል በቨርችዋል ቴክኖሎጂ በመታገዝ የሚቀርቡ የኤሌክትሮኒክ ስፖርቶችና ጌም ጨዋታዎች በርካታ የስፖርት አፕሊኬሽኖች እንዲፈጠሩ አድርጓል፡፡ የስፖርት አፕሊኬሽኖች
የስፖርት ውድድሮችን በልዩ ሁኔታ ለመከታተል ምቹ እድሎችን ፈጥረዋል:: የተለያዩ የስፖርት ብራንዶችን አገልግሎት እና አቅርቦት ቀላል ከማድረገቻውም በላይ፤ በኦፍላይን ሞድ መጠቀምን በማህበራዊ ትስስር መቀራረብን የሚያቀላጥፉ ሆነዋል፡፡ የስፖርት አፕሊኬሽኖች የስፖርተኞች እና የቡድኖቻቸው ሙሉ ካታሎግ፤ ውይይት፤ ዜና፤ የውድድር መርሃ ግብርን በትኩሱ አጠገብ ከማድረሳቸውም በላይ ነባራዊ የስፖርት ውድድሮች ባይኖሩም እንኳን በተለያዩ  የቀጥታ ስርጭቶች የኤሌክትሮኒክ ስፖርቶችን ገበያ እያሟሟቁ ናቸው፡፡ የኮረና ወረርሽኝ ከገባ በኋላ በተለይ በስማርት ሞባይል የስፖርት አፕሊኬሽኖች የሚጠቀሙና የሚከታተሉት ቁጥራቸው በ3 እጥፍ ጨምሯል:: ከኮሮና በፊት የስፖርት አፕሊኬሽኖቹ በስፖርት የውድድር ቦታዎች መገኘት የማይችሉና ያመለጣቸው፤ የሚደግፉትን ቡድን ጨዋታ ወይንም ውድድር ቅጂ ለመታደም፤ ምርጥ ነገሮችን ደጋግሞ ለማየት ብቻ ነበር፡፡ ከኮሮና በኋላ ግን የስፖርት አፕሊኬሽኖች በኤሌክትሮኒክ ስፖርትና የስፖርት ውርርድ እንቅስቃሴዎች ላይ ወሳኝ ቴክኖሎጂዎች ሆነዋል፡፡ በስፖርት አፕሊኬሽኖች አማካኝነት የቡድን አንድነትና መንፈስ ለማጠናከር፤ ወቅቱን የጠበቁ ውጤቶችና ሌሎች ዝርዝር መረጃዎች ለማግኘት፤ በስፖርት አፍቃሪዎችና ደጋፊዎች መካከል ውይይት ለመፍጠር እንዲሁም ከስፖርት ቡድን ጋር የተያያዙ የተለያዩ ምርቶችን ለማሻሻጥ እየተቻለም ነው:: በዓለም ዙርያ የስማርትሞባይል ተጠቃሚዎች ብዛታቸው 2.87 ቢሊዮን በላይ ሲሆን የተለያዩ አፕሊኬሽኖችን አንድና ከዚያም በላይ በመግዛት 62 በመቶው መሳተፋቸው የተክኖሎጂውን ተፈላጊነት ያመለክታል፡፡ በዓመት ከ194 ቢሊዮን በላይ አፕሊኬሽኖች ከኢንተርኔት ላይ እንደሚጫኑም ይታወቃል፡፡
በነባራዊ ዓለም የስፖርት ውድድሮች  በመቋረጣቸው  የተፈጠረውን የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ለመለወጥ ቴክኖሎጂን ዋንኛ አማራጭ በማድረግ መፍትሄ ተገኝቷል፡፡ ይሁን እንጂ ለኮሮና ቫይረስ ክትባት ካልተገኘና በዓለም ዙርያ በበቂ ሁኔታ የሚዳረስ ካልሆነ የስፖርት ውድድሮችን ማካሄድ ያስቸግራል፡፡ ቫይረሱን ለመከላከል በተቀመጡት ቅድመ ሁኔታዎች የተነሳ የስፖርት ውድድሮችን እንደተለመደው የመቀጠሉን እድል አዳጋች ያደርገዋል፡፡  ስፖርቶች ብዙዎችን የሚሰበስቡ፤ የሚያነካኩና የሚያቀራርቡ በመሆናቸው ህዝቦችን በከፍተኛ ደረጃ ለወረርሽኝ የሚያጋልጡ ናቸው፡፡ ኮሮና ወረርሽኝ  የዓለምን ስፖርት አጠቃላይ ገፅታ በአዲስ መልክ ይቀይረዋል፡፡ አሁን ባለው የኮረና ወረርሽኝ ሁኔታ ውድድሮችን ካቆሙበት መቀጠል ቢቻልም፤ ስፖርት አፍቃሪው ውድድሮችን በስፍራው ተገኝቶ መከታተል አይፈቀድለትም፡፡ በየውድድሮቹ ላይ የሚሳተፉ የስፖርት ቡድኖች ሙሉ አባላት፤ ድጋፍ ሰጭ ሰራተኞች እና ባለሙያዎች፤ የብሮዳካስት ባለሙያዎች፤ የቴክኒክ ሰራተኞች፤ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጭዎች፤ ፎቶግራፈሮች፤ የፀጥታ እና የደህንነት አባላት ከውድድሮች በፊት እና በኋላ ልዩ ምርመራ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህም የውድድሮችን መርሃ ግብር የሚያሰፋውና የሚያወሳስበው ይሆናል፡፡ በርካታ ሳይንቲስቶች ክትባቱ ተገኝቶ ሙሉ ለሙሉ ወደ ስራ ለመግባት ገና ከ6 እስከ 8 ወራት እንደሚቀር ይገልፃሉ፡፡ ይህ እውነታም የዓለምን ስፖርት ውስጥ ወደ ከፍተኛ ኪሳራ ውስጥ ይዞት ይገባል፡፡ ምክንያቱም በበርካታ አገራት የስፖርት ኢንዱስትሪው ከኢኮኖሚው ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ በውድድሮች መቆም የቱሪዝም፤ የሆቴል፤ የአየር ትራንስፖርት ኢንዱስትሪዎች ከፍተኛ የገቢ ምንጫቸው ይቋረጣል፡፡

Read 11489 times