Saturday, 07 July 2012 11:09

የቶም ክሩዝ ህይወት እየተቃወሰ ነው ተባለ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

ከሳምንት በፊት ከኬቲ ሆልምስ ጋር ለአምስት ዓመት የዘለቀ ትዳሩ የፈረሰበት ቶም ክሩዝ፤ ለከፍተኛ የኑሮ ቀውስ መዳረጉን ዘገባዎች አመለከቱ፡፡  ኬቲ ሆልምስ ለፍርድ ቤት ባስገባችው የክስ ማመልከቻ፤ ቶም ክሩዝን ለመፍታት የወሰነችው ከቤተሰቡ ይልቅ “ሳይንቶሎጂ” ለተባለው ሃይማኖቱ ያልተገባ ትኩረት አብዝቷል በሚል ምክንያት መሆኑን የጠቀሰው ሎስአንጀለስ ታይምስ፤ ሱሪ የተባለችውን የ6 ዓመቷን ልጃቸውን ለብቻዋ ማሳደግ እንደምትፈልግ መናገሩዋ ተዋናዩን እንዳስደነገጠው ጠቁሟል፡፡

የፍቺው ዋና ምክንያት የ6 ዓመቷ ሱሪ በሳይንቶሎጂ ሃይማኖት ትምህርት እንድታድግ ከመፈለጉ ጋር በተያያዘ እንደሆነ የጠቆመው ቲኤምዜድ፤ ኬት ሃይማኖቱን ጋብቻቸውን ሲፈፅሙ ብትቀበልም ታዳጊ ልጇ ግን እምነቱን እንድትቀበል ፍላጎት እንደሌላት   አመልክቷል፡፡ ሳይንቶሎጂ ከሌላ ዓለም የመጣን የላቀ አዕምሮ ያለን ፍጡሮች ነን በሚሉ ዝነኛ ሰዎች አማካኝነት የሚንቀሳቀስ ተቋም ሲሆን የሃይማኖሩ መሪ ዴቪድ ሚስካቭዬጅ፤ ቶም ክሩዝ ከኬቲ ሆልምስ ጋር ጋብቻ ሲፈፅም አንድኛ ሚዜው ነበረ፡፡ ኬት ሆልምስ፤ ከቶም ክሩዝ ጋር በፈፀመችው የጋብቻ ውል መሰረት በትዳር ለቆየችበት አምስት ዓመታት ለእያንዳንዱ 3 ሚሊዮን ዶላር ታስቦላት ከፍቺው በኋላ 15 ሚሊዮን ዶላር ታገኛለች ተብሏል፡፡  ከኬቲ ሆልምስ ጋር በትዳር በቆየባቸው አመታት እስከ 200 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ያገኘው ቶም ክሩዝ፤  ባለፈው አንድ ዓመት በሆሊውድ ከፍተኛ ገቢ ካስመዘገቡ ተዋናዮች በቀዳሚነት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ፎርብስ ሰሞኑን ጠቁሟል፡፡ ክሩዝ ባለፈው አንድ አመት ያገኘው ገቢ 75 ሚሊዮን ዶላር እንደሆነ ያመለከተው ፎርብስ፤ ሁለተኛ ደረጃን በ336 ሚሊዮን ዶላር ከተጋሩት ሊዮናርዶ ዲካርፒዮና አዳም ሳንድለር በእጥፍ ብልጫ ማሳየቱን አስታውቋል፡፡ የቶም ክሩዝ ቀጣይ የገቢ ምንጮች ከትዳሩ መፍረስ ጋር በተያያዘ እንዳይቀንስ የሚል ስጋት መኖሩን  ያወሳው ፎርብስ፤ ይሄም በቀጣይ ለእይታ በሚበቃው “ኦብሊቭዮን” የተባለ ሳይንሳዊ ልቦለድ ፊልሙ ምን ያህል ገቢ ሊያገኝ እንደሚችል ለመገመት አዳጋች አድርጎታል ብሏል፡፡

የ33 ዓመቷ ኬቲ ሆልምስ የፍቺ ማመልከቻ እንዳስገባች በድንገት የሰማው ቶም ክሩዝ፤ ከፍተኛ መረበሽ ውስጥ መግባቱን የገለፀው ኢንተርቴይመንት ዊክሊ፤ ሁኔታውን እንደመርዶ  የ50ኛ ዓመት ልደቱን በሚያከብርበት ዋዜማ ላይ መስማቱ እንዳስጨነቀው  ጠቁሟል፡፡

ክሩዝና ሆልምስ ከአምስት ዓመት በፊት በጣልያን በሚገኝ አንድ ጥንታዊ ቤተመንግስት ውስጥ ጋብቻቸውን በፈፀሙበት ወቅት “የሆሊዉድ ምርጥ ፍቅር” ተብሎ የነበረው ግንኙነታቸው ሰሞኑን ባልተጠበቀ ሁኔታ መፍረሱ ብዙዎችን ግራ አጋብቷል ተብሏል፡፡

በአክሽን ፊልሞቹ ከፍተኛ ገቢ በማስገባት ግንባር ቀደም የሆሊውድ ተዋናይ የሆነው ቶም ክሩዝ ከአሁኑ ጋር ትዳሩ ሲፈርስ ለሶስተኛ ጊዜ ሲሆን ከእሷ በፊት ሚሚ ሮጀርስና ኒኮል ኪድማን ከተባሉ እውቅ ተዋናዮች ጋር መስርቶ በነበረው ትዳር ሶስት  ልጆችን አፍርቷል፡፡

 

 

Read 1120 times Last modified on Saturday, 07 July 2012 11:16