Monday, 04 May 2020 00:00

የባቢሎን መንግስት ለማቋቋም?

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(1 Vote)

   “-- ኮሮና የሚባል የሰው ልጆች ሁሉ ጠላት ፊት ለፊታችን ተገትሮ፣ውጊያውን በሚገባ እንዳንዋጋ ነጋዴዎች ገበያውን ተቆርቋሪ በመምሰል እያምታቱ ነው፡፡ እነዚህ ነጋዴዎች ወረርሺኙን መንግስት አመጣው ከማለት ያልተናነሰ ወሬ መንዛታቸው ሌላው አስገራሚ ነገር ነው፡፡--”
            
               ብዙ ጊዜ ከሰማኋቸው ቀልድ መሰል ቁምነገሮች ሰሞኑን ትዝ እንዲለኝ የተገደድኩበት ነገር እያሳቀኝም እየገረመኝም ለዛሬው መጣጥፌ መነሻ ላደርገው ነው፡፡ ጉዳዩ ከጦርነት ጋር የተያያዘ ነው፤ባንድ ሀገር ላይ ጦርነት እየተካሄደ ጀግና ሲወድቅና ሲጥል፣ በጦርነቱ ውስጥ ሸቀጥ የሚሸጡ ሰዎች ወደ ግንባር ገብተው ነበር አሉ:: ነጋዴዎቹን በጦር ግንባር ላያቸው ሰው ተዋጊ፣ ለሀገር ግድ የሚላቸው ይመስላሉ፡፡ ይሁን እንጂ እነርሱ ያንን አጋጣሚ ለንግድ የሚጠቀሙ እንጂ የሀገር ነገር ግድ የሚላቸው አልነበሩም፡፡ እንዲያውም አንዳንድ የባሰባቸው፣ ጦር ሜዳው ላይ የሚሸጥ ነገር ይዘው፣ ብር ላለው በብሩ፣ለሌለው በሰዐቱና በወርቁ  ይቸበችቡ ነበር፡፡
ሀገሩን የሚወድድ፣ታሪኩን የሚያቀና ዜጋ ግን በክፉ ቀን የሚነግድበት ሕሊና የለውም፤ይልቅስ ነፍሱን ጭምር ለሀገሩ ይሰጣል፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ የዚህ ዐይነት ልበ ቀናዎች ነበሩ፡፡ ደማቸውን አፍስሰው ሀገር ያኖሩ ብዙ ናቸው፡፡ ባንዳዎችም ነበሩ፡፡ አለቃ ብሩ ደብተራውን የመሳሰሉ፣ ለሳንቲምና ለጥቅማጥቅም ራሳቸውን ሸጠው ዮሃንስን ከቱርክና ከግብጽ ጋር ሆነው ወግተው አልበቃ ሲላቸው፣ በምኒልክ ዘመነ መንግስት የዐድዋ ዘማቾችን ሊያጠፉ ሲሉ በዐውሳው ባላባት ቀብራቸው ውስጥ የገቡ ጨካኞች አሉ፡፡
በዐጼ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት፣ ሚኒስትር ሳይቀር ከድተው፣ ለጠላት ፕሮፓጋንዳ የሰሩና ሲመከሩ ‹‹ልጆቼን ላሳድግ›› ያሉ እንደነበሩ፣ ራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሃብተወልድ ለደርጉ መርማሪ ኮሚሽን ባቀረቡት ጽሁፍ ላይ አስፍረውታል፡፡ “የሃበሻ ጀብዱ” የሚለውን መጽሐፍ ስናነብብም፣ ሀገራችንን ለጠላት አሳልፈው የሰጧት የገዛ ልጆችዋ እንደሆኑ እንገነዘባለን፡፡
ያ ታሪክ በዚያ አላበቃም፤አሁንም ፊታችን ተገትሯል፡፡ ኮሮና የሚባል የሰው ልጆች ሁሉ ጠላት ፊት ለፊታችን ተገትሮ፣ውጊያውን በሚገባ እንዳንዋጋ ነጋዴዎች ገበያውን ተቆርቋሪ በመምሰል እያምታቱ ነው፡፡ እነዚህ ነጋዴዎች ወረርሺኙን መንግስት አመጣው ከማለት ያልተናነሰ ወሬ መንዛታቸው ሌላው አስገራሚ ነገር ነው፡፡ ለመሆኑ ታላላቅ ሀገራትን መያዣና መጨበጫ ያሳጣ ወረርሺኝ፣ ልክ ለፖለቲካ ጥቅም ተብሎ እንደመጣ ማስወራት ምን ዐይነት ቂልነት ይሆን!
በአንድ በኩል ምርጫው ለምን ተራዘመ! የሚል ጩኸት ፣በሌላ በኩል፣ የራስን ሕልም ለማሳካት የሽግግር መንግስት ይቋቋም!›› የሚል ጫጫታ መፈጠሩ፣ ከንግድና ከስልጣን ጥማት በቀር ሌላ ትርጉም ሊሰጠው ያስቸግራል፡፡ ለመሆኑ ችግሩን በጋራ መወጣት ይሻላል ወይስ በችግሩ ላይ ችግር እየፈጠሩ መንግስትን አቅም ማሳጣት? እንመራዋለን የሚሉት ሕዝብ የሚድንበትን መንገድ ትቶ፣ ስልጣን ላይ ብቻ ማፍጠጥ!!
ጉዳዩ በግልጽ እንደሚያሳየው፤ ብዙዎቹ የሽግግር መንግስት መዝሙር አቀንቃኞች፣ ጊዜና አጋጣሚን የመጠቀም ፍርሃት ላይ መሆናቸው ያስታውቃል፡፡ በተለይ በኦሮምያ ክልል፣ ሕዝቡ ለብልጽግና ፓርቲ የሰጠው ድጋፍ ብዙዎችን ተስፋ አስቆርጧል:: ስልጣን ደጅ የደረሱ የመሰላቸውን ቅዠታቸውን ከአፋቸው ነጥቋል፡፡ ስለዚህ ምርጫው አስፈርቷቸዋል፤እናም በግርግር ስልጣን ላይ ለመውጣት ያገር ያለህ እያሉ ነው፡፡ ወረርሺኙን መንግስትን ለመክሰሻ እየተጠቀሙበት ነው፡፡ ንግድ ማለት ይኸው ነው፡፡
ለመሆኑ የሽግግር መንግስት ይመስረት ቢባል ማንና ማን መንግስቱ ውስጥ ይወከላል:: ምስራቅና ምዕራብ፣ ሰሜንና ደቡብ? ዛሬ ተፎካካሪ የሚባሉት ፓርቲዎችኮ ልዩነታቸው የትየለሌ ነው:: የባቢሎን ሰዎች እንዴት ባንድ ላይ ተግባብተው ሀገር ይመራሉ፡፡ የባንዲራ ስምምነት፣ የቦታ ጥያቄ፣ የታሪክ ቁርሾ ያንጠለጠሉ ሰዎች እንዴት ሆነው መንግስት ሊመሰርቱ ነው? ግራ ያጋባል፡፡ ይህንን ስል ብልጽግና ፓርቲ ጨዋ ነው እያልኩ አይደለም፤የትናንት ጅቦች የትናንት ሆድ አደሮች አሁንም አሉበት፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ባለው ሁኔታ፣ ከየትኛዎቹም በተሻለ ሀገሪቱን አንድ አድርጎ ማስቀጠል የሚችል እንደሆነ መመስከር ይቻላል፡፡ ፓርቲው ብዙ የሚታዩ ችግሮች አሉበት፤ግን ደግሞ ሀገሪቱን ከመፍረስ የሚያድናትና በሀገሪቱ አንድነት የሚያምን፣ ለቅርጫ የተዘጋጁትን ስግብግብ የጎጥ ፖለቲከኞች የማምለጫው መንገድ “escaping route” እርሱ ነው፡፡
አሁን በሰሞኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታዘብኳቸው  ነገሮች፣ የፓርቲውን ደካማና ጠንካራ ጎን አሳይቶኛል፡፡ በአንድ በኩል የሰው ለሰው መረዳዳትን፣ ሰው መሆንን፣ ፍቅርን ሲያሳየኝ፤ በሌላ በኩል የቀደመውን ዐይነት ግልብና ስርዐተ አልበኝነትም አስተውያለሁ፡፡
ለምሳሌ ድቡብ ክልል በተለይ ጉራጌ ዞን ትብብሩና የተቸገሩትን መርዳቱ ደስ ቢያሰኝም፣ ሕጉን ተፈጻሚ በማድረግ ረገድ ራሳቸው አመራሮቹ ያላቸው ግንዛቤ የሚያሳፍር ሆኖ አግንቼዋለሁ፡፡ በጣም ከገረሙኝ ነገሮች አንዱ፣ “ሞተር ሳይክል ላይ ለሁለት መቀመጥ ተከልክሏል›› የሚል ሕግ ወጥቶ፣ ሕጉ አመራሮችን ያለማካተቱ ነው፡፡ ኮሮና የብልጽግና ፓርቲ አመራሮችን ይፈራ መስሏቸው ይሆን! መቸም ለጊዜው ተብሎ እንጂ ፓርቲው ውስጥ ምን ዐይነት ሰዎች እንዳሉበት እናውቃለን፡፡ ቀን እስኪያልፍ ያባቴ እንትን ይግዛኝ ብለን እንጂ፡፡
መንገድ ላይ በሞተር የተፈናጠጡ ትራፊኮች፣ እነርሱ ሁለት ሆነው ተቀምጠው፣ ሌሎችን ይከስሳሉ፡፡ ይህ ምን ማለት ነው፡፡ ባለስልጣናቱ ጆንያ ተሸክሞ ፎቶ ከመነሳት ያለፈ ልባዊ ተግባር ያስፈልጋቸዋል ባይ ነኝ::
ማንም ሰው ያሻውን ይበል፣የቱንም ሰበብ ፈጥሮ ይቃወም፤እኔ በጠቅላዩ ላይ ያለኝ አቋም አንድ ዐይነት ነው፡፡ በተለይ የልጅነት ታሪካቸውን ከያንዳንዱ ሰው ሰምቼ ከመጣሁ በኋላ ሰውየውን በክፋት መጠርጠር አልቻልኩም፡፡
በርግጥ ሁኔታው ግራ እንዲያጋባ የሚያደርጉ ብዙ ነገሮች ስላሉ በቅንነት በሚቃወሙት ላይ ጣቴን አልቀስርም፡፡ ምክንያቱም እርሳቸው በሚመሯት ሀገር የሚሰራ ብዙ ደባ አለ፡፡ መሃል ከተማ ሳይቀር መሬት ይሸነሸናል፤ብዙ ቦታዎች ዐይናችን እያየ ተወስደዋል፡፡
ግን ይህ ለምን ሆነ! ሰውየውስ ለምን ዝም አሉ? የሚለው ነገር ብዙ ቦታ ይወስደናል፡፡ ሁሉን ነገር በአንዴ አርማለሁ ብሎ በአንዴ ከሁሉ ጋር መተናነቅ፣ ሁሉን ማፍረስ ስለሆነ፣ ለጊዜው አንዳንዱን መዝለል ግድ የሚሆንበት ጊዜ አለ፡፡ አሁን ሕዝቡ በብዙ ተከፍሏል፡፡ ሁሉም ግን የየራሱ ክስ አለው:: ጠቅላዩ ኦነግ፣ ጠቅላዩ ባንዳ ሌላም ሌላም ናቸው፡፡ ታዲያ ለማን እያደሉ ይሆን? ለኦሮሞም ለአማራም ለወላይታም ካላደሉ ለማን አድልተው ነው? ወደድንም ጠላንም ያደሉት ለኢትዮጵያ ነው፡፡ ዛሬ የሰውየው አጋሮች ኢትዮጵያን የሙጢኝ ያሉ ናቸው:: ለሰፈርህ ካገዝክ ያናድዱሃል፤የሌላ ሰፈር ሽፍታ ሲመጣ እልል ብለህ ላንተ ስልጣን መወጣጫ የሚሆንህ መሰላል ሲሰበር ዐቢይ አምባገነን ነው፡፡
ጉዳዩ እኛ ጋ ነው፡፡ እኛ የራሳችንን ድምጽ እንሰማለን፤እኛ የራሳችንን የልብ ትርታ እናዳምጣለን፡፡ እኛ የፖለቲካ ቀሻቢዎችን ወሬ እናራግባለን፡፡ ስለዚህ ዐቢይ የሚሰራው አይጥመንም፡፡ ዐቢይ ሰው ነው፣ ዐቢይ መልዐክ አይደለም፡፡ ግን አውሬ አይደለም፤ ሌባም አይደለም፡፡ ካዝና አየሰበረ ብር እያከማቸ አይደለም፡፡ ወጣቶችን የሚያበረታታ፣ ተስፋን የሚናገር፣ ልትፈርስ የነበረች ሀገር ተረክቦ ሙሉዋን ለማዳን የሚተጋ፤ አውሬዎች ከቁጥር በላይ የከበቡት ጠንካራ ሰው ነው፡፡ ማኦ እንደሚለው፤ ‹‹ስልጣን የሚገኘው በጠመንጃ አፈሙዝ ነው›› ብሎ  ሳይሆን በንግግር የሚያምን፣ ይህ እምነቱ እንደ ስንፍና የተቆጠረበት መጥፎ ጊዜ ላይ የተገኘ መልካም መሪ ነው፡፡
በግሌ አበሳጭቶኝ ተቃውሜ አውቃለሁ:: ግን ኢትዮጵያ ልትድን የምትችለው በእርሱ አያያዝ እንደሆነ አምናለሁ፡፡  በቅርጹ በጣም የተበሳጨሁበት ‹‹መደመር›› የሚለው መጽሐፉ ላይ ያሉትን መልካም ሕልሞቹን እወዳቸዋለሁ፡፡ ስለዚህ አሁን በስልጣን ጥማት የሚያላዝኑትን ጥቅመኞች፣ አደብ ግዙ ማለት እፈልጋለሁ፡፡ ጉዳዩ በብዙ አቅጣጫ የሚታይ ስለሆነ ጥንቃቄም ይጠይቃል፡፡ ሁሉም ጤነኞች ናቸው ብዬም አላምንም፤ ቶርች የተደረጉ፣ ተስፋ የቆረጡ፣ እኛ ታግለን ሌሎች ስልጣን ላይ ተቀመጡ የሚሉም ስላሉበት ሕዝቡ ማስተዋል፤ መንግስትም ማገዝ አለበት፡፡
ማህበራዊ ሚዲያ፣ ተቃዋሚዎች ጩኸታቸው ለእንጀራ ስለሆነ፣ ኤልያስን የመገበ አምላክ ይመግባቸው ማለት ብቻ አይበቃም፡፡ ግን የባቢሎን ሰዎች አንድ መንግስት መስርተው፣ ሀገር እንደማይመሩ መንገር ያስፈልጋል፡፡ አንድን ከተማ በተለያየ ስም እየጠሩ፣ የተለያየ ባለቤትነት አላት እያሉ፣ ወይም ራሴን የቻልኩ ሀገር መሆኔ ነው እያሉ የሚያስፈራሩ ሃይሎች፣ እንዴት በአንድ የመንግስትነት ገበታ ቁጭ ይላሉ!!
ፈጽሞ አይሆንም፡፡ ያገኘነውን ዕድል በቅንነት ልንጠቀም ይገባል፡፡ ሃሳቤን በገጣሚ መዘክር ግርማ ግጥም ልቋጨው፡--
ዝምታ ወርቅ ነው! ዝምተኛ ሰው ወርቅ ቤት
የማንም ቁልፍ አይከፍተውም
ማንም ሌባ አይሰርቀውም፣ ቢጎደፍር
በቀን በሌት፡፡
ግን አንዳንድ ጊዜ
‹‹ዝምታ ወርቅ ቤት፣ ወርቁን ይሰረቃል፡፡
ወርቃችንን እንዳንሰረቅ ዝም አንበል፡፡ በጦርነትም ቀን፣ ወገን የሚመስሉ ዘራፊዎች አሉ፡፡ ሁላችንም ርቀታችንን ጠብቀን በጥንቃቄ እንኑር፡፡     


Read 2148 times