Saturday, 18 April 2020 15:03

ኮሮና ቫይረስ እና የበዓል አመጋገብ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

    - ጥሬ ሥጋ መብላት በፍፁም አይመከርም
        - በዓሉ የምናደርጋቸውን ጥንቃቄዎች ሊያስረሳን አይገባም
       - ትኩስ ነገር ሲበዛ ለባክቴሪያም ሆነ ለቫይረስ ያጋልጣል

          ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተይይዞ አመጋገብን በተመለከተ የጤና ባለሙያዎች፤ ያልበሰሉ የእንስሳት ተዋጽኦዎችን መመገብ እንደማይመከር ይናገራሉ፡፡
ወተትም ሆነ የአትክልት ምግቦችን አብስሎ መብላት እንደሚገባ አስረግጠው ይናገራሉ፡፡ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ነገ በድምቀት የሚከበረው የፋሲካ በዓል ደግሞ 55 ቀናትን ምዕመኑ ከስጋና ከጠቅላላ የእንስሳት ተዋጽኦ ታቅቦ ቆይቶ ፆሙን የሚፈታበት ጊዜ ስለሆነ ጥሬ ስጋ፣ ክትፎና ሌሎች ያልበሰሉ ምግቦችን በጉጉት የሚጠብቅበት ጊዜ ነው፡፡ ነገር ግን የኮሮና ወረርሽኝ እየተስፋፋ ባለበት በዚህ ወቅት ኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ የሚፈቀዱና የማይፈቀዱ ምግቦች ምንድን ናቸው? ጥሬ ስጋ መብላት ይፈቅዳል? በአጠቃላይ ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ አመጋገባችን ምን መምሰል አለበት? የሚጠጡ
ነገሮችስ? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የድንገተኛ እና ፅኑ ህክምና ረዳት ፕሮፌሰርና በጤና ሚኒስቴር በኮቪድ - 19 የጤና ቴክኒክ አማካሪ ቡድን አስተባባሪ ከሆኑት ዶ/ር ወልደሰንበት ዋጋ ነው ጋር በአመጋገብ ዙሪያ ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጋ


             ከኮሮና ጋር አመጋገብ ዙሪያ የተለያዩ መረጃዎች ይወጣሉ፡፡ ፋሲካ ደግሞ ለክርስትና እምነት ተከታዮች በአብዛኛው በመብላትና በመጠጣት የሚከበር በዓል ነው፡፡ ሆኖም አሁን የምንገኝበት ወቅት ደግሞ በአመጋገብ ላይ ምን ዓይነት ጥንቃቄ መደረግ አለበት?
አሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው ወረርሽኝ ከሰው ወደ እንስሳት፣ ከእንስሳትም ወደ ሰው የሚተላለፍ በመሆኑ፣ በዚህ በዓል፣ ጥሬ ስጋ መመገብ ጨርሶ የሚመከር አይደለም:: የበሽታውን መነሻ ስንመለከት፣ ያልበሰሉ የእንስሳት ሥጋ መመገብ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ በሽታውም በዚያው ልክ ሊተላለፍ እንደሚችል እናውቃለን፡፡ ስለዚህ በፍፁም ጥሬ የሆኑ ነገሮች አይመከሩም፡፡ ጥሬ ስጋም በፍፁም ባይበላ እንመክራለን፡፡ ይሄ አስቸጋሪ ጊዜ እስኪያልፍ ከጥሬ ነገሮች ተቆጥበን፣ በሌላ ነገር ፆሙን ብንፈታ የተሻለ ነው፡፡ አብስሎና በደንብ ንጽህናውን ጠብቆ መመገብ ይመረጣል፡፡
በአሁኑ ወቅት ብዙ መስዋዕትነቶች ከፍለን ሀገርንም ህዝብንም ሆነ አካባቢውን ለመጠበቅ እየታገልን ነው፡፡ እንደ ማህበረሰብ አንድ ሰው ከቤትህ አትውጣ፣ ፊትህን ሸፍን፣ የስራህ ሁኔታ እቤት እንድትውል የማይፈቅድ ከሆነ ቶሎ ቶሎ ታጠብ፣ ሳኒታይዘር ተጠቀም… እየተባለ ያለው ለራስም ለአካባቢም ደህንነትና ጤንነት ነው፡፡ ይህንን እያደረግን በምንገኝበት ጊዜ ላይ ሆነን፣ በሌላ በኩል ጥሬ ስጋና ያልበሰሉ ምግቦች ነየምንበላ ከሆነ፣ ሌላው ጥንቃቄ ገደል ገባ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ጥሬ ስጋም ሆነ ያልበሰለ ነገር ፈጽሞ የሚመከር አይደለም፡፡ እርድን በተመለከተም እርዱን የሚፈጽሙ ግለሰቦች፣ ራሳቸውንም እንስሳቱንም የሚጠብቁበት ዝግጅት መደረግ አለበት፡፡ ከአለባበስ ጀምሮ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል፡፡ ምክንያቱም ቅድም እንዳልኩት፤ ሰውየው ለሚታረደው ከብት ቫይረሱን ሊያስተላልፍ ይችላል:: ከዚያም ከበሬው ስጋ ወደ ሌሎች ሰዎች ቫይረሱ ሊተላለፍ ይችላል፡፡ በሌላ በኩል፤ የሚታረደው በሬ ወደ አራጁም ሊያስተላልፍ ይችላል፡፡ በሁለቱም በኩል ችግሩ እንዳይከሰት ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ አለበት፡፡ እርዱ ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ቄራዎች ድርጅት፣ ከጤና ሚኒስቴርም ከጤና ባለሙያዎች ምክር ተቀብሎ፣ በተመከረው ልክ ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ግድ ይላል፣
ከዚህ ውጭ ግን በቀድሞ ልማዳችን በየመንገዱ በቅርጫ መልክ የምናርደው አሰራር አደጋን ሊያስከትል ስለሚችል በየአካባቢው እርድ ባይፈፀም ይመከራል፡፡ ምክንያቱም በየአካባቢው እርድ በሚፈፀምበት ጊዜ፣ ሰው ጥሬ ስጋ እንኳን ባይበላ በእጁ፣ በቢላዋና በመሰል ነገሮች ስጋውን ነክቶ፣ አፉን አፍንጫውን ወይም አይኑን እጁን ሳይታጠብ የነካ እንደሆነ፣ ለሌሎች ሰዎች በሚያቀብልበት ጊዜ ከሰው ወደ እንስሳው ከእንስሳው፣ ስጋ ወደ ሰው ቫይረሱ የመተላለፍ እድሉ የሰፋ ነው፡፡ ስለሆነም በየሰፈሩ እርድና ቅርጫ ባይደረግ ነው የሚመከረው፡፡ ቄራዎች ድርጅት ደረጃውን ጠብቆ ያረደውን ስጋ ገዝቶ አብስሎ መመገቡ የተሻለ ይሆናል፡፡
ሌላው መረሳት የሌለበት ከበዓሉ ጋር ተያይዞ ሰብሰብ ብሎ በዓሉን ማሳለፍ አይመከርም:: ከበዓል ውጭ የምናደርጋቸው ሁሉም አይነት ጥንቃቄዎች፣ በበዓሉ ምክንያት ፈጽሞ ሊዘነጉም አይገባም፡፡ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፣ እጅን በሳሙና ቶሎ ቶሎ መታጠብ፣ ካልሆነም ሳኒታይዘር መጠቀም፣ ሰው ስብስብ ያለበት አካባቢ የግድ መገኘት ካለብን፣ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ መጠቀምም የግድ አስፈላጊ ነው፡፡ በዓሉ ይሄን ሁሉ ጥንቃቄ ሊያስረሳን አይገባም ማለቴ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ሰው ከቤቱ ሳይወጣ፣ ፀሎት እያደረገና ‹‹ይህንን ወረርሽኝ ከእኛ አርቅልን›› እያለ በቤቱ ቢያከብር ይበልጥ መልካም ነው፡፡
ይህንን ጊዜ በትዕግስትና ከቀድሞው ልማዳችን ርቀን ብናከብር፣ ለሌላው በዓል በሰላም እንደርሳለን፡፡ ያኔ ሁሉንም እንደርስበታለን፤ ምክንያቱም ወረርሽኙ ወቅታዊ ነው፡፡ ከታገስንና ከተጠነቀቅን እድሜውን እናሳጥረዋለን፡፡ የወረርሽኙን እድሜ የማሳጠርም የማስረዘምም ምርጫ ያለው በእጃችን ነው፡፡
ቅባት የበዛባቸው ምግቦችን መመገብ በማንኛውም ጊዜ ለጤና እክል እንደሚዳርግ ይታወቃል፡፡ ከኮሮና ጋር በተያያዘ ቅባት የበዛበት ምግብ መመገብ ችግር ያስከትላል? የአልኮል መጠጥስ? መጠጣትስ
ቅባትን በተመለከተ ቀድሞ ከሚመከረው የተለየ ጉዳት ይደርሳል የሚል ነገር አልተገለፀም:: ነገር ግን ቅባታማ ምግቦች በብዛት መመገብ ቶሎ የመፈጨት ችግር ስላለባቸውና ቢፈጩና ቢሰራጩም ከመጠን በላይ ከሆኑ፣ ያው የጤና ጉዳት ማድረሳቸው ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህ ቅባት የበዛባቸው ምግቦች ፈጽሞ የሚመከሩ አይደሉም፡፡ ከወቅቱ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ‹‹ይህንን ምግብ ብሉ፤ ይሄኛውን አትብሉ›› የሚል የንጥረ ነገር ልዩነት የለም፡፡ ቅባታማ ምግቦች የሚያደርሱት ጉዳት የቀድሞው አይነት እንጂ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የተለየ ጉዳት አያደርሱም፡፡ ጠቅለል ስናደርገው በየትኛውም ምግብ ላይ ከመጠን ያለፈ ቅባት ጨምሮ መመገብ አጠቃላይ የጤና ጉዳት ስላለው ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው እላለሁ፡፡
መጠጥን በተመለከተ በአሁኑ ወቅት ከኮሮና ቫይረስ ጋር የሚያገናኘው ምንድን ነው ከተባለ፤ አንደኛ አንድ ሰው መጠጥ አብዝቶ በሚጠጣበት ጊዜ መደበኛ የአስተሳሰብ ደረጃውን ሊቀይር ስለሚችል የጥንቃቄ ሁኔታውን ይለውጠዋል:: ቶሎ ቶሎ መታጠብ ካለበት፣ አካላዊ ርቀቱን ከመጠበቅ አኳያና ሌሎችንም ጥንቃቄዎች ሊዘነጋ ይችላል፡፡ ስለዚህ ተገቢ አይደለም፡፡ አንድ ሰው ምን ያህል ጠጥቶ ከመደበኛ አስተሳሰቡ ይለወጣል ወይም ይሰክራል ይህ የሚለው እንደሚጠጣው የአልኮል አይነትና መጠን፣ እንደ ሰውየው አልኮልን በተፈጥሮ የመቋቋም አቅምና ሌሎች ሁኔታዎች ይወሰናል፡፡ የሆነ ሆኖ፣ ይሄ ጊዜ እስኪያልፍ መጠጥ ባንጠጣና ቢያልፈን ነው የሚሻለው፡፡ በተደጋጋሚ እንዳልኩት፤ ቫይረሱን በብቃት ስንከላከልና እድሜውን ስናሳጥር፣ ወደ ቀድሞ ነፃነታችን እንመለሳለን፡፡ ስለዚህ አትስከሩ ብቻ ሳይሆን መጠጥ ባንጠጣ ይመከራል የሚል መልዕክት ነው ያለኝ፡፡ ለምን ከተባለ፤ ማን በምን ያህል መጠን እንደሚሰክር አይታወቅምና፣ ግዴለም መጠጥንም ከሌሎችም ከምናደርጋቸው ጥንቃቄዎች እንደ አንዱ ወስደን ለዚህ በዓል እንተወው እላለሁ፡፡
በበዓል ጊዜ ብዙ ሰው ቤቱ በግ ያርዳል፤ ነገር ግን ራሱ የማረድ ልምድ ስለሌለው ሌላ ሰው ጠርቶ ነው የሚያሳድረው፡፡ በዚህ ጊዜ ያ በግ ለማረድ የሚመጣው ወይም በግ የሚያሳርደው ግለሰብ ምን አይነት ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል?
አሁንም ቢሆን ባለንበት ወቅት አስቸጋሪነት የተነሳ፣ ቤት ውስጥና በአንድ አካባቢ ለቅርጫ እርድ መፈፀም ትልቅ አደጋ ሊፈጥር ይችላል:: በነገራችን ላይ እንኳን አሁን አደገኛ ወረርሽኝ ተከስቶ አይደለም፤ በመደበኛውም ጊዜ እንዲህ አይነት በቤት ውስጥና በመንደር የሚከናወኑ እርዶች ጤናውንና ንጽህናውን የጠበቀ የስጋ ምርት ለማግኘት አስቸጋሪ ነው:: አሁን ደግሞ አስቸጋሪ ጊዜ ላይ ስላለን፣ ያ ሊያርድ የሚመጣው ሰው ጤንነቱ የተረጋገጠ ነው ወይ? ያ ሰው በቫይረሱ የተያዘ ከሆነ፣ በግ ሲያርድ ስጋውን ይነካል፤ የሚያሳርደውም ያንን ተቀብሎ ይነካል፤ የሚያበስለውም ሰው መጀመሪያ ጥሬውን ይነካዋል፡፡ ቫይረሱ ረጅም ጊዜ ስለሚቆይ በቀጥታ በነካው ሰው ሁሉ ላይ ይዛመታል፤ ስለዚህ እርዶች ሁሉ ቄራ ላይ ቢፈፀሙ ይመረጣል፡፡
ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል እየተባለ ሻይ በነጭ ሽንኩርትና ዝንጅብል በብዛት መጠጣት እየተለመደ የመጣ ይመስላል፡፡
በተለምዶ እንደ ምግብ የምንጠቀማቸው ነገሮች፣ ትኩስ ነገርም ይሁን ሻይ ወይም ነገሮች የከፋ ጉዳት የላቸውም፡፡ በዚያው ልክ ጥቅምም የለውም፡፡ ለዚህ ቫይረስ የተረጋገጠና ይጠቅማል የተባለ ይሄ ነው የምንለው የአመጋገብ ሥርዓት እስካሁን የለም፡፡ እርግጥ በየትኛውም ጊዜ እንሚመከረው፤ የተመጣጠነ፣ ለጤና ተስማሚ የሆነ፣ ምግብ መመገብ አስፈላጊ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ እንደሚታወቀው፤ እኛም ለሳይንሱ ገና አዲስ እንደመሆናችን እየተጠና ነው፡፡ ስለዚህ በጥናት ተረጋግጦ ይፋ እስኪሆንና እስኪነገር ድረስ እንደ ሻይና መሰል ትኩስ ነገሮችን አብዝቶ ከልክ በላይ መውሰድ የሚጠቅም ነገር አይደለም፡፡ ለኮሮና ይጠቅማል ተብሎ የተለየ ንጥረ ነገርም የለም፡፡ አጉል በሚናፈስና እውነትነት በሌለው ወሬ፣ ያልተገቡ ነገሮችን አብዝቶ መውሰድ፣ ገበያም ላይ ማስወደድ ተገቢ አይደለም፡፡ ጉዳትም አለው፡፡ ለምሳሌ ነጭ ሽንኩርት መድሃኒትነት አለው ተብሎ፣ ብዙ ሰዎች አብዝተው እየወሰዱ ነበር፡፡ አንድ እናት ነጭ ሽንኩርት አብዝታ በመውሰዷ (ጉሮሮዋ እስኪቆስል ድረስ ማለት ነው) በጉሮሮ ህመም ሆስፒታል ጽኑ ህመምተኛ ክፍል እንደገባች መረጃው አለኝ፡፡ ስለዚህ ከልክ በላይ የሚወሰዱ ሁሉም ነገሮች ምግብም ቢሆን፣ ጉዳት አለው:: ሻይ ለምሳሌ ሁሌ እንደምንጠጣው አንድ ስኒ መውሰድ ችግር የለውም፤ ነገር ግን መድሃኒት ነው በሚል ቀኑን ሙሉ አብዝተን ስንጠጣ ከዋልን ጉዳት ይኖረዋል፡፡ ለጉሮሮ፣ ለጨጓራና ለሌሎች ህመሞችም ይዳርጋል፡፡ ትኩስ ነገር ሲበዛ ቁስለት ስለሚያስከትል፣ ለባክቴሪያም ለሌሎች ቫይረሶችም ያጋልጣል፡፡ ስለዚህ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
በእኛ ሀገር ባህልና የአኗኗር ዘይቤ ምክንያት በተለይ በበዓላት ወቅት ሰዎች አንድ ማዕድ ላይ ቀርበው እየተጐራረሱ መብላት የተለመደ ነው፡፡ ይህስ መቅረት አለበት ይላሉ?
አሁን በስፋት እንደሚገለፀው በወረርሽኙ ምክንያት ሰዎች በመካከላቸው በአንድ ሜትር ቢቻል ቢቻል ሁለት ሜትር መራራቅ አለባቸው:: አሁን ደግሞ ሰዎች ምልክቱ ሳይታይባቸው ቫይረሱን ማስተላለፍ መጀመራቸው በሳይንስ ተረጋግጧል፡፡ አንድ ሰው አፉን በነካበት ፈሳሽ ወይም ምራቅ በነካበት እጁ ሌላ ሰው አጐረሰ ማለት ቀጥታ ንክኪ ስላለው ምልክቱ ባይታይበትም ላጐረሰው ሰው ቫይረሱን ያስተላልፋል፡፡ ስለዚህ መጐራረስ በአሁኑ ወቅት ፈጽሞ የማይመከር ነው፡፡ ቢያንስ አንድ ሜትር መራራቅ ሲባል፣ ያለ ምንም ንክኪ የሚለውን ጨምሮ ነው፡፡ በአንድ ማዕድ ላይ መጋራት ራሱ፣ የሰዎቹ ርቀት ከአንድ ሜትር በታች ነው ማለት ነው፡፡ ይሄ አደገኛ ስለሆነ አንድ ላይ ባይመገቡ ባይጐራረሱ ጥሩ ነው፡፡
የምንቸገረው ለትንሽ ጊዜ፣ ለትንሽ ወቅት ነው ተባብረን ይህን ችግር እስክንሸኘው ድረስ ነባር ባህሎቻችንን ለጊዜው ወደ ጐን ትተን፣ ጤና ሚኒስቴር፣ የጤና ባለሙያና መንግስት የሚያወጧቸውን መመሪያዎች በመተግበር ርብርብ እናድርግ፡፡
አሁን ላይ ወረርሽኙን በተመለከተ ሰው ጤና ሚኒስቴር የሚያወጣቸውን መመሪያዎች በአግባቡ እየተገበረ ነው ይላሉ?
በአሁኑ ወቅት ማህበረሰቡ ላይ ጥሩ አይነት ሁኔታዎችን እያየን ነው ምክራችንን ሰምተው በመተግበር በኩል እያየን ያለነው ነገር አበረታች ነው፤ የበለጠ ትጋት ይጠይቃል፡፡ መልካም በዓል እመኛለሁ፡፡ አካላዊ እርቀታችንን እንጠብቅ፣ እንታጠብ፣ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሁሉ ያለመዘናጋት እንተግብር፡፡ ቫይረሱን በአጭር እንቀጨዋለን እላለሁ አመሰግናለሁ፡፡  

Read 1757 times