Saturday, 07 July 2012 10:59

ጊዮርጊስ ሊጉን 10 ጊዜ በላ፤ ከዚያስ?

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

ከሳምንት በፊት ቅዱስ ጊዮርጊስ የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ ማንሳቱን ያረጋገጠው ሁለት ጨዋታ እየቀረው ከተፎካካሪው ደደቢት በሰባት ነጥብ መራቅ በመቻሉ ነበር፡፡ በሊጉ ከቀሩት ጨዋታዎች አንዱን በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ያደረገው ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲዳማ ቡናን 4ለ3 በመርታት ሊጉን በ59 ነጥብ እየመራ ለዛሬው የፕሪሚዬር ሊጉ የመጨረሻ ቀን ደርሷል፡፡  የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ዛሬ የሚጠናቀቀው አዲስ አበባ ስታዲየም  ላይ ጊዮርጊስ ከመብራት  በሚያደርጉት የመጨረሻ ጨዋታ ሲሆን በውድድር ዘመኑ በተለያዩ የሽልማት ዘርፎች የተመረጡ ኮከቦችም ይታወቃሉ፡፡

የቅዱስ ጊዮርጊስ ሻምፒዮናነት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከተጀመረ ለ10ኛ ጊዜ ነው፡፡ከተመሰረተ 76 ዓመታትን ያስቆጠረው አንጋፋው የኢትዮጵያ ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአገር ውስጥ ውድድሮች የያዘው የውጤት ክብረወስን ከሌሎች የአገሪቱ ክለቦች በከፍተኛ ብልጫ ያስቀምጠዋል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ የዘንድሮ የፕሪሚዬር ሊግ ዋንጫ ድሉ 51ኛውን ዋንጫ ያገኘበት ሲሆን ከእነዚህ ዋንጫዎች መካከል 29 በሊግ ውድድር፤ 8 በጥሎ ማለፍ ሻምፒዮናዎች እንዲሁም 7 በሱፕርካፕ ድሎች የሰበሰባቸው ናቸው፡፡  በዘንድሮው ሻምፒዮን ቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ጣሊያናዊው ዳንኤሎ ሲሆኑ በተጨዋቾች ስብስቡ 3 ኡጋንዳዊያን፤ አንድ ሰርቢያዊ እና አንድ ጋናዊ ይገኛሉ፡፡

 

የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ የአገር ውስጥ ውድድሮች የበላይነት ግን በአህጉራዊ ውድድሮች ላይ ባለው ደካማ ተሳትፎ እንደሚደበዝዝ አስተያየት ሰጭዎች ይናገራሉ፡፡ በአፍሪካ ደረጃ በሚካሄዱ የክለብ ውድደሮች የ44 ዓመታት ተሳትፎ ያለው ክለቡ ተጠቃሽ ውጤት አለማስመዝገቡን ወደሚቀይርበት አዲስ ምእራፍ መሸጋገሩንም ብዙዎች ተስፋ ያደርጋሉ፡፡ ከ1997 እኤአ ጀምሮ በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ለ9 ጊዜ የተሳተፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ6ቱ እስከ ሁለተኛው ዙር የማጣርያ ምእራፍ በ3ቱ ደግሞ በቅድመ ማጣርያ ተሰናብቷል፡፡ የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ካፕ ላይ ደግሞ ከ1967 ጀምሮ ለ10 ጊዜ ተሳትፎ  አንድ ግዜ ብቻ ለግማሽ ፍፃሜ ሲደርስ 3 ግዜ በሁለተኛ ዙር፤ 3 ግዜ በአንደኛ ዙር እንዲሁም 2 ግዜ በቅድመ ማጣርያው በመሰናበት ደካማ ውጤት አስመዝግቧል፡፡  በአፍረካ ኮንፌደሬሽን ካፕ ላይ ደግሞ ዘንድሮ ለመጀመርያ ግዜ ተሳትፎ ከሁለተኛው ዙር ማጣርያ መሰናበቱም አይዘነጋም፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ከአፍሪካ የክለብ ውድድሮች ተሳትፎ ባሻገር በምስራቅ አፍሪካ የክለቦች ሻምፒዮና ካጋሜ ካፕ ላይም የረባ ውጤት የለውም፡፡

 

 

Read 1757 times Last modified on Saturday, 07 July 2012 11:05