Saturday, 02 May 2020 13:54

ኮሮና ቫይረስና የጦቢያ ፖለቲከኞች

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(10 votes)

 ከኮቪድ-19 ይልቅ የምርጫው መራዘም ያሳስባቸዋል
                
            በርካታ የዓለም መሪዎች፤ “በሰው ልጅ ላይ የተቃጣ ጦርነት ነው” ብለውታል:: መጀመሪያ ግድም አናንቀውት የነበሩት የታላቋ አገር ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እንኳን ሳይቀሩ ወረርሽኙ ያዋከባቸው ጊዜ “ራሴን የማየው እንደ ጦርነት ዘመን ፕሬዚዳንት ነው” ብለዋል፤ የቫይረሱን አስከፊነት በተግባር ካዩት በኋላ ማለት ነው፡፡ አንዳንድ መሪዎች ደግሞ ‹‹የሰው ልጅ የጋራ ጠላት ነው›› ብለውታል - በአንድ ድምጽ፡፡ የጋራ ጠላት ነው ይበሉት እንጂ ለውጊያው ግን በጋራ አልቆሙም፡፡ ይባስ ብሎም ቫይረሱ ወደ አገራቸው ከገባ በኋላም ቸልታ በማሳየታቸውና እርስ በርስ ወደ መካሰስ በመግባታቸው የታዘብናቸው የታላላቅ አገራት መሪዎች አልጠፉም፡፡ ያኔ ታዲያ ኮቪድ-19 ሥራውን በትጋት እየሰራ ነበር፡፡ የስርጭት መጠኑን ለማስፋትና የጉዳት አቅሙን ለማጎልበት በቂ ጊዜ አገኘ:: በአውሮፓ አገራትና በአሜሪካም ብዙ ህይወት ለማጥፋት በቃ፡፡ አሁንም ድረስ ህይወት ማጥፋቱን ቀጥሎበታል፡፡  
ኮቪድ-19 ህይወትን በመቅጠፍ ብቻ አልተወሰነም፤ የዓለምን ኢኮኖሚ ክፉኛ እያንኮታኮተው ነው፡፡ በነገራችን ላይ ኮሮና የሰው ልጅ ጠላት ብቻ አይደለም:: ኮሮና የሥልጣኔም ጠላት ነው፡፡ ኮሮና የብልጽግናም ጠር ነው፡፡ ኮሮና የቴክኖሎጂ ቀበኛ ነው፡፡ ኮሮና የዲሞክራሲጠበኛ ነው:: የሱ ወዳጆች ድህነትና ጉስቁልና ናቸው:: ዝምድናው ከሞትና ከጥፋት ጋር ነው፡፡ ማናቸውም ወደዚያ የሚያደርሱ መንገዶች ሁሉ ይመቹታል፡፡ የሰውን ደስታ መንጠቅ፣ ተስፋውን ማጨለም፣ ህልሙን መቅጨት፣ ራዕዩን ማዳፈን፣ ጤናውን ማወክ---ደስታው ነው፡፡  
ወዳጆቼ፤ ኮሮናን እንደ ተራ ተርታ በሽታ እንዳታዩት፡፡ በእርግጥም በዘመናችን ከገጠሙን በሽታዎች ሁሉ የከፋ የሰው ልጅ የጋራ ጠላት ነው፡፡ በመላው ዓለም በአራት ወራት ውስጥ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር  ከ3 ሚሊዮን አልፏል፡፡ የሟቾች ቁጥር ከ200ሺ ልቋል፡፡ ከዚህ ውጭ ስንቶቹን ነው ከሥራ ያፈናቀለው? ስንቶቹን ነው ያደኸየው? የስንቱን አገራት ኢኮኖሚ ነው ያደቀቀው? ስንቶቹን ኩባንያዎች ነው በኪሳራ በራቸውን ያዘጋቸው? ስንቱን የኢኮኖሚ ዘርፍ ነው ቆላልፎ ያስቀረው?
ሃቁን ለመናገር -- ኮሮና በሕይወታችንና በእንጀራችን ብቻ አይደለም የመጣው:: በመብትና በነፃነታችንም ጭምር ነው:: በዓለም ታሪክ እንደ ኮረና ያለ የመብትና ነፃነት አፋኝና ደፍጣጭ ታይቶ የሚታወቅ አይመስለኝም - ከኮቪድ - 19 ውጭ! ከቤት አለመውጣት (Stay at home ይሉታል አጠራሩን ሲያሳምሩት!) በሚል ይጀምራል - የነፃነት አፈናው፡፡ ሰርቶ የመኖር መብትንም ይነጥቃል - ቫይረሱ:: ትምህርት የመማር መብትንም ይቀማል:: በመላው ዓለም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ህጻናት ትምህርት አቁመው በየቤታቸው ተከተዋል፡፡ የመሰብሰብና የመደራጀት፣ ምርጫ የማካሄድ፣ ድምጽ የመስጠት፣ በአደባባይ ተቃውሞንና ድጋፍን የመግለጽ ወዘተ-- ሕገ መንግሥታዊ መብቶችንም ይደፈጥጣል - ኮሮና፡፡ በመላው ዓለም 18 የሚደርሱ አገራት የምርጫ ጊዜያቸውን በኮሮና ምክንያት ለማራዘም ተገደዋል፡፡ የእኛንም ጨምሮ ማለት ነው፡፡ (ከኮሮና ጎን ለጎን ምርጫው እንዲካሄድ የሚፈልጉ ደፋር ፖለቲከኞች ቢኖሩም!)
ትናንሽ የሚመስሉ ነፃነቶችንም በብዛት አጥተናል፤ ተነጥቀናል፡፡ እንዘርዝራቸው፡- የመጨባበጥ፣ የመሳሳም፣ የመተቃቀፍ፣ የመጐራረስ፣ የመጠያየቅ (እናትንም ጨምሮ) ነፃነታችን ጠራርጎ ወስድቦናል:: ሌላው ቀርቶ የስንት ዘመን ጥሬ ሥጋ የመብላት ኢትዮጵያዊ ባህላችንንም አልተወልንም፡፡ እግር ኳስ ለመመልከት ስቴዲየም መግባት፣ ትያትርና ፊልም ማየት፣ የኪነ ጥበብ ምሽት መታደም ታሪክ ሆነዋል:: በትዝታ የምናወራቸው፡፡ ዕድሜ ለኮሮና ቫይረስ!
ተጨማሪ የሰብአዊ መብት ገደቦችን የሚጥለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የወጣው በማነው? በጠ/ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥት ነው እንዳትሉኝና እንዳታስቁኝ፡፡ (ከመቃወም ውጭ ሙያ የሌላቸው ቢሉ አይገርመኝም!) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ ሰበቡ ሌላ ሳይሆን ኮሮና ነው!! በእኛ አይነቱ ታዳጊ አገር ብቻ ሳይሆን የነፃነት አገር በምትባለዋ አሜሪካ ሳይቀር የዜጐችን የማይደፈር መብትና ነፃነት ተጋፍቷል - ቫይረሱ፡፡
ወዳጆቼ፤ ኮሮና ቫይረስ የነጠቀንን መብትና ነፃነት ከመዘርዘር ይልቅ ያልነጠቀንን ብንዘረዝር ሳይቀል አይቀርም:: ድል ያለ ሰርግ ደግሶ ትዳር መመስረት አይፈቀድም - በዘመነ ኮሮና፡፡ ቀብርና ልደትም ቅንጦት ሆኗል፡፡  
ነጋዴዎች ነግደው ማትረፍ አይችሉም፡፡ መብታቸውን በጠራራ ፀሐይ ተነጥቀዋል:: ሆቴሎች እንግዶችን ተቀብለው አያስተናግዱም፡፡ ስብሰባዎች በመታገዳቸው የአዳራሽ ገቢ እንኳን አያገኙም፡፡ ሰርግ የለም፤ ስብሰባ የለም፤ ኮንሰርት የለም፤ የፓርቲ ጉባኤ የለም፤ ሴሚናር የለም፤ኤግዚቢሽን የለም፤የፋሽን ትርኢት የለም፡፡ ያማሩና የተቀናጡ የመኝታ ክፍሎቻቸው ኦናቸውን እያደሩ ነው፡፡ እንግዶች የሉም፡፡ አሁን ያለው ምን መሰላችሁ? ምንም! ከኮሮና ውጭ ምንም የለም፡፡  
እኔ የምለው ግን፣ በዚህ ሁሉ መሃል፣ መቶ ምናምን ይደርሳሉ የተባሉት የጦቢያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፤ በዘመነ ኮሮና የት ገቡ? ከኮሮና በኋላ ድምጻቸውን ሰምቼ አላውቅም፡፡(ተደበቁ እንዴ?) ቢደበቁም አይፈረድባቸውም፡፡ ዕድሜ ልካቸውን እርስ በርስ ሲታገሉ ኖረው፣ ቤተ መንግስት ሊገቡ ትንሽ ሲቀራቸው በኮሮና ህልማቸው መቀጨት የለበትም፡፡ በአካል መደበቃቸው ምንም አልነበረም፤ድምፃቸውን ግን ማሰማት ነበረባቸው፡፡ እነሱ ግን ዝም ጭጭ አሉ፡፡ የትግራይ ክልሉ ገዢ ፓርቲ ህወኃትና ሳልሳይ ወያኔ የተባለው ተፎካካሪ ይሁን “ተባባሪ” ፓርቲ፤ ምርጫው በነሐሴ ካልተካሄደ ሞተን እንገኛለን ማለታቸው ያስገርማል፡፡ ገዳይ ወረርሽኝ አገር ውስጥ ገብቷል እየተባሉ፣ ለምርጫ ሞተን እንገኛለን ማለት ምን ማለት ነው? ሥልጣንም እኮ በህይወት ሲኖረን ነው፡፡ በነገራችን ላይ ሥልጣን ብቻ ሳይሆን የራስን ዕድል በራስ መወሰን በሉት፣ ሕገ መንግስት ማሻሻል ወይም ሌሎች ፖለቲካዊ ጉዳዮች---ሁሉም እዬዬ ሲዳላ ነው፡፡  ሕዝብ በሕይወት ሲኖር - አገር ከቀውስ ስትሻገር ነው ትርጉም ያለው!
ወዳጆቼ፡- ኮሮና ቫይረስ የእምነት መብታችንንም ጭምር ገፎናል፡፡ ፀሎትና ምህላ በቤተ እምነት ተገኝተን ሳይሆን በቴሌቪዥን የቀጥታ ሥርጭት ከቤታችን ሆነን እንድንከውን ተገደናል፡፡ የመስጂዶችና ቤተ ክርስትያናት ደጃፎች ተከርችመዋል፡፡ ታዲያ ከዚህ በላይ የመብትና ነፃነት ጥሰት ከየት ይመጣል?!  
በነገራችን ላይ ኮሮና የሰው ልጅን በጤንነት የመኖርና የጤና ክብካቤ የማግኘት መብት ሁሉ ነጥቆታል፡፡ የኮሮና ወረርሽኝ ከመጣ ወዲህ እኮ ሌሎች የበሽታ ዓይነቶች ትኩረት ተነፍገዋል፡፡ በሌሎች በሽታዎች የሚሞቱ ሰዎች ሁሉ የተዘነጉ ይመስላሉ፡፡ ቅድምያ ለኮሮና እየተባለ ስንቱ እኮ በማይገድል በሽታ እየሞተ ነው:: ዕድሜያቸው የገፋ የቫይረሱ ተጠቂዎች የመዳን ዕድላቸው አናሳ ነው በሚል (በቬንትሌተርና የመተንፈሻ መሳሪያዎች እጥረት ሳቢያ) የቅድምያ ትኩረት ለወጣቱና ለብርቱዎቹ እየተሰጠ በመሆኑ በአረጋውያን ላይ የሞት ፍርድ እየተፈረደባቸው መሆኑን እየሰማን ነው፡፡
እናላችሁ…የኮሮና ቫይረስ እንዲህ እንዳሻው እየፈነጨ ባለበት በዚህ ወቅት፤ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ከወዴት ገቡ? የሃገሬ ተቃዋሚዎች የት ተሸሸጉ? መንግስት መብት ጣሰ፣ ነጻነት አፈነ፣ የፖለቲካ ምህዳር አጠበበ እያሉ በመግለጫ የሚያጥለቀልቁን ተፎካካሪ ፓርቲዎች፤ በኮሮና ላይ አንዲት እንኳን የአቋም መግለጫ እንዴት ማውጣት አቃታቸው? (ከልባቸው ባይሆንም ማለቴ ነው!) በየግላቸው ባይሆንላቸው እንኳን አንድ የጋራ መግለጫ እንዴት አያወጡም? የዜጎች የመብትና ነፃነት ጥሰቶች አያገባንም ቢሉ እንኳን በጉጉት ሲጠብቁት የነበረውን ምርጫ ድንገት መጥቶ ሲያራዝምባቸው እንዴት አያወግዙትም? (ወደ ሥልጣን የሚያደርሳቸው ብቸኛው መንገድ እኮ ነው!) በመሳሪያ ሥልጣን መቆናጠጥ እንደሆነ ያለፈበት ፋሽን ሆኗል - ያልሰሙ ሃይሎች ቢኖሩም፡፡
እርግጥ ነው የተቃዋሚዎች አጀንዳ የተለየ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ብዙ ጊዜ የህዝብ መፈናቀል፣ የሥራ አጥ ዜጐች ቁጥር መጨመር፣ በእርዳታ እህል የሚኖሩ ሰዎች ጉዳይ፣ የትምህርት ጥራት ማሽቆልቆል፣ የዋጋ ግሽበት፣ የታክስ ቅነሳ ወዘተ-- የመሳሰሉት የተቃዋሚዎችን ትኩረት አይስብም:: የብዙዎቹ የፖለቲካ ሃይሎች ትኩረትና ዋና አጀንዳ ምርጫ ነው (ሂደቱ ሳይሆን ውጤቱ!) ከምርጫም ቢሆን የሚፈልጉት ዲሞክራሲያዊ ሂደቱን አይደለም፡፡ ዜጐች በመረጡት አካል የመመራታቸውም ጉዳይ አያሳስባቸውም፡፡ እነሱ የሚሹት ሥልጣን ነው፡፡ በተራቸው ቤተ መንግስት መግባት ነው ጥማታቸው፡፡ የሽግግር መንግስት መመስረትን የሚያቀነቅኑም አሉ - አቋራጭ የሥልጣን መንገድ በመሆኑ፡፡ ብሔራዊ እርቅና መግባባትን የሚሰብኩም አልጠፉም - አምነውበት ሳይሆን የሚሉት በማጣታቸው ብቻ!
እናላችሁ---በኮቪድ ሳቢያ ጠፍተው የከረሙት የጦቢያ ፓርቲዎች፤ባለፈው ሳምንት ድንገት በቴሌቪዥን መስኮት ከች ብለው አስደነገጡን፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በምርጫው መራዘምና አገራዊ መንግስቱን በሚያስቀጥሉ የህገ መንግስት አማራጮች ላይ ከሥልጣን ተፎካካሪያቸው ብልጽግና ጋር ሊወያዩ ነው!! (የልብ ትርታቸው የሆነውን የሥልጣን ጉዳይ!) አይፈረድባቸውም፡፡ ሲታገሉ የኖሩት ለሥልጣን ነው፡፡ (ለህዝባችን መብትና ጥቅም ነው እያሉ ቢፎግሩንም!)
አያችሁ የጦቢያ ፖለቲከኞች ዓላማ የህዝብን ህይወት ከኮረና መታደግ አይደለም፡፡ ሰብዓዊ መብቶችንም ማስከበር ሆኖ አያውቅም፡፡ (ተሳስቼ ይሆን?) ከሆነም እንግዲህ እናየዋለን፡፡ ኮቪድ 19… ፖለቲከኞቻችንን ትዝብት ላይ ሊጥል እነሆ በአገራችን ተከስቷል፡፡ ከሰብአዊ መብት ተሟጋቾችና ከፖለቲካ ፓርቲዎች ቁርጠኛ ምላሽ ይጠበቃል፡፡
በነገራችን ላይ ወረርሽኙን መከላከልም ሆነ ምርጫውን ጎን ለጎን ማድረግ ይቻላል እያሉ ደቡብ ኮሪያን በምሳሌነት የሚጠቅሱ ፖለቲከኞች አጋጥመውኛል፡፡ ግን እያፌዙ ነው የመሰለኝ፡፡ ጦቢያና ደቡብ ኮሪያ በምን ይገናኛሉ? አንድ ጥያቄ እግረ መንገዴን ጣል ላድርግ፡- ለመሆኑ ከኮቪድ-19 እና ከምርጫው የበለጠ ስጋት ላይ የሚጥለን የትኛው ይመስላችኋል? መልካሙን ጊዜ ያምጣልን! ኮሮናን ያጥፋልን! ከዘር ፖለቲካ ያውጣን!  
ጽሁፌን ከመቋጨቴ በፊት ግን ምስጋና የሚገባቸውን ላመስግን፡፡ የጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር ዓለም አቀፉን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የያዘበት መንገድ በብዙዎች ዘንድ ምስጋናም አድናቆትም አስገኝቶለታል:: ይገባዋል፡፡ በኮሮና ወረርሽኝ ማግስት በኢኮኖሚው ላይ ለሚደርሰው ቀውስም ለጦቢያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ጭምር ከወዲሁ መፍትሔ ለማበጀት የሚያደርገው ጥረትም አስደማሚ ነው (ጠ/ሚኒስትሩ በፋይናንሻል ታይምስና ብሎምበርግ ላይ ለዓለማቀፉ ማህበረሰብ ያቀረቧቸውን የድጋፍ ጥያቄዎች ጨምሮ) ኢትዮጵያ ለዓለም በአርአያነት የሚጠቀስ አመራር እየሰጠች ነው ማለት ይቻላል፤ኮሮናን በመዋጋት ረገድ:: ስኬታማው አየር መንገዳችን ከቻይናም ሆነ ከሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ለአፍሪካ በእርዳታ የሚለገሱ የህክምና መሳሪያዎች እርዳታን እንዲያከፋፍል መመረጡም ቀላል ነገር አይደለም፡፡ የኮሮና መርገምትን ወደ በረከት እየለወጥነው ይሆን? ያድርግልን! ያድርግልን!



Read 4095 times