Saturday, 02 May 2020 12:07

ኮሮና እና አለማችን በሳምንቱ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

  ቁጥሩ ማሻቀቡን ቀጥሏል...
መሽቶ በነጋ ቁጥር አለም በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ የደረሱባትን የተለያዩ ጥፋቶች የሚገልጹ እጅግ አስደንጋጭና ተስፋ አስቆራጭ ቁጥሮችን መስማት የተለመደ ሆኗል፡፡
አንዳች መላ ሳይገኝለት በአለም ዙሪያ በስፋት መሰራጨቱን የቀጠለው ኮሮና ቫይረስ እስካለፈው ሐሙስ አመሻሽ ድረስ በመላው አለም በሚገኙ 211 አገራትና ግዛቶች ውስጥ ከ3,249,792 በላይ ሰዎችን ሲያጠቃ ከ229,442 በላይ የሚሆኑትንም ለሞት እንደዳረገ ተነግሯል፡፡
በቫይረሱ የተጠቁባት ዜጎቿ ቁጥር በሳምንቱ በሚሊዮን መቆጠር በጀመረባት አሜሪካ እስካለፈው ሐሙስ አመሻሽ 1,067,382 ሰዎች በቫይረሱ ሲጠቁ፣ ከ61,849 በላይ የሚሆኑ ደግሞ ለሞት መዳረጋቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ከአሜሪካ በመቀጠል ስፔን 239,639፣ ጣሊያን 203,591፣ ፈረንሳይ 166,420፣ እንግሊዝ 165,221 ሰዎች በቫይረሱ የተጠቁባቸው ቀዳሚዎቹ አምስት የአለማችን አገራት ሆነዋል፡፡
ከ61,849 በላይ ሰዎች ከሞቱባት አሜሪካ በመቀጠል፣ ጣሊያን በ27,682፣ እንግሊዝ በ26,097፣ ስፔን በ24,543፣ ፈረንሳይ በ24,087 የሟቾች ቁጥር እንደ ቅደም ተከተላቸው በርካታ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ለሞት የተዳረጉባቸው ቀዳሚዎቹ አምስት የአለማችን አገራት መሆናቸውንም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ግማሹ የአለማችን ሰራተኛ
ስራ ሊያጣ ይችላል
በመላው አለም ከሚገኙ ሰራተኞች ግማሹ ወይም ከ1.5 ቢሊዮን በላይ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ቀውስ ጋር በተያያዘ የሚተዳደሩበትና ኑሯቸውን የገቢ ምንጫቸው ሊደርቅና ለከፋ ኑሮ ሊዳረጉ እንደሚችሉ የአለም የሰራተኞች ድርጅት አስጠንቅቋል፡፡
በኮሮና ሳቢያ ክፉኛ ተጎጂ ይሆናሉ ተብለው ከሚጠበቁት ሰራተኞች መካከል መደበኛ ባልሆነው ዘርፍ፣ በምርትና በምግብ አገልግሎቶች ኢንዱስትሪዎች ተቀጥረው የሚሰሩ እንደሚገኙበት የገለጸው ድርጅቱ፣ ኮሮና በተከሰተበት የመጀመሪያው ወር ብቻ መደበኛ ባልሆነው ዘርፍ የሚሰሩ 2 ቢሊዮን ሰዎች ገቢያቸው በአማካይ በ60 በመቶ ያህል መቀነሱንም አስታውሷል፡፡
አፍሪካ
የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠር ማዕከል ባወጣው መረጃ መሰረት እስካለፈው ሐሙስ አመሻሽ ድረስ በ52 የአፍሪካ አገራት ከ35,371 በላይ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ሲጠቁ፣ የሟቾች ቁጥር ደግሞ ከ1,534 አልፏል፤ ከህመሙ ያገገሙት ደግሞ ከ11,727 በላይ ደርሰዋል፡፡
እስካለፈው ረቡዕ ድረስ ከ5 ሺህ 42 በላይ ሰዎች ባይረሱ የተጠቁባት ግብጽ በአህጉሩ ብዙ ሰዎች የተጠቁባት ቀዳሚዋ አገር ሆና የተቀመጠች ሲሆን፣ ደቡብ አፍሪካ ከ4 ሺህ 996 በላይ፣ ሞሮኮ 4 ሺህ 246፣ አልጀሪያ ከ3ሺህ 649 በላይ፣ ካሜሮን 1 ሺህ 705 ሰዎች የተጠቁባቸው ተከታዮቹ የአፍሪካ አገራት መሆናቸው ተነግሯል፡፡
ከአፍሪካ አገራት በኮሮና ቫይረስ ሟቾች ቁጥር አልጀሪያ በ437 በቀዳሚነት ስትቀመጥ፣ ግብጽ በ359፣ ሞሮኮ በ163፣ ደቡብ አፍሪካ በ93፣ ካሜሩን በ58 ይከተላሉ ተብሏል፡፡
በናይጀሪያ ከ40 በላይ የህክምና ባለሙያዎች በኮሮና ቫይረስ መጠቃታቸውን የዘገበው ዴይሊ ሞኒተር፣ ከዚህ ቀደም 3 የህክምና ባለሙያዎች በኮሮና ሳቢያ ለሞት መዳረጋቸውንና ይህም ወረርሽኙን ለመከላከል የሚደረገውን አገራዊ ጥረት እያሰናከለው እንደሚገኝ ገልጧል፡፡
የጊኒ ቢሳኡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኑኖ ጎሜዝ ናቢያም እና ሶስት የካቢኔ አባላት በኮሮና ቫይረስ መጠቃታቸው ባለፈው ማክሰኞ በተደረገላቸው መረጋገጡ የተዘገበ ሲሆን፣ ከአለማችን እጅግ ግዙፍ የስደተኞች መጠለያ ካምፖች አንዱ የሆነውና ከ220 ሺህ በላይ ስደተኞች የሚገኙበት የኬንያው ዳባብ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ በተፈጠረ ከፍተኛ ስጋት ከሰሞኑ ዝግ መደረጉንና ምንም ሰው እንዳይገባና እንዳይወጣ መታገዱን ብሉምበርግ ዘግቧል፡፡
የኡጋንዳ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ስለኮሮና ቫይረስ ግንዛቤ ለማስጨበጥ በሚል እያንዳንዳቸው 5 ሺህ ዶላር ወስደው እንደነበር ያስታወሰው አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ፣ ከሰሞኑ ግን አባላቱ የወሰዱትን 2.6 ሚሊዮን ዶላር ያህል አጠቃላይ ገንዘብ በአስቸኳይ እንዲመልሱ በፕሬዚዳንት ሙሴቬኒ መታዘዛቸውን ዘግቧል፡፡
በዚህ የጭንቅ ወቅት ባልተገባ ሰበብ የህዝብ ገንዘብ የተቀበሉትን የምክር ቤቱ አባላት “ህሊና የለሾች” ሲሉ የተቹት ፕሬዚዳንት ሜሴቬኒ በአንጻሩ እሳቸው ከሚያገኙት መደበኛ ወርሃዊ ደመወዝ ግማሹን ለኮሮና መከላከልና መቆጣጠር ስራዎች በስጦታ እንደሚያበረክቱ አስታውቀዋል፡፡
ኬንያውያን በበኩላቸው ለኮሮና ወረርሽኝ የተመደበውን 37 ሺህ ዶላር ያህል የህዝብ ገንዘብ የጤና ሚኒስትር ሰራተኞች ለሻይ ቡና እና ለሞባይል ካርድ መግዣ እያዋሉት ነው በሚል በማህበራዊ ድረገጾች ከፍተኛ ተቃውሞ በማሰማት ላይ እንደሚገኙ ኦልአፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡
የዛምቢያ መንግስት ኮሮና ቫይረስን በቁጥጥር ስር ለማዋል በሚደረገው ጥረት ውስጥ ቁልፍ ሚና ለሚጫወቱ የህክምና ባለሙያዎች የማበረታቻ የገንዘብ ሽልማት እንደሚሰጥ ማስታወቁ ተዘግቧል፡፡
በማዳጋስካር መዲና አንታናናሪቮ ዜጎች ከቤታቸው ውጭ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ሁሉ የፊት ጭምብል እንዲያደርጉ የሚያስገድድ መመሪያ ካለፈው ሰኞ ጀምሮ ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን፣ ጭምብል ሳያደርጉ ሲንቀሳቀሱ የተገኙ ዜጎች መንገዶችን በማጽዳት እንደሚቀጡ ተዘግቧል፡፡

1 ሚ. ያልተፈለጉ እርግዝናዎች፤ 15 ሚ. የቤት ውስጥ ጥቃቶች
ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ በመላው አለም እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ከቤት እንዳይወጡ መታገዳቸው 1 ሚሊዮን ያህል ያልተፈለጉ እርግዝናዎች እንዲከሰቱ እንዲሁም የቤት ውስጥ ጥቃቶች በ20 በመቶ ያህል እንዲጨምሩ ሰበብ ሊሆን እንደሚችል ተመድ አስጠንቅቋል፡፡
አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው 114 የአለማችን አገራት 44 ሚሊዮን ያህል ሴቶች ኮሮና በሚፈጥራቸው ቀውሶች ሳቢያ የእርግዝና መከላከያዎችን ላያገኙ እንደሚችሉና ይህም ከ1 ሚሊዮን በላይ ያልተፈለጉ እርግዝናዎች ሊያስከትል እንደሚችል የጠቆመው ድርጅቱ፣ 13 ሚሊዮን ልጃገረዶች በግዳጅ ወደ ትዳር ሊገቡ፣ 2 ሚሊዮን ሴት ህጻናት ግርዛት ሊፈጸምባቸው እንደሚችልም አስታውቋል፡፡
ከኮሮና የቤት ውስጥ መዋል ገደቦች በኋላ በበርካታ የአለማችን አገራት የቤት ውስጥ ጥቃት አቤቱታዎች በከፍተኛ ሁኔታ መጨመራቸውን ጠቅሶ ሰዎች ለሶስት ወራት ያህል ከቤት ውስጥ እንዳይወጡ መታገዳቸው በአለማቀፍ ደረጃ ተጨማሪ 15 ሚሊዮን የቤት ውስጥ ጥቃቶች እንዲፈጸሙ ሊያደርግ እንደሚችል የጠቆመው ተቋሙ፣ ይህም በተለይ በሴቶች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር አመልክቷል፡፡

“ሰላሳ አራቱ”
ዙሪያ ገባው አለም በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ጭንቅ ውስጥ በወደቀበት በዚህ የመከራ ወቅት፣ እስከ ትናንት በስቲያ ድረስ ቫይረሱ ድንበራቸውን አልፎ ያልገባባቸው 34 የአለማችን ሉዑዋላዊ አገራትና ግዛቶች እንዳሉ ሮይተርስ አስነብቧል፡፡
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እውቅና ከተሰጣቸው 247 የአለማችን አገራትና ግዛቶች መካከል እስካለፈው ሚያዝያ 12 ቀን ድረስ ኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው የተረጋገጡት አገራት 213 መሆናቸውን ያስታወሰው ሮይተርስ፣ ከእነዚህ አገራትና ግዛቶች መካከል በኮሮና ቫይረስ ሰዎች ለሞት የተዳረጉባቸው 162 መሆናቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡
እስከተጠቀሰው ዕለት ድረስ አንድም ሰው በቫይረሱ እንዳልተጠቃባቸው ከተነገሩት 34 አገራትና ግዛቶች መካከል ኮሞሮስ፣ ሌሴቶ፣ ተርኬሚኒስታንና የሶሎሞን ደሴቶች እንደሚገኙበት የጠቆመው ዘገባው፣ ያም ሆኖ ግን አንድም ሰው በቫይረሱ አልተያዘም ማለት ቫይረሱ ወደ አገራቱ አልገባም ማለት እንዳልሆነ አመልክቷል፡፡
ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች እንዳሉ ካስታወቁ በኋላ በሂደት ቫይረሱን ማጥፋት መቻላቸውንና ነጻ መሆናቸውን ያወጁ አምስት የአለማችን አገራትና ግዛቶች አንጉሊያ፣ ግሪንላንድ፣ የካረቢያን ደሴቶች፣ የመን፣ ሴንት ባርትስና ሴንት ሉሲያ መሆናቸውንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡
 
አሜሪካ
የአለም ቀንድ የሆነው የአሜሪካ ኢኮኖሚ ዕድገት በመጀመሪያው ሩብ አመት የ4.8 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱንና ይህም ካለፉት አስር በላይ አመታት ወዲህ እጅግ የከፋው ነው መባሉን የዘገበው ብሉምበርግ፣ አንዳንድ ባለሙያዎችም የኢኮኖሚ እድገቱ በመጪዎቹ ሶስት ወራት ከ30 በመቶ እና ከዚያ በላይ ሊቀንስ እንደሚችል መተንበያቸውን አመልክቷል፡፡
በአሜሪካ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ለስራ አጥነት የተጋለጡ ሰዎች ቁጥር ከ30 ሚሊዮን በላይ መድረሱንና ይህም በአገሪቱ ታሪክ እጅግ ከፍተኛው ቁጥር እንደሆነ ዘገባው ገልጧል፡፡
ከኮሮና መስፋፋት ጋር በተያያዘ የእንቅስቃሴ ገደብና የስራ መቀዛቀዝ ሳቢያ በ2020 የመጀመሪያው ሩብ አመት የቻይና ኢኮኖሚ እድገት በ6.8 በመቶ መቀነሱን ያስታወሰው ዘገባው፣ የጀርመን መንግስት በበኩሉ በዚህ አመት መጨረሻ ላይ ከዚህ በፊት አይቶት የማያውቀው የ6.3 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት ቅናሽ ሊገጥመው እንደሚችል ባለፈው ረቡዕ ማስታወቁንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በመጀመሪያው ሩብ አመት ሽያጬ በ26 በመቶ የቀነሰበትና 17 ቢሊዮን ዶላር ያጣው የአሜሪካው የአውሮፕላን አምራች ኩባንያ ቦይንግ በቅርቡ ከደረሰበት ቀውስ እና ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ በተፈጠረበት የስራ መቀዛቀዝ ሳቢያ 15 ሺህ የሚደርሱ ሰራተኞችን ከስራ ገበታቸው እንደሚያሰናብት ከሰሞኑ ይፋ አድርጓል፡፡

“የኮሮና ፖለቲካ”
ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ቻይናን ተጠያቂ ሲያደርጉ የሰነበቱት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ረቡዕ ደግሞ፣ በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ ከአሜሪካ የእጇን ታገኛለች ሲሉ የዛቱባትን ቻይና በቀጣዩ ምርጫ ሽንፈትን እንድጎነጭላት አሳር መከራዋን እያየች ነው ሲሉ መክሰሳቸውን ሮይተርስ ተዘግቧል፡፡
አለም ስለወረርሽኙ ቀድሞ እንዲያውቅ አላደረገችም በሚል በወነጀሏትና ቀደም ብለው የንግድ ጦርነት ባወጁባት ቻይና ላይ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ የራሳቸውን እርምጃ እንደሚወስዱ የተናገሩት ትራምፕ፣ ቻይና እኔ እንድሸነፍላትና ዲሞክራቱ ጆ ባይደን እንዲያሸንፍ የማትፈነቅለው ድንጋይ የለም፤ ይህ ግን በፍጹም የሚሆን አይደለም ምክንያቱም አሜሪካውያንን ማንን እንደሚመርጡ ጠንቅቀው ያውቃሉ ሲሉም ተናግረዋል ትራምፕ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ከኮሮና ጋር በተያያዘ አለማቀፍ ምርመራ እንዲካሄድ አበክራ ስትጠይቅ የነበረችው አውስትራሊያ፣ ከሰሞኑም ኮሮና ቫይረስ መቼ፣ የት፣ እንዴት እንደተቀሰቀሰ በገለልተኛ አካል እንዲጣራ በድጋሜ ጥሪ ማቅረቧ ተዘግቧል፡፡
የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን ኮሮና በምን መልኩ እንዲህ አለምን ሊያጥለቀልቅ እንደቻለ በተጨባጭ ማስረጃ ላይ የተመሰረተ ትክክለኛ የምርመራ ውጤት ከገለልተኛ አካል መቅረቡ ፋይዳው የጎላ ነው ሲሉ ቢናገሩም፣ በአውስትራሊያ የቻይና አምባሳደር በበኩላቸው ነገሩ በገለልተኛ አካል ይጣራ መባሉን ለቃውመውታል፤ አልፎ ተርፎም አገራቸው የአውስትራሊያን ምርቶች ከመግዛት ልትታቀብ እንደምትችል ማስፈራሪያ ቢጤ ጣል አድርገዋል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ ኩባውያን የህክምና ዶክተሮችን ለኮሮና ህክምና ድጋፍ እንዲሰጧቸው ፈቅደው ወደ ግዛታቸው በማስገባታቸው ሳቢያ ደቡብ አፍሪካን እና ኳታርን መተቸታቸው ተዘግቧል፡፡
ኮሚኒስቷ ኩባ ከወረርሽኙ የራሷን ትርፍ ለማጋበስ የምትለፋ አገር ናትና የእሷን ዶክተሮች መቀበላችሁ አይበጃችሁም ወደመጡበት ብትሸኙዋቸው ይሻላችኋል ሲሉ ምክር መለገሳቸውንም ዘገባው አመልክቷል፡፡

አስደንጋጭ ቁጥሮች - የ“ሬምዴስቪር” ተስፋ
ኢንተርናሽናል ሪስኪዩ ኮሜቴ የተባለው አለማቀፍ ተቋም ባለፈው ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ ኮሮና ቫይረስ በአለማችን 34 አገራት ውስጥ ብቻ 1 ቢሊዮን ያህል ሰዎችን ሊያጠቃና 3.2 ሚሊዮን ሰዎችነም ለሞት ሊዳርግ እንደሚችል አስጠንቅቋል፡፡ ተቋሙ ያወጣውን መግለጫ ጠቅሶ ቪኦኤ እንደዘገበው፣ ኮሮና ቫይረስ አፍጋኒስታን፣ ሶርያና የመንን ጨምሮ በቀውስ አዙሪት ወይም በጦርነት ውስጥ በሚገኙ 34 አገራት ውስጥ የሚደርሰውን ጥፋት ለመቀነስ ሁሉም ርብርብ ማድረግ ይጠበቅበታል ተብሏል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ፣ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ባለፈው ሐሙስ ማለዳ ከወደ አሜሪካ የተሰማው በጎ ዜና በብዙዎች ልብ ውስጥ የተስፋን ብርሃን የፈነጠቀ ስለመሆኑ በስፋት እየተነገረ ነው፡፡
አሜሪካውያን ተመራማሪዎች በላሰንት መጽሄት ላይ ያወጡትን መረጃ ጠቅሶ ዘ ጋርዲያን እንደዘገበው፣ “ሬምዴስቪር” የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ የምርምር ውጤት በ15 ቀን ይታዩ የነበሩትን የኮሮና ቫይረስ ምልክቶች ወደ 11 ቀን ዝቅ እንደሚያደርግ የተነገረ ሲሆን፣ በሆስፒታሎች ያለውን ጫና በመቀነስ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ይጠበቃል፡፡
ከዚህ በፊት የኢቦላ ቫይረስ ተጠቂዎችን ለማከም በአገልግሎት ላይ ይውል እንደነበር የተነገረለት “ሬምዴስቪር”፣ ከዚህ በተጨማሪም በሌሎች የኮሮና ቫይረስ አይነቶች ህክምና በእንስሳት ላይ ተሞክሮ አመርቂ ውጤት ማሳየቱም ተዘግቧል፡፡

“የሚፈቱ” አገራትና ከተሞች ተበራክተዋል
ከኮሮና ቫይረስ ስርጭት መስፋፋት ጋር በተያያዘ የእንቅስቃሴ ገደብና አስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ጨምሮ የተለያዩ እርምጃዎችን ወስደው የነበሩ በርካታ የአለማችን አገራትና ከተሞች ተግባራዊ ሲያደርጓቸው የቆዩዋቸውን እርምጃዎች ማቋረጣቸውንና ይህም የችኮላ እርምጃ ተብሎ በብዙዎች እየተተቸ እንደሚገኝ ተነግሯል፡፡
የስራ አጡ ቁጥር በእጅጉ ይጨምራል ተብሎ መነገሩን ተከትሎ በርካታ የአሜሪካ ግዛቶች ተዘግተው የነበሩ የንግድ ተቋማት ወደ ስራ መመለሳቸውን የዘገበው ሮይተርስ፣ በስፔን ካለፈው እሁድ ጀምሮ አንዳንድ ጠንካራ ቁጥጥሮችን ያላላች ሲሆን፣ ለወራት በቤታቸው ውስጥ ታጉረው የነበሩ የአገሪቱ ህጻናት በወላጆች ድጋፍ ከቤት ወጥተው መንቀሳቀስ መጀመራቸውን አመልክቷል፡፡
በቱኒዝያ ተዘግተው የነበሩ የምግብና የግንባታ ዘርፎች በከፊል መከፈት የጀመሩ ሲሆን፣ ግማሽ ያህሉ የአገሪቱ የመንግስት ሰራተኞች ወደ መደበኛ ስራቸው መመለሳቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በፖላንድ ተቋርጦ የቆየው መደበኛ የንግድ እንቅስቃሴ በመጪው ሳምንት እንደሚጀመር እንዲሁም የተዘጉ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች እንደሚከፈቱ የተነገረ ሲሆን፣ ጣሊያን አንዳንድ ፋብሪካዎችን እንደምትከፍት፣ ናይጀሪያ ከነገ በስቲያ ጀምሮ የመንግስት መስሪያ ቤቶችንና ባንኮችን እንደምትከፍት አስታውቀዋል፡፡


Read 12484 times