Saturday, 07 July 2012 11:09

“ዘ አሜዚንግ ስፓይደር ማን” በገቢ አዲስ ሪከርድ አስመዘገበ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

“ዘ አሜዚንግ ስፓይደር ማን”  ባለፈው ማክሰኞ በሰሜን አሜሪካ ሲታይ በአንድ ምሽት 35 ሚሊዮን ዶላር በማስገባት አዲስ ሪከርድ አስመዝገበ፡፡ ፊልሙ ከአምስት ዓመት በፊት በ27.9 ሚሊዮን ዶላር “ትራንስፎርመርስ” የተባለው ፊልም ያስመዘገበውን የ27.9 ሚሊዮን ዶላር ሪከርድ ነው የሰበረው፡፡ እስከ ነገ እሁድ ድረስ የፊልሙ የስድስት ቀናት ገቢ 140 ሚሊዮን ዶላር ሊደርስ እንደሚችል ተገምቷል፡፡

ከሰሜን አሜሪካ በፊት በህንድና በሌሎች 13 አገራት ለእይታ የበቃው “ዘ አሜዚንግ ስፓይደር ማን”  50.2 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቶበታል፡፡ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ በሰሜን አሜሪካ መታየት የጀመረው ፊልሙ፤ በመጀመርያ ሳምንታዊ ገቢው እንደተጠበቀው ስኬታማ ሲሆን ፊልሙ ዕድሜያቸው ከ25 ዓመት በታች በሆኑ ፊልም አፍቃሪዎች ዘንድ በጉጉት  ሲጠበቅ እንደቆየ ይታወቃል፡፡ ዘ ሆሊውድ ሪፖርተር እንደጠቆመው፤ ፊልሙ ከቀደምት የስፓይደርማን ፊልሞች ጋር የሚመሳሰሉ ታሪኮችን መያዙ ያስተቸው ሲሆን በአክሽን ትእይንቶቹም ብዙ ለውጥ አልታየበትም ተብሏል፡፡ ፊልሙን ዳይሬክት ያደረገው ማርክ ዌብ ፤ በትወና እና በተለያዩ የስራ ዘርፎች ከአንድ ሺ በላይ ሰዎችን እንዳሳተፈ ታውቁዋል፡፡

በማርቭል ፒክቸርስ እና በኮሎምቢያ ፒክቸርስ ጥምረት እንደተሰራ የተነገረለት ፊልሙ   230 ሚሊዮን ዶላር ወጥቶበታል፡፡ አንድሪው ጋርፊልድ እና ኤማ ስቶን የሚተውኑበት “ዘ አሜዚንግ ስፓይደርማን”፤ በከፍተኛ የቴክኖሎጂ ቅንብርና ጥራት እንደተሰራ የጠቆመው ዘ ሆሊውድ ሪፖርተር፤ 56 የስፓይደርማን ትጥቆችን መጠቀሙን ጠቁሟል፡፡፡ የፊልሙ አዲስ የስፓይደርማን ገፀባህርይ መሪ ተዋናዩ አንድሪው ጋርፊልድ፤ከሶስት ዓመቱ ጀምሮ የስፓይደር ማን ገፀባህርይ አድናቂ ሆኖ ማደጉን የገለፀው ሎስአንጀለስ ታይምስ ፤ በፊልሙ ላይ ትወናውን በብቃት ለመወጣት ለስድስት ወራት ያህል በሳምንት ለስድስት ቀናት ጥናት ማድረጉን አብራርቷል፡፡ ከስፓይደርማን ትጥቆች 17 ያህሉን እየለበሰ የተወነው አንድሪው ጋርፊልድ፤  በቀረፃ ወቅት ልብሱን ለመታጠቅ 20 ደቂቃዎች ይፈጅበት እንደነበር ታውቁዋል፡፡

 

 

 

Read 1387 times Last modified on Saturday, 07 July 2012 11:16