Saturday, 07 July 2012 11:09

የ“ደቦ ባንድ” የመጀመሪያ አልበም ማክሰኞ ይወጣል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

በኢትዮጵያና አሜሪካ ሙዚቀኞች ጥምረት የሚንቀሳቀሰው ደቦ የሙዚቃ ባንድ፤ የመጀመሪያ  አዲስ አልበሙን ለዓለም ገበያ እንደሚያቀርብ ተገለፀ፡፡ አልበሙ “ደቦ ባንድ” የሚል መጠሪያ የተሰጠው ሲሆን ከሚቀጥለው ማክሰኞ ጀምሮ በሲዲ፤ በኤልፒ እና በተለያዩ የዲጂታል ፎርማቶች ለገበያ እንደሚቀርብ ያመለከተው ኤንፒአር የተባለ ድረገፅ፤ አልበሙ “የፍቅር ወጋገን”፣ “አሻ ገዳዎ” ፤ “ተነሽ ከልቤ ላይ”፤ “ነይ ነይ ወለባ” እና “አካሌ ውቤ” የተባሉት ዕውቅ የአማርኛ ዘፈኖች እንደተካተቱበት ጠቁሟል፡፡  ከኤሌክትሪክ ጊታር አንስቶ ሳስፎን እስከተባለ የትንፋሽ የሙዚቃ መሣሪያ ድረስ የሚጫወቱ ዘጠኝ የመዚቃ ባለሙያዎችንና አንድ ድምፃዊ የያዘው ደቦ ባንድ፤በመላው አሜሪካ ሊሰሙ ከሚገባቸው ምርጥ የኮንሰርት ባንዶች ተርታ የሚሰለፍ ሆኗል፡፡ ዘ ፎኒክስ የተባለ ጋዜጣ ፤ባንዱ ቦስተንን በዓለም አቀፍ መድረክ ለማስጠራት የበቃ አምባሳደር ሲል አወድሶታል፡፡

ደቦ በቦስተን ከተማ ነዋሪ በሆነው ኢትዮ - አሜሪካዊ ዳኒ መኮንን የተመሠረተ ሲሆን በባንዱ ውስጥ የሚገኘው ሌላው ኢትዮጵያዊ ድምፃዊው ብሩክ ተስፋዬ ነው፡፡ በአማርኛ የሚቀነቀኑት   የባንዱ ሙዚቃዎች በእንግሊዝኛና ሌሎች ቋንቋዎች ተናጋሪዎች ዘንድም ተደማጭ እንደሆኑ የጠቆመው ኤንፒአር፤ ሙዚቃዎቹ ባህላዊና ዘመናዊ ዜማዎችን በማጣመር መሰራታቸው ተደማጭነታቸውን ዓለምአቀፍ አድርጎታል ብሏል፡፡ በ1960ዎቹና 70ዎቹ የተሠሩ የኢትዮጵያ ምርጥ ሙዚቃዎችን በድጋሚ በማቀናበር መስራት የባንዱ ዋና ትኩረት ቢሆንም፤ በመጀመርያ አልበማቸው አዳዲስ ዘፈኖችን እንዳካተቱ ታውቆዋል፡፡

 

Read 1038 times Last modified on Saturday, 07 July 2012 11:16