Tuesday, 28 April 2020 00:00

ከፌስቡክ ገጾች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

   ዘላቂ ጠባሳ እንዳያመጣ--
ትላንት ከሰዓት በኋላ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ለመጎብኘት እድል አግኝቼ ነበር። ደስ ብሎኝ ተመልሻለሁ። ከውጭ መዓት የሚያወራ ቢኖርም፤ ወጣቶች በተስፋ በትጋት ይሰራሉ። በዓለም ላይ የመጣ መከራ አየር መንገዱን የከፋ ጉዳት ሳይደርስበት ለ2035 እየተዘጋጁ ነው። ጎበዝ፤ ከ2020 የማያልፍ ኮሮና፤ ዘላቂ ጠባሳ እንዳያመጣ፣ አየር መንገዱን ከማጠልሸት እንታቀብ። ስህተትም ሲኖር በልኩ ይነገር፣ ለማቃናት እንጂ ለመስበር እንዳይሆን። ምልክቶቻችንን እንጠብቅ። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለእርስዎ ምንድነው?
እጃችንን እንታጠብ!
ርቀታችንን እንጠብቅ!
(ከግርማ ሰይፉ ማሩ ፌስቡክ)
***
የምግብ ዋስትና እና የምግብ ሉዓላዊነት ጉዳይ
አንዳንድ ሰዎች በምግብ ዋስትና እና በምግብ ሉዓላዊነት መካከል ያለውን ልዩነት ባለመረዳት ጥያቄ አቅርበዋል። አንዳንዶቹ ደግሞ ተሳድበዋል። ያው ተሳዳቢ ብሎክ ስለሚደረግ ማብራሪያው አይደርሰውም:: የምግብ ዋስትና ማለት አገራት የምግብ ፍላጎታቸውን ለማቅረብ ከመቻላቸው ጋር የተያያዘ ነው። አገራት ምግብን በማምረት ብቻ ሳይሆን በግዢም ያቀርባሉ። ይህ የአገራትን የምግብ ዋስትና በሌሎች ሀይሎች ላይ ጥገኛ ያደርጋቸዋል። አንዳንድ አገሮች ምርጫ ሳይኖራቸው ሲቀር በሰው አገር መሬት ሊዝ በመያዝ እራሳቸው ያመርታሉ። ለምሳሌ ሳውዲ በኢትዮጵያ ያሰበችው ሩዝ ፋብሪካ።
ይህ በነፃ ገበያ ህግ ችግር የለውም፣ ነዳጅ ካለህ ምግብ ትገዛለህ። ወይም ሰሊጥ ሸጠህ ስንዴ ትገዛለህ፤ እንደ እኛ አገር። ይህ አገራት የምግብ ሉዓላዊነትን (food soverginity) ለማረጋገጥ አይረዳቸውም። እንደ አሜሪካ ያሉ አገሮች መሰረታዊ ምግቦችን (ስንዴ ለምሳሌ) በድጎማ በአገር ውስጥ ያመርታሉ እንጂ ርካሽ ስለሆነ ከካናዳ ወይም ዩክሬን አይገዙም። ኢትዮጵያ መስራት ያለባት በምግብ ራስን መቻልን፣ የሉዓላዊነት ጉዳይ አድርጋ ነው። ኑግ ሸጣ ዘይት ማስገባት ትክክል አይደለም። ኢትዮጵያ መሰረታዊ የምግብ ምርቶችን መቶ በመቶ በአገር ውስጥ የመሸፈን የሉዓላዊነት ደረጃ ያለው ፖሊሲ ያስፈልጋታል። ምግብ ከውጭ በገበያ ህግ በመግዛት፣ የምግብ ዋስትና የማረጋገጥ ፖሊሲ ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም።
(ከግርማ ሰይፉ ማሩ ፌስቡክ)
***
የመንታ ትንሳኤዎች ወግ፤
1978 እና 2012
በመንታነታቸው መሀል ሰላሳ አራት አመታት አሉ፡፡ በ1978 ብሄራዊ ወታደር ነበርኩ፤ ወታደር ብቻ! ዛሬ መምህር፣ ደራሲና ገጣሚ ነኝ፤ ብዙ ነገር ነኝ፡፡ ሁለቱ እኔዎች የሚገናኙት እንደ ሸረሪት ድር በቀጠነ ክር ነው፡፡ ይህን ቀጭን ክር አንዳንዴ ወቅትና ገጠመኝ ብረት (ያውም ማግኔት) ያደርጉታል፤ ሁለቱን እኔዎች አሳስሞ ይሰፋቸዋል፡፡ አንድ መንታ ያደርጋቸዋል፡፡ የዛሬው ትንሳኤም ያንን ጉልበት አግኝቷል፡፡.
እነዚህ ሁለት ፋሲካዎች ብቻዬን ያሳለፍኩባቸው ናቸው፤ የ1978ቱ በተዘጋ ቤርጎ፤ የ2012ቱ በተዘጋ ጎጆ:: ጎጆ ከቤርጎ ቢሰፋም፣ ነፍስህ ብቻዋን መሆኗን ካመነች ለውጥ የለውም፡፡
በ1978 ለትንሳኤ በአል ወር ገደማ ሲቀረው አንድ ኤሮግራም ደረሰኝ፤ ከወንድሜ:: ሙሉ ኤሮግራሙ ግጥግጥ ተደርጎ ቢጻፍበትም፣ ዋናው ሀሳብ፣ ‹‹ለትንሳኤ በአል ደሎ መና እመጣለሁ፤ ፍቃድ ጠይቅና ና፡፡›› የሚል ነበር፡፡ የቅዳሜ ስኡር በጠዋት ወደ ደሎ መና፡፡ መንገድ ላይ ሶስት ብሄራዊ ወታደሮችና በርካታ መደበኛ ወታደሮች ነበሩ፡፡ ወደ አስር ኪሎ ሜትር በእግር ሄደን፣ ከሪራ የመጣ የጭነት መኪና አገኘን፤ ለቀሪው 12 ኪሎ ሜትር፡፡
ደሎ መና ደረስኩ፤ ወንድሜን በየሆቴሉ ፈለግኩት፤ የለም፡፡ የምሳ ሰአት እስኪደርስ ከነዚያ ሶስት ብሄራዊ ወታደሮች ጋር ወዲህ ወዲያ እያልን ቆየን፡፡ ከተማዋ ከማነሷና ከአቧራዋ ጋር፣ የወፍጮ ቤት ቋት አራጋፊ መዳፍ ታክላለች፤ ትመስላለችም:: ወታደሮች፣ ባለ ሌላ ማእረግተኞችና መኮንኖች አጨናንቀዋታል፡፡
ሙሉ ሆቴል የጀርባ በረንዳ ላይ አራታችን ምሳ ስንበላ፣ አንድ በቀበቶ ወገቡን ሰርስሮ ሊበጥስ የተወራረደ የሚመስል መደበኛ ወታደር፤ ‹‹ብሄራዊ ጦር! እንዴት ናችሁ? የአብዮታዊት እናት ሀገር አለኝታዎች፡፡›› እያለ መጣና በቁሙ ለአራት ያዘዝነው 3 ሚስቶ ላይ ወረደበት:: ‹‹ብሉ እንጂ! ወታደሮች አይደላችሁም!››
ባዶ ትሪ ትቶልን ሄደ፡፡
‹‹ቢበላስ፣ ምግብ እንጂ የሰው ነፍስ አይደል!›› ላለማለት የምትችለው፣ ከ20 ብር የኪስ ገንዘብህ ላይ 3 ብር ተቀንሶ 17 ብር በወር የሚከፈልህና እሷን ይዘህ ከተማ የወጣህ ብሄራዊ ከሆንክ ብቻ ነው፡፡
ወደ 8 ሰአት አካባቢ፣ የወንድሜ አለመምጣት ቁርጥ ሲሆን፣ ቢታታ የሚባለው ሰፈር የማውቃት ልጅ አለች፤ እሷ ጋ ሄድኩ፡፡ በሳጠራ የታጠረች፣ አነስ ያለች የአሞራ ክንፍ ቤት ናት፡፡ ከምትሸጠው ጠጅ በነጻ ቀዳችልን፡፡ እኔም አሳቅኳት፤ ሞቅ ሲለኝ ሳቋ እየጨመረ መጣ፡፡ ይባስ ብዬ ናፍቃኝ እንደመጣሁ ነገርኳት፤ አሁንም ይባስ ብዬ፣ ፍቃድ ከልክለውኝ የፈለገው ይምጣ ብዬ እንደመጣሁ ነገርኳት፡፡ በጠጅ ድልቅቅ ብዬ፣ ጠጅ መስዬ፣ እስዋ ዶሮ የሚባርክላት ፍለጋ ስትወጣ አብሬያት ወጣሁ፡፡
‹‹እንዳታመሽ›› ስትለኝ፣
‹‹ትንሳኤ እኮ ነው›› አልኳት፡፡
የማላውቀው ኩራት ድብልቅ ስሜት ተሰማኝ፤ አሁን ሳስበው የአባወራነት ስሜት ሳይሆን አይቀርም፡፡ ከነዚያ ብሄራዊ ወታደሮች ጋር ቀጠሮ ነበረን፡፡ አገኘኋቸው:: እንደ እኔም ባይሆን ጠጅ ጠጥተው ሞቅ ብሏቸዋል፡፡ ጠጅ ጋበዝኳቸው፤ ከመጣሁ ብዙ አላወጣሁም፤ ወደ 14 ብር ገደማ ነበረኝ:: ለሁለት ጠርሙስ ጠጅ 6 ብር ከፈልኩ፡፡
ሁለት ሰአት ላይ ቀን ምሳ የበላንበት ሆቴል ለእራት ስንገባ፣ ያ አራዳ ነኝ ባይ ፍልጥ ወታደር ከበርካታ ወታደሮች ጋር ባንኮኒ ተደግፎ ይጠጣል፤ ወገቡ እስካሁን አለመበጠሱ ገረመኝ፡፡ ሁለቱ ይደንሳሉ፤ የተቀመጡትን አልቆጠርኳቸውም:: በጓሮው በረንዳ፣ ቀን ምሳ የበላንበትን ጠረጴዛ ከበን ተቀመጥን፡፡ ሁለት ሚስቶ አዘዝን፡፡ በጠጅ ጥግብ ብለናል፡፡ አንዳንዴ እንደጎረስን፣ ያ ቀን ምሳችንን ጠራርጎ የበላ ወታደር መጣ፡፡
‹‹ብሄራዊ ጦር፤ የአብዮታዊት እናት ሀገር መከታ!››
እጁን አሹሎ መጣ፡፡ ተበሳጨሁ፤ ነጠቃው ሳይሆን፣ እርድናው አበሳጨኝ:: በእሱ ቤት በቃ እኛን ጨላ ባላገር አድርጎናል::
ጠረጴዛው ላይ ውሀ የተሞላ አናናስ የመሰለ ጆግና አራት ኒኬል ብርጭቆዎች ከትሪው እየተገፋፉ ተቀምጠዋል፡፡
አንዴ ጎርሶ ሁለተኛውን ሲሰነዝር . . .
‹‹አንተ እናትክን . . . አራዳ መሆንህ ነው!››
ጆጉን አነሳሁና ውሀውን ከክንዱ ጀምሬ ከለበስኩበት፡፡ ትሪው በማእበል ተመታ፡፡ ተጥለቀለቀ፡፡ እሱ ወደ ኋላው ተፈናጠረ፡፡ ሌሎቹ እጃቸውን ሰበሰቡ፤ መቀመጫዎቻቸውን ስበው ገለል አሉ፡፡
ወዲያው ሳቅ ፈነዳ፡፡ ቀጥሎ የወታደር ጫማ ፊቴ ላይ ፈነዳ፡፡
‹‹የእኔን እናት? ... የእንጭቅ ልጅ፣...” (ይህቺን ስድብ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማኋት የዚያን እለት ነው)፡፡
ካልገደልኩት አለ፡፡
አልሞትም አልኩ፡፡
ተደባደብን፡፡
በጂን የሰከሩ ጓደኞቹ ተንጋግተው መጡ::
‹‹ምን ተፈጠረ?››
ጠየቁ፡፡
‹‹ይሄ ኩታራ የእኔን እናት. . .››
የጸባችን ዋና ምክንያት የእሱ ሌማታችንን በተደጋጋሚ መድፈር መሆኑ ቀርቶ፣ የእኔ እናቱን በስድብ መድፈር (ያውም በደም ፍላት) ሆነ፡፡
ፈረዱብኝ፡፡
‹‹ጠጅ አሳስቶኝ ነው›› ብል የሚሰማኝ አጣሁ፡፡
‹‹የት ይሄድብናል፤ የእኛው ነው:: በዚህ በር አይደል የሚወጣው፡፡››
ጓደኞቹ አባብለው ይዘውት ገቡ፡፡
ላልበላነው 2 ሚስቶ 3 ብር ከፈልን:: እንዴት እንውጣ? ተመካከርን፡፡
እነሱ ያሉበት የሆቴሉ ሳሎን፣ የፊት ለፊት በርና መስኮት ወለል አድርጎ የግቢውን አጥር የብረት በር ያሳያል፡፡ በዚያ ላይ ለበረንዳው መብራት የገጠሙለት አምፑል ሳይሆን ጨረቃን ራሷን ነው፡፡
‹‹አንተ እዚሁ አልጋ ያዝ፡፡ እኛ በውጭ በኩል ወደ አጥሩ በር ተጠግተን፣ ወጥተን እንሩጥ፡፡ አይዙንም፣ ከያዙንም አንተ ትድናለህ፤ እኛን ምን ያደርጉናል፤ አባረው ከያዙን እሱ ቀድሞን ሮጧል እንላቸዋለን›› አለ አንዱ ብሄራዊ፡፡ አብዛኛው ብሄራዊ ወታደር፣ በተለይ አንደኛው ዙር፣ እራሱን እንደ ወታደር አይቆጥርም ነበር:: ተስማማን:: አንዱ ቤርጎ ገብቼ ቆለፍኩ:: ወደ በሩ ተጠግተው ሸመጠጡ፡፡
ጠጅና ድብድቡ አካሌን እንጂ ህሊናዬን አላደከመውም፡፡ አስብ ነበር ስለ ዘመኑ . . . ኢትዮጵያውያን ‹‹አብዮታዊት እናት ሀገር ወይም ሞት!›› ብለው፣ እጃቸውን እየወነጨፉ፣ ከአስገንጣይ ወንበዴው ወያኔና ከገንጣይ ሻእቢያ ሀገራቸውን ሊጠብቁ ይዘምሩ ነበር፡፡ ልጆቻቸውን ወደ ውትድርና ፈቅደው ይሸኛሉ፤ አኩርፈው ያሳፍሳሉ፡፡ ... ኪነት ለአብዮቱ ትዘምራለች፤ ጦር ሜዳ ገብታ ታዋጋለች፤ ከተማ ገብታ ታደራጃለች፣ ታስታጥቃለች፡፡ ... ግዳጅ ይታወጃል፤ የጭነት መኪና ግዳጅ፣ . . . አውቶቡስ ግዳጅ፣ . . .
ድንገት ዶሮ ጮኸ!
እየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ ተነሳ! ትንሳኤም ሆነ፡፡
በጠባብ ቤርጎ ውስጥ የህይወቴን የመጀመሪያውን የብቻ ፋሲካ ተቀበልኩ፡፡
ከ34 አመት በኋላ 2012 ሆነ፡፡
በ1978 እርስ በርስ ይዋጉ የነበሩት ኢትዮጵያውያን፣ ከኮቪድ-19 ጋር ውጊያ ገጠሙ፡፡ እጃቸውን ለመፈክር እየወነጨፉ ወደ ጦር ግንባር አልዘመቱም፡፡ እጆቻቸውን እየታጠቡ ወደ ቤታቸው ገቡ፡፡ መንግስት አዋጅ አወጀ፣ ግዳጅ ጣለ፤ ቲቪውና ራዴዮው በውሀና ሳሙና ተዘፈዘፈ፡፡ ኪነት እጅ ማስታጠብን፣ ሳኒታይዘር ማደልን፣ እርዳታ ማሰባሰብን . . . ተያያዘችው:: በ1978 በህግ ያስቀጣ የነበረው፣ የፈሪ ታቴላ የነበረው እቤት መደበቅ፣ ዛሬ የጀግንነት መለኪያ፣ አሸናፊነት ሆነ፡፡
አሸናፊነት የሰው ልጅ አራተኛ መሰረታዊ ፍላጎት ነው፡፡ የዛሬ 34 አመት በውትድርና ክላሽንኮቭ አንግቼ፣ የአሸናፊነት ሰዋዊ ፍላጎቴን (ቢያንስ ባለመሞት) ለማሳካት ሁለት አመት ተኩል ስታገል፣ አንድ ፋሲካ በባዶ ቤርጎ ውስጥ አለፈች፡፡ በዚያ ትግል አሸንፌ ይሁን ተሸንፌ እስካሁን አልገባኝም፤ ቢሆንም ግን እስከ ዛሬ አሸናፊነቴን ለማረጋገጥ እየታገልኩ ነው፤አልታከተኝም:: ይኸው ዛሬም በክላሽ ምትክ ሳኒታይዘርና አልኮል፣ በኮሾሮና ዝግኒ ምትክ ፓስታና የቲማቲም ድልሄን ይዤ፣ ጎጆዬን ዘግቼ ትግል ገጥሜያለሁ፤ ዛሬም አሸናፊ ልሁን አልሁን አላውቅም፤ ትግልን መርሄ አድርጌዋለሁ፤ ትግል ላይ ነኝ፡፡ . . .
ድንገት ዶሮ ጮኸ!
እየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ ተነሳ!
ትንሳኤም ሆነ፡፡
በተዘጋ ጎጆ ውስጥ የህይወቴን ሁለተኛ የብቻ ፋሲካ ተቀበልኩ፡፡
ሶስተኛ፣ አራተኛ . . . ይኖረው እንደሁ ማን ያውቃል!
(ሰኔ 1978)............. (ሚያዝያ 2012)
(ከበድሉ ዋቅጂራ ፌስቡክ)
***
የዘመኑ አራዳ
የዘመኑ አራዳ ሰልፍ የአካል ሳይሆን፣ የሀሳብ መስመር መሆኑን ያውቃል፡፡ ተፍ ተፍ - ከተፍ ማለት፣ ቀድሞ መገኘት፤ የገባው መምሰል፣ ሳይታጠቡ ማስታጠብ - ሳሙና ማቀበል፤ ሳኒታይዘርና አልኮል ለመግዛት መጋፋት፣ በጓንት መጉረስ፣ ጭንብል (ማስክ) እንደ ማስቲካ ተጠቅሞ ማሳደር፣ ቆንጆ መጥቀስ- ለመዳበስ . . . ተጋፍቶ ጋቢና መግባት፤ ትከሻ ቸብ አድርጎ የጀበና ቡና መጋበዝ፤. . . እነዚህን ካደረግህ አንተ አሮጌ አራዳ ነህ፡፡
የዘመኑ አራዳ ለሳኒታይዘርና አልኮል አይጋፋም፤ ግፊያና ልፊያ ካየ ላሽ ይላል፤ ወሸላ የተገጠመላቸው የላስቲክ ጋኖች ሞልተው፤ ለምን ይጋፋል?
 ይታጠባል፤ በባልዲ ውሀ ይዞ ሳይታጠብ የሚያስታጥብ አሮጌ አራዳ ካጋጠመውም አሪፍ! ከሚጨነበል መራቅን፤ ከቻለ ቤቱ መከተትን ይመርጣል፡፡ እንኳን ታክሲ ሊፍት ቢያገኝ በጭራሽ፤ በእግሩ ይሄዳል፡፡ ሰልፍ እንደ ምድር ወገብ የሀሳብ መስመር መሆኑ ገብቶታል፤ በአካሉ ተራርቆ - ተዘባርቆ ሰልፉ ቀጥ ያለ ነው፣ ወረፋው አይዛነፍም:: የራቀች ቆንጆም ሲያገኝ፣ እንደራቀ ይጠቅሳል- ያደንቃል፤ ከባሰበት ከንፈሩን ይነክሳል፡፡ የጀበና ቡና ስትጋብዘው፣ ‹‹ጀበና ግዛልኝ፣ ቤቴ አፈላለሁ›› ይልሀል፤. . . . እና ነገ በታክሲ ይሄዳል፤ የጠቀሳትን ይዳስሳል፤ ከፈለገ ያገባታል፤ ካገባት ልጅ ይወልዳል፤ ልጁን ትምህርት ቤት ያስገባል፤ .. . . . . ያራዳ ልጅ ህይወት ይቀጥላል፡፡
(ከበድሉ ዋቅጂራ ፌስቡክ)
April 16
***
የብሔር ፖለቲከኞች ሥነልቦና
የብሔር ፖለቲከኞች እንደ ግለሰብ ማሰብ ያቅታቸዋል፣ ሁሉንም ነገር ማስተናገድ የሚፈልጉት በብሔራቸው ጥላ ሥር ሆነው ነው። ስለዚህም እንደ አንድ ግለሰብ ለተተቹበት ምላሻቸውን የሚሰጡት እንደ ብሔር ነው፣ “ይህ እገሌ የሚባል ብሔር ጥላቻ ነው፣ ይህ እገሌ የሚባል ብሔር ላይ የተከፈተ ጦርነት ነው” በማለት ራሳቸውን በብሔራቸው ውስጥ ይወሽቃሉ። የዚህ የቡድንተኝነት “groupism” መንፈስ ተልዕኮው በጥቂቱ ሁለት ነው፦
1. ራስን የመከላከል እርምጃ ነው.”. It is a kind of self-defence mechanism” ...እንደ ግለሰብ ያጠፉት ጥፋት በቡድንተኝነት ውስጥ በመወሸቅ የሚሰወር ይመስላቸዋል። ልክ እስስት ራሷን ከአካባቢው ጋር አመሳስላ ከጠላቷ ለመሰወር የምታደርገው ዓይነት ጥረት እንደ ማለት። እውነት ይሁን ውሸት ባላውቅም አንድ በተደጋጋሚ የሚነገር የቻይናዊና የሀገራችን ገበሬ ገጠመኝ አለ፦ በአንድ የሀገራችን ክፍል አንድ ቻይናዊ፣ የገበሬውን አህያ በመኪናው ገጭቶ ይገድለዋል፤ ቻይናዊውም ለገበሬው “የሚኖርበት ካምፕ እዚሁ አካባቢ ስለሆነ ካምፕ ውስጥ ገብቼ ለአህያህ የሚመጥን ብር ላምጣልህ” ይለዋል፣ ይህን የሰማ ገበሬ ኡኡታውን ያቃልጠዋል፣ ምን ሆንክ? ተብሎ ሲጠየቅ፦ “እሱ እዚያ ካምፕ ዘመዶቹ ውስጥ ገብቶ ከተቀላቀለ በኋላ ማን ይለየዋል? ሁሉሞ ቻይናዊያን መልካቸው ይመሳሰል የለም ወይ?” በማለት መለሰ ይባላል። የብሔር ፖለቲከኞችም ራሳቸውን ለመከላከል የሚጠቀሙት ተመሳሳይ ታክቲክ ነው፦ላጠፉት ጥፋት ተጠያቂነቱ ሲመጣ ዘልለው ወደ ብሔር ካምፓቸው መግባትን ይመርጣሉ፦ ከአጥራቸው ውስጥ እንደገቡም .”.እኔን የነካ የኔን ብሔር የነካ ነው..” የሚለውን ዲስኩራቸውን ያሰማሉ...አያድርስ ነው።
2. ሁለተኛው የብሔር ቡድንተኝነት ተልዕኮ፣ ብሔሩን የመቀስቀሻ ስልት መሆኑ ነው፣ የድረሱልኝ ጥሪ ነው፣ የማስፈራሪያ ታክቲክም ነው.”.Look I am not alone, many more are in my side..” ዓይነት ማስፈራርያ! I mean It is one of the strategies to mobilise their ethnic group. እዚህ ጋ አንድ ምሳሌ ልጥቀስ፦ በአንድ ወቅት ጋዜጠኛ አበበ ገላው፣ በፀጋዬ አራርሳ የዶክትሬት ዲግሪ የትምህርት ማስረጃ ላይ ጥያቄ ሲያነሳ፣ ፕሮፈሰር ሕዝኤል ገቢሳ ወዲያው በፌስ ቡክ ገፃቸው፦
“ፀጋዬ አራርሳን መንካት የኦሮሞን ሕዝብ መንካት ነው” የሚል መልዕክት አስተላለፉ። በእኔ አተያይ፤ አበበ ገላው ያቀረበውን ሙግት ፕሮፈሰሩ መከላከል የነበረባቸው የትምህርት ዶኩመንቶቹን በማሳየት ነበር። ከዚህ ባለፈ የአንድ ግለሰብ የትምህርት ዶኩመንት ሲጠየቅ፣ መላ ብሔሩ እንደተነካ አድርጎ ማቅረብ..It is typical mass mobilisation stratgey.
በእኔ ምልከታ፤ ለተጠየቅነው ጥያቄ ሁሉ በብሔር ኪስ ውስጥ መሸጎጥ (This is also TPLF’s number one self defence and group mobilisation strategy...ለምሣሌ..”ሕወኃትን የነካ የትግራይን ሕዝብ የነካ ነው”) ሕክምና የሚያሻው የማንነት ቀውስ ነው..I mean identity as an individual!!! ብዙውን ጊዜ የብሔር ፖለቲካ አቀንቃኞች ለብሔር ፖለቲካው ብዙም ትኩረት የማይሰጡትን ሰዎች የሚከሱት በግሩፕ ማንነት ቀውስ ነው፣ ማለትሞ በብሔራቸው ስለሚያፍሩ ነው ይህን አቋም የሚያራምዱት በማለት ይከሷቸዋል። በነገራችን ላይ አንድ ግለሰብ ከብሔሩ ጋር ሊኖረው የሚችለው የቁርኝት ዓይነቶች..level of ethnic incorporation.... በጥቂቱ ወደ አራት ዓይነት ሲሆኑ እነርሱም Ethnic catagory, Ethnic Network, Ethnic Association , እና Ethnic Community ናቸው። የኛ ሀገር ፖለቲከኞች፣ የብሔር ማንነትህን እንደ እነሱ እስከ ወዲያኛው ካላጦዝከው በብሔር ማንነትህ እንዳፈርክ ይቆጥሩሃል። ይህ ፍረጃ አንድ ግለሰብ ከብሔር ማንነቱ ጋር ሊኖረው የሚችለው የቁርኝት ዓይነት አንድ ዓይነት ብቻ ነው የሚለውን የተሳሳተ አመለካከት ከማራመድ የሚመነጭ ስህተት ነው። ነገር ግን አክራሪ ብሔርተኞች ሌሎችን በብሔር ማንነት ቅዝቃዜ (Cold ethnicity) የሚከሱትን ያህል እነርሱም እንደ አንድ ግለሰብ (being as an individual) በማንነት ቀውስ ውስጥ እንዳሉ አይረዱትም። እንዲያውም የግለሰብ ማንነትን ማጣት የከፋ የማንነት ቀውስ ነው።
(ከጌታሁን ሔራሞ ፌስቡክ)
April 20 ·
***
ለማድነቅ ዳተኞች አንሁን!
የዛሬ ስድስት ዓመት። የወዳጄ ባለቤት ልጇን አሜሪካን ሀገር ተገላግላ (ያረፈችው ከወንድሜ ቤት ነበር) ወደ ሀገሯ ኢትዮጵያ ልትመለስ ዋሽንግተን ዲሲ አይሮፕላን ማረፍያ ትደርሳለች። ትልልቅ ሻንጣዎቿን ካስጫነች በኋላ ልጇንና ሌላ ወደ ፕሌኑ ውስጥ ይዛ እንድትገባ የተፈቀደላትን ቦርሳዋን ይዛ ከሌሎች መንገደኞች ጋር ጉዞዋን ወደ አይሮፕላኑ ታደርጋለች፤ ገና የሶስት ወር አራስ ነበረችና ልጇን በሁለት እጆቿ ታቅፋ በዚያ ላይ ቦርሳዋን መያዝ አቅቷት ከብዷት ነበር። በዚህ መሃል አንድ በ30ዎቹ መጨረሻ ገደማ ያለ ኢትዮጵያዊ ወጣት ከርቀት የወዳጄን ባለቤት ችግር ተመልክቶ፣ መግባት የነበረበትን የ”VIP” መስመሩን ትቶ ሊያግዛት መጣላት። የወዳጄን ባለቤት ቦርሳም ተሸክሞላት እስከምትፈልገው ርቀት አደረሰላት። ታዲያ የወዳጄ ባለቤት በዚህ ሰው ደግነት በእጅጉ ተገርማ ፦ “ወንድሜ ማን ልበል ስምህን?” ብላ ስትጠይቀው “ስሜ ይቅርብሽ” አላት፣ ስልኩንም ስትጠይቀው፤ ተመሳሳይ ምላሽ ሰጣትና ወደ VIP መስመሩ ተመልሶ ሄደ።
ታዲያ ይህች የወዳጄ ባለቤት፣ ከአራት ዓመታት በኋላ፣ አንድ ሰው በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለፓርላማ ንግግር ሲያደርግ ትመለከታለች። አተኩራ ስታያው ከአራት ዓመታት በፊት አሜሪካን ዋሽንግተን ኤር ፖርት ቦርሳዋን የተሸከመላት ሰው ነው፦ ክቡር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ አሊ...የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር።
ወዳጄና የሕፃኗ አባት አቶ አድማሱ አርፍጮ ይባላል። በደቡብ አፍሪካና በኢትዮጵያ በልዩ ልዩ ኢንቨስትመንት መስክ የተሰማራ. ሀገሩን የሚወድ ወጣት ባለሀብት ነው። ከአንድ ወር በፊት እኔም እሱም ከዶ/ር ዐቢይ ጋር አብረን ባለንበት፣ እንዲህ ብሎ ጠየቀው፦ “ከዓመታት በፊት አሜሪካ ዋሽንግተን አየር ማረፊያ  ውስጥ የሆነች አራስ እናት፣ ልጇን ታቅፋ፣ ቦርሳዋን መያዝ ሲያቅታት ያገዝካት ትዝ ይልሃል?” በማለት! ዶ/ር አብይ ለማስታወስ ጊዜ አልፈጀበትም፦ “አዎን፣ እንዳልተመቻት ስመለከት ሄጄ አገዝኳት” ብሎ ከመለሰ በኋላ አቶ አድማሱ “ያኔ ቦርሳዋን የተሸከምክላት የኔ ባለቤት ነች” ብሎ ለዶ/ር ዐቢይ ሲነግረው፣ ዶ/ር ዐቢይም ግጥምጥሞሹ ገርሞት “ታዲያ ሕፃኗ አደገችልህ?” በማለት ጠየቀው። ምላሻችን፦ “ያኔ የእናቷን ቦርሳ ያሸከመችህ ሕፃን አዎን አድጋለች፣ ስድስተኛ ዓመቷንም ይዛለች፣ ፎቶዋንም ለጥፈንልሃል” የሚል ነው።
ዶ/ር ዐቢይ ከ”VIP” መግቢያው ተመለከተ፡፡ በነገራችን ላይ ዶ/ር ዐቢይ፤ የአራሷን እህታችንን ቦርሳ ለመሸከም ፈቃደኝነቱን በገለፀበት ወቅት የኢትዮጵያ ሳይንስና ቴክኖሎጂ መረጃ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ነበር--- የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ከመሆኑ ስድስት ወራት ያህል አስቀድሞ ማለት ነው።
በእርግጥ ብዙዎቻችን ተመሳሳይ ሰናይ ተግባር ፈፅመን ይሆናል፦ አንድ የመንግስት ባለሥልጣን የ”VIP” መስመሩን ቀይሮ አንዲት እናትን ለመርዳት መምጣት ግን ትህትናን ይጠይቃል። ከሰናይ ምግባር በኋላ ደግሞ ማንነቱንና ስልኩን ይፋ ለማድረግ ያለመፈለጉም ሌላ ትኩረት የሚስብ እውነት ነው፦ ለሁሉ ጊዜ አለው አይደል? ይኸው ጊዜ ደርሶ ይህን የዶ/ር ዐቢይ መልካም ምግባሩን በአደባባይ ለመግለጥ ቻልን! የቆየ ከእርሱ ዘንድ የከረመ ነው... ለሰው ልጅ አሳቢነቱና አዛኝነቱ...ዛሬ ቤተ መንግስት ገብቶ የፈበረከው አይደለም፣ ካላመናችሁ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሠራተኞችን ጠይቁ! ስህተቶችን ባየን ቁጥር ለመንቀፍ የምንሽቀዳደመውን ያህል፣ አስተማሪ የሕይወት ልምምዶችንም ባስተዋልን ቁጥር፣ ለማመስገንም ሆነ ለማድነቅ ዳተኞች አንሁን።
(ከጌታሁን ሔራሞ ፌስቡክ)


Read 3000 times