Print this page
Sunday, 12 April 2020 19:24

“ወፍ እንደ አገሯ ትጮኻለች!”

Written by  በተስፋዬ ድረሴ - አዲስ አበባ
Rate this item
(3 votes)

 ሳይንስና ሀይማኖት ርቀታቸውን ጠብቀው ኮሮናን እየተዋጉ ነው!
                  
                  ቻይና፣ ኮቪድ 19/ኮሮናን ለመዋጋት ሀይማኖታዊ መፍትሔ አልፈለገችም:: የበሽታውን መተላለፊያ መንገዶች እንዳወቀች፣ ወይም ብዙም ሳትቆይ፣ ነው ተገቢ ያለቻቸውን “ሰዋዊ” የመከላከያ እርምጃዎች ነው መውሰድ የጀመረችው፡፡ ህዝቡ የተሰጠውን ትምህርት ተቀብሎም  ይሁን፣ የመንግሥትን ኮምኒስታዊ ዱላ ፈርቶ - እዚህ ጋ “የትም ፍጪው፣ ዱቄቱን አምጪው”ን ያስታውሷል - በአካል መነካካቱን እርግፍ አድርጎ ተወው፡፡ ከቤቱ ተከተተ፡፡ እናም፣ አገሪቱ ችግሩን በአጭር ጊዜ ውስጥ በቁጥጥር ስር ለማዋል ቻለች:: በዚህ አያያዝዋ፣ ወረርሽኙ ቢያገረሽም መቆጣጠርዋ አይቀርም - አቅሟን አስመስክራለች፡፡ ብራቮ ቻይና!
የቻይና ኮሮናን የመከላከል ስኬት ለተቀረው ዓለም ጥሩ ማስተማሪያ ሆነ:: ብልህ ሰው ከሌሎች ተሞክሮ ይማራል እንዲሉ፣ ብዙዎቹ በትምህርት የገፉ አገሮች፤ ከመካከላቸው የመከላከል እርምጃውን ጥቂት ዘግይተው የጀመሩ ቢኖሩም፤ ዘዴዋን ኮርጀው የበሽታውን ስርጭት እድገት መግታት ቻሉ፡፡ ሞታቸውን መቀነስ ተሳካላቸው፡፡
ወደ አገራችን ስንመጣ፣ አብዛኛው ህዝቧ ሀይማኖተኛ መሆኑ የሚነገርላት ኢትዮጵያ በኮሮና መጠቃት ስትጀምር፣ ህዝቦቿ ከቫይረሱ ጋር የሚያደርጉትን ጦርነት እንደ ቻይና “መሬት ለመሬት” የሚያስኬዱት አልሆኑም፡፡ በሽታው በቫይረስ የሚተላለፍ መሆኑንና መራራቅ፣ አለመነካካት ስርጭቱን እንደሚገታ ቢቀበሉም፣ እንደ ሀይማኖተኛነታቸው፣ ችግሩ ሊከሰት የቻለው በፈጣሪ (እግዚአብሔር/አላህ) ቁጣ ምክንያት ነው ብለው ስላመኑ ከሰማይ ተጨማሪ ሀይል መጠየቅ ጀመሩ:: ለየአምላካቸው የሚያስተላልፉትን የምህረት ልመና፤ ፀሎት/ዱዓ ከመከላከሉ ጎን አፋፍመው ቀጠሉ፡፡ የዚህ አይነት፣ ሀይማኖታዊ ምላሽ እና የሀይማኖት ተቋማት ህብረት፣ በዓለም ላይ፣ በየትኛውም ዘመንና በየትኛውም አገር ወዘተ ታይቶም ተሰምቶም የሚያውቅ አይመስልም፡፡ ሆነ፡፡
ወረርሽኙ የተለያየ እምነት ያላቸውን ሰዎችና ተቋማት ለአንድ አላማ ያሰለፈውን ያህል “ሳይንስ” እና ሀይማኖትም “ርቀታቸውን ጠብቀው” ለአንድ አላማ እንዲሰሩ ምክንያት ሆኖ ቀጠለ፡፡ የአንዱ መጉላት የሌላውን መክሰም ቅድመ ሁኔታ ሳያደርግ ሥራዎች እስከተሰሩ ድረስ፤ ማለት፣ ሀይማኖቶች “ሰዋዊ” የመከላከል እርምጃዎችን እስካላስተጓጎሉ ድረስ፣ የጤና ተቋማት የሀይማኖት ተቋማትንና ሀይማኖተኞችን፣ “የእናንተ ተሳትፎ አያስፈልገንም፣ ቫይረሱን እንደ ቻይና ብቻችንን እንፋለመዋለን፣” እስካላሉ ድረስ፤ በንድፈ-ሀሳብ ደረጃ የሚታይ ችግር አይኖርም፡፡
አገራችን፣ ከቻይና የወሰደቻቸውን፤ ተሞክረው ውጤታቸው የተረጋጋጠ፤ “ሰዋዊ” የመከላከል እርምጃዎች እየተገበረች፣ እንደ እምነቷ ፀሎት/ዱዓ መጨመሯ ከቫይረሱ ጋር እየተካሄደ የሚገኘውን ጦርነት በአዝማችነት ከፊት ተሰልፈው በማፋፋም ላይ የሚገኙትን፣ ከብዙዎች መካከል፣ የመንግሥትና የጤና ባለሙያዎች እንቅስቃሴ አያውክም፡፡
ችግር ሊኖር ይችል የነበረው፣ የሀይማኖት ተቋማት (ሀይማኖተኛ የሆኑ ዜጎች) “ቫይረሱ የፈጣሪ ቁጣ ውጤት ነው” የማለታቸውን ያህል መፍትሔ የምንፈልገው ከእግዚአህሔር ወይም ከአላህ ብቻ ነው፤ ለዚህም ከፀሎት ወይም ዱዓ በስተቀር “ሰዋዊ” የመከላከያ እርምጃዎችን አንሞክርም (አንራራቅም፣ እንተቃቀፋለን፣ ወዘተ) ቢሉ ነበር፡፡ ወይም ደግሞ፣ መንግሥትና የህክምና ባለሙያዎች (የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር)፤ ለሀይማኖታዊ ምላሾች መድረክ የለኝም፤ ይህ “ሀይማኖታዊ ያልሆነ” መንግሥት (Secular state) ነውና ሀይማኖቶች ከኔ ራቁ ብሎ ቢሆን ነበር፤ ችግሩ፡፡ ለነገሩ፣ ለማስመርም ጊዜ አለው!
አንጋፋው ገጣሚ ነቢይ መኮንን “ ... እንግዲህ ምን ትሆን? ይቺ ናት አገርህ!” እንዳለው፤ ሰዋዊ (ሳይንሳዊ) እና ሀይማኖታዊ ምላሾች ርቀታቸውን ጠብቀው እየተጋገዙ መፍትሔ ለማምጣት እስከተጉ ድረስ “እንዴት ሊሆን ቻለ?”ን የመሰሉ ጥያቄዎች ጊዜያቸው አሁን አይመስልም፡፡ በቃ ሆኗል::
አሁን መጠየቅ ያለበት፤ በእምነት ረገድ አብዛኛውን የአገሪቱን ዜጎች በማገልገል ላይ የሚገኙት የሀይማኖት ተቋማት ተከታዮቻቸው ላይ ያላቸውን ሥልጣን በመጠቀም የመከላከያ እርምጃዎችን ተፈፃሚነት እንዴት ያረጋግጡ? ነው፡፡ እንደየ እምነታቸው ስለ ቫይረሱ አመጣጥና አጠፋፍ (ተስፋ) ማስተማራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ሰዋዊ የመከላከያ እርምጃዎችንም ለመውሰድ ከቻሉ፤ ጥሩ ውጤት ሊገኝ ይችላል - አገር በቀል ስልቱ “ኢትዮጵኛ ስልት” ተብሎ ሊታወቅም ይችል ይሆናል - በዓለም፡፡ ቀና ቀናውን ቀና ብለን እንይ!
ከላይ ያነሳኋቸው ነጥቦች እንዳሉ ሆነው፣ እንደ ማሳሰቢያ የሚከተሉትን ሀሳቦች እጨምራለሁ፡፡ ሀይማኖታዊ ትንተናዎችን ለሀይማኖት መሪዎችና የሙሉቀን “ሥራቸው” ሀይማኖትን ማስተማር ለሆኑ ሰዎች ብንተው፡፡ ... ምንጫቸው ምንም ይሁን ምን፣ “ኢትዮጵያ ልዩ አገር ናት፣ ... ታያላችሁ፤ ምንም አንሆንም!” አይነት አዘናጊ መልዕክቶችን ባናሰራጭ፡፡ አደራዬ! ፌስቡከኞችን ጨምሮ ለፀሀፊዎች፣ ለዘፈን ግጥም ደራሲዎች (ዘፋኞች)፣ በቴሌቪዥን፣ በሬዲዮ፣ በዩ-ቲዩብ እና በጋዜጦች ላይ ታዋቂ ሰዎችን (አርቲስቶችን ጨምሮ) በእንግድነት ለምታነጋግሩ ጋዜጠኞችና ሌሎች የሚዲያ ሰዎች ይድረስ! ሌሎች የሙያ ዘርፎች - ሶሽዮሎጂ፣ ሳይኮሎጂ፣ ሶሻል ወርክ፣ ፐብሊክ ሄልዝ፣ወዘተ (ባለሙያዎች) አሁን የተከሰተው የማይገናኙ ይመስሉ የነበሩ ሀይሎች መካከል የታየው መተጋገዝ በጥሩ ውጤት ይጠናቀቅ ዘንድ፣ ሰዋዊ መፍትሔዎች ላይ ትጉ፡፡ ለምሳሌ፣ የሶሾሎጂስቱ የንግግር መደምደሚያ “እግዜር በቃ ይበለን” አይነት ባይሆን (የሰዋዊ አካሄድን በዜሮ ያጣፋልና)፡፡
ቫይረሱንም አናግንነው - ደግሞ:: በነገራችን ላይ፤ ቫይረሱ እንደ እኔና እንደ እናንተ ምግብ ፈላጊ ነው፡፡ ሰዎች በአፍንጫቸው፣ በአይናቸውም ይሁን በአፋቸው በኩል ወደ ውስጣቸው አንዴ ካስገቡት ኑሮውን እዚያው አንድ ብሎ ይጀምራል፡፡ ይበላል፣ ይጠጣል (ሲመስለኝ - ይፀዳዳል)፣ ይራባል እናም ይሞታል፡፡ ቫይረሱ፣ ማን የሚባል ሰው ውስጥ መኖር እንደ ጀመረ፤ ሰውየው የጦር ጄነራል ይሁን ፀጉር አስተካካይ፣ መሀይም ይሁን ምሁር፣ ከተሜ ይሁን ባላገር፣ አያውቅም፡፡ ምን የሚባል የሰውነት አካል እያጠቃ (እየተመገበ) ስለመሆኑም የሚያውቀው ነገር የለም፡፡ በተጨማሪም፣ እሱ (ቫይረሱ) የሰፈረበት ሰው ይታመም፣ አይታመም፤  ያስለው፣ አያስለው፤ ያተኩሰው፣ አያተኩሰው፤ አካላዊ ገለልታ (Quarantine) ውስጥ ይሁን፣ አይሁን፤ ከፖሊስ አምልጦ ይጥፋ፣ አይጥፋ፤ በተደበቀበት ታሞ ይሙት አይሙት፤ ምናምኒት አያውቅም፡፡
ልጨምር፡- ቫይረሱ  ስታትስቲክስ መያዝ ስራው አይደለም፡፡ እናም፡- በዓለም ላይ ስንት ሰዎችን እንዳጠቃ (ስንት ሰዎችን እንደተመገበ)፣ ቀድሞ ነገር አሁን ያለው ማን በሚባል አገር ውስጥ እንደሆነ አያውቅም:: ልክ ሱሪ ውስጥ የገባ ጉንዳን ከሰውየው ጋር ሲጓዝ ቆይቶ ከብዙ ኪሎ ሜትሮች በኋላ ሰውየውን ብሽሽቱ ውስጥ ወይም ሌላ ቦታ እንደሚነክሰው - ቫይረሱ ከየት ተነስቶ የት እንደ ደረሰ፣ አያውቅም፡፡ ከቻይና ተነስቶ ዱከም ስለመድረሱ ማን ነግሮት? ይሄ አገላለጽ ራሱ ልክ አይደለም፡፡ ድሮስ ቫይረስ ምንድን ነውና ነው የሚነገረው:: ለማንኛውም፤ አገር፣ ፓስፖርት፣ ድንበር የሚባሉ ጽንሰ-ሀሳቦች የእሱ አይደሉም:: ከሚቀበለው፣ ከወደቀበት ካነሳው ሰው ጋር “የትም ይመቸኛል” በሚል ፈሊጥ መጓዝ  ነው ሥራው፡፡ ከቦታ ቦታ መጓጓዝ፣ አገር መጎብኘት ግን ዓላማው ወይም ጊዜ ማሳለፊያው (ሆቢው) አይደለም፡፡ ከአህጉር አህጉር፣ ከአገር አገር የሚንከራተተው ምግቡን ፍለጋ ነው፡፡
ይህን ያልኳችሁ አንደኛ፣ የቁጥሮችን ብዛት በመስማት እንዳንሸበር፣ ሁለተኛ፤ ቫይረሱን ልክ እንደ ጦር ሰራዊት፤ “እነ እንትና እንኳን ያልቻሉት፣ የእነ እገሌን ጉራ ያጋለጠ ... ያንበረከከ፣ ወዘተ” እያልን ምናባዊ ግዝፈት እንዳንሰጠው፣  አንጋጠን እናያቸው የነበሩ አገሮችንና ህዝቦችን ሁሉ ከእኛ እኩል ያደረገ አንዳይመስለን፣  አጎንብሰው በንቀት ይመለከቱን የነበሩት አገሮችንና ህዝቦች (ከነበሩ) ቫይረሱ ለኛ ወግኖ እንደ ተበቀለልን አድርገን እንዳንሞኝ ነው፡፡
አንዴ፣ እዚሁ እኛው አገር ውስጥ ነው፤ ብዙ ሚስቶች ካሉት ሰው ጋር ሳወራ፣ ከጎኔ ያለች ሁለተኛ ዲግሪ ያላት የሥራ ባልደረባዬን እያመለከትኩት፣ “አንተ በእድሜ ትልቅ ነህ፤ አራት ሚስቶችም አሉህ፣ አሁን፣ እገሊት ላግባህ ብትልህ ታገባታለህ?” ብዬ ጠየኩት::
“አታስጎምዠኝ” በሚል ሁኔታ አየኝና፤ “እንክት!” አለኝ፡፡
`እሷ ወጣት ናት፣ በዚያ ላይ የከተማ ሰው፤ እና ደግሞ በጣም የተማረች!” እንዴት ይሆንልሃል?” አልኩት፡፡ “ጎርፍ ምን ይመርጣል፣ ያገኘውን ይዞ ነው የሚሄደው:: እኔ እንደዚያ ነኝ” ብሎኝ እርፍ፡፡ ለካስ ሰውየው የሚያየው ሴት መሆንዋን ብቻ ነው፡፡ የትምህርት ደረጃዋ፣ ከተሜነቷ ወዘተ ለሱ ምንም አልነበሩም፡፡ ጨዋታ ላክልበት ብዬ ነው፡፡  ኮሮናም እንደዚያ ነው፤ የሚፈልገው ምግቡን ነው፡፡ ሰዎችን ለይቶ የመጥቀምና የመጉዳት፣ የዓለምን ኢ-ፍትሀዊነት የማስተካከል ተልዕኮ ላይ አይደለም፡፡ ያገኘውን ይበላል፡፡ ላለመበላት መሸሽ ብቻ ነው መላው፡፡
የመተላለፊያ መንገዶቹ ብዙ ቢሆንም ኮቪድ እንደ ጉንፋን፣ እንደ ትራኮማ፣ እንደ ጉበት በሽታ ወዘተ ተላላፊ በሽታ ነው፤ አለቀ፡፡ በቫይረሱ ዙሪያ ያሉ ሀተታዎችን እንቀንስ! እንጥስ ከሚል ሰው እንራቅ! እንጥስ ማለት ከጀመረንም ለሌሎች ስንል ተገቢውን ጥንቃቄ እንውሰድ፡፡ በሽታውን በመከላከል ረገድ ለመንግሥትም ይሁን ለሀይማኖት መሪዎች የማይታዘዙትን እናጋልጥ፡፡
Read 541 times