Saturday, 02 May 2020 12:07

በኒውዮርክ ከተማ በኮረና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 150ሺ እንደሆኑ ዕለታዊ ሪፖርት ይገልጻል፡፡

Written by  ዮሃን
Rate this item
(1 Vote)

  (ከ1ሺ ነዋሪዎች ውስጥ 18 ሰዎች በቫይረሱ ተጠቅተዋል እንደ ማለት ነው፡፡) ቫይረሱ በብዙ እጥፍ እንደተዛመተና 1.7 ሚ. ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው እንደነበር ይገልጻል-- አዲሱ የጥናት ውጤት፡፡ ጥናቶችና ቁጥሮች ምን ይላሉ? “ከ1ሺ የኒውዮርክ ከተማ ነዋሪዎች፣ 210 ያህሉ በኮሮና ቫይረስ ተይዘው ነበር” ማለት ነው
          ዮሃን


          - አደገኛው ኮሮና ቫይረስ፣ ከተገመተው በላይ በብዙ እጥፍ የሚዛመት ቫይረስ እንደሆነ በበርካታ አገራት የተካሄዱ ጥናቶች አረጋግጠዋል- ከጣልያንና ከስፔን እስከ አሜሪካ ሎሳንጀለስና ኒውዮርክ ድረስ፡፡
- በርካታ የካሊፎርኒያ ከተሞችን ያካተተ በሳንትክላራ ዞን ዉስጥ የተከናወነው የስታንፎርድ ዩኒቨርስቲ ጥናት እንዲህ ይላል፡-
“ቫይረሱ በጣም የተዛመተ አይመስልም ነበር፡፡ ከ2 ሚሊዮን ነዋሪዎች መካከል1000 ሰዎች በቫይረሱ እንደተያዙ ነበር፤በወቅቱ በዕለታዊ ሪፖርት የተመዘገበው፡፡ በሰፊው በተካሄደ የናሙና ምርመራ አማካኝነት የተገኘው ውጤትስ.... ቢያንስ ቢያንስ 50.000 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው እንደነበረ በምርመራ አረጋግጠናል ብለዋል አጥኚዎቹ:: በዕለታዊ ሪፖርት ሲገለጽ ከነበረው ቁጥር ጋር ሲነጻጸር፤ 50 እጥፍ ማለት ነው ይላል፤ የዎልስትሪት ጆርናል ዘገባ፡፡
በኒውዮርክ ደግሞ ሰፊ ጥናት ከመካሔዱ በፊት ሌላ አነስ ያለ የምርመራ መረጃ ተገኝቶ ነበር፡፡ በህመም ምክንያት ሳይሆን፣ ለወሊድ ወደ ጤና ተቋም የመጡ እርጉዞች፣ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ይደግላቸዋል:: ከ200 መካከል በ30ዎቹ ዉስጥ ኮሮና ቫይረስ ተገኝቷል - 15 ከመቶ መሆኑ ነው:: ይሄ በወቅቱ በይፋ ሲመዘገብ ከነበረው የስርጭት መጠን ጋር ሲነፃፀር በ15 እጥፍ ይበልጣል፡፡
በጣሊያን፣ በፈረንሳይና በስፔን ከተሞች የተካሄዱ በርካታ ጥናቶችም፤ተመሳሳይ ውጤት አሳይተዋል፡፡ በአንዳንድ ከተሞች፣ የቫይረሱ ስርጭት በእለታዊ ሪፖርት በይፋ ከሚገለፀው ቁጥር በ40 እና በ30 እጥፍ እንደሚበልጥ ጥናቶቹ ገልጸዋል፡፡ አነሰ ቢባል፤ ከ10 እጥፍ አያንስም፡፡
በካሊፎርኒያ የ10 ሚሊዮን ሰዎች መኖሪያ በሆነው የሎሳንጀለስ ዞን የተካሄደ ሌላ ሰፊ ጥናትም፣ ቫይረሱ በሰፊው እንደተሰራጨ አመልክቷል፡፡
በሎሳንጀለስ፤ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 8ሺ ደርሷል ተብሎ በተገለፀበት ወቅት ነው ጥናቱ የተካሄደው፡፡
አጥኚዎቹ እንደገለፁት ግን የቫይረሱ ስርጭት፣ በ30 እጥፍ እንደሚበልጥ ነው፡፡ ቢያንስ ቢያንስ 250ሺ የሎሳንጀለስ አካባቢ ነዋሪዎች፣ በቫይረሱ ተይዘው እንደነበር አረጋግጠናል ብለዋል - የሳውዝ ካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪዎች፡፡
በዚህ ሳምንት የተዘገበው ሌላ ሰፊ ጥናት ደግሞ፤ ብዙ ሰው በሞተበት በኒውዮርክ የተካሄደ ነው፡፡ በየቀኑ የሚገለፀውን ሪፖርት ስንመለከት፤ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች 150 ሺህ ገደማ እንደሆነ ያሳያል (የዛሬ ሳምንት)፡፡ በሰፊው የተካሄደው የናሙና ጥናት ግን፣ ቫይረሱ እጅጉን በስፋት እንደተዛመተ ያረጋግጣል፡፡
ከ8.4 ሚሊዮን የኒውዮርክ ነዋሪዎች መካከል፤ 1.7 ሚሊዮን ያህሉ በቫይረሱ ተይዘው እንደነበረ አጥኚዎቹ ገልፀዋል፡፡ ከ10 እጥፍ በላይ ነው - ቫይረሱ የተዛመተው፡፡ በዚሁ ወቅት፣ በአሜሪካ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ገና ወደ 1 ሚሊዮን እንደተጠጋ ነበር በእለታዊ መረጃ የተመዘገበው:: በኒውዮርክ ከተማ ብቻ፣ ኮሮና ቫይረስ ከአንድ ሚሊዮን ተኩል በላይ ሰዎችን አዳርሷል ይላል - ጥናቱ፡፡
ታዲያ በየአገሩ እየተዘጋጀ በዓለም ጤና ድርጅት የሚሰበሰበው እለታዊ ሪፖርት ውሸት ነው? አይደለም፡፡
በኒውዮርክ ከተማ፣ እስካለፈው ሳምንት ድረስ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 150ሺ ገደማ ነው የሚለው እለታዊ ሪፖርት፤ ውሸት አይደለም፡፡ የቫይረስ ምርመራ የሚካሄደው፣ የበሽታ ምልክት የታየባቸው፣ ወይም ብሶባቸው የታመሙና ወደ ሆስፒታል ለህክምና የመጡ፣ ወይም ለበሽታው የተጋለጡ ሰዎች ላይ ብቻ ነው፡፡ የምርመራ ዉጤታቸዉም በእለታዊ ሪፖርት ይመዘገባል፡፡ ነገር ግን በቫይረሱ የተያዘ አብዛኛው ሰው፣ ምልክት ሳይታይበት፣ ለቫይረሱ እንደተጋለጠም ሳያውቅ፣ “ሳይታመም ይድናል”፣ በጥቂት ሳምንታት ውስጥም ከቫይረሱ ይገላገላል:: በሌላ አነጋገር አብዛኛው ሰው፤ ህመም ስለማይሰማው ወደ ሆስፒታል አይሄድም:: አይመረመርም፡፡ በእለታዊ ሪፖርትም አይመዘገብም፡፡
ለምሳሌ 3000 ሰዎች ቫይረሱ ቢተላለፍባቸው፣ 200ዎቹ፣ ቢበዛ ደግሞ 300 ያህሉ ናቸው በህመም ወይም በጥርጣሬ ተመርምረው ቫይረሱ የሚገኝባቸው፡፡ በእለታዊ ሪፖርት የሚመዘግቡትም እነዚህ ብቻ ይሆናሉ፡፡
 በዚህ መንገድ እስከ ዛሬ ድረስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ3 ሚሊዮን በላይ እንደሆነ በእለታዊ ሪፖርት ይገለጻል፡፡ የቫይረሱ ስርጭት ግን፤ ከዚህ በ10 እጥፍ ወይም ከዚያ በላይ እንደሚበልጥ ታይቷል፡፡ ቫይረሱ ቢያንስ ቢያንስ ከ30 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን አዳርሷል ማለት ነው፡፡  


Read 3250 times