Saturday, 07 July 2012 10:34

ኢትዮጵያና ኬንያ በኦሎምፒክ ለአፍሪካ ስኬት ተስፋ ሆነዋል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

ሊጀመር 3 ሳምንት በቀረው 30ኛው የለንደን ኦሎምፒያድ ኢትዮጵያና ኬንያ ለአፍሪካ ስኬት ተስፋዎች መሆናቸው ተገለፀ፡፡በኦሎምፒኩ የአፍሪካን አህጉር በመወከል ከሚሳተፉ 53 አገራት ኢትዮጵያና ኬንያ እንደልማዳቸው በአትሌቲክስ ውድድሮች ከፍተኛ የበላይነት በማሳየት ለበርካታ የሜዳልያ ድሎች እንደሚጠበቁ  ያወሱ ዘገባዎች ደቡብ አፍሪካና ናይጄርያ በብዙ ውድድሮች በመሳተፍ ልዩ ትኩረት እንደሚኖራቸው ገልፀዋል፡፡ከ4 ዓመት በፊት ቤጂንግ ባስተናገደው 29ኛው ኦሎምፒያድ ከአፍሪካ አህጉር 53 አገራትን የወከሉ 857 አትሌቶች ሲካፈሉ 40 ሜዳልያዎች (12 ወርቅ፣ 14 ብርና 14 ነሐስ) የተገኙ ሲሆን  ቢያንስ 1 ሜዳልያ ያገኙት አገራት 13 ነበሩ፡፡ በቤጂንጉ 29ኛው ኦሎምፒያድ ለአፍሪካ ከተገኙ ሜዳልያዎች ግማሹን የሰበሰቡትና 10 የወርቅ ሜዳልያዎችን የተጎናፀፉት ኬንያና ኢትዮጵያ ነበሩ፡፡ በወቅቱ ኬንያ 14 ሜዳልያዎች (6 ወርቅ፣ 4 ብርና 4 ነሐስ) በማግኘት ከአፍሪካ 1ኛ ከዓለም 15ኛ ደረጃ ማግኘቷ ሲታወስ የአፍሪካን 2ኛ ከፍተኛ ውጤት  በ7 ሜዳልያዎች (4 ወርቅ፣ 1ብርና 2 ነሐስ) ያስመዘገበችው ኢትዮጵያ ከዓለም 18ኛ ደረጃ መያዟ  አይዘነጋም፡፡

በለንደን ኦሎምፒክ ኢትዮጵያና ኬንያ በአትሌቲክስ ውድድሮች ለከፍተኛ ውጤት ከመጠበቃቸው ባሻገር ብዙዎቹ የአፍሪካ ኦሎምፒክ ቡድኖች  በተለያዩ የስፖርት ውድደሮች ንቁ ተሳትፎ ማድረጋቸውም ይጠቀሳል፡፡ ከእነዚህ የውድድር መደቦች መካከል  ባድሜንተን፤ ቴክዋንዶ፤ውሃ ዋና፤ሆኪ፤ ቅርጫት ኳስ፤ እግር ኳስ ይጠቀሳሉ፡፡ ደቡብ አፍሪካ በራግቢ እና በሆኪ፤ አንጎላ በቅርጫት ኳስ፤ ናይጄርያ በአጭር ርቀት የአትሌቲክስ ውድድሮች በኦሎምፒኩ የሜዳልያ ተስፋ ይኖራቸዋል ተብሏል፡፡ በለንደን ኦሎምፒክ ለአፍሪካ የሜዳልያ ተስፋ ከተጠበቁት መካከል በማራቶን በመካከለኛ እና በረጅም ርቀት ውድድሮች የኬንያ እና የኢትዮጵያ አትሌቶች የአንበሳውን ድረሻ ቢይዙም በ800 ሜትር የደቡብ አፍሪካዋ ካስተር ሴማንያ፤ በ800ሜትር የሱዳኑ አቡበከር ካኪ እንዲሁም በመካከለኛ ርቀት የሞሮኮ እና የኤርትራ አትሌቶች ተፎካካሪነትም ይኖራል፡፡ ለአፍሪካ የኦሎምፒክ የሜዳልያ ተስፋዎች ዋና ተቃናቃኞች ይሆናሉ የሚባሉት አገራት አዘጋጇ እንግሊዝ፤ አሜሪካ፤ ጃፓንና አውስትራሊያ ይገኙበታል፡፡ ከአትሌቶች በረጅም ርቀት የአትሌቲስ ውድድሮች በውጤታማነታቸው ለአፍሪካ የሜዳልያ ተስፋ እንቅፋት እንደሚሆኑ ግምት ከወሰዱት መካከል የእንግሊዙ ሞ ፋራህ፤ የአሜሪካው በርናንድ ላጋት ዋናዎቹ ሲሆን በ3ሺ ሜትር መሰናክል የፈረንሳይና የራሽያ አትሌቶች፤ በመካከለኛ ርቀት የጃማይካ፤ የአሜሪካ እና የራሽያ አትሌቶች ለአፍሪካውያኑ ከባድ ፉክክር እንደሚፈጥሩ ተጠብቀዋል፡፡የአፍሪካ ኦሎምፒክ ኮሚቴዎች ማህበር በለንደን ኦሎምፒክ በኬንሲንግተን ጋርደን በተዘጋጀው የአፍሪካ መንደር በርካታ ስራዎች ለማከናወን ዝግጅቱን እንዳጠናቀቀ አስታውቋል፡፡ በአፍሪካ መንደር በአህጉሪቱ ሙዚቀኞች ዘመናዊ እና ባህላዊ የሙዚቃ ኮንሰርቶች የሚያሳዩ ዝግጅቶች፤ የባህልና የታሪክ ገፅታዎችን የሚያሳዩ ኤግዚብሽኖች እንዲሁም የፋሽንና የዳንስ ትርኢቶች እንደሚቀርቡም ታቅዷል፡፡ በኦሎምፒክ ሰሞን እስከ 3 ሚሊዮን ጎብኝዎች ይኖሩታል በሚባለው የአፍሪካ መንደር ከሚሳተፉ አገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ናት፡፡

የኢትዮጵያ ዝግጅት

በለንደን ኦሎምፒክ ኢትዮጵያን የሚወክሉ  ኦሎምፒያኖች ሙሉ ለሙሉ የታወቁት ሐሙስና አርብ ከተደረጉት የ10ሺና የ5ሺ ሜትር የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች በኋላ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ኃላፊ አቶ ዱቤ ጅሎ፣ የኦሎምፒክ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ዶ/ር ይልማ በርታ እና የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ዋና ፀሐፊ ወ/ሪት ዳግማዊ ብርሃኔ ለተለያዩ የዓለም ሚዲያዎች በሰጡት አስተያየት ኢትዮጵያ በለንደን ኦሎምፒክ በሚኖራት ተሳትፎ አመርቂ ውጤት ለማስመዝገብ ከፍተኛ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡ “ዝግጁ ነን፣ አትሌቶቻችን በጥሩ ብቃት ላይ ናቸው” በማለት ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የተናገሩት የቴክኒክ ክፍል ኃላፊው አቶ ዱቤ ጅሎ ናቸው፡፡ የኦሎምፒክ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ዶ/ር ይልማ በርታ በበኩላቸው ለሮይተርስ በሰጡት አስተያየት ለንደን ላይ ኢትዮጵያ በውጤታማነቷ ከምትታወቅባቸው  የረዥም ርቀት የአትሌቲክስ ውድድሮች ባሻገር በመካከለኛ ርቀት  ከፍተኛ ውጤት ይጠበቃል ብለዋል፡፡ በቤጅንግ ኦሎምፒክ በ10ሺና በ5ሺ 4 ወርቅ ሜዳሊያዎች በተገኘበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በሌሎች የአትሌቲክስ የውድድር መደቦች  በሚኖር ተሳትፎ ላይ ጥረት እንዲደረግ ማሳሰባቸውን ለሮይተርስ የገለፁት ዋና አሰልጣኙ  ዶ/ር ይልማ በርታ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኑ በተለይ በመካከለኛ ርቀት የዳበረ የስልጠና ልምድና የፋይናንስ አቅም ባይኖርም በአጭር ግዜ በስፋት በመንቀሳቀስ የተከናወኑ ተግባራት በለንደን ኦሎምፒክ የሜዳልያ ውጤት ለማግኘት ተስፋ መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ዋና ፀሐፊ የሆኑት ወ/ሪት ዳግማዊት ብርሃኔ ከወር በፊት  ቮይስ ኦፍ ሩስያ ከተባለ ሚዲያ ጋር ባደረጉት አጠር ያለ ቃለምልልስ በለንደን ኦሎምፒክ ኢትዮጵያ ከአትሌቲክስ ባሻገር በሌሎች ስፖርቶች ለመሳተፍ መጣሯን ሲያስረዱ በውሃ ዋና አንድ ኦሎምፒያን ለማካፈል መብቃቱን አበረታች ብለውታል፡፡ ወ/ሮ ዳግማዊት ኢትዮጵያ ከ4 ዓመት በፊት ቤጂንግ ላይ ካስመዘገበችው ውጤት ለንደን ላይ እስከ 30 በመቶ ጭማሪ የሚያሳይ የሜዳልያ ስብስብ  ለማስመዝገብ እንጠብቃለን ብለውም ተናግረዋል፡፡

 

የኬንያ ዝግጅት

በ30ኛው ኦሎምፒያድ ኬንያ  54 ስፖርተኞችን በያዘው ቡድኗ ከአትሌቲክስ ባሻገር በክብደት ማንሳት፤ በውሃ ዋና እና በቦክስ በአራት የስፖርት መደቦች ለመካፈል ተዘጋጅታለች፡፡ የኬንያ ኦሎምፒክ ቡድን ሙሉ ዝርዝር ከሳምንት በፊት ሲታወቅ የአገሪቱ መንግስትና ድጋፍ ሰጭ ኩባንያዎች ሜዳልያ ለሚያመጡ አትሌቶች ከ3500 እስከ 11ሺ ዶላር ለመሸለም ቃል ገብተዋል፡፡ ኬንያ በለንደን ኦሎምፒክ በአትሌቲክስ ውድድሮች የምታሳትፋቸውን 38 አትሌቶች የመረጠችው ከሳምንት በፊት በመጨረሻ ማጣርያ  በአገሯ ላይ ባደረገችው ብሔራዊ ሻምፒዮና ላይ ነው፡፡ በናይሮቢ ናያዮ ብሄራዊ ስታድየም የተደረገውን አገር አቀፍ ሻምፒዮና 15ሺ ተመልካች ፤በርካታ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሐናት፣ የአትሌቶች ማናጀሮችና የውድድር አዘጋጆች በስፍራው በመገኘት ተከታትለውታል፡፡  በዚሁ  ብሄራዊ ውድድር የዓለምና የአፍሪካ ሻምፒዮናዎች፤ የኦሎምፒክ ሻምፒዮናዎች እና በአጠቃላይ የኬንያ ምርጥ አትሌቶች የለንደን ትኬታቸውን ለመቁረጥ ተሳትፈዋል፡፡ ታላላቆቹ የኬንያ አትሌቶች ቪቪያን ቼሮይት፣ ፖሚላ ጄሊሞ፣ ዴቪድ ሩዲሻ፣ እዝቄል ኬምቦይ እና ሌሎችም የኦሎምፒክ ተሳትፎዋቸውን ሊያረጋግጡ የበቁት በዚሁ የመጨረሻ ማጣርያ ምእራፍ ነበር፡፡በኬንያ ኦሎምፒክ ቡድን በ10ሺ እና በ5ሺ ሜትር ውድድሮች ደርበው እንዲሮጡ እድል ያገኙት ቪቪያን ቼሮይትና ሳሊ ኪፕዮጌ ናቸው፡፡ በ800 ሜትር  የተያዙት ፓሚላ ጄሊሞ እና ዴቪድ ሩድሻም ለኢትዮጵያ አዳዲስ የሜዳልያ ተስፋዎች ከባድ ተፎካካሪ እንደሚሆኑ ግምት የሚሰጣቸው ናቸው፡፡  የኬንያን ኦሎምፒክ ቡድን በዋና አሰልጣኝነት ለመምራት የተሾሙት ከ4 ዓመት በፊት በቤጂንግ ኦሎምፒክ የሰሩት ጁልየስ ኪሪዋ ናቸው፡፡ በኮርያ ዳጉ ተደርጎ በነበረው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ10ሺ እና በ5ሺ ሜትር ድርብ ድል ያስመዘገበችው ቪቪያን ቼሮይት ሰሞኑን ለኬንያው ዴይሊ ኔሽን በሰጠችው አስተያየት  በለንደን ኦሎምፒክ የጥሩነሽ ዲባባ መኖር ለከፍተኛ ውጤት ያነሳሳኛል እንጅ አልፈራትም ብላለች፡፡ ጥሩነሽ ዲባባ እና ቪቪያን ቼሮይት ከለንደን ኦሎምፒክ በፊት በተገናኙባቸው 17 ውድድሮች 15ቱን ያሸነፈችው ጥሩነሽ ነበረች፡፡እጅግ ከፍተኛ ልምድ ያለው ጥሩ የቡድን ስብስብ አለን፡፡ አገራችንን በለንደን ኦሎምፒክ ልናኮራት ተዘጋጅተናል ብለው የተናገሩት ዋና አሰልጣኙ ጁሊዬስ ኪሪዋ  በኦሎምፒክ በጠንካራ ዝግጅት እየሰሩ ያሉ ተቃናቃኞች ስላሉን  ምንም አይነት መዘናጋት የለንም ባለን ኃይል በለንደን የሜዳልያ ስብስባችን በማብዛት አዲስ ታሪክ ለመስራት ቁርጠኞች ነን ብለዋል፡፡የኬንያ ኦሎምፒክ ቡድን በዝግጅቱ የመጨረሻ ሁለት ሳምንታት የሚያደርገውን ልምምድ በእንግሊዝ በመሰረተው የብሪስቶል ካምፕ ለማከናወን ሰሞኑን 40 አትሌቶችን ወደ ስፍራው ልኳል፡፡የኬንያ መንግስትና በለንደን ኦሎምፒክ ድጋፍ በማድረግ እየሰሩ ያሉት ስፖንሰሮች ቡድናቸው ለሚኖረው ውጤታማነት የተለያዩ ዘመቻዎች በማድረግ ላይ እንደሆኑም ታውቋል፡፡ አንጋፋ እና የቀድሞ ውጤታማ አትሌቶች ለኦሎምፒክ ቡድኑ ዝግጅት ምክር በመስጠትና ልምዳቸውን በማጋራት የቻሉትን ድጋፍ እያደረጉም ናቸው፡፡ የኬንያ ኦሎምፒክ ቡድን ከታወቀ በኋላ ታዋቂው አትሌት ፖል ቴርጋት ለአገሩ ኦሎምፒያኖች ባስተላለፈው መልዕክት በለንደን ኦሎምፒክ የቡድን ስራን በታላቅ አርበኝነት መተግበር እንደሚገባ አሳስቧል፡፡ የኬንያ መንግስት በበኩሉ ሜዳልያ ለሚያገኙ አትሌቶች ለወርቅ 8918 ዶላር ለብር 5945 ዶላር እንዲሁም ለነሐስ 3567 ዶላር እንደሚሸልም ሲያስታውቅ የአገሪቱ የቴሌኮም ኩባንያ በበኩሉ ለወርቅ 11891 ዶላር ለብር 7134 ዶላር እና ለነሐስ 4756 ዶላር ለማበርከት ማቀዱን ይፋ አድርጓል፡፡ የኬንያው ፕሬዝዳንት ሞያኪ ኪባኪ በለንደን ኦሎምፒክ መክፈቻ ላይ በመገኘት የኦሎምፒክ ቡድናቸውን ለማበረታት ፍላጎት እንዳላቸው ያስታወቁ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራኢላ ኦዲንጋ በበኩላቸው በመዝጊያው ስነስርዓት ላይ በመታደም ድጋፌን እገልፃለሁ ብለዋል፡፡ ሁለቱም የኬንያ መንግስት መሪዎች  በለንደን ኦሎምፒክ አትሌቶቹ ባንዲራቸውን ከፍ በሚያደርግ ውጤታማነት ህዝባቸውን እንደሚያኮሩ ተስፋ አድርገዋል፡፡

 

 

Read 2884 times Last modified on Saturday, 07 July 2012 11:07