Saturday, 18 April 2020 14:45

በኮቪድ-19 ሳቢያ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

      - በዓለም የስፖርት ኢንዱስትሪ የሚንቀሳቀሰው መዋዕለ ንዋይ በ200 ቢሊዮን ዶላር ይቀንሳል፡፡
         - ከ75 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም ስፖርት ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ መግባቱ ነው፡፡
         - የአውሮፓ ታላላቅ ሊጐች በአጭር ጊዜ ውስጥ በዝግ ስታዲዬም የውድድር ዘመናቸውን መቀጠል አለባቸው
         - ከፍተኛ ገቢ ካላቸው 12 የአውሮፓ ክለቦች 10 ተጨዋቾች ደሞዝ ይቀንሳሉ
         - እግር ኳስን ከኪሣራ ለመታደግ በፊፋ 2.7 ቢሊዮን ዶላር ተመድቧል
         - የተጨዋቾች የዝውውር ሂሳብ በ28% ይወርዳል


               የዓለም ስፖርት ኢንዱስትሪ በዓመት ከ756 ቢሊዮን ዶላር መዋዕለ ንዋይ የሚንቀሳቀስበት ሲሆን፤ በኮቪድ -19 ሳቢያ ገበያው በ200 ቢሊዮን ዶላር ሊቀንስ ይችላል፡፡ በመላው ዓለም በ200 አገራት የተዛመተው የኮቪድ -19 ወረርሽኝ ለኢንዱስትሪው ገበያ መቀዛቀዙ ምክንያት የሚሆነው፤ በስፖንሰርሺፕ፤ በማስታወቂያ ንግድ፣ በኢንቨስትመንት የዓለም ስፖርቶች የሚደግፉ ትልልቅ ዓለምአቀፍ ኩባንያዎች በኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ በመግባታቸው ነው:: በዓለም የስፖርት ኢንዱስትሪ ከሚንቀሳቀሰው መዋዕለ ንዋይ አሜሪካ 420 ቢሊዮን ዶላር፣ አውሮፓ፤ 250 ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም ቻይና 150 ቢሊዮን ዶላር ድርሻ አላቸው፡፡ እነዚህ የዓለማችን ክፍሎች ወረርሽኙ ክፉኛ በማጥቃቱ በሚቀጥሉት 5 ዓመታት የዓለም የስፖርት ኢንዱስትሪ ከሚያገኘው ገቢ ግማሹን ሊያጣ ይችላል፡፡ በመላው ዓለም ከ2 ቢሊዮን በላይ ስፖርት ተመልካቾች የሚከታተሏቸው የተለያዩ የስፖርት ውድድሮች በመዘጋታቸው የዕድገት ሂደታቸው፣ የውድድር ደረጃቸውና ከስፖርት አፍቃሪው የሚያገኙት ትኩረት ይቀንስባቸዋል:: በትልልቅ የስፖርት ስታዲዬሞች እና ሌሎች መሠረተ ልማቶች የሚካሄዱ ውድድሮች በሚቀጥሉት 2 ወራት ተጠቃልለው ካልተጀመሩ በየደረጃው የነበራቸውን ድምቀት ለመመለስ እንደሚከብድ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ በመላው ዓለም የስፖርት ውድድሮች በሚካሄድባቸው ቦታዎች፣ በሁሉም የሚዲያና አውታሮች የሚያገኙት ሽፋን በመቀነሱና ትኩረቱን በማጣቱ ዓለምአቀፍ የሚዲያ እና የማስታወቂያ ተቋማት ከፍተኛ ገቢ አጥተዋል፡፡
የዓለም የስፖርት ኢንዱስትሪ በእንዲህ አይነቱ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ሲገባ ከ75 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን ከቶኪዮ 2020 ኦሎምፒክ ባሻገር የአውሮፓ ዋንጫ የደቡብ አሜሪካው ኮፓ አሜሪካ በ1 ዓመት መራዘማቸው ያልተጠበቀ ነበር፡፡ የኮቪድ -19 ወረርሽኝ የስፖርት ኢንዱስትሪውን የተለያዩ የገቢ ምንጮችን  ከማድረጉም በላይ የስፖርት ውድድሮችና የግጥሚያ መርሐ ግብሮች ያለፈውን 1 ወር መዘጋታቸው አስተካክሎ መርሐ ግብራቸውን መልሶ ለመቀጠል ቀላል አይሆንም፡፡ በስፖርት ኢንዱስትሪው ያለውን የፋይናንስ መቃወስ በውድድሮች መቋረጥና አለመጨረስ ይመሳሰላል፡፡
የኢንተርኔት ቀጥታ ስርጭት (Live streaming) YouTube, Netflix- ሌሎችም ድረገፆችና ማህበራዊ ሚዲያዎች በወረርሽኙ ሳቢያ ተከታታዮቻቸው እየጨመሩ ቢሆንም አዳዲስና በቀጥታ ስርጭት የሚተላለፉ የስፖርት ውድድሮች ባለመኖራቸው አማራጭነታቸው ጐልቶ ሊወጣ አልቻለም፡፡
በዓለም የስፖርት ኢንዱስትሪ ላይ ዓለምአቀፍ ኩባንያዎች በአትሌቶች፣ በቡድኖች እና በውድድሮች ላይ  ከ55 ቢሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስት በማድረጋቸው ከቀውስ ማግስት ይህን ኪሣራ ለማካካስ የሚከብድ ነው፡፡
ላለፉት 5 ሳምንታት በአውሮፓ 5 ታላላቅ ሊጐች ውድድሮች ተቋርጠዋል፡፡ ትልልቆቹ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ፣ የአውሮፓ ማህበረሰብ ዋንጫ መርሐግብሮችም እንደተስተጓጐለ ናቸው፡፡ ሰሞኑን የሚወጡ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት የአውሮፓ ታላላቅ ሊጐች ከወር ላለፈ ጊዜ መቋረጣቸው በአስቸኳይ እልባት ያስፈልገዋል፡፡ ትልልቆቹ የአውሮፓ ሊጐች የውድድር ዘመኑን ካቆመበት ለመቀጠል በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት መጠነ ሰፊ ተግባራት ማከናወን አለባቸው፡፡
የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ክለቦች ውድድራቸውን ለመቀጠል ትናንት የተሰበሰቡ ሲሆን የ9 ሳምንታት ጨዋታዎች እንደሚቀራቸው ይታወቃል፡፡ የጀርመን ቦንደስ ሊጋ ክለቦች ወደ ልምምድ መርሐ ግብራቸው ባሳለፍነው ሳምንት በመመለስ በአውሮፓ የመጀመሪያዎቹ ሲሆኑ፤ ልምምዳቸውንም አምስት አምስት ሆነው በመቧደን እየሠሩ መሆናቸውን ከየአቅጣጫው ትችት እየገጠመው ነበር፡፡ በስፔን ላሊጋ ክለቦች በሚቀጥሉት 2 ወራት ውድድር እንደሚጀመር  ተስፋ ያደረጉ ቢሆንም የሊጉ አስተዳደር በወረርሽኙ ስፔን ክፉኛ በመጐዳቷ የውድድር ዘመን ለመሰረዝ በሚገደዱበት ስጋት ውስጥ ገብቷል፡፡ የፈረንሳይ ሊግ 1 ደግሞ በጁን 1 ላይ መልሶ ለመጀመር እቅድ መያዙ ቢገለጽም፣ ሌኢክዊፔ የተባለ የአገሪቱ ጋዜጣ እስከ ነሐሴ ወር አጋማሽ ውድድር ሊጀመር እንደሚችል አውስቷል፡፡ በጣሊያን ሴሪኤ የሚወዳደሩ ክለቦች የተጨዋቾችን ምርመራ ከአንድ ወር በኋላ ለማካሄድ ያቀዱ ሲሆን 12 ዙር ጨዋታዎች የቀሩበትን የውድድር ዘመን መልሶ ለመቀጠል የጣልያን መንግስት ይሁንታ ይጠበቃል ተብሏል፡፡
ክሪስቶር ቺክሃርዳት የተባለ እውቅ ጀርመናዊ የስፖርት ጠበቃ እንደሚናገሩት የአውሮፓ እግር ኳስ በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ የሚጋፈጣቸው ችግሮች ብዙ ለውጦች ይፈጠሩበታል፡፡ የተጨዋቾች ዝውውር ክፍያና ደሞዝ መቀነሱ አይቀርም የኩባንያዎች ኢንቨስትመንትም ይናጋል፡፡ ስለዚህም ክለቦች የኢኮኖሚ ስትራተጃቸውን እንዲከልሱ ያስገድዳቸዋል፡፡ በተጨዋቾች ደሞዝ ከፍተኛ ወጭ የሚያወጡት የጣሊያን ሴሪኤ፣ የስፓኒሽ ላሊጋ እና የፈረንሳይ ሊግ 1 በገቢያቸው መቀነስ ህልውናውን የማፈንና ከባድ የፋይናንስ ቀውስ ያጋጥማቸዋል፡፡ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ የጀርመን ቦንደስ ሊጋ ከዚህ አንፃር ቀውስን ሊቋቋሙ ይችላሉ ነው የተባለው፡፡   
በስፖርት ኢንዱስትሪው ላይ ከሚያጋጥሙ ለውጦች መካከል የሚዲያና ብሮድካስት ስርጭት መብቶች መከለሳቸው ተገቢ ነው፣ ከማስታወቂያና ከስፖንሰርሺፕ ጋር የተያያዙ የውል ስምምነቶች መሠረዛቸውና በድርድር መቀነሳቸውም ይጠበቃል፡፡ የስፖንሰርሺፕ ወጭዎች በግማሽ ይቀንሳሉ፡፡ የስፖርተኞች ደሞዝ እና ሌሎች ጥቅሞችም ይወርዳሉ፡፡ በአምስቱ የአውሮፓ ታላላቅ ሊጐች በየዓመቱ እስከ 9.8 ቢሊዮን ዶላር ለተጨዋቾች ደሞዝ የሚከፈል ሲሆን፤ ይህም ክለቦች ከሚያገኙት ገቢ 62% ድርሻ ነበር፡፡ ፋይናንሽያል ታይምስ እንደዘገበው የአውሮፓ እግር ኳስ ከፍተኛ ገቢ ከሚያገኙ 12 ክለቦች መካከል 10 የሚሆኑት የተጨዋቾችን ደሞዝ ለመቀነስ በድርድር ላይ ናቸው፡፡ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ አስተዳደርና ክለቦች በበኩላቸው በገጠመው ቀውስ ተጨዋቾች የራሳቸውን ውሳኔ በማድረግ ለደሞዝ ቅነሳ ድርድር እንዲዘጋጁ ይጠይቃል፡፡ በኮቪድ -19 ሳቢያ የአውሮፓ 5 ታላላቅ ሊጐች የተጨዋቾች የዝውውር ዋጋ ከ36,12 ቢሊዮን ዶላር ወደ 25.9 ቢሊዮን ዶላር መውረዱን ሪፖርት ያደረገው፡፡ CIES የተባለ የእግር ኳስ ጥናት አድራጊ ተቋም፤ ለአውሮፓ 5 ታላላቅ ሊጐች የተጨዋቾች የዝውውር ሂሳብ 28% ይወርዳል ብሏል፡፡ KPMG የተባለው የስፖርት ኢኮኖሚክስ አማካሪ ተቋም ደግሞ የአውሮፓ አምስት ታላላቅ ሊጐች ከብሮድካስቲንግ፣ ከቲኬት ሽያጭና ስፖንሰርሺፕ ገቢያቸው ከ44 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚከስሩ አመልክቷል:: ዓለምአቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ ካለው ተቀማጭ ገንዘብ በእግር ኳስ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለማገዝ ያቀደ ሲሆን 2.7 ቢሊዮን ዶላር ወጭ በማድረግ የአደጋ ጊዜ ፈንድ ለክለቦች ለአባል ፌዴሬሽኖችና ለስፖርቱ አስተዳደሮች ለመለገስ ወስኗል፡፡
በተለያዩ ዓለማችን አገራት በከፍተኛ የኢኮኖሚ አስተዋጽኦ የሚታወቁ የስፖርት ቡድኖችን ለመታደግም መንግስታት አስተዋጽኦ ሊኖራቸው ይችላል፡፡
ከእግር ኳስ ባሻገር በኮቪድ - 19 ሳቢያ ቀውስ የገጠመው አትሌቲክስና አትሌቶቹ ናቸው፡፡ በተለይ በዓለም አትሌቲክስ ከፍተኛ የሽልማት ገንዘብ የሚገኝባቸው ትልልቅ የማራቶን ውድድሮች መሠረዛቸው በአዘጋጆችም እንዲሁም አትሌቶችም ላይ ኪሣራ አስከትለዋል፡፡ የለንደን፣ ቶኪዮ፣ የቦስተን ማራቶኖች ከተሰረዙ ውድድሮች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በዓለም ትልልቅ የትራክ፣ የጐዳና ላይ እና የአገር አቋራጭ አትሌቲክስ ውድድሮች በአንድ የውድድር ዘመን እስከ 25 ሚሊዮን ዶላር የሽልማት ገንዘብ ይቀርባል፣ በማራቶን፣ የጐዳና ላይ ሩጫዎች ከ21.8 ሚሊዮን ዶላር በላይ፣ በትራክ ውድድሮች ከ1.3 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንዲሁም በአገር አቋራጭ ውድድሮች እስከ 710ሺ ዶላር ላይ ነው፡፡


Read 1309 times