Tuesday, 05 May 2020 00:00

ምርጫ ማራዘምና መንግስትን የማስቀጠል ህገ መንግስታዊ አማራጮች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 • ክልሎች ለብቻቸው ምርጫ ማካሄድ የሚችሉበት የህገ መንግስት አግባብ የለም
  • ጠ/ሚኒስትሩ የአገሪቱን መንግሥት ለማስቀጠል በርካታ አማራጮች አሏቸው

       የትግራይ ክልላዊ መንግስት በህገ መንግስቱ መሠረት ዘንድሮ ምርጫ የማይካሄድ ከሆነ በክልል ደረጃ የራሱን ምርጫ ሊያካሂድ እንደሚችል መግለፁን ተከትሎ በርካቶች በማህበራዊ ሚዲያ አስተያየት ሲሰጡበት ሰንብተዋል፡፡ የኮሮና ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ ከምርጫው መራዘም ጋር በተያያዘ ሰሞኑን ገዥው ፓርቲና ተፎካካሪዎች የአገሪቱን መንግስት በማስቀጠል አማራጮች ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡ ለመሆኑ የምርጫ ጊዜንና ሁኔታን የመወሰን ስልጣን ያለው ማን ነው? ቀጣዩን ምርጫ ህገ መንግስትን መሠረት አድርጐ እንዴት ማካሄድ ይቻላል? ክልሎች ከፌደራሉ መንግስት ውጭ የራሳቸውን ምርጫ ማካሄድ የሚችሉበት የህገ መንግስት አግባብ ይኖር ይሆን? በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ የቀድሞ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባልና የህግ ባለሙያውን አቶ ወንድሙ ኢብሣን  እንደሚከተለው አነጋግሯቸዋል፡፡ ማብራሪያቸውን ከህገ መንግስቱ ይጀምራሉ፡፡
 
        እንደሚታወቀው ይሄ ሀገር እንደ ሌሎች ሀገሮች ሁሉ የተፃፈ ህገ መንግስት አለው፡፡ ይህ ህገ መንግስት በገዥዎች አይከበር እንጂ ብዙ በሰብአዊነት የቆሙ አንቀፆች ያሉት ነው፡፡ ወደ 31 የሚደርሱ አንቀፆቹ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብትን የተመለከቱ ናቸው፡፡ ህገ መንግስቱ ካሉት 106 አንቀፆች መካከል ስለ ምርጫና ቦርዱ የተደነገገው በአንቀጽ 102 ላይ ነው የሚገኘው፡፡ አንቀጽ 102 ምንድን ነው የሚለው ከተባለ፤ በፌደራልና በክልል የምርጫ ክልሎች ነፃና ትክክለኛ ምርጫ በገለልተኝነት እንዲያካሂድ፣ ከማንኛውም ተጽእኖ ነፃ የሆነ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ይቋቋማል ይላል፡፡ በፌደራል ደረጃ አንድ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይቋቋማል ነው የሚለው ህገ መንግስቱ፡፡ በዚሁ የምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 2፣ የቦርዱ አባላት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት እንደሚሾሙ ይደነግጋል፡፡ እስካሁን ይሄ የህግ ሂደት ተፈጽሟል፡፡ ስለዚህ ክልሎች የራሳቸውን የምርጫ ቦርድ የማቋቋምም ሆነ ከፌደራሉ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ሂደት ውጭ ምርጫ ማካሄድ የሚችሉበት የህገ መንግስት አግባብ የለም፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን አሁን ያለነው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር ነው፡፡ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ በሚገባበት ጊዜ የህገ መንግስቱ አንቀጽ 93 ነው ሙሉ ለሙሉ የሚተገበረው፡፡
ህገ መንግስቱ 106 አንቀፆችና 481 ንኡስ አንቀፆች ያሉት ነው፡፡ ይሄ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚደነግግበት አንቀጽ 93 ከአራት የህገ መንግስቱ አንቀፆች ውጭ ያሉ አንቀፆችንና ንዑስ አንቀፆችን በሙሉ የሚያግድ ነው፡፡ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የማይነካቸው አንቀፆች አራት ብቻ ናቸው፡፡ እነዚህ አንቀፆች አንደኛው አንቀጽ 1 ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህገ መንግስት ስያሜን የተመለከተው ማለት ነው፡፡ ሌላኛው አንቀጽ 18 ነው፡፡ ይህ አንቀጽ ኢ-ሠብአዊ አያያዝን የሚከለክል ነው፡፡ ይህ አንቀጽ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አይደፈርም፡፡ ሌላኛው አንቀጽ 25 ነው፡፡ ይህ አንቀጽ የእኩልነት መብት ነው፡፡ አራተኛው አንቀጽ 39 ነው፡፡ አንቀጽ 39 በሙሉ ሳይሆን የአንቀጽ 39 ንዑስ አንቀጽ 1 እና 2 ናቸው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የማይነኩት፡፡ ስለዚህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን የሚደነግገው አንቀጽ 93፤ ከእነዚህ አንቀፆች ውጪ ያለውን በሙሉ ማገድ ይችላል ማለት ነው፡፡ ይሄ ማለት እንግዲህ የምርጫ ሁኔታም እንበለው ስለ ቦርድ የተደነገገውን በሙሉ ማገድ ይችላል ማለት ነው፡፡ ይሄን አዋጅ ደግሞ የማስፈፀም ብቸኛ ስልጣን የተሰጠው ለፖሊስ፣ ሚሊሻ፣ ለክልል ሃይል አይደለም፤ የሀገሪቱ ሉአላዊነት ዘብ ለሆነው መከላከያ ሠራዊት ነው፡፡ ስለ መከላከያ ሰራዊት መርሆዎች የሚያትተው የህገመንግስቱ አንቀጽ 87 ንዑስ አንቀጽ 3 እና 4 ስለ መከላከያ ሠራዊት ስልጣንና ኃላፊነት በሚገባ ይደነግጋሉ፡፡
በንዑስ አንቀጽ 3 የመከላከያ ሠራዊት፣ የሀገሪቱን ሉአላዊነት ከመጠበቅ በተጨማሪ በዚህ ህገ መንግስት መሠረት፣ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚሰጡትን ተግባሮች ያከናውናል ይላል፡፡ ንዑስ አንቀጽ 4 ደግሞ የመከላከያ ሠራዊቱ በማናቸውም ጊዜ ለህገ መንግስቱ ተገዥ ይሆናል ይላል፡፡ ስለዚህ የመከላከያ ሠራዊቱ ዋነኛ አላማ የሀገሪቷን ሉአላዊነት መጠበቅ ነው ማለት ነው፡፡ በዚህ ኃላፊነቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚሰጡትን ተግባሮች በሙሉ ያከናውናል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የማይቀበል፣ የምርጫ ቦርድን ስልጣንና ኃላፊነት የማይቀበል ክልል ካለ፣ ጉዳዩ ከሀገሪቷ ሉአላዊነት ጋር የሚጋጭ ስለሆነ መከላከያ ሠራዊት ኃላፊነቱን ይወጣል ማለት ነው፡፡ ክልሉ የራሴን ምርጫ አካሂዳለሁ ብሎ ሲነሳ በቀጥታ የሀገሪቷን ሉአላዊነት እየናደ ነው፡፡ ሀገሪቷ ደግሞ ዋና ተግባሩ ሉአላዊነትን ማስጠበቅ የሆነ መከላከያ ሠራዊት አላት፡፡ ከዚህ አንፃር ጉዳዩ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁና ለመከላከያ በተሰጠው ስልጣን ላይ ያረፈ ይሆናል፡፡
ምርጫ የሚካሄድበትን ጊዜና ሁኔታ ወሳኙ ማን ነው? የትኛው አካል ነው በህገ መንግስቱ የመወሰን ስልጣን ያለው?   
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ ያጋጠሙትን ችግሮች ዘርዝሮ ያቀርባል፣ ምክር ቤቱ ይወያይበትና ውሳኔ ይሰጥበታል፡፡ ምርጫውን ማራዘም ተገቢ ሆኖ ካገኘው፣ ፓርላማው የማራዘም ብቸኛ ስልጣን ይኖረዋል፡፡ ምርጫ ቦርድ ተጠሪነቱ ለህዝብ ተወካዮች እንደመሆኑ፣ የህዝብ ተወካዮች ያሳለፈውን ውሣኔ የማስፈፀም ሃላፊነቱን ይወጣል ማለት ነው፡፡ በሀገሪቷ ውስጥ የመጨረሻ ስልጣን ያለው አካል የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት መሆኑንም መዘንጋት የለብንም፡፡ የፌደራል መንግስትም፣ ስራ አስፈፃሚውም፣ ክልሎችም ስልጣናቸው ከህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ውሳኔዎች በታች ነው፡፡
ሰው ልብ ብሎ መገንዘብ ያለበት፣ አሁን ያለንበትን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገጊያ አንቀጽ 93 ስር የተዘረዘሩትን ጉዳዮች ነው፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚፈጽመው ስራ አስፈፃሚው ሲሆን የሚያስፈጽመው ደግሞ የሀገሪቷን ሉአላዊነት የመጠበቅ ብቸኛ ስልጣን ያለው የመከላከያ ሠራዊት ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ያሉ እንቅስቃሴዎች በቀጥታ በዚህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ የሀገሪቱን ሉአላዊነት የማስከበር ኃላፊነት ከተሰጠው የመከላከያ ሰራዊት ጋር የተያያዘ ይሆናል ማለት ነው፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከማያግዳቸው የሕገ መንግሥቱ አንቀፆች አንዱ የብሄር ብሄረሰቦች መብት የራስን እድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል ድረስ የሚደነግገውን አንቀጽ 39 ነው፡፡ ይሄንን ተጠቅሞ መገንጠል አሊያም የራስን ምርጫ ማካሄድ ይቻላል? እንዲህ ያለ ጥያቄ ቢነሳስ እንዴት ይስተናገዳል?
አንቀፅ 39 ንዑስ አንቀጽ 1 እና 2 በዚህ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አይነኩም፡፡ እርግጥ ነው ገደቡም ሊደረግባቸው አይችልም፡፡ ነገር ግን በዚህን ወቅት የራስን እድል በራስ እንወስናለን እንገነጠላለን ብሎ መነሳት በቀጥታ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለመከላከያ ሰራዊቱ ከተሰጠው ስልጣን ጋር መጋጨት ነው የሚሆነው፡፡ መከላከያው የአገር ሉዓላዊነትን መጠበቅ አለበት፡፡ በዚያው ልክ የራስን ዕድል በራስ መወሰን ሲባል ደግሞ በህገ መንግሥቱ የተቀመጠ የራሱ ሂደት አለው፡፡ ያንን ሂደትና ሥርዓት ጠብቆ ነው ሊፈፀም የሚችለው እንጂ በሃይል “በቃ ከዛሬ ጀምሮ ተገንጥያለሁ” ማለት አይቻልም። በቀጥታ ከመከላከያ ሠራዊት ጋር ያጋጫል፡፡ አንድ አካል ይህን አንቀፅ ተጠቅሞ መገንጠል ቢፈልግ፣ ከፌደራል መንግሥት ጋር መወያየት እንዳለበት ሕገ መንግሥቱ ይደነግጋል፤ ሕዝበ ውሳኔ፣ የምክር ቤት 2/3ኛ ድምፅ የመሳሳሉ ሂደቶች አሉ፤ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 4 ስር የተደነገጉ፡፡ ይህ የአፈጻጸም ሂደቶችን የሚዘረዝረው ንዑስ አንቀጽ 4 ደግሞ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገጊያ አንቀጽ 93 መሰረት ከሚታገዱት አንቀጾች አንዱ ነው፡፡ ታዲያ እንዴት በዚህ ጊዜ ውስጥ የራስን እድል በራስ መወሰን ይቻላል? ፈጽሞ አይቻልም። ሕጉም ለዚህ ክፍተት የለውም፡፡ ሌላው እግረ መንገድ መታወቅ ያለበት፣ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብትን ተጠቅሞ የመገንጠል ጉዳይ፣ እስከ 3 ዓመት ሊፈጅ የሚችል ሂደት እንዳለው፣ በሕገ መንግሥቱ መደንገጉን ነው፡፡ ከዚህ ውጪ በጉልበት ልሂድ ከተባለ የመከላከያን ስልጣን መንካት ይሆናል፡፡ በዚህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሰረት፤ አንዲት ቀበሌ እንኳ ከአገሪቱ ዳር ድንበር ፈቀቅ ማለት አትችልም፡፡ ይሄን ሉዓላዊነት የማስከበር ሥልጣን ሙሉ ለሙሉ የመከላከያው ነው፡፡ ሚሊሻ፣ ፖሊስ፣ የክልል ልዩ ሀይል ምንም ቦታ አይኖራቸውም፡፡
በዚህ ሁኔታ ውስጥ አንድ ክልል የራሱን ክልላዊ ምርጫ ማካሄድ የሚችልባቸው የሕግ ክፍተቶች የሉም?
ፈጽሞ የለም፡፡ ምንም ዓይነት የመከራከሪያ የሕግ ምክንያትና የሕግ መሰረት የለም፡፡ በሕገ መንግሥቱም ሆነ በአጠቃላይ በአገሪቱ ሕጎች ወይም ልማዳዊ ነገሮች ውስጥ የለም፡፡ ከሕግ ውጪ በሆነ አካሄድ ደግሞ ያው ጉልበት ነው ማለት ነው፡፡ አሁን ያለው ጉዳይ እንደኔ ከሆነ፣ ዝም ብሎ የፖለቲካ ጫጫታ እንጂ ሕጋዊ መሰረት ያለው መከራከሪያን የያዘ አይደለም፡፡ በጉልበት የሚካሄድ ከሆነ ግን መከላከያ በሕገ መንግሥቱ መሰረት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ይገደዳል፡፡ በአለማቀፍ ሕግም፣ ይህን የሕግ ጥሰት የፈፀመው አካል ድጋፍ አያገኝም ማለት ነው፡፡
የፌደራሉ መንግሥት ቀጣዩን ምርጫ በምን አግባብ ነው ሕገ መንግሥታዊ መሰረት አስይዞ ማካሄድ የሚችለው?
እስካሁን በኢትዮጵያ ውስጥ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጁት በሁለት ምክንያቶች ብቻ ነው። አንደኛ፤ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲፈጠርና በተለመደው መደበኛ ሕግ ማስተዳደር ሲያቅት ሲሆን ከእነዚህ ውጪ እስከ ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ በዚህ ሕገ መንግሥት መሰረት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታወጆ አያውቅም፡፡ አሁን ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ሕብረተሰብን አደጋ ላይ በሚጥል በሽታና ወረርሽኝ ምክንያት የታወጀው፡፡ ይህንንም ሁኔታ እንዲሁ መገንዘብ አለብን፡፡ እንግዲህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊቆይ የሚችለው ለ6 ወር ብቻ ነው። ከዚያ በኋላ ለ4 ወር ማራዘም ይቻላል። አሁን እኛ አገር የታወጀው ለ5 ወራት የሚቆይ ነው፡፡ ካልተራዘመ ከ5 ወር በኋላ ያበቃል ማለት ነው፡፡ እዚህ ጋ በተደጋጋሚ የሚነሳው ጥያቄ ፓርላማው ዘመኑ ካለቀ ማን ያራዝመዋል? የሚለው ነው፡፡ እዚህ ጋ የሕግ ክፍተት ያለው ይመስላል፡፡ ነገር ግን ይሄን የሕግ ክፍተት ራሱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀበት አንቀጽ 93 ይፈታዋል፡።
እንዴት አድርጎ ይፈታዋል?
እንግዲህ አንድ መንግሥት ሶስት አካላት ይኖሩታል፡፡ ሕግ አውጪ፣ ሕግ ተርጓሚና፣ ሕግ አስፈጻሚ፡፡ ከእነዚህ መካከል ሕግ ተርጓሚና ሕግ አስፈፃሚ ናቸው የመጨረሻዎቹ ወሳኞች፡፡ ሕግ አውጪው ሊቀርም ይችላል። ይህ ማለት ፓርላማው ማለት ነው። ደርግ ለ11 ዓመት ያለ ፓርላማ ነበር አገሪቱን የመራው። ፓርላማውን መበተን የሚቻልበት አንቀጽም በሕገ መንግሥቱ ተቀምጧል፡፡ ስለዚህ ሕግ አውጪውን ገለል አድርጎ፣ በሕግ ተርጓሚና አስፈጻሚ ብቻ አገርም መምራት ይቻላል ማለት ነው። ስለዚህ አንዱ ሕገ መንግሥታዊ አካሄድ፣ ፓርላማው የሥራ ዘመኑ ከመጠናቀቁ በፊት አገር በቀጣይ ልትመራ የምትችልበትን አግባብ በሕግ ደንግጎ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚያቀርቡለት ሀሳብ ሊበተን ይችላል፡፡ ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ ፓርላማው አልበተንም ማለትም ይችላሉ፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ ፓርላማውን ይበትናል የሚል ድንጋጌ በሕገ መንግሥቱ አለ፤ ግን ጠ/ሚኒስትሩ ይሄን የሚያደርገው ራሱ ፓርላማውን አስፈቅዶ ነው፡፡ ፓርላማው “እኔ አልበትንም፤ አገሪቷ ችግር ውስጥ ናት፤ አገሪቷን አደጋ ላይ ጥዬ አልሄድም፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እስከሚያልቅ በዚሁ እቀጥላለሁ” ካለ ይችላል፡፡ ምክንያቱም አንቀጽ 93 ስለሆነ አገር የሚያስተዳድረው፡፡ አንቀጽ 93 ደግሞ በፓርላማው መሻሻልም ከፍ ዝቅ ማለትም ይችላል፡፡ ስለዚህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕገ መንግሥቱ መሰረት፤ የአገሪቱን መንግሥት ለማስቀጠል በርካታ አማራጮች አሏቸው። ፓርላማውን በፍቃደኝነት መበተን፣ ካልተበተነም አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እያራዘመ     
ምርጫም ሆነ ሌሎች ነገሮችን ማዘጋጀት ይቻላል፡፡
ፓርላማው እንዴት ነው አልበተንም ማለት የሚችለው? ትንሽ ቢያብራሩልን?
የፓርላማውን የጊዜ ዘመን የሚደነግገው አንቀጽ 58 ነው፡፡ ይሄን አንቀጽ 58 የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ይገድበዋል፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ መበተንም የሚችለው በምክር ቤቱ ፈቃድ ነው፡፡ የህገ መንግስቱ አንቀጽ 60 ንዑስ አንቀጽ 1 እንዲህ ነው የሚደነግገው፡- ጠቅላይ ሚኒስትሩ የስልጣን ዘመኑ ከማለቁ በፊት አዲስ ምርጫ ለማካሄድ በምክር ቤቱ ፈቃድ ምክር ቤቱ እንዲበተን ለማድረግ ይችላል፤ ነው የሚለው፡፡ ምክር ቤቱ መበተን አልፈቅድም ካለስ? ሀገሪቷ አደጋ ላይ ነች፤ ለአደጋ አጋልጬ አልበተንም እቀጥላለሁ ቢልስ? አንቀፆችን ማሻሻል ይችላል ማለት ነው፤ የህገ መንግስቱንም አንቀጽ 93 ጨምሮ ማሻሻል ይችላል፡፡ እበተናለሁ ብሎ ካሰበም፣ ከመበተኑ በፊት ለሀገሪቱ ቀጣይነት ይበጃሉ የሚላቸውን ህጐች አውጥቶ ሊበተን ይችላል፡፡ ሌላኛው አማራጭ አሁን ያለው ስራ አስፈፃሚና ህግ ተርጓሚ ከፓርቲዎች ጋር ተነጋግረው፣ የብሔራዊ አንድነት መንግስት መመስረት  ነው፡፡

Read 7905 times