Print this page
Wednesday, 06 May 2020 00:00

በጥናትና ምርምር የተገኘ አስደናቂ ውጤት

Written by  ታደለ ገድሌ ጸጋየ (ዶ/ር)
Rate this item
(2 votes)

  ተመራማሪዋና ሳይንቲስቷ ማሪያ ሳሎሚያ ስክሎዶውስካ (ሜሪየ) ይባላሉ:: አባታቸው ስክሎዶውስካና እናታቸው ብሮኒስላዋ በዋርሶ ከፍተኛ ትምህርት ቤቶች የሳይንስ መምህራን ነበሩ፡፡ በዜግነት ፖላንዳዊት የሆኑት ሜሪየ የተወለዱት እ.ኤ.አ በ1867 ዋርሶ ውስጥ ሲሆን ያረፉት ደግሞ እ.ኤ.አ በ1943 ነው፡፡
ሜሪየ ስክሎዶውስኪ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በዋርሶ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የተማሩ ሲሆን ሳይንሳዊ ጥናትና ምርምር ማድረግን ሲያበረታቷቸው ከነበሩት ወላጆቻቸው ቀስመዋል፡፡ በዘመኑ ፖላንድ በሩሲያ ግዛት ሥር ነበረች፡፡ እናም ሜሪየና ቤተሰባቸው ፖላንድ ከሩሲያ አገዛዝ ነጻ እንድትወጣ  ከፍተኛ ፍላጎት ነበራቸው::
በዚህ ረገድ ሜሪየ ፀረ ሩሲያ ከሆነ የተማሪዎች አብዮታዊ ድርጅት ውስጥ ገብተው ሲታገሉ ነበር:: በመጨረሻ የጭቆናው ሁኔታ እየከረረ በመምጣቱ ከፍተኛ ችግር ላይ ወደቁ፡፡
የሜሪየ የልጅነት ዘመን በችግር የተሞላ ነበር፡፡ ሜሪየ 10 ዓመት ሲሞላቸው ወላጅ እናታቸው ሞቱባቸው፡፡ ከዚህም የተነሣ አዳሪ ትምህርት ቤት ገብተው ለመማር ተገደዱ፡፡
ከዚያም ጎበዝ ተማሪዎች ወደሚገቡበት ጂምናዚየም ገቡ፡፡ በ15 ዓመታቸው ሜሪየ የሁለተኛ ደረጃን ትምህርት አጠናቅቀው ለጎበዝ ተማሪዎች የሚሰጠውን ሜዳሊያ በመቀበል ተመረቁ::
ከልጅነታቸው ጊዜ ጀምረው በሳይንስ ትምህርት ላይ ይመሰጡ ስለነበር ወደፊት በዘርፉ ላይ ትኩረት አድርገው ለመሥራት ወሰኑ:: ነገር ግን  ወላጅ አባታቸው በቂ ገንዘብ ስላልነበራቸው፣ ልጃቸውን ዩኒቨርሲቲ አስገብተው ለማስተማርና ፍላጎታቸውን ለማሟላት ሳይሆንላቸው ቀረ፡፡ ይህ ዓይነቱ ችግር የሜሪን ታላቅ እኅት ብሮንያንም ገጥሟቸው ነበር፡፡
ሜሪየ የ16 ዓመት ልጃገረድ በነበሩበት ጊዜ
 የችግሩ ምክንት ደግሞ ሩሲያ ነበረች:: በዘመኑ ሩሲያ ፖላንድን ወርራ ሕዝቡን በባርነት ቀንበር ውስጥ አስገብታ ከፍተኛ በደል ታደርስበትና ከፍተኛ ግፍም ትፈጽምበት ነበር፡፡ በወቅቱ የፊዚክስ ፕሮፌሰር የነበሩት የሜሪየ አባት ቭላዲስላቭ ከሥራቸው ተወግደው የማስተማሩ ሥራ ለሩሲያውያን ተሰጥቶ ነበር፡፡ ከዚህም የተነሣ የነሜሪየ ኩሪየ ቤተሰብ የሚልሰውና የሚቀምሰው አጥቶ  በችግር ላይ ወደቀ፡፡
ከችግራቸው የተነሳም ሜሪየ የአንድ አዳሪ ትምህርት ቤት ሠራተኛ ሆነው ትንሽ ገቢ እያገኙ  ለመኖር ተገደዱ፡፡ በሩሲያውያን ዘመን የፖላንድ ሴቶች ዩኒቨርሲቲ ገብተው እንዳይማሩ ተከልክለው  ስለነበር  ሜሬ ኩሪየም ተስፋ ቆርጠው የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ተገደዱ፡፡ አርፈው ግን አልተቀመጡም፡፡ ፓሪስ ውስጥ የሕክምና ትምህርት በመከታተል ላይ የነበሩትን  እኅታቸውን ብሮንያን ለማገዝ በሚል እ.ኤ.አ በበ1891 ዋርሶን ለቅቀው ወደ ፈረንሳይ ሄዱ፡፡ እዚያም የአውሮፓ ሴት ተማሪዎች ወደሚማሩበት ሶርበኔ ዩኒቨርሲቲ ገብተው የሳይንስ ትምህርት ለመማር ይችሉ ዘንድ አመለከቱ፡፡ ጥያቄያቸውም ተቀባይነትን አገኘ፡፡ እንደ ልባቸው ሀገራቸው ፖላንድ ያላገኙትን ትኩስ ዳቦ፤ ፍራፍሬና ትኩስ ቼኮሌት እየተመገቡ ትምህርታቸውን ሲማሩ የተለየ ክብርና ነጻነት ይሰማቸው ነበር፡፡ ይህንኑ የፈረንሳይ መንግሥት ቸርነት ከጊዜ በኋላ እንዲህ ሲሉ ገልጸውታል፡-
«በተለያየ ምክንያት ሕይወቴ አሰቃቂና አስጨናቂም ነበር፡፡ ይህም በፈረንሳይ ሕዝብና መንግሥት የተደረገልኝ ችሮታና ወሮታ የነጻነት ስሜት እንዲሰማኝ አድርጎኛል» ሜሪ እ.ኤ.አ በ1894 በማቲማቲክስና በፊዚክስ የማስትሬት ዲግሪያቸውን (ባካሎሪያቸውን) ተቀብለዋል፡፡ በዚያው ዓመት በተማሩበት ዩኒቨርሲቲ የኬሚስትሪና የፊዚክስ ፕሮፌሰርና የላብራቶሪ ዲሬክተር ከነበሩት ፒሬ ኩሪየ ጋር ተዋወቁ፡፡ እ.ኤ.አ በ1895 ከፒሬ ጋር ጋብቻ ፈጸሙ፡፡ ሜሪየ ጋብቻ ከፈጸሙ በኋላ በባለቤታቸው ላብራቶሪ ውስጥ በነጻነት የምርምር ሥራቸውን መሥራት ጀመሩ፡፡
ሜሪየ በሽልማታቸው ወቅት
ሜሪየ በኬሚስትሪና በፊዚክስ መስክ ባካሄዱት ጥናትና ምርምር ባስመዘገቡት አዲስ ግኝት የኖቤል ተሸላሚ ሆነዋል:: በአንድ ወቅት  ዘመነኛቸው፤ የሙያ አጋራቸውና የቅርብ ወዳጃቸው የነበረው ታላቁ ሳይንቲስት አልበርት አንስታይን አድናቆቱን ሲገልጽላቸው፤ «የሜሪየ ኩሪየ ስም ገና ያልታወቀ ቢሆንም ወደፊት ሥራዋም ሆነ ስሟ ለዘለዓለም ሲዘከር ይኖራል፤ በሕይወቷ ውስጥ አስደናቂ ሥራ ስለሠራች ወይም በሰብዓዊነት ተነሳስታ የሰውን ልጅ ስለረዳች ብቻ ሳይሆን በከፍተኛ ሞራልና ጥንካሬ፤ የመንፈስ ጽናትና ውሳኔ አዲስ ነገር ስላስገኘች  ነው:: አብዛኛውን ጊዜ እንደዚህ ዓይነት ምሉዕነት ከአንድ ግለሰብ ለማግኘት ደግሞ ያዳግታል፡፡ እናም ሜሪየ ታላቁን የሳይንስ ምሥጢር በማግኘት ድል ያደረገች ሳይንቲስት ብቻ ሳትሆን በዓለም ዙሪያ የሰውን ልጅ ልብ የማረከች ጀግና ናት» ብሏል (ኒውዮርክ ታይምስ ጁላይ 5.1934)::
 አልበርት አንስታይን
 ሜሪየ በአንድ ወቅት ሳይንስን አስመልክተው ሲናገሩ፤ «እኔ ሳይንስ ታላቅ የሰው ልጅ ውበት ነው ከሚሉት ወገኖች አንደኛዋ ነኝ፡፡ ሳይንቲስትም ላብራቶሪ ውስጥ የሚገኝ ቴክኒሺያን ብቻ ሳይሆን በተፈጥሮ ክስተት ውስጥ የሚመስጥ ተረት ለማዳመጥ እንደተቀመጠ ሕጻን ይቆጠራል» ብለዋል፡፡ ሜሪየ ኩሪየ ራዲዮ አክቲቭንና ራዲየምን በምርምር ለማግኘት የቻሉ ሳይንቲስት ናቸው፡፡ ምርምራቸውን የጀመሩት ከባለቤታቸው ከፒየሬ ጋር በመሆን ነው፡፡ ሳይንቲስቱ ኩሪየ ባለቤታቸውን ሜሪየን፤ ሁለት ልጆቻቸውን ማለት ከባለቤቷ ጋር እ.ኤ.አ በ1935 በኬሚስትሪ የኖቤል ተሸላሚ የነበረችውን ኢሪኔ ኩሪየንና ኢቭ ኩሪየን ላብራቶሪ ውስጥ ትተው ወጣ እንዳሉ  እ.ኤ.አ በ1906 በመኪና አደጋ ካረፉ በኋላ ተስፋ ሳይቆርጡ  በፊዚክስ መስክ አዳዲስ ነገሮችን በማጥናት የአቶምን ቴክኒካዊ ቅንብር አመልክተዋል፡፡
ባልና ሚስቱ ፒየሬ ኩሪየና ሜሪየ
ባልና ሚስት ከአንድ ባሕር ይቀዳሉ እንደሚባለው፣ በመልክና በአፍንጫ ጭምር ይመሳሰላሉ፡፡ የሥነ ልቡና ባለሙያዎች ስለ ጥንዶች ሲናገሩ፤ ወንድ ራሱን ስለሚወድድ የእርሱን መልክ የያዘች የመሰለችውን ሴት ያገባል፤ ሴትም የራስዋን መልክ ስለምታፈቅር፣ ከራስዋ መልክ ጋር ተመሳሳይ መልክ ያለውን ወንድ ታገባለች ይላሉ፡፡
«ለማንኛችንም ሕይወት ቀላል አይደለችም፡፡ ነገር ግን ሁላችንም በውስጣችን ጽናት ኖሮን በራሳችን የምንተማመን መሆን አለብን፡፡ ማንኛችንም  በተፈጥሮ አንድ የተሰጠን ነገር  ያለን መሆኑን ማመን አለብን፡፡ እናም ማንኛችንም የትኛውንም ያህል ዋጋ መክፈል ይኖርብናል» የሚሉት ሜሪየ፤ ሥራቸው የመጀመሪያውን ቦታ ሲይዝ ባለቤታቸውንና ልጆቻቸውን ግን በሁለተኛ ደረጃ ይመለከቱ ነበር፡፡ የጥናትና የምርምር ቀመራቸው ያተኮረው በራዲዮ አክቲቭ ላይ ነበር፡፡ የምርምር ተግባራቸው በዩራኒየም ጨረር (ራዲየሽን) የአዲስ ግኝት ባለቤት የሆኑትን ኤ ኤች ቢስኩ የሬልን ጭምር በእጅጉ አነሳስቶት ነበር፡፡ በመጀመሪያ ሜሪየ ኩሪየ በታወቁ ንጥረ ነገሮች ጨረርን ለመለካት ሙከራ አድርገዋል፡፡ ቀጥለው የጨረርን ጥንካሬ ለማወቅ ሲሉ ከዩራኒየምና ቶሪየም  ከተሰኘ ቁስ አካል ጋር በማደባለቅ ልኩንና ልኬቱን አግኝተዋል፡፡ በዚህም ራዲዮ አክቲቭ ከአቶም ሊገኝ እንደሚችል አረጋግጠዋል፡፡
«እኔ እንደማስበው ዓለም አቀፍ ሥራ በጣም ከባድ ነው፡፡ ቢሆንም ሥራው ወሳኝና አስፈላጊም በመሆኑ ከባድ ነው ተብሎም የሚተውት አይደለም፡፡ ማንኛውንም ጥረት አድርጎና በእውነተኛ መንፈስ መሥዋዕትነት ከፍሎ ለውጤት መብቃት ይቻላል፡፡ ግን ጉዳት ሊኖር ይችላል፡፡ ይህ ግን ጄኔቭ ለእኛ የሚያደርገውን ድጋፍ ከፍተኛ ሊያደርገው ይችላል» የሚል አስተሳሰብ የነበራቸው ሜሪ፤ ግኝታቸው ዘመናዊ ፊዚክስን ለማሳደግና የአቶምን ውስጣዊ አካል ለመመርመር ምክንያት ሆኗቸዋል። እ.ኤ.አ በ1898 በዩራኒየም ውስጥ አዲስ ንጥረ ነገር እንደሚገኝ አረጋግጠዋል፡፡ ከባለቤታቸው ፔሪየ ኩሪየ ጋር በመሆን ፓሎኒየምና ራዲየም የተሰኙ ሁለት አዳዲስ የራዲዮ አክቲቭ ንጥረ ነገሮችን አግኝተዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ1900 ሜሪየ ኩሪየ የአልፋና ኦሜጋ ቀለማት ከራዲዮ አክቲቭ ንጥረ ነገር ሊገኙ እንደሚችሉ የቀመሩትን መላምት መጨረሻ ላይ  እንዳረጋገጡት ተመስክሮላቸዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ1903 ኩሪየ በራዲዮ አክቲቭ ላይ ምርምራቸውን ቀጥለውና አስፋፍተው የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ሠርተዋል:: እ.ኤ.አ በ1896 ኸንሪ ቢኳሬል ያገኘው የሬዲዮ አክቲቭ ውጤት፣ ባልና ሚስቱን ኩሪየንና ሜሪየን በበለጠ ስላነሳሳቸው ባላቸው እውቀት፤ የመመራመርና የመተንተን ጥበብ ተጠቅመው፣ ፖለኒየምና ራዲም የተባሉት ንጥረ ነገሮች የተለያዩ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡ እናም ሳይንቲስቷ ሜሪየ ራዲየም ከራዲዮ አክቲቭ ቅሬት የተለየ መሆኑን በምርምር ደርሰውበታል:: ምርምራቸውንም ወደ ከፍተኛ ደረጃ አሳድገውታል፡፡ ይህ የራዲም ግኝታቸው ሳይንቲስቱ ኤርነስት ሩዘርፎርድ የአቶምን አሠራር ለማግኘትና ለካንሰር በሽታ የራዲቴራፒ ሕክምና ለማድረግ እንደሚቻል መሠረት ሆኖታል፡፡  
ያደረጉት ሳይንሳዊ ምርምር በዓለም ላይ እውቅናን ስላተረፈላቸው ከላይ በተጠቀሰው ዓመት በፊዚክስ የኖቤል ሽልማት አግኝተዋል፡፡ ያገኙት ሽልማት በሳይንስና በሜዲስን ምርምር ለሚያካሂዱ ሳይንቲስቶች ታላቅ ማበረታቻ ሆኗቸዋል:: በሶርቦኔ ዩኒቨርሲቲ ብቸኛ የሴት ፕሮፌሰር የነበሩት ኩሪየ እ.ኤ.አ በ1910 ፒትር የተባለ ተመራማሪ በሜታል ላይ ባካሄደው ምርምር ተጨማሪ ጥናት አድርገው፣ በራዲዮ አክቲቪቲ ውጤታማ ስለሆኑ እ.ኤ.አ በ1911 በኬሚስትሪ ሁለተኛ የኖቤል ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ1993 ከባለቤታቸው ጋር የሮያል ሶሳይቲ ሜዳሊያ ተቀብለዋል:: በ1921 የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ሐርዲንግ በአሜሪካ ሴቶች ስም ለሥራቸው እውቅና ከመስጠቱ በላይ እ.ኤ.አ በ1911 ለሚያደርጉት የሳይንስ ጥናትና ምርምራቸው እንዲጠቀሙበት የአንድ ግራም ራዲም ስጦታ አበርክቷቸዋል፡፡ በሴት ልጅ ደረጃ የመጀመሪያዋ ሆነው በሳይንስ መስክ ያስገኙት የጥናትና ምርምር ውጤት በዘመኑ በሴት ልጅ ላይ የነበረውን የዝቅተኝነት አመለካከት እንዲቀየር ከፍተኛ ተጽዕኖ ፈጥሯል፡፡
ሜሪየ ኩሪየ ከመጀመሪያ ልጃቸው ኢሬኔጋር በመሆንም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በጦር ግንባር የመገናኛ አልግሎት ሊሰጥ የሚችል ተንቀሳቃሽ ራዲዮ ሠርተዋል:: በጦርነቱ ማብቂያ ላይም የኤክስሬይ ጣቢያ አቋቁመው በጦርነቱ የተጎዱና በቁጥር አንድ ሚሊዮን ለሆኑ ቁስለኞችና በሽተኞች የሕክምና አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡ ሜሪየ ኩሪየ በፓሪስ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሮፌሰር የነበሩ ሲሆን ተግባራቸው ሴቶች በሳይንስና ምርምር ዘርፍ ተሰልፈው ውጤታማ ሥራ እንዲሠሩ አነሣሥቷቸዋል:: የሁለተኛው ዓለም ጦርነት እንደተጠናቀቀ እ.ኤ.አ በ1914 በፈረንሳይ ዩኒቨርሲቲ ለተቋቋመው የኩሪየ ላብራቶሪ የራዲየም ተቋም በዲሬክተርነት ተሾመው አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡ ቀደም ሲል ከባለቤታቸው ጋር ሆነው ያካሄዱት ጥናትና ምርምር የላብራቶሪ ቁሳቁስ ባልነበሩበት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ነው፡፡   
ሜሪየ በተቋማቸው አማካይነት አሜሪካንን ለመጎብኘት የሚያስችል ፈንድ (እርዳታ) ለማሰባሰብ  ችለዋል፡፡ ሜሪየ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ ተሰሚነት ነበራቸው፡፡ ሜሪየ ገና በ25 ዓመት ዕድሜ ላይ እያሉ በዘመኑ ከነበሩ ዓለም አቀፍ ምሁራን ዘንድ በርካታ ሽልማቶችንና የክብር ስሞችን አግኝተዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ1920ዎቹ ላይ ዓይናቸውን በመታመማቸው የማየት ችግር ገጥሟቸው ነበር፡፡ ይህንኑ የዓይን ብርሃን ችግር አስመልክተው ፈረንሳይ ውስጥ ይኖሩ ለነበሩት እኅታቸው ደብዳቤ ሲጽፉ፤ «የዓይን ብርሃኔን አጥቼና በነጭ የደም ሴል ማነስ (በሊዩኬሚያ) ሕመም ተይዤ በመሠቃየት ላይ ብገኝም ያለ ላብራቶሪ መኖር አልችልም» ብለዋል፡፡ ሜሪየ በሥነ ጨረር (ራዲየሽን) ላይ ያለ ማቋረጥ ምርምር በማድረጋቸውና ሥራ በመሥራታቸው ምክንያት ጤንነታቸው ለአደጋ በመጋለጡ በ67 ዓመታቸው እንዲያርፉ ምክንያት ሆኖባቸዋል፡፡ የጀመሩትን የምርምር ሥራም ልጃቸው ኢሪኔ ጆላየት ኩሪየ ከባለቤታቸው ከፍሬድሪክ ጆላየት ኩሪየ ጋር በመሆን ሰው ሠራሹን የራዲዮ አክቲቭ በመፈልሰፋቸው እ.ኤ.አ 1935 ሁለቱም ባልና ሚስት የኖቤል ተሸላሚዎች ሆነዋል:: ሜሪየ መላ ሕይወታቸውን ለሳይንስ ሰጥተው በርካታ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ከመሥራታቸው ባሻገር በወቅቱ ራዲየም የተባለውን ቁስ ለመግዛት ይችሉ ዘንድ በአሜሪካ የሳይንስ ወዳጆች ማኅበር  አሳሳቢነት ከአሜሪካው ፕሬዚደንት ሆቨር እ.ኤ.አ በ1929  በተበረከተላቸው የ50 ሺህ ዶላር ስጦታ በትውልድ ሀገራቸው በዋርሶ ከተማ ላብራቶሪ ከፍተዋል፡፡
ባልና ሚስቱ
በመላው ዓለም ውስጥ በሚገኙ ሳይንቲስቶች ሁሉ ይደነቁ የነበሩት ሜሪየ እ.ኤ.አ ከ1911 እስከ ሞቱበት 1922 ድረስ የሶልቫይ ፊዚክስ ምክር ቤት አባል ነበሩ:: እንደዚሁም በተባበሩት መንግሥታት የምሁራን ኅብረት ምክር ቤት አባል ሆነው ሠርተዋል፡፡
.የአቶሚክ ፊዚክስ ቀዳሚዋ ፈልሳፊ የሆኑት ሜሪየ ኩሪየ በዘመናቸው የሠሩዋቸው ሥራዎችና ዝናቸው የአውሮፓ የሳይንስ ጁርናሎችን፤ በርካታ ጋዜጦችንና የመጽሔት ዐምዶችን አጨናንቀዋቸው ነበር:: ከዚህ በተጨማሪ እ.ኤ.አ በ1904 ስለ ሥነ ጨረር የሚያትት መጽሐፍ አሳትመዋል::
ይህም ትውልዱን ለጥናትና ምርምር እንዲነሳሳና ሴቶች በሳይንሳዊ ምርምር ከፍተኛ ውጤት ሊያስመዘግቡ የሚችሉ መሆናቸውን ያስገነዘበ ሲሆን በፊዚክስና በኬሚስትሪ የኖቤል ሽልማት ከተቀበሉ  በኋላ የሕይወት ታሪካቸው አምስተርዳም ውስጥ በተሟላ መልኩ እ.ኤ.አ በ1967 ተጽፎ ለኅትመት በቅቷል፡፡
የሳይንቲስቷ የሜሪየ ኩሪየ የሕይወት ታሪክ የተጻፈው በልጃቸው በኢቭ ኩሪየ ነው፡፡ በኖቤል የኅትመትና የትምህርት መርሐ ግብሮችም ሥራዎቻቸው በስፋት ተብራርተው ይገኛሉ:: እ.ኤ.አ በ1921 በፈረንሳይ በራሳቸው በሜሪ ኩሪየ የተመሰረተው ተቋም፤ እስከዛሬ ድረስ ዋነኛ የካንሰር ማዕከል ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡


Read 1539 times